Quantcast
Channel: ርዕሰ አንቀጽ
Viewing all 290 articles
Browse latest View live

‹‹ዳያስፖራው በሚኒስቴር ደረጃ ሊዋቀር ይገባዋል››

$
0
0

አቶ አብርሃም ሥዩም፤

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር የተመሠረተው በሰኔ 2004 ዓ.ም. ነው፡፡ ማኅበሩ ሲመሠረት በበጎ ፈቃደኞች ይንቀሳቀስ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ በቅጥር የሚሠሩ ሠራተኞችን ይዞ ከዚህ ቀደም በተሻለ መልኩ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ ለዳያስፖራው መረጃ በመስጠት፣ በችግሮች ላይ በማወያየትና ለመንግሥት የመፍትሔ ሐሳብ በማቅረብም ይሠራል፡፡ አቶ አብርሃም ሥዩም የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ማኅበሩ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ዙሪያ ምሕረት ሞገስአነጋግራቸዋለች፡፡    

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ መጀመሪያ አካባቢ እንቅስቃሴ የነበረው ቢሆንም መሀል ላይ ጠፍቶ ነበር፡፡ አሁን ዳግም መታየት ጀምሯል፡፡ ለማኅበሩ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ምክንያቱ ምን ነበር?

አቶ አብርሃም፡- ማኅበሩ ከተመሠረተ አምስት ዓመታት ያህል ሆኖታል፡፡ ሆኖም ይመሥረት እንጂ ሲተዳደርም፣ ሲሠራም የነበረው ማኅበሩን በፈቃደኝነት በሚያገለግሉ የቦርድ አባላት ነው፡፡ የተጠናከረ ሠራተኛ፣ ቢሮና ቁሳቁስ ሳይኖረው የበጎ ፈቃደኛ አባላቱ ጊዜ ሲያገኙ ዳያስፖራውን የመርዳትና መረጃ የመስጠት ሥራ ያከናውኑ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ለሦስት ዓመታት ያህል ሲሠራ፣ ሲቀዛቀዝ፣ ሲወድቅና ሲነሳ እንዲሁም ብዙ ውጣ ውረዶችን ሲያሳልፍ ቆይቷል፡፡ በኋላ ግን ይኼ ሁኔታ ሊያስኬድ እንደማይችል በመገንዘብ በዋናነት ማኅበሩ ሙሉ የሰው ኃይል ኖሮት ራሱን የቻለና ማኅበሩን በሙሉ ሰዓት ሊረዳ የሚችል ዋና ዳይሬክተር ቀጥሮ መሥራት ጀምሯል፡፡ ምክንያቱም አገር ውስጥ ያለው ዜጋ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ሚኒስቴሮች ብዙ ጉዳዮች እንዳሉት ሁሉ ዳያስፖራውም አለው፡፡ ዳያስፖራው አንድ የሕዝብ ክንፍ ነው፡፡ መረጃ ይፈልጋል፡፡ በትልልቅ ኢንቨስትመንት በመሳተፍና ካምፓኒዎችን በመምራት ላይ ነው፡፡ ስለሆነም የሚፈልገው አገልግሎት አለ፡፡  ዳያስፖራው ራሱን የቻለ አንድ ክልል ነው ለማለት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም እስከ አራት ሚሊዮን የሚደርስ ዳያስፖራ አለ፡፡ ይኼ ሕዝብ በአንድም ሆነ በሌላ ከአገሩ ጋር ቁርኝት አለው፡፡ አገሩም ሲመጣ ኅብረተሰባዊ የሆነ አገልግሎቶችን ይፈልጋል፡፡ አገልግሎት የሚሰጡ መንግሥታዊ ተቋማት ቢኖሩም፣ ዳያስፖራው የሚመጣው የተለየ ጉዳይና ጥያቄ ይዞ ነው፡፡ አንዳንዱ የውጭ አገር መኖሪያ ፈቃድ ያለው ነው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ዜግነት ቀይሮ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ እነዚህን ሊያስታርቅ የሚችል አገልግሎት ከታች እስከ ላይ መኖር አለበት፡፡ በተለይ በዋናነት ዳያስፖራው አገልግሎት በሚሻባቸው ሥፍራዎች ላይ የዳያስፖራ ተወካይ እንዲኖርና ከዳያስፖራው ጋር ቀጥታ ግንኙነት ኖሮ፣ የዳያስፖራውን ጉዳይ የሚፈታ ግንዛቤው ያለው ሠራተኛ እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ የማኅበራችን ሥራም የዳያስፖራው ድምፅ እንዲሠማ፣ ፍላጎቱ ምን እንደሆነ ማንፀባረቅ፣ ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲሰጠውና በአገሩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ዘርፎች የነቃ ተሳታፊ እንዲሆን፣ ራሱን፣ ቤተሰቡንና አገሩን እንዲጠቅም፣ የዳያስፖራው ጉዳይ እንዲታወቅና ተቀባይነት እንዲኖረው እንደ ድልድይ መሆን ነው፡፡ ወደ እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት የዳያስፖራውን ጉዳይ ይዘን በመሄድ እናቀርባለን፡፡ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት የሚሰጡባቸውን መመሪያዎች፣ ሕጎችና አዋጆችን ለዳያስፖራው እናስተዋውቃለን፡፡ ዳያስፖራው ፖሊሲዎችንና ሕጎችን እንዲሁም ጉዳይ የት ተጀምሮ የት መጨረስ እንዳለበትው አያውቅም፡፡ እዚህ ላይ ግንዛቤ እንዲኖር እንሠራለን፡፡ ማኅበሩም ካለፉት ጊዜያት በተሻለ የሰው ኃይል እየተመራ ነው፡፡ ሆኖም ለዳያስፖራው ከሚያስፈልገው አገልግሎት አንፃር በቂ ሠራተኛ የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማትና በክልል ደረጃም የዳያስፖራውን ጉዳይ የሚያዩ ዴስኮች ተቋቁመዋል፡፡ ከእነሱ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል? ችግሮችን የመፍታት አቅማቸውንስ አይታችኋል?

አቶ አብርሃም፡- እኛ ከምናደርገው ትግልና ውትወታ በመነሳት መንግሥት በተቻለ መጠን በየሴክተር መሥሪያ ቤቱ የዳያስፖራ ዴስክ ከፍቷል፡፡ የእኛ አባላት ለአገልግሎት በሚመጡበት ጊዜ ከየዴስኩ ተጠሪ ጋር እንዲገናኙ እናደርጋለን፡፡ ከየዴስኩ ኃላፊዎች ጋር ማኅበሩ ግንኙነት አለው፡፡ አንዳንዶቹ የዳያስፖራ ተወካይ ተብለው ቢቀመጡም ያን ያህል በአዋጅ የተሰጣቸው ሥልጣን ስለሌለ ገፍተው አንዳንድ ውሳኔዎችን አይሰጡም ወይም ውሳኔዎችን ለማሰጠት በቂ አቅም የላቸውም፡፡ ዳያስፖራውን ተቀብለው እንዴት መስተናገድ እንዳለበት ከማመቻቸት ባሻገር ውሳኔ በመስጠትና ጉዳዮችን በመፈጸም ዙሪያ ያን ያህል ሥልጣኑ አልተሰጣቸውም፡፡ ለምሳሌ ዳያስፖራው ካለው ችግር አንፃር ለአጭር ጊዜ ወደ አገር ቤት ስለሚመጣ አገልግሎት ሲፈልግ ቅድሚያ ይሰጠው ወይም ይስተናገድ የሚል መግባቢያ አለ፡፡ አንዳንድ ቢሮዎችም ቅድሚያ እየሰጡ ያስተናግዳሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በመመሪያ ወይም በጽሑፍ አልተሰጠንም ይላሉ፡፡ ሌሎች ሰዎች እያሉ ለምን ቅድሚያስ እንሰጣለን ይላሉ፡፡ በየዴስኩ የዳያስፖራ ጉዳይ ኃላፊዎች ቢኖሩም ጠንካራና ወጥ ሥራ ከመሥራት አንፃር ገና ይቀረዋል፡፡ ማኅበሩ ይኼንን እንደ አጀንዳ ይዞ መንግሥት ከታች ላሉ የዳያስፖራ ዴስክ ተወካዮች ሥልጣንና አቅም እንዲፈጥርላቸው እየሠራን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ዳያስፖራው ኢንቨስትመንት ይዞ ሊመጣ ቢችልም አገልግሎት በማግኘት በኩል አገር ውስጥ ካለው በምን ይለያል?እኩል ተጠቃሚ መሆን አለብን በሚልም በየአገልግሎት መስጫ ተቋማቱ የሚከራከሩ ያጋጥማሉ፡፡ እንደ ማኅበር እዚህ ላይ ምን አስተያየት አላችሁ? ምክንያቱም ዳያስፖራው ኢንቨስት ለማድረግ መጥቶ ለዓመታት ሳይሳካለት ሲቀር፣ ተሳክቶለት ሲሠራ ደግሞ በአካባቢው ማኅበረሰብ ተቀባይነት ሲያጣ ይስተዋላል፡፡ ታች ድረስ ወርዶ ግንዛቤ በማስጨበጡ ላይስ ምን ሠርታችኋል?

አቶ አብርሃም፡- በዋናነት ችግሩን እናውቀዋለን፡፡ በየግልም የሚያጋጥመን ችግር ነው፡፡ ስለ ዳያስፖራው ያለውን የተሳሳተ አመለካከት መቀየር የሚቻለው ከላይ ከመንግሥት ተቋማት ካሉ ከተማሩና የመንግሥትና የሕዝብ ኃላፊነት ከወሰዱ አመራሮች ጀምሮ ወዳታች ወደ ኅብረተሰቡ በመውረድ ነው፡፡ በአመራር ደረጃ እንኳን ስለዳያስፖራው የተሳሳተ አረዳድ ያላቸው አጋጥመውኛል፡፡ ዳያስፖራው መጥቶ መሬት ነው የሚጠይቀው፣ ይህን  ያንን አድርጉልኝ ነው የሚለው፤ በሚል ሁሉንም አንድ ቦታ የመፈረጅ ሁኔታ አለ፡፡ በእርግጥ በኅብረተሰባችን ውስጥ ጥሩ አምራች ዜጋ ያልሆነ እንዳለ ሁሉ በዳያስፖራ ውስጥ አፍራሽ የሆነ፣ የግል ጥቅም ያለው፣ አገራዊ አመለካከትና አጀንዳ የሌለው፣ የሕዝብንና የአገርን ጥቅም በሚጎዳ አቅጣጫ የተሰማራ አይኖርም አይባልም፡፡ ሆኖም ከፍተኛው ቁጥር አምራች፣ አልሚ፣ አገር ወዳድ አገሩን የሚፈልግ፣ በየትኛውም ሥፍራ የአገሩን ሰላም፣ ዕድገትና ዴሞክራሲያዊ ብልፅግና እንዲመጣ የራሱን ኃላፊነት ሲወጣ የኖረ ነው፡፡ የተለየ አመለካከት ያላቸው ጥቂት ናቸው፡፡ በውጭም ፖለቲካና አገርን ቀላቅለው የሚመለከቱ አሉ፡፡ ለፖለቲካ ፓርቲው ካላቸው ጥላቻ ወይም ካላቸው የተለያየ የፖለቲካ ፍልስፍና ተነስተው የአገርን ጥቅም ከዛ ጋር አያይዘው አገርን የሚጎዳ ድርጊት የሚፈጽሙ ጥቂት ናቸው፡፡ አብዛኛው አልሚ ነው፡፡ ሆኖም እኛ ዳያስፖራዎች ተቀበሉን ወይም ስለዳያስፖራ ያላችሁ አመለካከት መቀየር አለበት ከማለት ይልቅ በሥራ ማሳየት ይሻላል፡፡ ዳያስፖራው ምን ሠራ? ቢባል አገራችን በወጪ ንግድ፣ በዕርዳታ፣ በብድርና በተለያዩ መንገዶች የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው መንገዶች እጅግ በበለጠ ሁኔታ (ሐዋላ) ሪሜታንስ ወይም ዳያስፖራው ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ከሚልከው ተጠቃሚ እየሆነች ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ስምንት ወራት ብቻ እስከ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያደረገው ዳያስፖራው ነው፡፡ በዳያስፖራው ላይ ተጠናክሮ ቢሠራ አገሪቱ ያለባትን የውጭ ገንዘብ እጥረት ሊፈታና የኢኮኖሚው ጀርባ አጥንትም ሊሆን የሚችል ነው፡፡ ከመንግሥት ቀጥሎ የሥራ ዕድል በመክፈት እየሠራ ነው፡፡ ለዚህች አገር ዕድገት የዳያስፖራውን አስተዋጽኦ ማጤን ተገቢ ነው፡፡ ዳያስፖራው በርካታ ሥራ ቢሠራም ከመንግሥት ኃላፊዎች ጀምሮ እስከ ታች የኅብረተሰቡ ክፍል የተሳሳተ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች አሉ፡፡ የዳያስፖራውን አበርክቶ የማይገነዘቡ ቢኖሩም የዳያስፖራው ሥራ ገብቶት የሚያበረታታና የሚያግዝም አለ፡፡ ሆኖም አመለካከቱ እየተቀየረ ነው፡፡ ወደፊት የተሻለ እንደሚሆንም እናምናለን፡፡ በተሳተፍንባቸው መድረኮችም ከላይ ጀምሮ ግንዛቤው እንዲኖር ወትውተናል፡፡ የዳያስፖራውን አስፈላጊነትና ምንነት ከላይ ጀምሮ እንዲገነዘቡ ሥልጠና እንዲሰጥ ያስገነዘብንበት ሁኔታም አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል አባላት አሏችሁ?

አቶ አብርሃም፡- የማኅበሩን መታወቂያ የያዙና ዓመታዊ መዋጮ እየከፈሉ የሚገኙ ወደ ስድስት ሺሕ የሚጠጉ አባላት አሉን፡፡ በአዲስ አበባና በየትኛውም ዓለም የሚኖሩም ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ከእነዚህ ውስጥ በሕክምና፣ በትምህርት በሳይንስና በሌሎችም ዘርፎች አንቱ የተባሉ ይኖራሉ፡፡ የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ማኅበሩ ምን እያደረገ ነው?

አቶ አብርሃም፡- በቅርቡ የዳያስፖራ ወጣቶች ፎረም ተቋቁሟል፡፡ ዓላማው በውጭ የተወለዱ ወይም ያደጉ ዳያስፖራዎች በኔትወርክ እንዲያያዙ፣ ተማሪዎች በኢንተርንሺፕ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ ‹‹አገርህን እወቅ›› በሚል አገራቸውን እንዲያውቁ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት አገራቸው ላይ በግል ወይም በጋራ መሥራት እንዲችሉ ነው፡፡ አገሩ ሲመጣ ከነበረው ባህል የተነሳ ባይተዋር እንዳይሆን እርስ በርሳቸው እንዲተዋወቁና ችግሮችን በጋራ እንዲፈቱም ነው፡፡ አገር ውስጥ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና ከወጣቶች ማኅበር ጋር በጋራ ሆኖ ወጣቱ ለአገር ሊያበረክተው የሚገባው ምንድነው? ምንስ ይጠበቃል? በሚለው የዳያስፖራው ወጣት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ያደረግንበት ሁኔታ አለ፡፡ የወጣቱ ጉዳይ በዲፓርትመንት ተቋቁሞና የራሱ ኮሚቴ ኖሮት፣ ወጣቶቹ እርስ በርሳቸው በወር አንዴ ወይም ሁለቴ እንደአስፈላጊነቱ እየተገናኙ ሐሳባቸውን የሚለዋወጡበትና የሚያጠናክሩበት መንገድ አመቻችተናል፡፡ የዳያስፖራ የሴቶች ዲፓርትመንትም ተቋቁመናል፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ በሚከበረው የዳያስፖራው አገራዊ ጉባኤ ማግሥት ይህንን በይፋ እናሳውቃለን፡፡ ይህ ዲፓርትመንት ከሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን በውጭ የኖረች ዳያስፖራ በውጭ የተማረችውን፣ ያላትን ልምድ አገር ውስጥ እንድታካፍል ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ዳያስፖራዎች በምን መልኩ ሊሳተፉና ምን ሊያበረክቱ ይችላሉ? በግል ከሚያደርጉት በተጨማሪ በጋራስ እንዴት ይሳተፋሉ? የሚለውን የሚያይ ኮሚቴም ተቋቁሟል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች የትምህርት ተቋማት በመሥራት ከፍተኛ ልምድ ያዳበሩ ዳያስፖራዎችም አሉ፡፡ አገራችን ከገንዘብ ይልቅ ከዳያስፖራው በስፋት ልትጠቀም ይገባታል የምንለው በዕውቀት ሽግግርና በፈጠራ ሥራ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ፣ በየግል ትምህርት ተቋማቱ ገብተው ሥልጠና የሚሰጡ፣ በሕክምናው ለተወሰነ ጊዜ እየመጡ የልምድና የዕውቀት ሽግግር የሚያደርጉ አሉ፡፡ ነገር ግን በማኅበሩ በኩል ያየነው ክፍተት አሠራሩ የተደራጀና ወጥነት የጎደለው መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም ማኅበሩ ምሁራኑን የሚያሰባስብበት ሥራ ጀምሯል፡፡ ጡረታ ወጥተው አገራቸው የመጡም ይኖራሉ፡፡ እነዚህን በአገር ሽምግልና፣ በመንግሥትና በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል አጀንዳዎች ሲኖሩ መሀል ገብተውና ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው፣ የመነጋገሪያ መድረክ በመፍጠር ለአዲሱ ትውልድ ሊያበረክቱ የሚችሉበትን አሠራር ለመዘርጋት ወደፊት ዕቅድ ይዘናል፡፡ አገራችን ከዳያስፖራው መጠቀም ያለባትን ያህል ስላልተጠቀመች መልክ አስይዘን ለመሥራት እየተጋን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥትና ዳያስፖራው በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ተፈራርጀዋል፡፡ መንግሥትም ይህንን ያህል አያስቀርባቸውም፣ እነሱም መንግሥትን አርቀዋል፡፡ ሁለቱም ለኢትዮጵያ እስካሉ ድረስ ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ፣ ዳያስፖራው በፖለቲካ ልዩነቶቸ ተወጥሮና ግራ ተጋብቶ አገሩን ከመርዳት እንዳይቆጠብ በማኅበሩ በኩል የምትሠሩት ሥራ አለ?

አቶ አብርሃም፡- በሁለቱም አቅጣጫ ጉድለቶች አሉ ማለት እንችላለን፡፡  በዋናነት በዳያስፖራው በኩል ፖለቲካውን የመቃወም አለ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የአገርን ጥቅም እስማስነካት፣ የአገርን ሰላም እስከማደፍረስ፣ ተቋማት እስከ ማጥፋት ይሄዳል፡፡ ባለፈው በአገራችን ተፈጥሮ በነበረው ችግር የወደሙት ተቋማት የሕዝብና የአገር ናቸው፡፡ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሊሆን አይችልም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲና ድርጅት በአንድ ወቅት ይኖራል፣ በአንድ ወቅት ይቀየራል፡፡ ፖለቲካ ሁል ጊዜም ቅብብሎሽ ነው፡፡ በእኛ አገር ያልተለመደው አሁን ግን እየተለመደ መምጣት የጀመረውና ይቀጥላል ብለን የምናምነው ዘመናዊና በሳል የሆነ አመለካከት እየመጣ ነው፡፡ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ቢሆን፣ የተጀመረውን የሚቀጥል፣ ከነበረው በተሻለ አጠናክሮና አሻሽሎ የሚሄድ የጎደለውን እየሞላ የሚሠራ ይመጣል ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህም ሁላችንም ልንሠራ ይገባል፡፡ በዳያስፖራው በኩል አገርንና ፖለቲካን፣ ልማትና ፓርቲን ለይቶ ያለማየት ነገር አለ፡፡ የፖለቲካ ልዩነትና አስተሳሰብ ሁሌም ይኖራል፡፡ ልናቆመው አንችልም፣ ጥሩም ነው፡፡ በዳያስፖራው በኩል መሆን ያለበት በፖለቲካው በኩል በሰላማዊ መንገድ መወያየት ነው፡፡ መነጋገር ይቻላል፣ መድረክም አለው፡፡ ልማትንና አገራዊነትን ከፖለቲካ ነጣጥለን ማየት አለብን፡፡ ዳያስፖራው አገር ቤት የሚመጣው ለማልማት ነው፡፡ ሆኖም አንዳንዴ የመንግሥት ደጋፊ ተደርጎ ስም የሚሰጥበት ሁኔታ አለ፡፡ ማኅበራችንም የዚህ ሰለባ ሆኗል፡፡ ሆኖም ማኅበራችን ከሃይማኖትና ከፖለቲካ የፀዳ፣ ዳያስፖራውን ለልማትና ለኢንቨስትመንት የሚያግዝ ነው፡፡ ነገር ግን ማኅበሩን የመንግሥት መጠቀሚያ አድርገው የሚያስቡ አሉ፡፡ አገር ቤት የሚደረገውን ሁሉ ፖለቲካዊ ነው ብሎ መፈረጅም አግባብ አይደለም፡፡ እነዚህ በዳያስፖራው በኩል መስተካከል አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ አመለካከቱ እንዲዳብርም በማኅበራችን በኩል የተቻለውን ጥረት እናደርጋለን፡፡ አሉታዊ አመለካከት ያላቸው ዳያስፖራዎች ጥቂት ቢሆኑም ብዙው ሠርቶ የሚገባና የአገሩን ጥሩ ነገር የሚፈልግ ነው፡፡ ሆኖም መንግሥት ከዳያስፖራው ጋር በመቀራረብ፣ በኤምባሲዎች የአገራችንን ገጽታ በማሳየት፣ ትክክለኛው አካሄድ ምን መምሰል እንዳለበት ተቀራርቦ በመሥራት ሕዝብን በማወያየት፣ በዳያስፖራው የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎችን በመመለስ ጠንካራ የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲሆን በማድረግ ምን ያህል ሠርቷል የሚለው መታየት አለበት፡፡ በጥቂቶች ሰበብ መበረዝ የለበትም፡፡ ዳያስፖራው ከተለያየ አቅጣጫ ያለውን አመለካከት ማየት እንዲችል መንግሥት በኤምባሲዎች በኩል መሥራት የነበረበት ግን ያልሠራው በርካታ ክፍተት አለ ብለን እናስባለን፡፡ እንደ ዳያስፖራ ማኅበር ዓይነት ገለልተኛና ነፃ ማኅበራት ሲኖሩ በመንግሥት በኩል እነሱን በማበረታታትና በማጠናከር፣ በመካከል ያሉ ውጥረቶችን እንዲያለዝቡ መሥራት አለበት፡፡ ዳያስፖራዎች ዜጎች ናቸው፡፡ የፖለቲካና የአስተሳሰብ ልዩነት ሊኖር ይችላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ጭራሽ ፈጽሞ የሌለ ነገር በውጭ አገር ስለሚነገርና ሰላማዊው የኅብረተሰብ ክፍልም የዚህ ሰለባ ስለሚሆን መንግሥት ይህንን የማስረዳት ኃላፊነት አለበት፡፡ በመንግሥት በኩል ከዳያስፖራው ጋር ለመወያየት ዝግጁነት አለ በተባለ ጊዜ በእኛ በኩል አብረን ለመሥራት ዝግጁ ነን፡፡ የጋራ መድረኮች ይኖራሉ ብለንም እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ዜጋ በፋይናንስ ተቋማት መሳተፍ እንደማይችል በሕግ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከባንኮች በርካታ አክሲዮኖች ገዝተው ነበር፡፡ በዚህ ዓመት ግን መንግሥት በሰጠው መመሪያ መሠረት አክሲዮኖቻቸውን እንዲሸጡ ተገደዋል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ልማት እየተሳተፈ ያለውን ዳያስፖራ አስኮርፏል ይባላል፡፡ ማኅበራችሁስ ምን ይላል?

አቶ አብርሃም፡- ማኅበሩ ችግሩ ከመፈጠሩና አባሎቻችን አቤቱታ ከማቅረባቸው በፊት ሕጉ ምን ይላል? መመሪያውስ? ሕጉና መመሪያው ከነበረ ባንኮች የዳያስፖራውን ገንዘብ ተቀብለው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንዴት ተደረገ በሚሉትና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ስንጻጻፍና ስንጠይቅ ቆይተናል፡፡ በኋላም በመንግሥት በኩል እኛ የማናያቸው መንግሥት የሚያያቸው፣ ከአገር ጥቅም ጋር በማስተሳሰር የተነሱ ጉዳዮችም ነበሩ፡፡ ስለሆነም በአባሎቻችን የሚነሱ ጥያቄዎች ቢኖሩም በእኛ በኩል ያሉትን ቅሬታዎች አጠናክረን መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥ የማመቻቸት ሥራ እየሠራን ነው፡፡ አባሎቻችን የአገርን ኢኮኖሚ ሳይጎዱ አገርንና ራሳቸውን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ሥራዎች ሠርተዋል፡፡ በመሆኑም የአገርን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ሌላ አማራጭ የለም ወይ? በሚል አማራጭ ማቅረብ እንችላለን ብለው በግላቸው አጥንተው ለመንግሥት ለማቅረብ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አባላት እንዳሉ እናውቃለን፡፡ በማኅበራችን በኩል የምናደርገው መንግሥት አንዴ ስለወሰነ አክሲዮን ድርሻ የገዙ አባሎቻችን በተቀመጠው አካሄድ መሠረት ድርሻቸውን እንዲወስዱ ማስተዋወቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዳያስፖራው ፖሊሲ ሲወጣ ትውልደ ኢትዮጵያውን በምርጫ የሚሳተፉበት ሁኔታ እንደሚመቻች አካቷል፡፡ ተፈጻሚ ግን አልሆነም፡፡ አባሎቻችሁ ይህንን ያነሱላችኋል?

አቶ አብርሃም፡- ቀጥታ ከምርጫ ጋር ባይያያዝም የሚነሳው ጥያቄ ጥምር ዜግነት የማግኘት ነው፡፡ የዳያስፖራው ተሳትፎና ድምፅ ከፍ እንዲል፣ በኢኮኖሚውም ተፅዕኖ ስላለው፣ በፖለቲካውም በውጭ ያለው ተፅዕኖ አሉታዊና አዎንታዊው ቀላል ስላልሆነ፣ የዳያስፖራው ተሰሚነት እንዲያድግ ዳያስፖራውን ሊወክል የሚችል በተወካዮች ምክር ቤት መኖር አይገባም ወይ? ዳያስፖራውን የሚመለከት ደንብ፣ ፖሊሲና አዋጅ ሲወጣ በቀጥታ ዳያስፖራውን ያሳተፈ አይደለም የሚሉ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ክፍተቶችም ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹የውጭ ዜጎች›› እየተባለ የሚወጣ አዋጅ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑን ያላገናዘበ ነው፡፡ በዚህም መታወቂያ ለማደስ፣ የልደት ሰርተፍኬት ለማግኘት የተከለከለበት ሁኔታ አለ፡፡ ይኼ ሕጎች ሲወጡ የትውልደ ኢትዮጵያውያኑን ጉዳይ የሚመልሱ ካለመሆናቸው የተነሳ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ለመቅረፍ ከላይ ጀምሮ ስለ ዳያስፖራው ጥሩ አመለካከት እንዲኖር በማድረግ በከፍተኛ ደረጃ ዳያስፖራውን የሚወክል በፓርላማ ሊኖር ይገባል፡፡ ይኼ ካልሆነ ለዳያስፖራው ዳያስፖራውን የማያውቁ፣ ሕይወቱንና ችግሩን የማይገነዘቡ ሰዎች ሕግ ሊያወጡለት ይችላሉ፡፡ በፓርላማ ደረጃ መወከል ከቻልን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶናል እንላለን፡፡ በሌሎች አገሮች በሚኒስቴር ደረጃ አላቸው፡፡ ዳያስፖራው ቁጥሩና የኢኮኖሚ ጥቅሙ ከፍተኛ ከሆነ በሚኒስቴር ደረጃ ሊመራ ይገባዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ያነሰ ቁጥር ያላቸው አገሮች በሚኒስቴርና በኮሚሽን ደረጃ አዋቅረዋል፡፡ በእኛ አገር ዳያስፖራው በሚኒስቴር ደረጃ ለምን አይዋቀርም? የሚል ጥያቄ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ከዳያስፖራው መጠቀም ያለባትን ያህል አልተጠቀመችም፡፡ በሚኒስቴር ደረጃ ቢዋቀርና ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሆን ብዙ ችግሮች ይፈታሉ፡፡ አሁን ያለው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር በዳይሬክተር ጄኔራል ነው፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብዙ ሥራ አለበት፡፡ በዛ ላይ አንገብጋቢ የሆነው የዳያስፖራው ጉዳይ ሲጨመር ሊሰጠው የሚችለው ትረኩት የጠነከረ አይሆንም፡፡ ኢኮኖሚው ድህነትን እንዲያጠፋ የምናግዝና የዳያስፖራው አበርክቶ አስፈላጊ ከሆነ ዳያስፖራው የሚዋቀርበት መንገድ መፈተሽ አለበት በሚኒስቴር ደረጃ ሊዋቀር ይገባዋልም ብለን እናምናለን አባሎቻችንም ይኼንን ጥያቄ አቅርበዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- በዓረብ አገር የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በተለይም በቤት ሠራተኝነት የሚሄዱት ተጎጂ እንደሆኑ በተለያየ ጊዜ ተረጋግጧል፡፡ እንደ ዳያስፖራ ማኅበር በዓረብ አገር ለሚገኙ ዜጎች መብት ምን ሠርታችኋል?

አቶ አብርሃም፡- በገልፍ አገሮች የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ማኅበራችን ዜጎቻችን ከሚያቀርቡት ፍላጎት ጋር ተያይዞ የሚሠራው ሥራ አለ፡፡ ዳያስፖራው የበለጠ ችግር ያለበት የት አካባቢ ነው? ስንል መጀመሪያ የሚመጣው ገልፍ አገሮች ነው፡፡ ማኅበሩም ይህ እጅጉን ያሳስበዋል፡፡ አሜሪካና አውሮፓ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ለመክፈት ዕቅድ ቢኖረንም፣ በዋናነት ቅድሚያ የሰጠነው ዓረብ አገሮች ላይ ለመክፈት ነው፡፡ ከስድስት ወር በፊት የልዑካን ቡድን ይዘን ሳውዲ ዓረቢያ ሄደን ነበር፡፡ ከዓረብ አገር ኢትዮጵያውያን ሲመለሱ በኤርፖርት በኩል የሚገጥማቸው ችግር አለ፡፡ አገራቸው እንደሚመጡ ሳይሆን እንደምንም ተቆጥረው ይዘለፋሉ፣ ይገፋሉ፣ ክብርም አይሰጣቸውም፡፡ ስለሆነም በኤርፖርት ዙሪያ ያሉና ከገቢዎችና ጉምሩክ ኃላፊዎችን ይዘን በመነጋገር በጉዳዩ ላይ መፍትሔ እንዲደረግ አድርገናል፡፡ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከባንክ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከማኅበሩ የተውጣጡ ልዑካን ይዘን በጅዳና በሪያድ ጉዞ አድርገን ችግሩን ለመረዳት ሞክረናል፡፡ ሪፖርቱንም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመለከተው አካል አቅርበናል፡፡ ምላሹም እየጠበቅን ነው፡፡ የማኅበሩ ቅርጫፍ ቢሮ እንዲኖርም ጅማሮዎች አሉ፡፡      

 

Standard (Image)

‹‹ዕቅድን ከአፈጻጸም ጋር ብቻ አይቶ ማለፉ ኢቫሉዌሽን ሳይሆን ክትትል ነው››

$
0
0

አቶ ዮሐንስ በልሁ፣ የኢትዮጵያ ኢቫሉዌሽን አሶሲዬሽን ፕሬዚዳንት

ምዘና (ኢቫሉዌሽን) በአሠራር ውስጥ ለውሳኔ የሚረዱ ሐሳቦች ከአቅም፣ ከችሎታ፣ ከጥራት፣ ወዘተ አኳያ የሚመነጭበት ሒደት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ባለሙያዎች ሙያዊ የምዘና/ግምገማ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸውና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማከናወን ከስምንት ዓመታት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢቫሉዌሽን አሶሲዬሽን 200 አባላት አሉት፡፡ ማኅበሩ ስለሙያው ግንዛቤ በመፍጠር አርኣያ የሆነ ሳይንሳዊ የምዘና ሥራ እንዲስፋፋ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ይናገራል፡፡ በማኅበሩ እንቅስቃሴ ዙሪያ ፕሬዚዳንቱን አቶ ዮሐንስ በልሁን ሻሂዳ ሁሴንአነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከተቋቋመ ስምንት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ምን ሠርቷል?

አቶ ዮሐንስ፡-ባለሙያዎችን የማሰባሰቡ ሥራ ረዥም ጊዜ ፈጅቶብናል፡፡ ሙያው ገና አዲስ ነው፡፡ እስከአሁን በዚህ ሙያ የሠለጠኑ ብዙ ባለሙያዎች የሉም፡፡ ሙያው  እያደገ ቢመጣም፣ በደንብ ማሳወቅ አልቻልንም፡፡ የማስተዋወቅ ችግር አለ፡፡

ሪፖርተር፡-ማኅበሩ ሥራውን ከመሥራት የሚያግዱት ሌላ ችግሮች አሉበት?

አቶ ዮሐንስ፡-የሙያ ማኅበራት በግለሰብ በጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በተለያየ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከመደበኛ ሥራቸው ጊዜ ወስደው ለማኅበር ማድረግ ይቸግራቸዋል፡፡ እነዚህን ሰዎች ማግኘት ትልቅ ችግር ነው፡፡ ሌላኛው ችግር የገቢ ነው፡፡ ገቢያችን የተመሠረተው በአባላት መዋጮ ላይ ነው፡፡ የአባላት መዋጮ ደግሞ አነስተኛ ነው፡፡ እኛ በዓመት 300 ብር ነው እናስከፍላለን፡፡ ይኼንንም የሚከፍሉት መክፈል የሚችሉት ብቻ ናቸው፡፡ 200 አባሎቻችን በሙሉ ከፈሉ ብንል እንኳን፣ በዓመት የሚገኘው በጣም አነስተኛ ነው፡፡ በመሆኑም የተለያዩ ወጪዎችን ሸፍኖ ማኅበሩን ለማንቀሳቀስ አይበቃም፡፡ ቢሮውን የሚያንቀሳቅሱ ሠራተኞችም የሉንም፡፡ የቦርድ አባላትን ሐሳብና ውሳኔ ወደ መሬት አውርዶ የሚያስፈጽም ቋሚ ሰው የለንም፡፡ 

ሪፖርተር፡- ምዘና እንደ ሙያ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ዮሐንስ፡-ኢቫሉዌሽን ማለት በጥቅሉ ለውሳኔ የሚረዱ ሐሳቦችን የሚያመነጭ ሥራ ነው፡፡ ከቤት፣ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አገር ድረስ ውሳኔዎችን የሚጠይቁ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ትክክለኛ ውሳኔ ለመወሰን ጥሩ ኢቫሉዌሽን ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች ግን ኢቫሉዌሽንን ወይም ግምገማና ምዘናን በአሉታዊ ጎኑ ይረዱታል፡፡ ግምገማ ሲባል የአንድን ግለሰብ መጥፎ ጎን ብቻ ለይቶ ማውጣት እንደሆነ አድርገው የሚያስቡም አሉ፡፡ ይኼ ግን የተሳሳተ ሐሳብ ነው፡፡ ኢቫሉዌሽን ተጠያቂነትን ያካተተ ነው፡፡ ተጠያቂነት ያለውን ሥራ ከመሥራት ባሻገር ስህተቶች በድጋሚ እንዳይከሰቱ ትምህርትን እንወስድበታለን፡፡ የግምገማ ሪፖርቶች ለሚቀጥሉት ሥራዎች መንገድ የሚከፍቱ ናቸው፡፡ ኢቫሉዌሽን የተሠሩ ፕሮጀክቶችንና ፖሊሲዎችን የሚመዝንና ለቀጣይ ውሳኔ በቂ የሆነ መረጃ የሚሰጥ መሣሪያ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቶች የኢቫሉዌሽን ባለሙያ ይቀጥራሉ ወይ? ሳይንሱን የተማረ ሰውስ ማግኘት ይቻላልን?

አቶ ዮሐንስ፡-ለዚህ ማኅበር መመሥረት ዋናው ምክንያት ይኼ ነው፡፡ በሙያው ላይ የሠለጠኑ ሰዎች በቁጥር ናቸው፡፡ ግምገማ ወይም ምዘና ግን በእያንዳንዱ መሥሪያ ቤቶች ቁልፍ ሥራ ነው፡፡ ይኼንን ሥራ የሚሠሩት ሰዎች እነ ማን ናቸው? ብለን ስናይ ትክክለኛ የኢቫሉዌሽን ትምህርት ያልወሰዱ ከተለያየ ሙያ የተሰባሰቡና በልምድ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ሙያው ግን ራሱን የቻለ ሳይንስና ሥልቶች ያሉት በዚያው ሙያ የሠለጠኑ ሰዎችን የሚፈልግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በምዘና ሥራ የተሰማሩ በልምድ የሚሠሩ ሰዎች መሆናቸው  ምን ዓይነት ችግሮችን ያስከትላል፡?

አቶ ዮሐንስ፡-ኢቫሉዌሽን ለውሳኔ የሚያንደረድሩ ውሳኔዎች እንዲሰጡ የሚያደርጉ ሐሳቦችን ይዞ ይመጣል፡፡ አንድን ነገር ከብዙ አቅጣጫ ለማየት ያስችላል፡፡ ትክክለኛውን መንገድ የማይጠቁም ውሳኔ  የት እንደሚያደርስ ይታወቃል፡፡ የኢቫሉዌሽን ትምህርትና ክህሎት በሌለው ሰው የሚሠራ ከሆነ በኪራይ ሰብሳቢነት መጠቃቱ አይቀርም፡፡ ሙያው የእኔ ነው በሚል ባለሙያ ከተሠራ ግን ዋጋ ይኖረዋል፡፡ ትክክለኛ ውሳኔ መስጠትም አይከብደውም፡፡ ሁሉም በልምድ የሚሠሩ ሰዎችን እንዲህ ያደርጋሉ ማለት ባይቻልም አልፎ አልፎ የሚታይ ነው፡፡ ምዘናን ሙያዊ ማድረግ ሰው ለሙያው ሲል የተስተካከለ ሐሳብ እንዲያቀርብ ይረዳዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የተለያዩ አካላትና ሠራተኞች የሚመዘኑበት ወጥ የሆነ ደረጃ አለ?

አቶ ዮሐንስ፡-የምዘና ሥራ የራሱ የሆነ መሥፈሪያ አለው፡፡ እኛም ይኼንን መሥፈርት እንደ ደረጃ ሆኖ እንዲሠራበት ረቂቅ አዘጋጅተናል፡፡ መንግሥትና የተለያዩ ባለድርሻዎች አውቀውትና አስተያየት ሰጥተውበት እንዲወጣ ትግል እያደረግን ነው፡፡ ለምዘና ደረጃ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉ የተለያዩ አምስት መሥፈርቶች አሉ፡፡ እነሱ ትክክል ናቸው፡፡ ሆኖም ከዚያም በላይ ቢጨመርበት ውጤታማ ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- አምስቱ የትኞቹ ናቸው?

አቶ ዮሐንስ፡-አምስቱ የምንላቸው ስኬታማነት፣ አፈጻጸም፣ ቀጣይነት፣ ውጤታማነትና አስፈላጊነት የሚባሉት መሥፈርቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ወፍጮ ለሴቶች አስፈላጊ ነው ብላ የምታምን፣ እንሰት በብዛት በሚበላበት አካባቢ ወፍጮ ወስዳ ተከለች፡፡ ወፍጮው አስፈላጊ ቢሆንም መተከል የነበረበት ግን ሌላ ቦታ ነበር፡፡ ይኼ ለማኅበረሰቡ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ከንድፈ ሐሳብ ጀምሮ እስከ ክንውኑ ድረስ እነዚህን አምስት መሥፈርቶች መሠረት አድርጎ የሚሠራ ሥራ ምዘና (ኢቫሉዌሽን) ይባላል፡፡

ሪፖርተር፡- የምዘና ደረጃ ምን ምን ነገሮችን ይዟል?

አቶ ዮሐንስ፡-የተለያዩ ነጥቦችን ይዟል፡፡ ለምሳሌ የምዘና ሥራ ለመሥራት መሟላትና መከተል ያለባቸውን አካሄዶች አካቷል፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ ነጥቦችን ያካተተ ረቂቅ አዘጋጅተናል፡፡ የመንግሥት አካላት እንዲያዩትና ሐሳብ እንዲጨምሩበት ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር- ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚመዘኑት በተመሳሳይ መሥፈርት ነው ወይስ የተለያየ ነው?

አቶ ዮሐንስ፡- የተለየ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ተመሳሳይ ነው፡፡ ትልቁ ነገር አምስቱ መለኪያዎች መሟላታቸው ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራበትና በየትኛውም ቦታ መሣሪያ ሆነው ማገልገል የሚችሉ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ የሙያ መስኮች በምዘና ዘርፍ የሚሰማሩ ከሚሠሩበት መሥሪያ ቤት ለምሳሌ የሕክምና ተቋም ከሆነ ለሕክምና መዛኞች ተብሎ የሚሰጥ ተጨማሪ ትምህርት አለ? ወይስየምዘና ትምህርት መማራቸው ብቻ በቂ ነው?

አቶ ዮሐንስ፡-በየሴክተሩ የሞኒተሪንግና ኢቫሉዌሽን ኮርስ ይኖራል፡፡ ለምሳሌ እኔ ዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ ተምሬያለሁ፡፡ በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ ፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ ፕሮጀክት ሞኒተሪንግ ኤንድ ኢቫሉዌሽን የተባሉ ኮርሶች ይሰጣሉ፡፡ በጤናውም እንደዚሁ ጤናውን የሚከታተሉበትና የሚቆጣጠሩበት መንገዶች ይኖራሉ፡፡ የተሟላ ነው ማለት ባይቻልም አንዳንድ ጥሩ ጅምሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የጤናን ሥራ በተመለከተ ብቻ ሞኒተሪንግ ኤንድ ኢቫሉዌሽን በማስተርስ ዲግሪ ፕሮግራም ጀምሯል፡፡ አንድ ሴክተር መሆኑ እንጂ ጅምሩ መልካም ነው፡፡

ሪፖርተር- በአገሪቱ የኢቫሉዌሽን ትምህርት የሚሰጥባቸው ተቋማት አሉ?

አቶ ዮሐንስ፡-ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከሌሎች ጎረቤት አገሮች በተለየ ለሙያው አነስ ያለ አመለካከት እንዳላቸው ታዝቤያለሁ፡፡ ለምሳሌ በኬንያ ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች በሞኒተሪንግና ኢቫሉዌሽን ብቻ በድኅረ ምረቃ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ ዮጋንዳ፣ ታንዛኒያና ደቡብ አፍሪካ በዲግሪና ማስተርስ ፕሮግራም ያስተምራሉ፡፡ ይኼ ምን ያህል ለጉዳዩ ትኩረት እንደሰጡት የሚያሳይ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን በጣም ወደ ኋለ ቀርቷል፡፡ በኢቫሉዌሽን ሙያ ትምህርት የሚሰጥ የትምህርት ተቋም ከጅማ ዩኒቨርሲቲና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስተቀር የለም፡፡ ይኼ ዘርፍ ግን ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ስለዚህ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ነቃ ማለት አለባቸው፡፡ እያንዳንዱ ድርጅት የግድ በዚህ ሙያ የሠለጠነ ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ይኼ ሙያ ለአንድ ወንበር አራተኛ እግር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ይኼንን አስበው ትኩረት ቢሰጡት እላለሁ፡፡ አንድ አገር ከዚህ ደረጃ ተነስታ እዚህ ደረሰች ለማለት መመዘን ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ በአገሪቱ ያለው ፈጣን ዕድገትም ፈጣን የሆነ ምዘና ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ የመንግሥትም ሆኑ የግል የትምህርት ተቋማት የኢቫሉዌሽን ትምህርት ማስተማር መጀመር አለባቸው፡፡ ሙያው በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ አንዱ በሞኒተሪንግና ኢቫሉዌሽን ሙያ የተማረ አይደለም እንበል፡፡ የሚሠራው ግን የሞኒተሪንግና ኢቫሉዌሽን ሥራ ነው፡፡ ይኼ የሚሆነው የባለሙያ የእጥረት ስላለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-በልምድ በሚሠሩና ትምህርቱን ተምረው ሳይንሱን አውቀው በሚሠሩ መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው?

አቶ ዮሐንስ፡-ሙያው የራሱ የሆነ ዲሲፕሊን አለው፡፡ ፕሮግራሞች የሚታዩት በተለየ መነፅር ነው፡፡ በምሠራበት ድርጅት ውስጥ የፕሮግራም ሰዎች አሉ፡፡ የሞኒተሪንግና ኢቫሉዌሽን ሰዎችም አሉ፡፡ እኛ ፕሮራሞችን የምናይበትና እነሱ የሚያዩበት ዓይን የተለያየ ነው፡፡ እነሱ ይኼንን ያህል ሥራ ሠራን ይላሉ፡፡ እኛ ደግሞ እዚያ ጋር አንቆምም ከዚያስ ምን ለውጥ መጣ እንላለን፡፡ ስለዚህ እኛና ሌላው ነገሮችን የምናይበት መንገድ በጣም የተለያየ ነው፡፡ ሳይንሱን ተምረው የሚሠሩ ሰዎች ደግሞ ከእኛ የተሻሉ ይሆናሉ፡፡ የእኛም ጥረት ሴክተሩ ሳይንሱን ባጠኑ ባለሙያዎች እንዲመራ ማድረግ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ሙያው በልምድ በሚሠሩ ሰዎች መመራቱ አገሪቱን ምን ያህል ዋጋ  እያስከፈላት ይገኛል?

አቶ ዮሐንስ፡-ይኼንን ያህል የገንዘብ ኪሳራ እያደረሰ ይገኛል ለማለት ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በሚታየው ነገር ላይ ተመሥርቶ መናገር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በየዓመቱ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ይገመገማሉ፡፡ የሚገመገሙበት መንገድ ግን  ትክክለኛ ሳይንሱን የተከተለ ነው አልልም፡፡ ዕቅድን ከአፈጻጸም ጋር ብቻ አይቶ ማለፉ ኢቫሉዌሽን ሳይሆን ክትትል ነው፡፡ ክትትልና ግምገማ ደግሞ ይለያያሉ፡፡ ግምገማ ይኼ ነገር ተከናውኗል፣ ግን ምን ለውጥ አመጣ? የሚለውን ማየት ነው፡፡ ለምሳሌ የመንገድ ችግር ባለበትና መኪኖች በሚጨናነቁበት አካባቢ መንገድ መገንባት ሲገባ ብዙ ተጠቃሚ በሌለው ቦታ ላይ መንገድ ቢገነባ ሥራው ተከናውኗል ነገር ግን ኅብረተሰቡን ጠቅሟል ወይ? ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ወይ? አስፈላጊ ነው ወይ? የሚሉት ጥያቄዎችም መነሳት አለባቸው፡፡ የማኅበረሰቡ ፍላጎት ያልሆኑ ፕሮጀክቶች እየተፈጸሙ ሊሆን ይችላል፡፡ እነኚህን ማየት የሚችለው ጥሩ የሆነ የኢቫሉዌሽን ዕይታ ያለው ባለሙያ ሲኖር ነው፡፡ ነገር ግን ይኼ በሌለበት በሚካሄድ ግምገማና በሚወጣ ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ ይኼ ፕሮጀክት ይቀጥል! ይቋረጥ! ብሎ መወሰን ስህተት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግምገማ በየምን ያህል ጊዜ መደረግ አለበት ብለው ያምናሉ?

አቶ ዮሐንስ፡- ግምገማ መካሄዱ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ ምን ሠራሁ? ምን አመጣሁ? ከተያዘው ዕቅድ አንፃር ምን ያህሉን ሠራሁ? ብሎ መመዘን የሚቻልበት ነው፡፡ ነገር ግን ቃሉ ይሁን ሌላ በማኅበረሰቡ ውስጥ ስለ ግምገማ ጥሩ አመለካከት የለም፡፡ ግምገማ በመጥፎ ጎኑ መታየት የለበትም ምን እየሠራሁ ነው? ለምን? እና የመሳሰሉትን መሠረታዊ ነገሮች የምናሳይበት ነው፡፡ በበጎ ጎኑ አለመታየቱ ያሳዝነኛል፡፡ ይኼ እንዲሆን ያደረግነው እዚያ ውስጥ ያለን ሰዎች ልንሆን እንችላለን፡፡ ይሁንና ካለው ጠቀሜታ አንፃር ግምገማ በየዓመቱ ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ከዋጋ አንፃር በጣም ውድ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም የአምስት ዓመት ዕቅድን በሁለት ዓመት ተኩል ላይ መገምገም ከዋጋም ከዕቅዱም አፈጻጸምም አንፃር አዋጭ ነው፡፡ 

Standard (Image)

አዲሱ የደረቅ መኪና እጥበት

$
0
0

ሻይን ተንቀሳቃሽ የደረቅ መኪና እጥበት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በቅርቡ ወደ መኪና እጥበት ቢዝነስ የገባ ኢንተርፕራይዝ ሲሆን፣ መኪናን በግፊት ኃይል በሚሠሩ የመኪና ማጠቢያ ፕላስቲክ ማሽኖች ያለ ፈሳሽ ወይም በደረቅ የመወልወል አገልግሎት ይሰጣል፡፡ 106 የሚሆኑ ወጣቶች ተቀጥረው የሚሠሩበት ሲሆን፣ በአዲስ አበባ በሦስት ክፍለ ከተሞች በዋነኛነት በንግድ ማዕከል ሕንፃዎች እየሠሩ ነው፡፡ ስለ ማኅበሩ እንቅስቃሴ ምሕረተሥላሴ መኰንንየማኅበሩን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ይማም አነጋግራዋለች፡፡  

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ስለሚሰጠው የደረቅ መኪና እጥበት አገልግሎት ብታብራራልን?

አቶ ጥላሁን፡- የደረቅ መኪና እጥበት መሬት ላይ ውኃ ሳይፈስ መኪናን በማራስ ብቻ የሚደረግ የእጥበት ዘዴ ነው፡፡ አገልግሎቱ በተለያዩ አገሮች ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ  በአፍሪካ በደቡብ አፍሪካ፣ በኬንያና በሌሎችም አገሮች ይሰጣል፡፡ ሐሳቡን ያመጣነው በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተን ላቫጆ ሥራ በጠየቅንበት ወቅት ነበር፡፡ የቦታ ችግር ስላለ በመንግሥት በኩል በተወሰነ ደረጃ ላቫጆ መስጠት የተከለከለበት ጊዜ አለ፡፡ ይህንን በማየት ኢንተርኔት ላይ ሌላ አማራጭ ፈለግን፡፡ የመኪና እጥበት ውጭ አገር በአዲስ ቴክኖሎጂ እንዴት እንደሚሠራ አየንና ጀመርን፡፡

ሪፖርተር፡- የላቫጆ ሥራ ለመሥራት የቦታ እጥረት ችግር የሆነው እንዴት ነው?

አቶ ጥላሁን፡- ለላቫጆ ሥራ ቦታ የሚሰጠው ወንዝ ዳር ወይም ወጣ ያለ ቦታ ጥናት ተደርጎ ነው፡፡ ሒደቱ አሰልቺ ነው፡፡ እኛም ከተደራጀን በኋላ ቦታ ስለሌለን እንደ አማራጭ የደረቅ መኪና እጥበትን ወሰድን፡፡ ከዱባይ ያስመጣናቸው ማሽኖች ተንቀሳቃሽ ናቸው፡፡ ቦታም አይዙም፡፡ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት ብዙ ሒደቶች አልፈናል፡፡ ከኛ በፊት አንድ ከውጭ መጥቶ የጀመረ ልጅ ነበር፡፡ የሱ እጥበት አንድ የተወሰነ ቦታ ላይ ብቻ ነው፡፡ በላቫጆ ሥራ ባለመኪኖች  ወደ ላቫጆ ይሄዳሉ፡፡ እኛ ግን ወደ መኪናው እንመጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- የተደራጃችሁት ምን ያህል ሆናችሁ ነበር? ሒደቱስ ምን ይመስል ነበር?

አቶ ጥላሁን፡- መጀመርያ እኔና ጓደኛዬ ተደራጀን፡፡ ከዚህ በፊት የምንሠራው ሌላ ሥራ ነበር፡፡ ወደ መኪና እጥበት የመጣነው አዋጭነቱን በማየት ነው፡፡ ፕሮፖዛሉን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ጽሕፈት ቤት አስገባን፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የቢዝነሱን አዋጭነትና በሥሩ ብዙ ሥራ አጥ ወጣቶች የመያዝ አቅም ያለው መሆኑን አየ፡፡ እንደ ማሳያ የወሰድነው ሦስት ክፍለ ከተሞችን ነበር፡፡ የካ፣ ቂርቆስና ቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ያሉ ወጣቶች በኛ ኢንተርፕራይዝ ውስጥ ሆነው የስምምነት ሰነድ ተፈራርመው አብረን እንድንሠራ ያቀረብነውን ጥያቄ የከተማ አስተዳደር ከተቀበለ በኋላ ሥራ ጀመርን፡፡

ሪፖርተር፡- መነሻ ካፒታላችሁ ስንት ነበር?

አቶ ጥላሁን፡- 100 ሺሕ ብር ነበር፡፡ አሁን እያደገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ስንት ወጣቶች ታቅፈዋል? አገልግሎቱን መስጠት ከጀመራችሁስ ምን ያህል ጊዜ ሆናችሁ?

አቶ ጥላሁን፡- በመጀመርያ ዙር በኛ ሥር ያሉ ወጣቶች ወደ 160 ናቸው፡፡ ከእነዚህ 90ዎቹ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከአንድ ሳምንት በኋላ ይጀምራሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት 160ውንም አስመርቀናል፡፡ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ሆቴል ባካሄድነው የምርቃት ሥነ ሥርዓት ወደ 160 ወጣቶች ተገኝተዋል፡፡ በፕሮግራሙ ከትንሽ ቦታ ተነስተው ትልቅ ደረጃ የደረሱ እንደ ኢያሳያስ አድቨርታይዝመንትና አምባሳደር ልብስ ስፌት ባለቤት ያሉ ሰዎችን ጋብዘን ለወጣቶቹ ምክር እንዲሰጡ አድርገናል፡፡ የጋበዝናቸው ሰዎች ስለ ሥራ ምንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥተዋል፡፡ የሦስቱ ክፍለ ከተሞች አመራሮች ተገኝተውም የማሽን ርክክብ ተደርጓል፡፡ ሥራውን ወደ መሬት ካወረድነው ወደ ሃያ ቀን ሊሆነን ነው፡፡ ጥናት ሠርተን ፕሮፖዛሉን ለመንግሥት እስክናቀርብ ስምንት ወር ገደማ ፈጅቶብናል፡፡ ሥራው ሁለት ዓይነት ነው፡፡ በሞሎችና መንገድ ለመንገድ እንሠራለን፡፡ ሞሎች ላይ ሠራተኞች ቀጥረን መኪኖች በቆሙበት እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ ቦሌና መርካቶ እየሠራንባቸው ያሉ ሕንፃዎች አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ሰው መኪና ለማሳጠብ ጊዜ የለውም፡፡ ላቫጆ ሲሄድ 30 ወይም 40 ደቂቃ ስለሚፈጅ በሳምንት አንዴ ወይም ሁለቴ ብቻ ይሄዳል፡፡ እኛ የሕንፃ አስተዳዳሪዎችን በማናገር መኪናውን ፓርክ ባደረገበት እንዲታጠብ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- የደረቅ መኪና እጥበት በተለምዶ ከሚታወቀው የመኪና እጥበት ጋር ሲነፃፀር ፍሳሽ ውኃን ከማስቀረት ባሻገር ምን የተለየ አገልግሎት ያካትታል?

አቶ ጥላሁን፡- ሥራው አሁንም በዘልማድ ይሠራል፡፡ ዋናው ነገር የደረቅ መኪና እጥበት ጊዜ ቆጣቢ መሆኑ ነው፡፡ ባለ መኪናው ሳይንገላታ ሥራ ላይ እያለ መኪናው ይፀዳለታል፡፡ ሥራው ተንቀሳቃሽ ስለሆነ ብዙ ወጣቶችን ይዘን መሥራት እንችላለን፡፡ ከላቫጆ እጥበት የሚለየው መሬት ውኃ አለመፍሰሱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሥራውን ስትጀምሩ ከመንግሥት ምን ዓይነት ድጋፍ አገኛችሁ?

አቶ ጥላሁን፡- ሐሳቡን ይዘን ስንሄድ በሦስቱም ክፍለ ከተሞች ማሳያ እንድንሠራ ተደርጓል፡፡ በክፍለ ከተሞቹ ያሉ ወረዳዎችን አስተባብረው በዘልማድ ይሠሩ የነበሩ ወጣቶች በኛ ሥር እንዲሠሩ አድርገዋል፡፡ ሌላው ትልቅ ድጋፍ የመኪና መጨናነቅ የሌለባቸው አውራ ጎዳናዎች (ሃይ ዌይ) ያልሆኑ መኪና የሚቆምባቸው መንገዶች ላይ እንድንሠራ መፍቀዱ ነው፡፡ የከተማው የጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ቢሮ ያደረገልን ድጋፍ እንዳለ ሆኖ በእጃችን ያሉን ማሽኖች ግን የተወሰኑ ነበሩ፡፡ አዲስ ካፒታል ሊዝ ፋይናንስ የቢዝነሱን አዋጭነት በማየት እስከ 250 ሺሕ ብር የሚሆን ማሽን ሊያስገቡልን መሆኑ ነው፡፡ ከአንድ ወይም ከሁለት ወር በኋላ እጃችን ላይ ይደርሳል ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- አሽከርካሪዎች በአገልግሎታችሁ እንዲጠቀሙ በቂ ማስታወቂያ ሠርታችኋል ?

አቶ ጥላሁን፡- ሞሎች ላይ የቪአይፒ ኩፖኖች እንሰጣለን፡፡ ኩፖኖቹን የያዘ ሰው በምንሠራበት በማንኛውም ቦታ ይጠቀማል፡፡ በኩፖኑ ፓኬጅ አንድ ሰው ስምንት ቀን መኪናውን ካሳጠበ በወር 400 ብር ብቻ ይከፍላል፡፡ የአራት ቀን ፓኬጅም አለ፡፡ ሁለተኛው በበራሪ ወረቀት የሠራነው ማስታወቂያ ነው፡፡ የአቅም ጉዳይ ችግር ሆኖብን እስካሁን ባናደርገውም ለወደፊት በሬድዮና በቴሌቪዥን ማስታወቂያ ለመሥራትም እናስባለን፡፡ በምንከራያቸው ሞሎች ባነሮች አሉን፡፡ መንገድ ላይ ለሚሠሩ ወጣቶች የኛን ድርጅት የሚገልጹ ተንጠልጣይ ባንዲራዎች ይኖሩናል፡፡ ሥራው አዲስ በመሆኑ አንዳንዶች መረጃው የላቸውም፡፡ እንዴት በደረቅ መኪና ይታጠባል? የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ግን በደረቅ መኪና እጥበት መኪናው ስፕሬይ ተደርጎ ርሶ በፎጣ ውስጡንም ውጪውንም ማፅዳት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከ400 ብር ፓኬጅ ውጪ አንዴ የሚያሳጥብ ሰው ስንት ይከፍላል?

አቶ ጥላሁን፡- ክፍያው እንደየቦታው ቢየለያይም አንዴ የሚያሳጥብ ሰው ቢበዛ 40 ብር ይከፍላል፡፡ ከሕንፃ አስተዳደሮች ጋር በጋራ ስለምንሠራ 60 በመቶውን ድርጅቱ 40 በመቶውን ደግሞ የሕንፃ አስተዳደሮች ይወስዳሉ፡፡ 40 ብር የምናስከፍለው መኪና ከላይ ብቻ ሲታጠብ ሲሆን፣ ውስጡም ሲጨመር 50 ብር ይከፈላል፡፡ የምንጠቀማቸው የተለያዩ ሻምፖዎችና የዳሽ ቦርድ ቅባቶች አሉ፡፡ ዋጋው እንደየመኪናው ዓይነትም ይለያያል፡፡ ለምሳሌ ዶልፊንና ኮሮላ የሚታጠቡበት ዋጋ አንድ አይደለም፡፡ ዶልፊን የሚታጠበው 60 ብር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የመንገድ እንዲሁም የሕንፃ ግንባታ እምብዛም የመኪና ፓርኪግን ታሳቢ ባለማድረጉ መኪና ማቆሚያ ቦታ በማጣት የሚቸገሩ አሽከርካሪዎች ብዙ ናቸው፡፡ የእናንተ ቢዝነስ ፓርኪንግ ቦታን ያማከለ እንደመሆኑ ይህ ሥራችሁ ላይ እንቅፋት አይፈጥርም?

አቶ ጥላሁን፡- ሞሎች ላይ እንዲህ ዓይነት ችግር የለም፡፡ ነገር ግን የኛም ትልቁ ሥጋታችን ነው፡፡ መጀመርያ ጥናት ስንሠራ ለእጥበቱ የለየናቸው ቦታዎች አሉ፡፡ እነዚህ የምንሠራባቸውን ቦታዎች በፎቶ አስደግፈን ለከተማ መስተዳድሩ ፕሮፖዛል አስገብተናል፡፡ ለምሳሌ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብሔራዊ ቴአትር ፊት ለፊት ብዙ መኪናዎች ይቆማሉ፡፡ የመኪና መጨናነቅ የሌለበት ዋና መንገድ ያልሆነም ቦታ ነው፡፡ እንደዚህ ዋና ዋና ብለን የለየናቸው ቦታዎች አሉ፡፡ እንደዚህ ሆኖም ሥራው መሬት ሲወርድ ነው ችግሮቹ የሚታዩት፡፡

ሪፖርተር፡- ከፓርኪንግ ቦታ ውጪ በሥራችሁ የገጠሟቸሁ እንቅፋቶች አሉ?

አቶ ጥላሁን፡- ሥራውን ስንጀምር ሁለት ሥጋቶች ነበሩን፡፡ አንዱ ልጆቹ እኛ ካስቀመጥንላቸው ቦታዎች ወጥተው ከሠሩ የመኪና አደጋ ሊደርስባቸው መቻሉ ነው፡፡ ይኼ እስካሁን አልገጠመንም፡፡ ሆኖም ሊገጥመን ስለሚችል ከፍተኛ ክትትል ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛው በዘልማድ ከሚሠሩት ልጆች አብዛኞቹ የክፍለ አገር ልጆች ስለሆኑ የአዲስ አበባ መታወቂያ የላቸውም፡፡ ስለዚህም ተደራጅተው መሥራት አይችሉም፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ቢሮ አሠራር እኛ የወሰድናቸው ልጆች ወረዳው የሚያውቃቸው የአዲስ አበባ ልጆች ናቸው፡፡ እንደነዚህ ልጆች ሁሉ መታወቂያ የሌላቸውንም ወደኛ መስመር አስገብተን የምንሠራው እንዴት ነው? የሚል ችግር ገጥሞናል፡፡ ሁለቱም ዜጎች ናቸው፡፡ ሁላችንም ስለምንሠራውም ለአገር ነው፡፡ እዚህ ላይ ወደኛ ሥርዓት አስገብተን የምንሠራበትን መንገድ ከየወረዳዎቹ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ በዘልማድ ለሚሠሩ ልጆች ዘመናዊ ማሽኖች አቅርበን ከኛ ጋር እንዲሠሩም እያመቻቸን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የእጥበት አገልግሎቱ ሰዎች በአንድ ሕንፃ ውስጥ ገብተው የሚቆዩበትን ጊዜ ያማከለ ነው?

አቶ ጥላሁን፡- እጥበቱ የሚፈጀው ከ20 እስከ 30 ደቂቃ ነው፡፡ አንድ ሰው መኪናውን አቁሞ ሲሄድ የኛ ሱፐርቫይዘር ምን ያህል ደቂቃ እንደሚቆይ ይጠይቃል፡፡ አምስት ወይም አሥር ደቂቃ ከሆነ መኪናው አይፀዳም፡፡ ካለን ተሞክሮ ሲኒማ ቤት፣ ካፌ ወይም ሱቅ የገባ ሰው የሚወጣው ቆይቶ ነው፡፡ አገልግሎቱን በሃይማኖት ተቋሞች አካባቢ የመስጠት ዕቅድም አለን፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን አገልግሎቱን የምትሰጡባቸውን ቦታዎች ብትገልጽልን?

አቶ ጥላሁን፡- ኢንተርኮንቲነንታልና ኢሊሊ ሆቴል ጀርባ፣ ብሔራዊ ቴአትርና ስቴዲየም ፊት ለፊት፣ ሞርኒንግ ስታር ሞልና ቦሌ ሀይስኩል ጀርባና መርካቶ ድር የገበያ ማዕከልም እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ባላችሁ ተሞክሮ ከአሽከርካሪዎች ምን ዓይነት ምላሽ አገኛችሁ?

አቶ ጥላሁን፡- የኛ አገልግሎት ዋናው ጥቅም ጊዜ ቆጣቢነቱ ነው፡፡ ሁለተኛው አሽከርካሪዎች በፊት በየመንገዱ በሚያሳጥቡበት ወቅት የማያገኟቸውና በኛ አገልግሎት ውስጥ የተካተቱ እንደ መኪና ሽታ፣ የዳሽ ቦርድ ቅባትና የጎማ ቀለም ያገኛሉ፡፡ ዋጋችን መንገድ ላይ ካለው እኩል ነው፡፡ ስለዚህ በአገልግሎቱ የተጠቀሙ ደስተኛ ሆነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ቢዝነሱ እንዲያድግና የተጠቃሚዎች ቁጥርም እንዲጨምር ምን መደረግ አለበት?

አቶ ጥላሁን፡- በየሄድንበት ቢሮ ሥራው አያዋጣም ያለን ሰው አልነበረም፡፡ ከዚህ በኋላ እኛ ብቻ ሳንሆን ብዙ ሺሕ ኢንተርፕራይዞች ይፈልቃሉ ብለን እናስባለን፡፡ ለላቫጆ የሚወጣው ውኃ ብዙ ስለሆነ  የሥራው ጥቅም ውኃ መቆጠቡም ነው፡፡ በየዓመቱ ብዙ መኪናዎች ወደ አገሪቷ ይገባሉ፡፡ ወጣቶች በዚህ ሥራ ቢሰማሩ አዋጭነቱ አያጠያይቅም፡፡ መንግሥትም ትልቅ ድጋፍ እያደረገልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው?

አቶ ጥላሁን፡- ለወጣቶቹ መጀመሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንሰጣለን፡፡ ልምድ ባይኖራቸውም ሥልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡ ወጣቶቹ ከሱስ ነፃ መሆን አለባቸው፡፡ ልጆቹ ቁጠባም አላቸው፡፡ አንድ ልጅ በቀን ማጠብ ያለበት ዘጠኝ መኪና ነው፡፡ ከዘጠኙ ሁለቱ ቁጠባ ስለሆነ በቀን 80 ብር ይቆጥባል ማለት ነው፡፡ በዘልማድ የሚሠሩ ልጆች ቁጠባ ስለማይኖራቸው ሕይወታቸው አይለወጥም፡፡ በቀጣይ ብዙ መኪናዎች ባሉባቸው ክፍለ ከተሞች ሥራውን እንጀምራለን፡፡ ችግሮችን እየፈታን ስኬታችንን እያጠናከርን እንሄዳለን ብለን እናስባለን፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ትልልቅ ሕንፃዎች እየተሠሩ ነውና በሆቴሎች፣ በአፓርትመንቶችና በኮንዶሚኒየሞች አገልግሎቱን መስጠት እንፈልጋለን፡፡

 

Standard (Image)

‹‹ራሴን በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መሀል ላይ ያለ ድልድይ አድርጌ ነው የምወስደው››

$
0
0

ገጣሚና ጸሐፊ ለምን ሲሳይ

ትውልደ ኢትዮጵያ ብሪታንያዊው ለምን ሲሳይ ዕውቅ ገጣሚና ጸሐፊ ነው፡፡ በተለያዩ ጥበብ ተኮር ተቋማት እየሠራ ይገኛል፡፡ በሳውዝ ባንክ ማዕከል ተባባሪ አርቲስት፣ በሌተር ቦክስ ክለብ ድጋፍ ሰጪ፣ የቺልድረንስ ሪዲንግ ፈንድ አምባሳደር ሲሆን የክብር ዶክትሬት (ዶክተር ኦፍ ሌተርስ) ተሰጥቶታል፡፡ ለለንደን ኦሊምፒክ ግጥም የደረሰ፣ የበርካታ ተለጣጣቂ መጻሕፍት፣ መጣጥፎች፣ ሪከርዶች ወዘተ ጸሐፊ ነው፡፡ ከሰኔ 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ሆኖ ለሰባት ዓመታት አገልግሎት ተመርጧል፡፡ ኢትዮጵያ ተወልዶ ብሪታኒያ በጉዲፈቻ ያደገው ለምን ሕይወቱን ከአፄ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዓለማየሁ ጋር ያገናኘዋል፡፡ የልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ አፅም ወደ አገሩ እንዲመለስ ምኞቱ መሆኑንም ይናገራል፡፡ መሰንበቻውን ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ያለውን ለምን ሲሳይን ዳዊት እንደሻው ስለ ዐውደ ሕይወቱ አውግቶታል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅድሚያ ስለነበረህ የአንድ ሳምንት  ቆይታ እስኪ ግለጽልን፡፡

ለምን፡- እስካሁን የነበረኝ ቆይታ በጣም አዝናኝና ፍሬያማ ነበር፡፡ ከብዙ ሰዎች ጋር የመገናኘቱን ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ከሪታ ፓንክረስት ጋር የመገናኘቱን ክብር አግኝቻለሁ፡፡ በተጨማሪም አሉላ ፓንክረስት ጋር ተገናኝቼ ከማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት እንዴት የውጭ የትምህርት ዕድል ለኢትዮጵያውያን ማመቻቸት እንደምንችል መክረናል፡፡

እሱ ብቻ አይደለም ከብሪትሽ ካውንስል አዲስ ዳይሬክተር ፒተር ብራውን ጋር ተገናኝተናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአዲስ አበባና ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ከመጡ ምሁራን ጋርም የመገናኘቱን ዕድልም አግኝቼ ከውጭ የትምህርት ዕድሉ ጋር በተያያዘ እንዴት የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ከማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ጋር እንዴት መሥራት እንደሚችሉ ተነጋግረናል፡፡ እንግዲህ እኔ ራሴን በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መሀል ላይ ያለ ድልድይ አድርጌ ነው የምወስደው፡፡ አሁን አሁን ጊዜዎች ባለፉ ዕድሜያችንም በገፋ ቁጥር እኔ እዚህ ያለሁት ለምክንያት ነው የሚለው ሐሳብ ሁሌም ይመጣብኛል፡፡ ይኼ ደግሞ ለእኔ መባረክ ነው፡፡ በዚች ታላቅ አገር ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቀባይነትን ባገኘሁ ቁጥር በታወኩ ቁጥር ለእኔ ይሄ ትልቅ ነገር ነው፤ ስጦታ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆን ከኢትዮጵያ መፈጠር ትልቅ ስጦታ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እስኪ ደግሞ ወደ ልጅነት ታሪክህ እንመለስ ከኢትዮጵያ ቤተሰቦች ተወለድክ፣ ለእንግሊዛዊ ቤተሰቦች ተሰጠህ እንደገና ደግሞ ተላልፈህ የልጆች ማሳደጊያ ማዕከል ወስጥ አደግክ፡፡ እስኪ ይኼ የልጅነት ጊዜህ የአሁኑን ለምን ሲሳይን በምን መንገድ ቀርጿል?

ለምን፡- ከምንም በላይ ብዙ አሉታዊ ነገሮች ቢያልፉም አሁን ያለሁበት ላይ ደርሻለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን ለምን በልጅነቱ በብዙ መጥፎ ነገሮች ስላለፈ በዚህም ምክንያት አሁን ያለበት ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት አይደለም፡፡ እርግጥ ነው በብዙ መጥፎ ነገሮች ውስጥ አልፌያለሁ ስለዚህ መጠየቅ ያለብኝ በዚህ ውስጥ እኔ ማን ነኝ? የሚለውን ነው በመጥፎ ነገሮች ውስጥ በማለፌ ንዴት ውስጥ ገባሁ፣ ሌሎችን ጎዳሁ ወይስ ራሴን አደጋ ላይ ጣልኩ? በተቃራኒው የእኔ መገፋት፣ ሕመምና ስቃይ የሌሎችን ሕመም እንድረዳ እንዲሁም የመዳንን ኃይል እንድረዳ አድርጎኛል፡፡ እንደ እኔ የመዳን ኃይል ከመሠረቴ ነው ሥር መሠረቴ ደግሞ ከዚሁ ከኢትዮጵያ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች እንግሊዝ ስላደገ፣ ጥሩ ትምህርት ስለተማረ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል ይላሉ ነገር ግን ጥሩ ትምህርት አልነበረኝም ነበር፣ ተጎድቼ ነበር፡፡ እኔ እማውቀው ይኼን ሁሉ አሽንፌ መምጣቴን ነው፡፡ ብዙዎቻችን በቤተሰበ፣ በማኅበረሰብ ውስጥ እንዲሁም በተለያዩ ነገሮች ስናልፍ ብዙ መጥፎ ልምዶች ሊኖሩን ይችላሉ፣ ልንጎዳ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ጥያቄው የእኛ መጎዳት ሌሎችን እንድንጎዳ መብት ይሰጠናል ወይ? የእኛ መጎዳት ሌሎችን እንድንጎዳ በፍጹም መብት አይሰጠንም፡፡ በተቃራኒው የእኛ መጎዳት የሌሎችን ሕመም፣ መገፋት እንዲሁም መነጠልን እንድንረዳ ያደርገናል፡፡ ይረዳናል፡፡ ይኼን ያህል ካወቅኩ እኔ ላይ የሆነው ሌሎች ላይ እንዲደገም አልፈልግም፡፡ ማነህ አንተ? እንግሊዛዊ ነህ? አይሪሽ ነህ ወይስ ኤርትራዊ ወይስ ደግሞ ሶማሊያዊ … ለእኔ አንተ ማለት ወንድሜ ነህ እዚህ ላይ በመተማመን አብሮ መሥራት፣ መኖር ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- እስኪ ከወላጅ እናትህ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስትግናኙ ስለነበረው ነገር ንገረኝ?

ለምን፡- የሚገርም ስሜት ነበር፡፡ የማርሸት ሲሳይ ወላጅ እናቴ በጣም የምትገርምና ጠንካራ ሴት ነች፡፡ እንደ አብዛኛው 1950ዎቹ 60ዎች ትውልድ ለትምህርት ወደ ውጭ የመሄድ ዕድል አግኝታ ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ ለትምህርት ወደ ውጭ የሄዱት የእናቴ ዓይነት ወጣቶች በዚያን ጊዜ የነበረውን የኢትዮጵያ መንፈስ ይዘው ዓለምን ዞረዋል፡፡ በጊዜው እናቴ እኔን አረገዘች ከዚያ ለጉዲፈቻ ሰጠችኝ፡፡ ብዙ ሰው የማያውቀው እናቴ ተመልሳ እኔን ለማግኘት ሞክራ እንደነበር ነው፡፡ እኔ ለሕፃናት ማዕከሉ በጻፈችው ደብዳቤ ልጇን እንደምትፈልግ፣ ልጇ በአገሩ እንዲያድግ እንደምትፈልግና በሰው አገር መገለል እንዳይደርስበት ገልጻ ነበር፡፡ በጊዜው እናቴ 21 ዓመቷ ነበር፡፡ እናቴ የሚቻላትን አድርጋ ነበር ግን እንግሊዞቹ መልሰው እኔን ሊሰጧት አልፈለጉም፡፡

ሪፖርተር፡- ለእናትህ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል?

ለምን፡- በጣም እንጂ ማሰቡ ራሱ ይከብዳል፡፡ ከዚያ እናቴ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች፣ መመለስም ነበረባት ምክንያቱም በጊዜው አባቷ ታመው ነበር ከዚያም አቶ አሸናፊ ሽፈራውን አገባች፡፡ ከዚያም ከአምስት ዓመት በኋላ ደርግ ሥልጣን ያዘ፣ ባሏ ታሰረ፡፡ ስለዚህ ለሕይወቷ ስትል አገሩን ለቃ መሄድ ነበረባት፡፡ ጠንካራ ሴት ነበረች፡፡ ከብዙ ዓመት በኋላ 21 ዓመት ሲሆነኝ እናቴን አገኘሁ፡፡ ቀላል አልነበረም በእውነቱ፣ በጊዜው እሷን ማግኘት ውብ ነበር፡፡ እሷን ማግኘት ወደ ቤት እንደመመለስ ነበር ወደ ኢትዮጵያ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልጄ፣ አድጌ ቢሆን ብለህ ታውቃለህ?

ለምን፡- እሱንማ በምን ዕድሌ፡፡ ሁሌም የምፈልገው ነው ግን ደግሞ ማግኘት ያልቻልኩት ነው፡፡ ስለዚህ ያለኝን መቀበልና ባለኝ ነገር መኖር ነው፡፡ እውነቱን ለመቀበል በልጅነቴ የሚያውቁኝ እናት፣ አባት እንዲሁም እህትና ወንድም የለኝመ፡፡ ትልቁን የሕይወት ዘመኔን ሕልምና ምኞት ልንገርህ? የልዑል ዓለማየሁ አፅም ወደ አገሩ ሲመለስ ማየት ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሕይወቱ ከእኔ ጋር ይገናኛል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የእሱ ሕይወት ከአንተ ጋር ይገናኛል ብለህ ታስባለህ ማለት ነው?

ለምን፡- በእንግሊዞች ከአገሩ ተወስዷል፡፡ አሥራ ስምንት ዓመት እስኪሞላው በካፒቴን ስፒዲ ሥር ሆኖ አድጓል፣ ከዚያም ሊድስ ወደ ተባለ ሰሜን ኢንግላንድ ወሰዱት፡፡ ከዚያም በዓመት ውስጥ ሞተ፡፡ እንደሚሉት ሞቱ የተፈጥሮ ሞት ነው ይላሉ፡፡ ለእኔ ይኼ አይዋጥልኝም፡፡ የሆነ ነገር ነበር የሆነ! ብዙ መጠናት ያለባቸው ብዙ የማናውቃቸው ነገሮች አሉ፡፡ እኔ ወደ አገሬ እንደተመለስኩ እሱም እንዲመለስ እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ራስህን ማን ነኝ የምትለው?

ለምን፡- ኢትዮጵያዊ፣ እንግሊዛዊ፣ የዓለም ዜጋ፣ የሞሎኪሎች የመንፈሶች ስብስብ፡፡

ሪፖርተር፡- ስለራስህ ስናነሳ ብዙ ሰዎች በኢትዮጵያ እንግሊዝኛ ማንበብም ሆነ መረዳት አይችሉም ሥራህን ለመተርጎም ያሰብከው ነገር አለ?

ለምን፡- የተወጠኑ ነገሮች አሉ እስካሁን ባይሳኩም፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ከኤፍሬም ሥዩም ጋር አብረን እየሠራን ነው፡፡ ጥሩ የቋንቋ ችሎታ ያለው የጥበብ ሰው ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ገጣሚዎች ኤፍሬምን እንዲሁም የበውቀቱ ስዩምን ሥራዎች አደንቃለሁ፡፡ ትልቅ የሥነ ግጥም ሀብት ያለበት አገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ ስለ መነሳሳት ወይም መነቃቃት ትናገራለህ፡፡ በአንዱም ንግግር የአንተ ዓላማ በሰዎች መነሳት ወይም ደግሞ ሰዎችን ማነሳሳት (Inspire) ማድረግ ነው ብለህ ነበር፡፡ አንተን በጠዋት አንቅቶ ግጥም እንድትጽፍ የሚያደርግህ ምንድን ነው?

ለምን፡- ሁሌም ከእንቅልፌ ስነቃ ግጥሞችን በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ እለቃለሁ ይኼን ደግሞ እስክሞት የምቀጥለው ነገር ነው፡፡ ….. ፈጠራ ሙሉ በሙሉ በአርቲስቶች ቁጥጥር የተያዘ አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው በራሱ መንገድ ፈጣሪ ነው፡፡ ስለዚህ የእኔ ሥራ መነቃቃትን ወይም ሰዎችን ማንቃት መፈለግ ነው፡፡ መማር እና ማስተማር፡፡

ሪፖርተር፡- መቼ ነው ግጥም መጻፍ እንደምትችል ያወቅከው?

ለምን፡- ለምን የሚለው ስሜ መሆኑን ከማወቄ በፊት መግጠም ጀምሬ ነበር፡፡ ለምን የሚለውን ስም ይዤ እንዴት ገጣሚ መሆን አልችልም፡፡ እንግሊዞቹ የሰጡኝን ስም ይዤ እገጥም ነበር፡፡ ስለዚህ ገጣሚ ሆኜ ነው የተወለድኩት ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ያለህ የቻንስለርነት ቆይታ ምንይመስላል?

ለምን፡- ጥሩ ነው፡፡ ለተማሪዎቼ የተስፋ ምንጭ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የራስህ ቤተሰብ የመመሥረት ሐሳብ አለህ?

ለምን፡- ምን አልባት ወደ ፊት፡፡

 

                                                                                                          

Standard (Image)

‹‹ሆስፒታላችን በሕፃናት አጥንት ቀዶ ሕክምና የልቀት ማዕከል ነው ለማለት ይቻላል››

$
0
0

ወ/ሮ አደይ አባተ፣ የኪዩር ኢትዮጵያ የልጆች

ሆስፒታል ኤክሲኪዩቲቭ ዳይሬክተር

ወ/ሮ አደይ አባተኪዮር ኢትዮጵያ የልጆች ሆስፒታል ኤክሲኪዩቲቭ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የተወለዱትና የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ወደ አሜሪካ አቅንተው የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽንና ፋይናንስ የመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በሥራ ዓለም ሲያትል በሚገኘው የቦይንግ አውሮፕላን ኩባንያ ውስጥ ተቀጥረው ያገለገሉ ሲሆን፣ በዋሽንግተን ዲሲ ለመከላከያ የሚውል ሚሳይል ማምረቻ ኩባንያ ውስጥም የፕሮግራም ማኔጀር ነበሩ፡፡ ለቡዝ አለን ሀሚልተን ሰብ ኮንትራክተርም አገልግለዋል፡፡ ታደሰ ገብረማርያምበሆስፒታሉእንቅስቃሴ ዙርያ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡-ኪዩር ኢትዮጵያ የልጆች ሆስፒታል የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች  ቢገልጹልን?

ወ/ሮ አደይ፡-ኪዩር ኢትዮጵያ የልጆች ሆስፒታል በተፈጥሮ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው በሺዎች ለሚቆጠሩ ሕፃናትና ልጆች ያለምንም ክፍያ በነፃ ዘመናዊና የተሟላ የቀዶ ሕክምና፣ ፊዚዮቴራፒና የመሰል ማስተካከያ ሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝና መንግሥታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ነው፡፡ ሆስፒታሉ የተቋቋመው ሐምሌ 19 መናፈሻ አጠገብ ሲሆን፣ ከተገነባም ዘጠኝ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ሥራውን ከጀመረ ግን ስምንት ዓመቱ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ  የልጆች፣ የአዋቂዎች የተሟላ የተመላላሽ ታካሚዎች ክሊኒክ፣ ሙሉ የምርመራ ማዕከል፣ አራት የቀዶ ሕክምና ክፍሎች የፊዚዮቴራፒ ሕክምና ክፍል፣ ፋርማሲና ላቦራቶሪ አለው፡፡ ሆስፒታሉን ያቋቋሙት በአሜሪካ የኪዮር ኢንተርናሽናል መሥራችና የአጥንት ቀዶ ሕክምና ባለሙያ ዶ/ር ስኮት ሐርሰን ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የሆስፒታሉ ወጪ በማን ነው የሚሸፈነው?

ወ/ሮ አደይ፡- የሆስፒታሉን ወጪ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ እየሸፈኑ ያሉት አሜሪካ ቴክሳስ ውስጥ የሚገኘው የሬስ ጆንስ ፋውንዴሽን መሥራችና ባለቤት ሚስተር ሬስ ጆንሰን ሲሆኑ፣ ሌሎች አሜሪካውያን ባለሀብቶችም የበኩላቸው አገዛ ያደርጉልናል፡፡ በተለይ ዩኤስአይዲ እና ሲቢኤም የተባሉት ተቋማት ለኤክስሬይና ለቀዶ ሕክምና የሚውሉ መሣሪያዎችን በመለገስ አግዘውናል፡፡

ሪፖርተር፡-ሆስፒታሉን ያቋቋሙት ባለሀብቱ ወጪውንም በቀጣይነት ለምን አይሸፍኑም?

ወ/ሮ አደይ፡-ባለሀብቱ በወቅቱ ከራሳቸው ገቢ ቀንሰው ሆስፒታሉን መሥርተዋል፡፡ ለተወሰኑ ዓመታትም ወጪውን ሲሸፍኑ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም የሕክምና ተቋሙ ከአንድ ግለሰብ በሚገኝ የገንዘብ ሽፋን ብቻ ሊቀጥል አይችልም፡፡ ስለዚህ ሆስፒታሉ የሚሰጠው አገልግሎት እየተጠናከረና የተጠቃሚውም ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የተነሳ ሌሎች በጎ አድራጊ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን መሻት ግድ ሆነ፡፡

ሪፖርተር፡- ለሕክምና ከሚመጡት መካከል አብዛኞቹ ምን ዓይነት ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው?

ወ/ሮ አደይ፡-ብዙዎቹ የአጥንት ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ክለብ ፉት (የተቆለመመ የእግር መጫሚያ) ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ እንዲሁም ጉልበትና ጉልበት የመጋጨት፣ የአከርካሪ ችግሮች ያሉባቸው፣ በመውደቅ የአካል ጉዳት ያጋጠማቸው ሁሉ አሉ፡፡ በእሳት ቃጠሎ አደጋ የቆዳ መጨማደድ ችግር ያለባቸው ብዙ  ልጆች ነገር ግን በዚህ ጉዳት ለሚደርስባቸው ልጆች ያዘጋጀነው አልጋ አምስት ብቻ ነው፡፡ ሆስፒታሉ የሚቀበለው ደግሞ ባለው አልጋ ቁጥር ስለሆነ ለሕክምና በሚመጡት በዚሁ መጠን ቁጥራቸው አነስተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሆስፒታሉ በተሟላ የሕክምና መሣሪያ የተደራጀ ነው ወይስ ገና ይቀረዋል?

ወ/ሮ አደይ፡-ትልቁ ጥቅማችን እጅግ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችን መያዛችን ነው፡፡ ወይም በየትኛውም ያደጉ አገሮች ውስጥ ያለው ዓይነት መሣሪያ በኛም ሆስፒታል መኖሩን በእርግጠኝነት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ኪዮር ኢትዮጵያ የልጆች ሆስፒታል በአገር ውስጥ ከሚገኙ የመንግሥትና የግል ሆስፒታሎች ለየት የሚያደርገው ምንድንነው?

ወ/ሮ አደይ፡-በልጆች አካል ጉዳት ላይ ከኪዩር ሆስፒታል በስተቀር በብዛት የሚሠራና ስፔሻላይዝ ያደረገ ሌላ ሆስፒታል የለም፡፡ ነገር ግን አንድ ታካሚ ጥቁር አንበሳ ወይም ሌላ ሆስፒታል ሂዶ ይኼን ዓይነቱን ሕክምና አያገኝም ማለት አይደለም፡፡ የልጆች አጥንት ሕክምና ላይ ስፔሻላይዝ ያደረገ ኪዩር ኢትዮጵያ የልጆች ሆስፒታል ብቻ ነው፡፡ ልዩ የሚያደርገን በልጆች አጥንት ቀዶ ሕክምና ላይ ብቻ ሳይሆን ለአዋቂዎችም ጭምር ነው፡፡ በተረፈ ለአዋቂዎች የጉልበት መቀየሪያ (ኒል ሪፕለስመንት) በሆስፒታላችን ብቻ ይሰጣል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ከዚህም ሌላ ለየት የሚያደርገን ለልጆች ወይም ስኳር፣ ኩላሊትና ሌሎች በሽታዎች ላለባቸውና በዕድሜ ለገፉ አዋቂዎች ከቀዶ ሕክምና በፊት ሰመመን ወይም ማደንዘዣ (አኒስቴዢያ) አሰጣጥ ነው፡፡ በሆስፒታላችን ውስጥ ሰመመን የሚሰጡ ነርሶች ብቻ ሳይሆኑ ሁለት ዶክተሮችም አሉን፡፡ የሰመመን መርፌ ማለት ለተወሰነ ሰዓት በማስተንፈሻ መጠቀም ማለት ነው፡፡ በታካሚው ላይ አንድ ችግር ቢከሰት ሰመመን ሰጪው ባለሙያ በቀጣዩ ምን መሠራት እንዳለበት የሚያውቀው፡፡

ሪፖርተር፡- በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉት ልዩ ልዩ የሕክምና ባለሙያዎች በቋሚነት የሚሠሩ ናቸው ወይስ ጥሪ ሲደረግላቸው እየመጡ የሚሠሩ?

ወ/ሮ አደይ፡-ሁሉም ቋሚ ናቸው፡፡ በተረፈ ከአንገት በላይ፣ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸውን የሚያክሙት በዓመት ሁለቴ ወይም ሦስቴ እየመጡ የሚሠሩ ናቸው፡፡ እነሱም የሚመጡት በማስታወቂያ ጥሪ ሲያደርግ ነው፡፡ ካሉን የሕክምና ባለሙያዎች መካከል ስድስቱ የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ የቀሩት የውጭ አገር ዜጎች ናቸው፡፡ የቀዶ ሕክምና ሐኪሞቻችን ኬንያ በሚገኘው የማሰልጠኛ ማዕከላችን ገብተው በልጆች የአጥንት ቀዶ ሕክምና ላይ ሰልጥነው የተመለሱ ናቸው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ የፕላስቲክ ሰርጀሪ ሐኪምም አለን፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ በሕክምና ላይ ያሉት ሕፃናት ስንት ይሆናሉ?

ወ/ሮ አደይ፡-በጠቅላላው 50 ሕፃናት ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ጋር ያላችሁን ግንኙነት እንዴት ይገልጹታል?

ወ/ሮ አደይ፡-በጣም ቅርብ የሆነ ግንኙነት ያለን በተለይ ከአጥንት ቀዶ ሕክምና  ዲፖርትመንት ጋር ነው፡፡ አጥንት ሕክምና ላይ የሚማሩ ዶክተሮች ሆስፒታላችን ይመጡና ከኛ ዶክተሮች ጋር በሕፃናት የአጥንት ቀዶ ሕክምና አብረው እየሠሩ፣ እየሰለጠኑና ስፔሻላይዝድ እያደረጉ ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ የአነስቴዢያ (የሰመመን) ተማሪዎች ናቸው፡፡ እዚህ እየመጡ በአንስቴዢያ አሰጣጥ ላይ ስልጠና ይከታተላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ኪዩር ኢንተርናሽናል የልጆች ሆስፒታልና የልቀት ማዕከል (ሴንተር ኦፍ ኤክስለንስ) ነው ለማለት ይቻላል?

ወ/ሮ አደይ፡-እንችላለን፡፡ ስም ብቻ እንዳይሆንም አጥብቀን እየሠራን ነው በተለይ የሕፃናት አጥንት ቀዶ ሕክምና እና አነስቴዢያ ላይ የልቀት ማዕከል ነን ለማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ለዚህ ሲባል ሌሎች አገሮች ያመጡትና እኛም የተቀበልናቸው መስፈርቶች ስላሉ ማሟላት አለብን ብለን እየሠራን ነው፡፡ ምክንያቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጡትን ስታንዳርዶች ለማሟላት የሚቀሩን አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር ያላቸው ግንኙነት በምን ደረጃ ላይ ነው?

ወ/ሮ አደይ፡-ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሆነ ከቢሮው ጋር በቅርበት እየተረዳዳን እየሠራን ነው፡፡ በተለይ ሚኒስቴሩ ይቆጣጠረናል፡፡ የተሳሳተ ነገር ካለ ያርመናል፡፡ ከዚህ የበለጠ መሥራት አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ በሕፃናት አጥንት ቀዶ ሕክምና ላይ በይበልጥ እኛ ስለምንሠራ የዕውቀት ሽግግሩ ላይ መተጋገዝ ወይም ማዳበር ይኖርብናል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ሆስፒታሉን የማስፋፋቱን ጉዳይ እንዴት ይዛችሁታል?

ወ/ሮ አደይ፡-የማስፋፋት ሥራ ጀምረናል፡፡ አዲስ ያስገባነው የመልሶ የማስተካከያ (ሪሀብሊቴሽን) ሕክምና ዋርድ በቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ ሚያዝያ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ከዚህም ሌላ የአከርካሪ አጥንት ላይ ችግር ያለባቸው ልጆች በብዛት ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ካሉን ሌላ ሁለት ተጨማሪ የቀዶ ሕክምና ክፍል ለማቋቋም አስፈላጊውን እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ የሚቋቋመው ክፍል የአከርካሪ አጥንት ችግር ላለባቸው ልጆች አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  ለአዋቂዎች ሕክምና አገልግሎት መስጠት ጀምሯችሁ አቋርጣችኋል፡፡ ለምን?

ወ/ሮ አደይ፡- 95 ከመቶ ያህሉ አገልግሎታችን ለሕፃናት ብቻ ነው፡፡ የተቀረው ግን እየተከፈለ የሚሰጥ ሕክምና ሲሆን፣ ለዚህም የሚሆን አራት አልጋዎች አሉ፡፡ የምንሰጠው አገልግሎት የታፋ መቀየር ነው፡፡ ይህም ከባድ ቀዶ ሕክምና የሚጠይቅ ነው፡፡ አንድ ታካሚ ውጭ አገር ሄዶ ከሚያገኘው ሕክምና የበለጠ ሕክምና እንሰጣለን፡፡  የአዋቂዎች ሕክምና ለተወሰነ ገቢ ማሰባሰቢያ እንዲሆነን ለማድረግ ሲባል ነው የጀመርነው፡፡ ምክንያቱም ዕድሜ ልክ በዕርዳታውና በልመና መኖር የለብንም፡፡ 20 ከመቶ ያህል ገቢያችንን በራሳችን ማሰባሰብ አለብን በሚል መንፈስ የተጀመረ ነው፡፡ 95 ከመቶ በነፃ አገልግሎት ሰጥተን የቀረውን አምስት በመቶ ያህሉ እያስከፈልን አገልግሎት ብንሰጥ 20 በመቶ ያህል ገቢ ልናገኝ እንችላለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ይህ ዓይነቱ አገልግሎት ለጊዜው ተቋርጧል፡፡ ይህም የሆነው አገልግሎቱና አፈጻጸማችን ከአገሪቱ ሕግና ደንብ ጋር ስላልተጣጣሙ ነው፡፡ ነገር ግን አገልግሎቱ በተቋረጠበት ጊዜ ሕክምና የጀመሩ የቀድሞ ታካሚዎችን እንድናክም ተፈቅዷል፡፡ በተረፈ መደበኛውን አገልግሎት ለመቀጠል ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር ውይይት እያደረግን ነው፡፡

 

 

Standard (Image)

ትምህርትን በቴክኖሎጂ የማዘመን ጉዞ

$
0
0

የአሁኑ የትምህርት ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽንስ ቴክኖሎጂ ማዕከል እ.ኤ.አ. በ1964/65 የኦዲዮ ቪዥዋል  ማዕከል ተብሎ ሲመሠረት አጠቃላይ የአገሪቱን ትምህርት በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ለመደገፍና ከኢትዮጵያም አልፎ ለምሥራቅ አፍሪካ እንዲያገለግልም ነበር፡፡ የትምህርት በሬዲዮው እያደገ  ከአዲስ አበባ አካባቢ ‹‹ለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ›› አልፎ በየክልሎችም ተመሳሳይ የትምህርት በሬዲዮ ጣቢያዎች ተመስርተዋል፡፡ ኦሮሚያ ባሌ ሮቤ፣ ሐረር፣ ጊምቢ፣ ጎሬና በሌሎችም ትምህርት በሬዲዮ ይተላለፋል፡፡ በደቡብ ይርጋለምና ሶዶ ያለ ሲሆን፣ የመጀመርያው የትምህርት በሬዲዮ ማሰራጫ የነበረውም ሶዶ ያለው ነው፡፡ የአማራ ክልል አራት ጣቢያዎች አሉት፡፡ ደቡብም እያስፋፋ ነው፡፡ የሌላቸው የኢትዮጵያ ሱማሌ፣ አፋርና ቤኒሻንጉል ሲሆኑ፣ በእነዚህም ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ከንኑሡ ጊዜ አንስቶ ለሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ብቻ ይሰጥ የነበረው ትምህርት በቴሌቪዥን ተስፋፍቶ ፕላዝማ ላይ ደርሷል፡፡ የፕላዝማ ትምህርቱ የሚሰጠውም ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ነው፡፡ ዶ/ር ገበየሁ ወርቅነህቦጋለየትምህርት ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በማዕከሉ ከ1979 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ሙያዎች ሠርተዋል፡፡ ማዕከሉ ትምህርት ቤቶችን በቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዙርያ ምሕረት ሞገስአነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡-ትምህርት በቴሌቪዥን ሲጀመር ሥርጭቱ የት ድረስ ነበር?

ዶ/ር ገበየሁ፡-  ሥርጭቱ አዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱና አዳማ አካባቢ ድረስ ነበር፡፡ ሰባተኛና  ስምንተኛ ክፍሎች ተጠቃሚ የነበሩ ሲሆን፣ የሚተላለፍበት ቴክኖሎጂም መሬት ለመሬት (ቴሪስቴሪያል) ነበር፡፡ በመሆኑም ተራራ ካለ ሞገዱን ያግደዋል፡፡ ተራራማ አካባቢ ካልሆነ ከእነዚህም አካባቢዎች አልፎ ይደርስ ነበር፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል አሁን ኢቢሲ በተባለው ጣቢያ እየገባ የተወሰነ ገንዘብ እየከፈልን ይሰራጭ ነበር፡፡ ቴሪስቴሪያሉ በቂ ስላልነበረና የመምህራንና የተለያዩ የትምህርት መርጃዎች እጥረት ስላለ ይህንን ለመደገፍ ሲባል ከቴሪስቴሪያሉ ወደ ሳተላይት ገብተናል፡፡

ሪፖርተር፡-ይህ መቼ መሆኑ ነው? ፕላዝማ ወደምንለው የተሸጋገረበት ነው?

ዶ/ር ገበየሁ፡-አዎ በ1995 ዓ.ም. ሥራው ተጀምሮ ወደ ሥርጭት የተገባው በ1996 ዓ.ም. ነው፡፡ በቴሪስቴሪያል የነበረውን ወደ ሳተላይት ከመቀየር ባለፈም ትምህርት በቴሌቪዥን የሚሰጥባቸው ክፍሎችም ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ሆኗል፡፡ የሬዲዮውን ክልሎች እንዲይዙት ተደርጓል፡፡ የቴሌቪዥኑ በማዕከሉ ይመራል፡፡ 12 የቴሌቪዥን ማሰራጫ ቻናል ያለን ሲሆን፣ ፕሮግራሙ ከማዕከሉ ለየትምህርት ቤቶቹ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡-ሥርጭቱ ለሁሉም ክልሎች ተሟልቶ ይሄዳል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ገበየሁ፡-ኔትወርክ ባለበት አካባቢ በሙሉ ይደርሳል፡፡ ሥርጭቱን መደበኛው ማለትም በየቤታችን የምንጠቀምበት ዲሽ አይቀበለውም፡፡ ለፕላዝማው የተለየና ሲባንድ የተባለ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በየትምህርት ቤቶቹ ዲሽ ይተክላል፡፡ እያንዳንዱ የትምህርት ክፍልም በኔትወርክ ይያያዛል፡፡ ይህ የተያያዘላቸውና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባላቸው ትምህርት ቤቶች ይሠራል፡፡ ተማሪዎች ወይም መምህሩ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ካላጠፉት በስተቀር ይሠራል፡፡ እንደ ድሮው የመልክዓ ምድር አቀማመጡ ተፅዕኖ አይፈጥርበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ፕላዝማ ትምህርት ሲጀመር ከኔትወርክ፣ ከመምህር ፍላጎት፣ ከአስፈላጊነቱ ጋርም ተያያዞ ጥያቄ ሲነሳ ነበር፡፡ ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርት በፕላዝማ ቴሌቪዥን ለመስጠት ሲታቀድ የነበረው ሒደት ምን ይመስል ነበር?

ዶ/ር ገበየሁ፡-  በወቅቱ የማስተዋወቅ ችግር ነበር፡፡ ጥናት ተካሂዶ መምህሩና ተማሪው እንዲሳተፍ ባላመደረጉ እጥረት እንዳለ ታውቋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ትምህርት በቴሌቪዥን ቀድሞም ነበረ፡፡ በ1995 ዓ.ም. የተደረገው የማስፋፋት፣ የማሻሻልና የማዘመን ሥራ ነው፡፡ ከቴሪስቴሪያል ወደ ሳተላይት፣ ከሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ወደ ከዘጠኝ እስከ 12 እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ሆኖም ይህንን ለኅብረተሰቡ ቀድሞ የማስተዋወቅ ሥራ ይጠበቅብን ነበር፡፡ መምህራንን ይተካል ይባል የነበረውም፣ በፊት ስንጠቀምበት የነበረው ትምህርት በቴሌቪዥን ለ15 ደቂቃ ሆኖ፣ የፕላዝማው 30 ደቂቃ በመሆኑ ነው፡፡ የትምህርት ቤቶች አንድ የትምህርት ክፍል ጊዜ ደግሞ 40 ደቂቃ ነው፡፡ 30 ደቂቃ የፕላዝማ ትምህርቱ ከያዘ መምህሩ 10 ደቂቃ ነው ይኖረዋል፡፡ መምህሩ በዚህ ምንም መሥራት ስለማይችል መምህር ሊተካ ነው የሚል ስሜት ተንፀባርቋል፡፡ ይህንን ቀድመን ከመምህሩና ከኅብረተሰቡ ጋር ተነጋግረን ቢሆን ኖሮ ክፍተቱ አይፈጠርም ነበር፡፡ አንዳንዴም ወዳልተፈለገ ፖለቲካ ተቀይሮ ብዙ ነገር ይራገብበት ነበር፡፡ ይህም አግባብ አልነበረም፡፡ መምህሩ በውዥንብር ውስጥ ሆኖ ቢናገርም አይፈረድበትም፡፡ ምክንያቱም ማዕከላችንም አላስተዋወቀም፣ ለስንት ደቂቃ ቢሆን ይሻላል የሚለውንም ከመምህሩ ጋር አልመከርንም፡፡

ሪፖርተር፡-ከዚህስ በኋላ እንዴት ሄዳችሁበት?

ዶ/ር ገበየሁ፡-  ከአመራሩም ከኅብረተሰቡም በዚህ መልኩ መሄድ አይቻልም የሚል አስተያየት ሲመጣ፣ ከመምህራንና ከትምህርት ማኅበረሰቡ ጋር ተመካክረን የፕላዝማ ትምህርት ደቂቃውን ወደ 20 ዝቅ አደረግነው፡፡ የመማሪያ መጻሕፍቱንም እንደ መጀመርያው ከሀ እስከ ፐ ሳይሆን ከመምህራን ጋር ቁጭ ብለን የትኛው በቴሌቪዥን ቢታገዝ ጥሩ ነው፣ የትኛውስ ክፍል በመምህሩ መሸፈን አለበት ብለን ከፋፈልነው፡፡ ይህንን ያደረግነው ከየክልሉ ከመጡ መምህራን ጋር ነው፡፡ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮም ተግባራዊ ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡-ይህን ስታደርጉ ምን ዓይነት ግብረመልስ አገኛችሁ?

ዶ/ር ገበየሁ፡-በፊት የነበረው ዓይነት ክፍተት የለም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቴክኖሎጂውን እየወደዱት ነው፡፡ ሆኖም እጥረቶች አሉ፡፡ ከቴሌ ጋር የተያያዙ የኔትወርክና የሞጁሌተር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ከኛም ጋር የተያያዙ ቴክኒካል ችግሮች አንዳንዴ ያጋጥማሉ፡፡ መምህራንንና ርዕሰ መምህራንን በደንብ ስላላሰለጠንን አጠቃቀም ላይም ችግሮች ይታያሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለወደፊት ተጠናክረን እስካልሞላን አሁንም ችግሮቹ ይቆያሉ፡፡ እዚህ ላይ ሦስት ነገሮችን እናያለን፡፡ የአጠቃቀም ክህሎት፣ ወደ አዲስ ቴክኖሎጂ ሲገባ በቀላሉ ያለመቀበልና የአመለካከት እንዲሁም የመሠረተ ልማት ችግሮች አሉ፡፡ የቴክኒክ ዕቃዎችን በአግባቡ አሟልቶ ከመጠቀምና የቴክኒክ ባለሙያዎችን ከማሰማራት አንፃርም ችግሮች ይታያሉ፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ ችግሮች ትምህርቱ በሥርዓት እንዳይዳረስ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ፡፡ ቴክኖሎጂው በአግባቡ ካለመተግበር ጋር ተያያዞ ችግሮች ሲያጋጥሙ ክፍተቶች በምን ይሞላሉ? ኔትወርክ ሳይኖር ትምህርቱ በምን ይሸፈናል?

ዶ/ር ገበየሁ፡-ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በየ15 ቀኑ ስብሰባ አለን፡፡ ችግር ካለ ከቴሌዎች ጋር እንነጋገራለን፡፡ እነሱም ከክልሎች ጋር ተነጋግረው መፍትሄ ይሰጣሉ፡፡ በየክልሉ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች አሉ፡፡ ባለሙያዎቹም ማዕከላችንም የሚቻለውን ያህል ያሰለጥናሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ ዓይነት ቴክኖሎጂ ብቻ ይዞ ሁሌ መጓዝ አይቻልም፡፡ በየጊዜው ይቀያየራል፡፡ ከሬዲዮ ቴሌቪዥን ብንደርስም ቴክኖሎጂው ወደ ኮምፒውተር፣ ኢንተርኔትና ታብሌት አድጓል፡፡ በመሆኑም ክልሎች በየትምህርት ቤታቸው የኮምፒውተር ቤተ ሙከራ በማቋቋም ላይ ናቸው፡፡ ማዕከሉም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ መቆራረጦችን ለማስቀረትም እየሠራን ነው፡፡ በተለያየ ምክንያት የፕላዝማ ትምህርቱ ላመለጣቸው ቅዳሜ ጠዋት የሚተላለፍበት ፕሮግራም አለ፡፡

ሪፖርተር፡- የፕላዝማ ሥርጭቱ በመላ አገሪቱ በምን ያህል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይሰራጫል?

ዶ/ር ገበየሁ፡-ቁጥራቸው በየጊዜው እየጨመረ ነው፡፡ አሁን ወደ 3,000 የሚጠጉ ሁለተኛ ደረጃ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ እነዚህን በሙሉ ማዳረስ ይከብዳል፡፡ ዘንድሮ የተከፈተን ትምህርት ቤት ሁሉንም ቁሳቁስ አሟልቶ ማስጀመር ያስቸግራል፡፡ የኤሌክትሪክ፣ የቪሳት ዲሽ (ኢትዮቴሌኮም የሚተክለው) ያስፈልጋል፡፡ 1624 ትምህርት ቤቶች ሁሉም ነገር የተሟላላቸው ናቸው፡፡ ሆኖም ሁሉም ፕላዝማ ይጠቀማሉ ማለት አይደለም፡፡ ወደ 1,000 የሚጠጉት ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ እየተጠቀሙበት ነው ማለት እንችላለን፡፡ ቀሪዎቹ ከአጠቃቀምና ከመብራት ጋር ተያይዞ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ ከእኔና ከፕላዝማ ማን ይሻላል የሚሉ መምህራን እንዳሉም ሰምተናል፡፡ የማስተማር አዎንታዊ ፍላጎት ያላቸው መምህራንም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡-የፕላዝማ ትምህርት ሥርጭት ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የራሱ ባለሙያ ያስፈልገዋል፡፡ ከዲሹ፣ ከኔትወርኩና ከሌሎችም ጋር የተያያዙ የቴክኒክ ችግሮች ሲያጋጥሙ እዛው ሊያስተካከል የሚችል ባለሙያ በየትምህርት ቤቱ አለ?

ዶ/ር ገበየሁ፡-ከፍተኛ የሆነው ችግር ይህ ነው፡፡ ከፍተኛ ብልሽት ሲገጥም ከማዕከላችን ባለሙያዎች ይሄዳሉ፡፡ እያንዳንዱ ክልልም የቴክኒክ ባለሙያዎች አሉት፡፡ ችግር ሲኖር የሚጠሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ሆኖም ለምሳሌ ኦሮሚያ ባሌ አካባቢ ከፍተኛ ችግር ቢያጋጥም ክልሉ ባሌ ባለሙያ እስኪልክ ሁለት ቀን ሊወስድ ይችላል፡፡ ይህ ከሚሆን ማዕከላችን እየመከረ ያለው በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት አንድ ባለሙያ ይኑር ነው፡፡ ክልሎች ደግሞ የበጀት ችግር ያነሳሉ፡፡ ሆኖም ለምሳሌ አማራ ክልል በየትምህርት ቤቶቹ ባለሙያ ቀጥሯል፡፡ አንዳንድ ክልሎች ደግሞ የላቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- ዕቅዳችሁ ፕላዝማ ቴሌቪዥን ላይ ለመቆየት ሳይሆን ወደ ኮምፒውተር ቤተ ሙከራም መሄድ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ባለሙያ የግድ ነው?

ዶ/ር ገበየሁ፡-ይህ ትክክል ነው፡፡ በየትምህርት ቤቱ ባለሙያ ከሌለ በስተቀር በአንድ ቤተ መኩራ 50 እና 60 ኮምፒውተር አስቀምጦ መጠቀም ከባድ ነው፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ከኮምፒውተር ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲያጋጥሙ እንኳን ባለሙያ ወዲያው ይጠራል፡፡ በየትምህርት ቤቱም የቴክኒክ ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡ ይህ መደረግ እንዳለበት በከፍተኛ አመራሩም በእኛም ተነግሯል፡፡ አንዳንድ ክልሎች ሰምተውናል፡፡ ቴክኖሎጂውን ከተጠቀምን ባለሙያ በየትምህርት ቤቱ ያስፈልገናል፡፡

ሪፖርተር፡-  ማዕከሉ ሲቋቋም የነበረውን አገልግሎት እያሰፋና የትምህርት አሳጣጡን እያዘመነ ነው፡፡ ስሙም የትምህርት ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ተብሏል፡፡ ትምህርት ቤቶችን ምን ያህል በቴክኖሎጂው እያዘመነ ነው?

ዶ/ር ገበየሁ፡-መንግሥት ያቅሙን ያህል ቴክኖሎጂውን በየትምህርት ቤቶች ለማዳረስና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ሁሉም አካባቢ ባሉ ሬድዮኖች ተማሪዎች በየቋንቋቸው እንዲማሩ እየተደረገ ነው፡፡ ወደ 36 ሺሕ የሚደርሱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ ለእነዚህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን እናሟላለን ብንል ከአገሪቱ አቅም በላይ ነው፡፡ በመሆኑም አንደኛ ደረጃን በሬዲዮ፣ ሁለተኛ ደረጃን በቴሌቪዥን ትምህርት እየረዳን ነው፡፡ ይህንኑ ዘመናዊ ለማድረግ ወደ ኮምፒዩተር ቤተ መኩራ ስናቀና ታብሌትም እየመጣ ነው፡፡ ቢሆንም ክልሎች የኮምፒውተር ቤተሙከራ እንዲኖር ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከሌሎች ክልሎች የተሻሉ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ግቢ ውስጥ የመረጃ ቋት (Data Center) አለ፡፡ በዚህ በቀጥታ በ65 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች (አዳዲሶቹ አሁን ላይኖራቸው ይችላል) በኔትወርክ ተያይዘዋል፡፡ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለው መቀበያ (Server) ከመረጃ ቋቱ፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ክፍል ካለ ፕላዝማ ጋር ስለተያያዘ ተማሪዎች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶችም ከማዕከሉ ወይም ከትምህርት ቢሮው መረጃ ቋት እየተቀበሉ ያስተምራሉ፡፡ ማዕከላችንም ዓላማው ይህ ነው፡፡ በገጠር ትምህርት ቤቶችስ እንዴት ነው ለሚለው መነሻ ጥናት በማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ 120 ትምህርት ቤቶችን ለእያንዳንዳቸው 40 ኮምፒውተር በኔት ወርክ አያይዘናል፡፡ ኮምፒውተሮችም ከፕላዝማው ጋር ተያይዘዋል፡፡

ሪፖርተር፡-ይህ ተማሪዎች ከትምህርት ክፍለ ጊዜው ቀድመው ትምህርቱን እንዲያገኙ ያስችላል?

ዶ/ር ገበየሁ፡-የኮምፒውተር ቤተ ሙከራ ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም መምህራንም ሆኑ ተማሪዎች ቀድመው የትምህርት መርጃውን ማግኘትና ማጥናትም ይችላሉ፡፡ ሆኖም ቀድመን እንዳነሳነው የቴክኒክ ባለሙያ ኖሮ፣ መምህራን በደንብ ሰልጥነው ተግባራዊ ለማድረግ ካልተቻለ ኮምፒውተሩ በየቤተ ሙከራው ቢቀመጥ ዋጋ የለውም፡፡ ፕላዝማ ቴሌቪዥን አሜሪካ ሲጠቀሙ አይተናል፡፡ በኔትወርክ የተያያዘ ሲሆን፣ እያንዳንዱ መምህርም የፕላዝማውን ቴክኒክ ያውቀዋል፡፡ ይህ የሆነው መምህራን ስለሰለጠኑ ነው፡፡ የኛንም መምህራንና ርዕሰ መምህራን ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ እንዲሰለጥኑ ማድረግ አለብን፡፡ የአይሲቲ ማኔጅመንትም ያስፈልጋል፡፡ ቴክኖሎጂው ላይ ሥልጠና ካልሰጠን ዕቃውን ብናሟላ ዋጋ የለውም፡፡ እኛም ሥልጠናውን እያገዝን ቴክኖሎጂው እንዲስፋፋ ጥረት እያደርግን ነው፡፡ ለምሳሌ አማራ ክልል አምና ወደ 7,000 ኮምፒውተሮች ለትምህርት ቤቶች ገዝቷል፡፡ የማስፋፋትም ዕቅድ አለው፡፡ ሌሎችም ክልሎች ዕቅድ ይዘዋል፡፡ አዲስ አበባ፣ ሐረርና ድሬዳዋ እያሟሉ ነው፡፡ አሮጌውን ጥለን አዲሱን ለማድረግ ሙሉ አቅሙ ስለሌለን ያሉትን በኔትወርክ እያገናኘን ትምህርት ቤቶችን ለማዘመን ቴክኖሎጂውን እያስፋፋን ነው፡፡ ስሙን የትምህርት ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ያልነው ሬዲዮና ቴሌቪዥን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ቴክኖሎጂዎች አማክሎ እንዲሄድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን የተነጋገርንባቸው ቴክኖሎጂዎች ከአንድ ማዕከል የሚላኩ ናቸው፡፡ የመረጃ ልውውጡ ወይም ትምህርቱ በቀጥታ ሥርጭት የሚሆንበት፣ ተማሪዎችም ከማዕከል ከሚኖሩ መምህራን ጋር በቀጥታ የሚወያዩበትን ቴክኖሎጂ ለማምጣት ምን ታስቧል?

ዶ/ር ገበየሁ፡-የፕላዝማ ቴሌቪዥን ሲጀመር ሁለቱንም ወገን የሚያሳትፍ ማለትም (ቱ ዌይ ኦዲዮ ዋን ዌይ ቪዲዮ) በሚል ነበር፡፡ ሁኔታዎች ስላልተመቻቹ ከሁለቱም ወገን የሚለውን በአንድ ወገን ኦዲዮና ቪዲዮ አድርገነዋል፡፡ ከመጀመሪያው ጥናቱ የተሠራው ግን ይህንን ለማድረግ ነበር፡፡ እንደዚህ ግን አይቀጥልም፡፡ 120 ትምህርት ቤቶችን በኔትወርክ አያይዘናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአዲስ አበባ 65 ትምህርት ቤቶች ተያይዘዋል፡፡ ሥርጭቱ የሁለት ወገን መስተጋብር እንዲኖረው በማዕከሉ የመረጃ ቋት ለማቋቋም ታስቧል፡፡ የቻይና ኩባንያ ጨረታውን ያሸነፈ ሲሆን፣ በስምንት ወር እንዲጨርስ ተዋውሏል፡፡ በክላውድ ቴክኖሎጂ ማለትም ትምህርት ቤቶች መረጃ የሚለዋወጡበት መረብ የሚዘረጋ ይሆናል፡፡ 1064 ትምህርት ቤቶች ኢንተርኔት ገብቶላቸዋል፡፡ ዕቅዳችን የትምህርት አሰጣጡን ከአንድ ወገን ወደ ሁለት ወገን ምልልስ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሚኒስትሮች በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ያለውን እንቅስቃሴ ከያሉበት ሆነው ማወቅ የሚችሉበትን ቴክኖሎጂም ማስረፅ ነው፡፡ በዚህ የትምህርቱን ይዘት፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜና ሌሎች መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡ ወላጆችም የልጆቻቸውን መረጃ ለማግኘት መክፈቻ (Password) ተሰጥቷቸው ስለትምህርቱ ሆነ ስለልጆቻቸው የሚከታተሉበት ሥርዓት ይኖራል፡፡ ቴክኖሎጂውን እስከዚህ ለማድረስ አስበናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለወላጅ መክፈቻ (Password) ሊሰጥ ነው፡፡ ተማሪዎችም በኢንተርኔት ሊገናኙ ነው፡፡ በመሆኑም የኢንተርኔት ደህንነት ወሳኝ ነው፡፡ የኮምፒውተር (የሳይበር) ጥቃት እንዳይደርስ ምን ታስቧል?

ዶ/ር ገበየሁ፡-በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መክረናል፡፡ ይህንን ብቻችንን አንሰራም፡፡ ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ማዕከሉ ተጠሪነቱ ለትምህርት ሚኒስቴር ቢሆንም፣ በየጊዜው እንነጋገራለን፡፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ከኛ ጋር ይሠራል፡፡ ይህ የአገር ጉዳይ ነው፡፡ የተነሳው ሥጋት በሙሉ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ለተማሪዎችም ኢንተርኔት ዝም ተብሎ አይለቀቅላቸውም፡፡ ትምህርትና ትምህርት ነክ የሆኑ መረጃዎች ብቻ ተገድቦ ይለቀቅላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል አሁን 120 ትምህርት ቤቶች ጋር ነው እንዲህ ዓይነቱ ሲስተም ያለው፡፡ ሌሎቹስ ትምህርት ቤቶች? ስለዚህ የሁሉም መሠረተ ልማት መሟላት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡-ቴክኖሎጂው ውድ ነው፡፡ ወጪያችሁ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ገበየሁ፡-በቅርቡ ለምሳሌ አንድ 20 ደቂቃ ያለው 120 ፕሮግራም (Episode) በአማርኛ ለማሠራት ጨረታውን ያሸነፈው አገር ውስጥ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ነበር፡፡ 18 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል፡፡ በጣም ውድ ነው፡፡ አምስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍለን ከዚህ ቀደም አሠርተናል፡፡ የፕላዝማ ፕሮግራሙ ሲጀመርም ብዙ ተከፍሏል፡፡ ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል በሚሰጥበት ጊዜ ግን በራሳችን ባለሙያ እናሠራ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡-  ማዕከሉ ለምን በራሱ ባለሙያዎች፣ ምሁራንና ኤክስፐርቶች ለማሠራት አልቻለም?

ዶ/ር ገበየሁ፡- በ1996 ዓ.ም. ሁሉንም መጽሐፍ ወደ ቴክኖሎጂው በምናስገባበት ወቅት በቂ ባለሙያና ዕቃ አልነበረንም፡፡ አሁን የሰው ኃይል አጠናክረን መግባት ይጠይቀናል፡፡ 12 ቻናል አለን፡፡ ትምህርት ነክ ጉዳዮች እንዲተላለፉበት ለኅብረተሰቡም አንዱን ቻናል ማዋል እናስባለን፡፡ ያልተማረው ጭምር ግብርናውን እንዴት ማቅናት ይችላል፣ ጤናውን እንዴት ይጠብቅ? በሚል እንዲሠራበት እያሰብን ነው፡፡ አንዷን ቻናል ከናይልሳት ጋር ለማያያዝ እሥራኤል ካለው ኩባንያ ጋር ተነጋግረናል፡፡ በዓመት 3መቶ ሺሕ ዶላር ትከፍላላችሁ ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማስተማር ከቻልን ብሩ ብዙ አይባልም፡፡ ኢንሳም አዲስ ሳተላይት እናስጀምራለን ብሎናል፡፡ ፕሮግራሞቻችንን የሚሠሩ የራሳችን ባለሙያዎች እንዲኖሩን ከትምህርት ሚኒስትሩ ጋር ተወያይተናል፡፡ የትምህርቱን ይዘት የሚያዘጋጅ ባለሙያ ግድ ነው፡፡ ቀጥታ ሥርጭትና ትምህርቱ ከሁለቱም አቅጣጫ እንዲሆንም በአዲስ መልክ ተጨማሪ ባለሙያ ያስፈልገናል፡፡ ጥሩ ክፍያ መኖርም አለበት፡፡ ይህን ያሰብንበትና የከፍተኛ አመራሩን ውሳኔ የሚጠይቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-ወደ ቴክኖሎጂው እየተገባ ባለበት ሰዓት ተማሪዎች ሁለተኛ ደረጃ ሲደርሱ ለኮምፒውተር አጠቃቀም አዲስ መሆን የለባቸውም፡፡ በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች የኮምፒውተር ትምህርት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጣል፡፡ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲጀመርና ተማሪዎች ከሥር ክህሎት ይዘው እንዲያድጉ ለማድረግስ ታስቧል?

ዶ/ር ገበየሁ፡- እያንዳንዱ ትምህር ቤት ቴክኖሎጂው ተሟልቶለት ቢሄድ ደስ ይለናል፡፡ መንግሥትም ያስባል፡፡ በኮሪያ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሶፍትዌር ዴቨሎፕመንት ይማራል፡፡ የኛ ኮምፒውተር ነክቶ የማያውቅ ነው፡፡ በዘመነ ሉላዊነት (Globalization) እነዚህን ልጆች ማወዳደር አይቻልም፡፡ ይህ እንዳይሆን በቴክኖሎጂ ለማስታጠቅ ጥረት አለ፡፡ ሆኖም አንደኛ ደረጃንም ለማዳረስ አቅም አይፈቅድም፡፡

ሪፖርተር፡-የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን በቴክኖሎጂው ታግዛላችሁ፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች ከቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑና መረጃ እንዲያገኙ ዕድሉን ትሰጣላችሁ?

ዶ/ር ገበየሁ፡-የግልም ተማሩ የመንግሥት ሁሉም የአገራችን ዜጎች ናቸው፡፡ አቅሙ ያላቸው የግል ትምህርት ቤቶች ፍላጎቱ ካላቸው ያለንን የትምህርት መርጃ ለመስጠት ማዕከላችን ክፍት ነው፡፡ ለምሳሌ የፕላዝማ ትምህርት ፋሲሊቲ አሟልቶ ሲዲ ቢጠይቅ ይሰጠዋል፡፡ መሸጥ ግን አይችልም፡፡ የቴክኒክ ምክርም መስጠት እንችላለን፡፡

                                         

                                   

                                         

                                         

                                          

Standard (Image)

‹‹ዓረቢካን የመሰለ ቡና ለዓለም ከሰጠን እኛ ለምን ሳይንሱን አንመራውም››

$
0
0

 

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የቡና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር፣ ገዛኸኝ በሬቻ (ዶ/ር)

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርና እና የእንስሳት ሕክምና ኮሌጅ በበመምህርነትና በተመራማራነት ማገልገል ከጀመሩ 16 ዓመታትን ያስቆጠሩት ገዛኸኝ በሬቻ (ዶ/ር)፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቡና ምርምር ተቋም (International Institute of Coffee Research At Jimma University) መሥራችና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ዶክተር ገዛኸኝ ከ19 ዓመታት በፊት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የፕላንት ሳይንስ ተማሪ ነበሩ፡፡ ከዚያ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሆርቲካልቸር፣ ማስተርስ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኦርጋኒክ ፋርሚንግ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በቡና ዘረመል ላይ ሰርተዋል፡፡ በአገሪቱ ስላለው የቡና ምርት ሁኔታና የተቋሙን እንቅስቃሴ በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴንዶክተር ገዛኸኝን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡-ተቋሙ የተመሰረተበት አላማ ምንድነው?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡-እንደሚታወቀው ጅማ የቡና መገኛ ቦታ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክም ትልቁ የቡና ማሳ በጅማ ነው የሚገኘው፡፡ በአጠቃላይ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ እንደሆነ ነው የሚታወቀው፡፡ አጋጣሚው ዩኒቨርሲቲው በቡና ላይ ትኩረቱን አድርጎ ቢሠራ ጥሩ ስም የሚያሰጠው እንደሆነ አምኖ ከሰኔ 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በቡና ላይ ትኩረቱን ያደረገ የቡና ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋም አቋቋመ፡፡ ቀደም ሲል ዩኒቨርሲቲው ላለፉት 40 ዓመታት በቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ላይ በስፋት ሲያሠለጥን ቆይቷል፡፡ ይህን የምርምር ተቋም እንዲቋቋም ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ በቂ የሠለጠነ  የሰው ሀብት አለው፡፡ ቡና እንደሌሎቹ ሰብሎች አይደለም፡፡ ቡና ብዙ ነገር ነው፣ ቡና ኢኮኖሚ ነው፣ ቡና አንትሮፓሎጂ ነው፣ ቡና ከኢኮ ሲስተም ጋር ትልቅ ቁርኝት አለው፣ ቡና ከቱሪዝም ጋር ይገናኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም በቡና ላይ አሥር የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራሞች መስጠቱም በቡና ላይ የሚሠሩ በቂ ባለሙያዎች እንዲኖሩን አድርጓል፡፡ እኔም የዶክትሬት ዲግሪዬን የሠራሁት በቡና ላይ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የተለየ ነገር መፍጠር የሚችለው በዚህ በአረንጓዴ ወርቅ በቡና ላይ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ አጋሮቻችንም ይህንኑ ነው የሚሉት፡፡ ቡና በአንድ የሙያ ዘርፍ ብቻ የሚሠራ አይደለም፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሙያዎችና የትምህርት ዘርፎች በዩኒርሲቲው መኖራቸው ደግሞ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ቡናን ለማጣጣም ቡና መቆላት፣ መፈጨት አለበት፡፡ በዚህ ውስጥ ብዙ የኬሚካል ሪአክሽኖች አሉ፡፡ ለቡና ጣዕም የሚሰጡ በርካታ ይዘቶች አሉ፡፡ እነዚህን የሚያጠና ኦርጋኒክ ኬሚስትሪ በመሆኑ ከተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ጋር ያገናኘዋል፡፡ ግብርና ላይ ብቻ ተመሥርቶ የሚሠራ ሳይሆን ከሌሎች የሙያ ዘርፎች ጋር የሚያገናኘው በመሆኑና እነዚህ የሙያ ዘርፎች እዚሁ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው የምርምር ተቋሙ እንዲቋቋም ሌላው የተመቸ አጋጣሚ ነው፡፡ በቡና ዘረመል ሀብት ላይ ያሉት የተለያዩ ሥጋቶች በንጥረ ነገር ይዘቱ ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግር በተመለከተ ምርምር አድርገናል፡፡ ለምሳሌ ጫካዎች ሲመነጠሩ በቡና ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንደሚፈጥር፣ ምርምር አድርገን የጥበቃ ስትራቴጂ ዲዛይን አዘጋጅተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የጥበቃ ስትራቴጂውን ቢያብራሩልን

ዶ/ር ገዛኸኝ፡- በኢትዮጵያ ሁሉም ቦታ ቡና አለ፡፡ የቡና ዘረመል ሀብትን ለማስጠበቅ በአገሪቱ ሁሉም ቦታ ላለው የቡና ምርት ጥበቃ ማድረግ አይቻልም፡፡ ትልቁ የቡና ዝርያና ብዝኃነት የሚገኝበት ቦታ ግን መጠበቅ አለበት፡፡ ስለዚህ ያ ቦታ የትነው? የሚለው መለየት አለበት፡፡ ቦታው ከተለየ በኋላ ደግሞ በምን ዓይነት መልኩ በማን መጠበቅ አለበት? ምን ዓይነት ጥቅምስ መገኘት አለበት? የሚሉትን ያካተተ ነው ስትራቴጂው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በቡና ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ የሚገኙ በሽታዎች የትኞቹ ናቸው? በተደጋጋሚ ጊዜ በመከሰት ምርት የሚያጠቁትስ የትኞቹ ናቸው?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡- በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በስፋት የነበረ አሁንም በከፊል ያለ ኮፊቤሪ የተባለው የቡና በሽታ ነው፡፡ አንዳንዴ ገበሬዎች ኮሌራ ይሉታል፡፡ ይህ ቡናን በጣም በማጥቃት የሚታወቅ ነው፡፡ ሌላውና በጣም አስቸጋሪው ኮፊ ዊልት ዲዚዝ ነው፡፡ ይኼ በሽታ አንዴ ከተከሰተ አይድንም፡፡ ያለው አማራጭ ወደ ሌላ እንዳይዛመት ግንዱን ነቅሎ ማቃጠል ነው፡፡ ሌላው ኮፊ ሊፈረስት የምንለው ነው፡፡ ይሄ በሽታ ለአገሪቱ በተለይም ካለው የአየር ለውጥና ከሙቀቱ ጋር ተዳምሮ ትልቅ ሥጋት ሆኗል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደ ቴፒና በበቃ ባሉ ዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ብቻ ነበር እንደችግር ይታይ የነበረው፡፡ አሁን ግን ወደ ሌሎቹ የቡና አብቃይ ቦታዎች በስፋት እየታየ ያለ ሌላው ሥጋት ነው፡፡ በዓለም ደረጃ ግን አንደኛ ሥጋት ነው፡፡ ለምሳሌ ከዓመት በፊት 34 በመቶ የሚሆነው የኮሎምቢያ ቡና በዚህ በሽታ ምክንያት እንዲወገድ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የኮፊ ሊፈረስት በሽታ መገለጫው ምንድነው?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡- በቅጠሎች ጀርባ ላይ የሚታይ ዝገት የመሰለ ነገር ነው፡፡ ይህ ዝገት መሳይ ነገር እየሠፋ ሲመጣ ቅጠሎች ይረግፋሉ፡፡ ምግብ የሚሠራው የአጠቃላይ ምርቱን ሕይወት የሚደግፈው ቅጠሉ ረገፈ ማለት ደግሞ በቂ ፍሬ እንዳይሰጥ፣ ቡናው እንዲደርቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በጊዜ መፍትሔ ካልተሰጠው እንደ ኮፊ ዊልት ግንዱን ሊያደርቀው ይችላል፡፡ ነገር ግን በሽታውን ለመከላከል ኬሚካል መርጨት ይቻላል፡፡ ከአየር ለውጥ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም በቡና ላይ ብዙም ለውጥ አያመጡም የሚባሉ አሁን ግን ከፍተኛ ችግር እያስከተሉ ያሉ ተባዮችም አሉ፡፡ ብሎች ሊፍ ማይነር የሚባለው ተባይ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ አሁን ከአየር ለውጥ ጋር ተያይዞ በስፋት እየተከሰተ ይገኛል፡፡ በተለይ ከዓመት በፊት በቡና ላይ ከፍተኛ ችግር አስከትሎ ነበር፡፡ ሁለተኛው አንቴስቲያበግ ነው፡፡ አንቴስቲያበግ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በስፋት ይታያል፡፡ ሌላው ኮፊቤሪቦረር የሚባል በሌላው ዓለም ትልቅ ችግር እየፈጠረ ያለው ተባይ ነው፡፡ በእኛ አገር ወደ እነ ቴፒና በበቃ አካባቢ ይታያል፡፡ ወደ ሌላ አግሮ ኢኮሎጂም እየመጣ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ከአየር ንብረቱ ጋር ተያይዞ በተባዮችና በሽታዎች ለቡና ትልቅ ሥጋት እየሆኑ መተዋል፡፡ ስለዚህ የቡና ጥናት፣ የቡና እንክብካቤ አያያዝ ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ለቡና የሚያሠጉ የበሽታ፣ የተባዮች፣ የአረም እንደዚሁም ተለዋዋጭ የሆነው የአየር ንብረት በቡና ምርት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ሳይቀር ነው የምናጠናው፡፡ አንደ ምሳሌ የምጠቅሰው በጅማ ዞን ውስጥ ሰንጠማ በሚባል አካባቢ ያደረግነው አንድ ጥናት አለ፡፡ ቦታው ከዚህ በፊት ከፍተኛ ዝናብ የሚያገኝ ቦታ ነው፡፡ ስለዚሀ የአየር ለውጥ በእርግጥ ለቡና ሥጋት ነው ወይ? እየተከሰተ ያለ ነገርስ ነው ወይ? በቡና ተባዮችና በሽታዎች ላይ ምን ዓይነት ለውጥ እየፈጠረ ይገኛል በሚል ቀደም ተብሎ የተደረገ አንድ ጥናት አለ፡፡ በጥናቱ መሠረት በአካባቢው ለሚቀጥሉት 30 ዓመታት የሙቀት መጠን በሦስት ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይጨምራል፡፡ የዝናቡ መጠን ግን አሁን ባለበት መጠን ነው የሚቀጥለው፡፡ ይኼ ደግሞ ለቡና ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ ቡናው ከሚፈልገው በላይ አንድ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት መጨመር በራሱ ትልቅ ችግር ነው፡ በሌላ በኩል ሙቀቱ ለአንዳንድ ተባዮች አመቺ ሁኔታን ይፈጥል፡፡ ለዚህ መፍትሔ የሚሆኑ ሥራዎችን ፕሮጀክት ቀርፀን በገበሬው ማሳ የላይ እየሠራን እንገኛለን፡፡ የተለያዩ የቡና ዝርያ ያላቸውን ማለትም የውኃ እጥረትና በሽታን የመቋቋም አቅም ያላቸው ዝርዎች በአየር ለውጥ በሚጠቁ ቦታዎች ላይ እንዲተከሉ የችግኝ ማፍላትና  ተከላ እንዲካሄድ እያደረግን እንገኛለን፡፡ በሌላ በኩል የአየር ለውጥ የቡና ምርት ላይ ችግር እንዲከሰት የሚያደርግ  ከሆነ ለማኅበረሰቡ ኑሮውን የሚደግፍበት አማራጭ መፍጠርም ግድ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የአካባቢው ማኅበረሰብ በንብ ማነብ እንዲሠማራ ተደርጓል፡፡ የምግብ አቅርቦትን በተመለከተም በቀላሉ በበሽታ ማይጠቁ የበቆሎ ዝርያዎች በአካባው እንዲስፋፉ አድርገናል፡፡ ከዚህም ሌላ ለቡና ጥበቃ የሚሆኑ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን የመትከል ዘመቻም እንጀምራለን፡፡ ይህም የአየር ለውጥ በአካባቢው ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ከወዲሁ መከላከል የሚያስችል ነው፡፡

ሪፖርተር፡-ተቋሙ በሽታን የሚከላከሉ ችግኞችን አፍልቶ ለገበሬው በማሠራጨት ረገድ ትልቅ ክፍተት እንዳለበት አርሶ አደሮች ያማርራሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርሶ አስተያየት ምንድነው?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡-በቂ ዘር አባዝቶ ለገበሬዎች በማሠራጨት በኩል ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ በዚህ ውስጥ ብዙ ባለድርሻዎች አሉ፡፡ የምርምር ተቋም ተመራምሮ ያገኘውን አንድ መነሻ ዘር ለባለድርሻ አካል ይሰጣል፡፡ ነገር ግን አብሮ የመስራቱ ነገር በጣም የላላ ነው፡፡ እንደዚህ ያሉ የምርምር ተቋማት ምርምር ውጤቶችን በባለቤትነት ማስፋፋት ያለበት ግብርና ሚኒስቴር ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ፣ በምርምር ተቋማትና በግብርና ቢሮዎች በኩል ያለው ግንኙነት ላይ ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ ተናቦ በመሥራት ረገድ ትልቅ ችግር አለ፡፡ ገበሬዎቹ የሚያነሱት ነገር በጣም ትክክል ነው፡፡ ገበሬዎች አለማቋረጥ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ አዲስ ቴክኖሎጂ ለግብርና ይረዳል ብዬ ለገበሬው ጥዬለት ብመጣ ዋጋ ለውም፡፡ ከቴክኖሎጂው ጋር ልናስተዋውቀው፣ ልናስተምረው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ልንሰጠው ይገባል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ አጠገቡ የግብርና ባለሙያ አለ፡፡ ነገር ግን ተገቢውን ነገር እያደረጉ ነው? እኔ እጠራጠራለሁ፡፡ ቡና ላይ ለውጥ አልመጣም በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን በጀት ዓመት ቡና ላይ ለማስመዝገብ የተያዘውን ዕቅድ 50 በመቶው እንኳን ማሳካት አልተቻለም፡፡ ይህ የሚያሳየው ሁሉም ባለድርሻ አካል ተናቦ አለመሥራቱን ነው፡፡ ትልቅ ክፍተት ነው፡፡ እኛ ግን እንደ አንድ ተቋም የተወሰኑ ዘሮችን አባዝተን ለተወሰኑ ገበሬዎች በዓመት እንሠጣለን፡፡ ነገር ግን በጣም ጥቂት ነው፡፡ እንደ መንግሥት በስፋት ሊኬድበት የገባል፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ጉዳዩን በባለቤትነት ሊሠራበት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡-ድርጅቱ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ምን ያህል የተሻሻሉ ዝርያዎችን ማውጣት ችሏል?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡-አንድ ዝርያ ለማውጣት በትንሹ ከአሥር እስከ አሥራ አምስት ዓመታት ይፈጃል፡፡ በድሮ ኮንቬንሽናል ብሪዲንግ ደግሞ እስከ 30 ዓመታት ያስፈልጋል፡፡ በጣም ረዥም ጊዜ ይፈጃል፡፡ ነገር ግን አንድ ችግር ሲከሰት ለችግሩ የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛ የረዥም ጊዜ ስትራቴጂ ይቀመጣል፡፡ በሽታው ሲከሰት  ከነበሩት ዝርያዎች ውስጥ በሽታውን መቋቋም ሚችሉ መኖራቸውን ማረጋገጥና ከተገኙ በሁለትና ሦስት ዓመት ውስጥ ወደ ሥራው መግባት ነው፡፡ ሌላው በአጭር ጊዜ ሊጠናቀቅ የሚችል በሽታውን መቆጣጠር የሚችል ኬሚካል ካለ ፍተሻ ማድረግ ነው፡፡ በሌላ አገር ጥቅም ላይ የሚውሉ ኬሚካሎችን ማስገባት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቡና ኦርጋኢክ (የተፈጥሮ) ቡና ነው፡፡ ገበሬዎቻችን ያንን ያህል ኬሚካል እንዲጠቀሙ አናበረታታም፡፡ ስለዚህ ተፈጥሯዊ የሆኑ የመከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም በሽታውን እንዲከላከሉ ይደረጋል፡፡ ይሁንና ችግሩ እየገዘፈ የሚሄድ ከሆነ ምርቱን ማጣት ስለሌለብን ወደ ኬሚካሉ ልንሄድ እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡-የቡናን ደኅንነት በባህላዊ መንገድ እንዴት ማስጠበቅ ይቻላል?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡-ጥሩ ምግብ ካገኘ ንፅህናው ከተጠበቀ በቂ ነው፡፡ በጣም ሲታፈን፣ ከፍተኛ ጥላ ሲኖር፣ የአየር እርጥበቱ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ይህም ለአንዳንድ በሽታዎች መከሰት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ ከቡና ላይ ጥላን በማሳሳት ፀሐይ እንዲገባና ነፋስ እንደ ልብ እንዲዘዋወር ማድረግ የቡና ምርትን ከበሽታ የሚከላከሉበት አንዱ ባህላዊ ዘዴ ነው፡፡ ከግንዱ ላይ የሚወዳድቁ ቅጠሎችም ሳይነሱ መቅረት የለባቸውም፡፡ ተባዮችም በጣም ካልበዙ በስተቀር በእጅ ለቅሞ ማንሳት ይቻላል፡፡ ዋናው ክትትል ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተደራሽነታችሁ በጅማ ዙሪያ የተወሰነ ነው ወይስ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች?   

 ዶ/ር ገዛኸኝ፡- እኛ ሁሉም የቡና አካባቢዎች ላይ ሄዶ ለመሥራት ነው ዕቅዳችን፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ተመሳሳይ ሥራ ከሚሠሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነው የምንሠራው፡፡ ይህም በቡና ዙሪያ ከባድ ተፅዕኖ መፍጠር እንድንችል ያደርገናል፡፡ ቡናን በተለይም ዓረቢካን  የመሰለ ቡና ለዓለም ከሰጠን እኛ ለምን ሳይንሱን አንመራውም የሚል ራዕይ ነው ያለን፡፡

ሪፖርተር፡- የቡና መገኛ አገር የሆነቸው ኢትዮጵያ ከቡና ማግኘት የሚጠበቅባትን ጥቅም እያገኘች አይደለም ይባላል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተየያየት ምን ይመስላል? ምክንያቱስ ምንድነው ይላሉ?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡- ይህ ሰፊ ነው፡፡ ቡናን ለብዙ ዘመናት ስናመርት የቆየን ነን፡፡ ነገር ግን የምናመርትበት መንገድ ኋላ ቀር ነው፡፡ ሁለተኛና ትልቁ ነገር እኛ ከቡና ማግኘት ያለብንን ጥቅም የማናገኝበት ምክንያት ባለው የጥራት ችግር ነው፡፡ በዓለም ላይ እጅግ ተፈላጊ የሆነውን ዓረቢካ ቡና እናመርታለን፡፡ ነገር ግን በሚፈለገው መጠን ጥራቱን ጠብቆ መላክ ላይ ክፍተት አለ፡፡ የቡና ግብይቱ ላይም ራሱን የቻለ ትልቅ ችግር አለ፡፡ የአንድ አካባቢ ቡናን ከሌላው ጋር የመቀላቀል ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ የጅማ ቡናን ከይርጋ ጨፌ ጋር የመቀላቀል ችግር አለ፡፡ የጅማ ቡና ራሱን የቻለ ጣዕም አለው፡፡ የይርጋ ጨፌም ራሱን የቻለ ጣዕም አለው፡፡ በሚቀላቀሉበት ጊዜ በጥራቱ ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡ የይርጋ ጨፌን ቡና ለሚፈልግ ዓለም አቀፍ ደንበኛ የተቀላቀለው ሲላክ ላይቀበል ይችላል፡፡ ሌላው ዋናውና ትልቁ ችግር ቡናችንን ብራንድ አድርገን አንልክም፡፡ ቡናችን በሚመረትበት አካባቢና በጣዕማቸው ብራንድ አድርገን አለመላካችን ማግኘት የሚገባንን ጥቅም እንዳናገኝ አድርጎናል፡፡ ከዚህም ሌላ ላለፉት በርካታ ዓመታት እሴት ሳንጨምር አረንጓዴ ቡና ነው ምንልከው፡፡ አሁን ብቅ ብቅ የሚሉ እሴት ጨምረው የሚልኩ ድርጅቶች  አሉ፡፡ መንግሥትም በዚህ ዙሪያ ለሚሠሩ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማድረግ ጀምሯል፡፡ ቡናን እሴት ጨምረን አለመላካችን ትልቅ ችግር ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ የቡና ጥራት እዚያው ማሳ ላይ ነው የሚጀመረው፡፡ ማሳ ላይ የተሻለ እንክብካቤ፣ ንጥረ ነገር አግኝቶ ካላደገ የምርት ጥራቱ ላይ ችግር ይፈጠራል፡፡ አዘገጃጀቱ አጫጫኑ ሁሉ በጥራቱ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ በዚህ ረገድ ትልቅ ችግር አለ፡፡ ስለዚህም ነው መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ አገሪቱ በቡና ተጠቃሚ እንድትሆን እየሠራ ያለው፡፡ የእኛ ተቋምም ይኼንን አገራዊ ንቅናቄ ጥናት በሚያስፈልግበት ቦታ በጥናት፣ ሥልጠና በሚያስፈልግበት ቦታ ሥልጠና በመስጠት የራሳችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ በቡና ምርት ምን ያህል  እምቅ አቅም አላት? መጠቀም የተቻለውስ በምን ያህል ነው?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡- በአገሪቱ ወደ ቡና ማሳነት መለወጥ የሚችሉ በጣም ብዙ ቦታዎች አሉ፡፡ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በአማራ ክልል ለቡና ምርት የተመቹ ቦታዎች አሉ፡፡ ዝቅተኛ ቦታዎችን ሳይቀር መስኖን በመጠቀም ቡና አምራች ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አገሪቱ ያላትን አቅም 50 በመቶ ያህል እንኳ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም፡፡ ይህን ለማድረግ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ በዓለም ላይ አንደኛ ቡና አቅራቢ አገር ብራዚል ነች፡፡ ከብራዚል ቀጥሎ ከዛሬ 27 ዓመታት በፊት ቡና ማምረት የጀመረችው ቬትናም ነች፡፡ ኢትዮጵያ ላለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በአምስተኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ቬትናምን ከቦታዋ ለማንሳት ዕቅድ ተይዟል፡፡ የገበያ ድርሻችንን ወደ አሥርና 15 በመቶ ለማድረስም ታስቧል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓመት 390,000 ሜትሪክ ቶን ቡና ነው ወደ ውጭ የምንልከው፡፡ ከአምስት ዓመታት በኋላ ወደ 1,000,000 ለማድረስ ነው የምንሠራው፡፡ ይህንን ለማድረግ ብዙ መሥራት ያለብን የቤት ሥራዎች አሉ፡፡ የቡና ምርታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከዝርያ መምረጥ፣ ከእንክብካቤ መሥጠት፣ ከበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ጀምሮ ብዙ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ጥራቱን ጠብቆ ማዘጋጀት፣ እሴት ጨምሮ መላክ ከተቻለ፣ ከተሳካልን ደግሞ ይኼ የጅማ፣ ይኼ የሊሙ እያልን መላክ ከቻልን ከቡና ማግኘት የሚገባንን ጥቅም ማግኘት እንችላለን፡፡   

  

 

 

 

 

Standard (Image)

‹‹የቱሪዝም ዘርፉ በሌላ ሙያ በሠለጠነ ሰው መሞላቱ አንዱ ክፍተት ነው››

$
0
0

 

አቶ ልዑል ዮሐንስ፣የአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የስሜን ተራራ፣ ፋሲለደስና ሌሎችም በርካታ ቅርሶች የሚገኙበት የአማራ ክልል ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የተለያዩ የባህልና ቱሪዝም ውይይቶች አስተናግዷል፡፡ በጎንደር የባህልና ቱሪዝም ዐውደ ጥናት ሲካሄድ በላሊበላ ለሙዚየም አስተዳዳሪዎች፣ አስጎብኚዎችና ሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ስለ መርሐ ግብሮቹና በክልሉ ስላሉ ቅርሶች ጥበቃና አጠቃላይ የቱሪዝም ዘርፉ እንቅስቃሴ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ልዑል ዮሐንስን ምሕረተሥላሴ መኰንን  አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡-ላሊበላ የተካሄደው የአራት ቀናት ሥልጠና የትኩረት አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው?

አቶ ልዑል፡- ሥልጠናውን የሰጠነው በቱሪዝም ልማት፣ በቅርስ እንክብካቤና በባህል ፖሊሲው ላይ ነው፡፡ በክልሉ ትላልቅ ገዳማትና ቅርሶች ስላሉ የሃይማኖት አባቶች ቅርሶቹን ስለሚይዙበት መንገድና ስለ ግምጃ ቤት አስተዳደር አሠልጥነናል፡፡ ለምሳሌ እንደ ዋልድባ፣ ማኅበረ ሥላሴና ጣና ያሉ ገዳማት ላይ ትላልቅ ሙዚየም የሚያስተዳድሩ አባቶች አሉ፡፡ ሥልጠናው በአመራሮች፣ ባለድርሻ አካላትና የሃይማኖት ሰዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የሰጡት የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ሥልጠናውን የምንሰጠው በየዓመቱ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት የተካሄደው ደብረ ማርቆስ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡-ከቅርስ ጥበቃ ጋር በተያያዘ በክልሉ ያሉ ተግዳሮቶችን ሥልጠናው በምን መንገድ ይቀርፋል ተብሎ ይታሰባል?

አቶ ልዑል፡-የቱሪዝም ልማቱን በተመለከተ ትልቁን ምስል ያለመመልከት ችግር አለ፡፡ ባለሙያው ቱሪዝም ምን ማለት ነው? ከሚለው ጀምሮ እንዴት ይለማል የሚለውን አያውቅም፡፡ አብዛኛው በቱሪዝም ያልሠለጠነ ስለሆነ ሥልጠና ያስፈልጋል፡፡ የቱሪዝም ዘርፉ በሌላ ሙያ በሠለጠነ ሰው መሞላቱ አንዱ ክፍተት ነው፡፡ በመዳረሻ ልማት በተለይም ከሙዚየም አስተዳደር ጋር በተያያዘም ክፍተት አለ፡፡ ትልቆቹ ሀብቶችና የቅርሶች ምሽጎች ገዳማት ስለሆኑ እነዚህን የሚያስተዳድሩ አባቶች በእውቀት መታገዝ አለባቸው፡፡ ቅርሶቹን ወደ አንድ ማዕከል መሰብሰብ ስለማንችል የሙዚየም ግንባታ ዲዛይን ሰጥተናል፡፡ በጀት እንመድብና እንዲገነባ እናደርጋለን፡፡ የሙዚየም አስተዳደር ከቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ ጋር ይያያዛል፡፡ በገዳማቱ ግምጃ ቤቶች ዕቃ በዕቃ ተደራርቦ ይገኛል፡፡ የትኛው ዕቃ ከየትኛው ቀጥሎ እንደሚመጣ፣ እንዴት ማናፈስ እንደሚችሉና በአጠቃላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ እንዴት እንደሚከላከሉ ስለ ዘመናዊ ሙዚየም ሳይንስ አሠልጥነናል፡፡ አባቶቹ ላሊበላ እንዲመጡ የፈለግነው ተከዜ ገዳምን ለማሳየት ነው፡፡ በገዳሙ ጥላ ዘርግተው አይለምኑም፡፡ አባቶቹ በዕደ ጥበብና እርሻ ላይም ኢንቨስት የሚያደርጉበት ተሞክሮ ወደ ሌሎች ገዳሞችም እንዲስፋፉ እንፈልጋለን፡፡  ባረጁ ቅርሶች ጥገና በኩል በክልሉ ብዙ ክፍተት አለ፡፡ በባህል ፖሊሲው መጤ ባህሎችን ስለማቋቋም ማስገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡ ባለድርሻ አካሎቹ መረጃ ስለሌላቸው ፈተናዎቹን አያውቋቸውም፡፡ አመራሮች ነገ ቦታውን ለቀው ሲሄዱ፣ አብዛኞቹ ባለሙያዎች ግን ጡረታ እስከሚወጡ በቦታው ስለሚቆዩ በየዓመቱ ሥልጠናውን እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡-አብዛኞቹ የዘርፉ ሠራተኞች በሙያው አለመሠልጠናቸው ምን ተፅዕኖ አሳድሯል?

አቶ ልዑል፡- በቅርስ ጥገና ያለብን ፈተና ከቴክኖሎጂ፣ ከገንዘብና የሰው ኃይል ጋር ይያያዛል፡፡ አላዋቂ ሰዎች ይጠግናሉ፡፡ ላሊበላን አላዋቂ ሰዎች ጠግነውት እንዴት እንደተበላሸ ማየት ይቻላል፡፡ በየቦታው እየገጠመን ያለው ፈተና አላዋቂዎች ወደ ቅርስ ጥገና መግባታቸው ነው፡፡ በሙያው ያልሠለጠነ ሰው ዘርፉን ሲመራው፣ ቅርሱን ሲጠብቅ፣ ባህሉን ለማልማት እንቅስቃሴ ሲያደርግ፣ ሙዚየም አስተዳድራለሁ ሲልም ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ ለምሳሌ በክልሉ የሙዚየምን ችግር ለመፍታት በየገዳማቱ ሙዚየም መሠራት ተጀመረ፡፡ በፊት እያገለገሉ ዕጣን ይታጠኑ የነበሩት ዕቃዎች በሙዚየሙ ሳይታጠኑ አይጥ እና ብል በልቷቸው ተበላሹ፡፡ የሙዚየሙ አስተዳዳሪዎች ሙዚየሞች መታጠን እንዳለባቸው ማወቅ አለባቸው፡፡ በዚህ ወቅት እሳት እንዳይነሳ ጥንቃቄም ያስፈልጋል፡፡ የአጭር ጊዜ ሥልጠና የንቅናቄው አንድ አካል ሲሆን፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ረዥም ሥልጠና እየሰጠን ነው፡፡ በየቦታው የሕዝብ ውይይትም እያደረግን ነው፡፡ ዘርፉን የሚመሩት ሰዎች ለረዥም ጊዜ ስለሠሩ ችግሮቹን ያውቋቸዋል፡፡ መፍትሔውን ከነገርናቸው አብዛኛው ሰው ስህተቱን አርሞ ለውጥ ይመጣል፡፡ ከሥልጠና በኋላ በየቦታው የመጣውን ለውጥ እንከታተላለን፡፡ ያሠለጠናቸው ሰዎች በየዞኑ ሄደውም ያሠለጥናሉ፡፡ ውጤቱ በረዥም ጊዜ ስለሚታይ ጊዜ ይወስዳል፡፡ የአስጎብኚዎች ማኅበር ተወካዮችም በየአካባቢያቸው ስላለው ክፍተት ሠልጥነዋል፡፡ ለምሳሌ ስሜን ተራራ አካባቢ ያለው ዋናው ችግር እንግዶች ሲታመሙ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ዕርዳታው ጥሩ አለመሆኑ ነው፡፡ ላሊበላ ቤተ ክርስቲያናት ከተሠሩለት ሃይማኖታዊ ዓላማ አንፃር ክብር ያለመስጠት ክፍተት አለ፡፡ የጎንደር ችግር ከመስተንግዶ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የባህር ዳር ክፍተት ከውኃ  ቱሪዝም ጋር ይያያዛል፡፡ ገዳማቱ ሲጎበኙ በጀልባ ጉዞና በከተማዋ መካከል ያለው አገልግሎት ከፍጥነትና ከጥራት አንፃር መሻሻል አለበት፡፡

ሪፖርተር፡-በጎንደር ከተማ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በተዘጋጀ ጉባኤ በክልሉ ካሉ ችግሮች መካከል ከአስጎብኚዎች ሙያዊ ብቃትና ከመስተንግዶ ጋር የተያያዙ ክፍተቶች ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህን ለመፍታት ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ልዑል፡- የጥናትና ምርምር ጉባኤውን ስናዘጋጅ ከምርምሮቹ የሚገኙ ሐሳቦችን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ አብዛኞቹ የጥናት ውጤቶች በክልሉ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ከሌሎች ክልሎች የተነሱትም ከኛ ጋር ይመሳሰላሉ፡፡ ችግሮቹ ምን እንደሆኑና ስለሚፈቱበት መንገድ አስተምረውናል፡፡ የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረምና የባህልና ቱሪዝም ቢሮና ከሚኒስቴሩ ጋር ያዘጋጀው የመጀመሪያው የጥናት ጉባኤ በጋራ መሥራት እንደምንችልና የተሻለ ነገር እንደምናገኝ ያየንበት ነው፡፡ ቱሪዝም ለኢትዮጵያ አዲስ ቢዝነስ ነው፡፡ ከሌሎች ዘርፎች አኳያ አዲስ በመሆኑ አሠራሩ ግድፈት ቢኖረውም እየሄድንበት ያለው ፍጥነት ይደነቃል፡፡ ከ10 እና 15 ዓመታት በፊት የነበረውና አሁን ያለው ሲነፃፀር በጎንደር ብቻ ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በመስተንግዶ ቱሪስቶች የሚጠብቁት ዓለም አቀፍ ደረጃ አልደረስንም፡፡ ቱሪስቱ ምሳውን አንድ አገር እራቱን ሌላ አገር የሚበላበት ዘመን ነው፡፡ ይህ ማለት በአንድ ቀን የሁለት አገሮችን አገልግሎት ያነጻጽራል፡፡ በዚህ በኩል ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአጭርና የረዥም ጊዜ ትምህርት ይሰጣል፡፡ የማስጎብኘት ቢዝነስን ሳይንስ በማድረግ ክፍተት ቢኖርም አብዛኞቹ በልምድ ረዥም ጊዜ ስላስጎበኙ የጎላ አይደለም፡፡ ሌላው ለቢዝነሱ ያላቸው አመለካከት ነው፡፡ አስጎብኚ ከቱሪስቶቹ ጋር ፊት ለፊት የሚገናኝ አምባሳደር ነው፡፡ በአስጎብኚዎቹ ዘንድ የባህል አምባሳደር ነኝ ብሎ ያለመመልከትና ቢዝነሱን ብቻ የማየት ነገር አለ፡፡ በዘርፉ የገፅታ ግንባታ የኢኮኖሚ ጠቀሜታን መቅደም አለበት፡፡ በሥነ ምግባር በኩል ከታማኝነት ጀምሮ በአለባበስ ኢትዮጵያዊ ማንነት መግለጽንም ይጨምራል፡፡ በአለባበስ ክፍተት አለ፡፡ የባህል አምባሳደር የባህል ልብስ ለብሶ መቅረብ አለበት፡፡ በዚህም ከአስጎብኚዎች ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ የቱሪስቶችን ደኅንነት አደጋ ላይ መጣልና ማጭበርበር ባይኖርም ከፍተኛ ሒሳብ መጠየቅ አለ፡፡ ወጥ የሆነ ክፍያ አውጥተን ለማስተካከል ሞክረናል፡፡

ሪፖርተር፡-ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዎችን በማፍራት ይጠቀሳል፡፡ የተማረውን የሰው ኃይል በዘርፉ በመቅጠር እየተጠቀማችሁበት ነው?

አቶ ልዑል፡- አሁን ዘርፉን እየተቀላቀሉ ያሉት አስጎብኚዎች የቱሪዝም ተመራቂዎች ናቸው፡፡ ሌሎቹ ትምህርት ክፍሉ ከመከፈቱ በፊት በሌላ ዘርፍ የሠለጠኑ ናቸው፡፡ አብዛኞቹን ባለሙያዎች ስፖንሰር አድርገን ሁለተኛ ዲግሪ አስተምረናቸዋል፡፡ ተከታታይ የአጭር ጊዜ ሥልጠናም ይሰጣል፡፡ ከቋንቋ ዕውቀት ጋር የተያያዘ ክፍተት አለ፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምረው መሠረታዊ የቱሪዝም ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ለአስጎብኚዎች የሚያስፈልጉ ከእንግሊዝኛ ወጪ ያሉ ቋንቋዎች ላይ ተጨማሪ ዕውቀት ለመስጠት ሥርዓተ ትምህርቱን ማስተካከል አለበት፡፡

ሪፖርተር፡-በመዳረሻ ልማት በኩል የመሠረተ ልማት በስፋት አለመዘርጋትና የመስተንግዶ ጥራት አለመኖር በቱሪዝሙ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ አይደለም?

አቶ ልዑል፡- አዲስ ቢዝነስ በመሆኑ ገንዘብ ያለውና ዕውቀት ያለው ተቀናጅተው እየሠሩ አይደለም፡፡ ከአገልግሎት ጋር የተያያዘ ችግር በኛ ክልል ብቻ ሳይሆን የአጠቃላይ ኢትዮጵያ ችግር ነው፡፡ ሽንት ቤትና ማዕድ ቤት በግርግዳ መለየቱ ለንፅሕና ግድ እንደሌለን ያሳያል፡፡ መስተንግዶና ንፅሕና ላይ መሠራት አለበት፡፡ የመዳረሻ ልማት ኢንቨስትመንት ያስፈልገዋል፡፡ በባህልና ቱሪዝም ቢሮ አቅም የሚሠራ አይደለም፡፡ መንገድ፣ ውኃና መብራት መዘርጋት ምን ያህል እንደሚያስቸግር ይታወቃል፡፡ አንድ መዳረሻ፣ መዳረሻ እንዲሆን ከተፈለገ ግን የግድ መሠረተ ልማቶች መሟላት አለባቸው፡፡ ሥራችንን እንድንሠራ በቅድሚያ መሠረተ ልማቶቹ መሟላት አለባቸው፡፡ በዚህ ክልል በመዳረሻ ልማት ያለው ችግር አብዛኞቹ የቱሪስት መስህቦች ተራራ አካባቢ መገኘታቸው ነው፡፡ አስቸጋሪ መልክአ ምድር ላይ በመሆናቸው አስቸጋሪ ግንባታ ይጠይቃሉ፡፡ ጊዜና ገንዘብ ይወስዳልም፡፡

ሪፖርተር፡-የቱሪስቶች ፍሰት እንዲጨምር ከመዳረሻ ልማት ባሻገር ለቅርሶች እንክብካቤ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቅርሶችን ከመንከባከብ ጋር ከተያያዘዙ ችግሮች ባሻገር ጉዳት ሲደርስባቸው የሚደረግላቸው ጥገናም ተግዳሮቶች ይገጥሙታል፡፡

አቶ ልዑል፡- ስለ ቅርስ ስናወራ አንደኛው ያለውን ቅርስ ለማወቅና እንዳይዘረፍም የሚደረገው የቅርስ ምዝገባ ነው፡፡ ሁለተኛው የቅርስ እንክብካቤ ቅርስ ተበላሽቶም ተሰንጥቆም ከሆነ ጉዳቱ እንዳይቀጥል የሚሠራ ነው፡፡ በፀሐይና ዝናብ ከተበላሸ ላሊበላ እንደተደረገው በመከላከያ ጉዳቱ ባለበት እንዲቆም ማድረግ ነው፡፡ ሦስተኛው ጉዳቱን ጠግኖ ወደነበረበት መመለስ ነው፡፡ ከምዝገባ አኳያ እንደ አገርም የተሻለ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ከእንክብካቤ አኳያም ጥሩ ብንሠራም በጥገና መሠረታዊ ክፍተት አለ፡፡ አብዛኞቹ ቅርሶች የተሠሩት በአገር በቀል ዕውቀት ሲሆን፣ ይኼ ስለጠፋ መመለስ ይጠበቅብናል፡፡ በተቻለው አቅም እየሠራን ቢሆንም የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ርብርብ እንፈልጋለን፡፡ ቴክኖሎጂውን ተረድቶ የሚሠራ የሰው ኃይል ያስፈልገናል፡፡ በክልሉ ያሉ ቅርሶች የተሠሩት በኖራ ነው፡፡ የኖራ ቴክኖሎጂ አገር በቀል ዕውቀት ሲሆን፣ አሁን እየጠፋ ነው፡፡ በክልሉ ያሉ በርካታ ሥዕሎች የተሠሩበት ቀለምም አገር በቀል ነው፡፡ ዘመናዊ ቀለም አሲድ ስላለው መጠገን አልተቻለም፡፡ ይህንን ተረድቶ የሚሠራ ሰው ስለሌለ ገበያው ክፍት ነው፡፡ የቅርስ ጥገና ጨረታ ስናወጣ ትንሽ ዕውቀት ያለው ሰው ያሸንፋል፡፡ የጎንደር ሥልጣኔ ለ250 ዓመት በኢትዮጵያ መናገሻነት የተገነባ ግዙፍ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ይህን ግዙፍ ሀብት ሙሉ በሙሉ እንጠግን ከተባለ ብዙ ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል፡፡ ይኼ በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ርብርብም የሚፈታ ነው፡፡ ገንዘቡ እንዴት እንደሚሰበሰብና እንደሚተዳደር ሥርዓት አዘጋጅተን ጽሕፈት ቤት እያቋቋምን ነው፡፡

ሪፖርተር፡-ስለ ቱሪዝም ሲነሳ የሚዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች (ታንጀብል ካልቸራል ሔሪቴጅስ) የሚሰጣቸው ትኩረት ያህል ለማይዳሰሱ (ኢንታንጀብል) ሲሰጥ አይስተዋልም፡፡ ባህላዊ ቅርሶችን ለቱሪዝም በማዋል ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ልዑል፡- ይኼ አገራዊ ችግር ነው፡፡ ቱሪዝሙ የተመሠረተው በውጪ ቱሪስቶች ነው፡፡ በአገር ውስጥ ቱሪዝም ላይ ተመሥርቶ የውጪው እንደ ማሟያ መታየት አለበት፡፡ ለውጪው ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚቻለው አገሩን ተንቀሳቅሶ የተረዳ ዜጋ ስንፈጥር ነው፡፡ የማስታወቂያ ሥራው በአብዛኛው የሚታወቁና ግዙፍነት ያላቸው ቅርሶችን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ይህን የምንሠራው ቀላሉ ሥራ ስለሆነ ነው፡፡ በማስታወቂያ ሥራ የመጀመሪያው አዲስ ነገር ወደ ሰው ማስተዋወቅ ነው፡፡ ሁለተኛው የሚያውቁትን የማስታወስ ሥራ ነው፡፡ የሚያውቁትን ማስታወስ ብዙ ገንዘብና የሰው ኃይል ስለማይጠይቅ እየተሠራበት ነው፡፡ በእርግጥ ማስታወቂያ ከመሥራት በፊት መሠረተ ልማት መዘርጋት አለበት፡፡ ካስተዋወቅን ቱሪስቱ ይመጣል፡፡ ስለዚህ ማስታወቂያ ከመሥራታችን በፊት የመሠረተ ልማትና የመስተንግዶ ሥራዎቹ መጠናቀቅ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የአካባቢው ኅብረተሰብ አኗኗር ማራኪ ነው፡፡ ይህ ወደ ካፒታልነት ሳይቀይር እንግዳ መጥራት ግን አንችልም፡፡ እንግዳ መጥቶ ተከፍቶ ከሚሄድ አለመጥራት ይሻላል፡፡ ከዚያ በኋላ የሚያምነን አይኖርም፡፡ በክልሉ ‹‹አክቲቪቲ ቤዝድ ቱሪዝም›› [አሳታፊ ቱሪዝም] ብለን የጀመርነው ፕሮጀክት አለ፡፡ ቱሪስቱ መጥቶ ከማየት በዘለለ ፈጭቶና አቡክቶ የሚጋግርበትና ሌላም የኛ ሕዝብ የሚሠራውን የሚሠራበት አንድ መንደር ለመሥራት እያሰብን ነው፡፡ ይህንን ባለሀብትም ሊሠራውም ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ ትውፊታዊ ተውኔቶችን፣ ፊልሞችንና ሌሎችም የኪነ ጥበብ ሥራዎችን መጠቀም ይቻላል፡፡ እናንተ ኪነ ጥበቡን ምን ያህል ተጠቅማችሁበታል?

አቶ ልዑል፡- የባህል ኢንዱስትሪው ፊልምን ጨምሮ ምንም ያልተሠራበት ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ በኩል ከቢሮ ጀምሮ እስከ ወረዳ ያለውን በአዲስ መልኩ እያዋቀርን ነው፡፡ የቴአትር፣ የፊልምና የሥነ ጽሑፍ ሥራው ባህላችንን እንዲያስተዋውቅ በማድረግ በኩል ክፍተት አለ፡፡ በመጀመሪያ አደረጃጀታችንን አስተካክለን በቀጣይ የምንለውጠው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በክልሉ ይገነባል ካሉን የባህል ማዕከል ባሻገር አሁን ያሉት የባህል ማዕከሎች በቂ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው?

አቶ ልዑል፡- በትልልቅ ከተሞች ላይ የባህል ማዕከላት ለመገንባት መሠረተ ድንጋይ ተጥሏል፡፡ አንዳንዶቹ ተጀምረዋል፡፡ በክልሉ ወደ አንድ ሚሊዮን ብር አካባቢ የሚያወጣ ሙዚየም ለመሥራት ድንጋይ ጥለናል፡፡ ባህል እንዲያድግ ከተፈለገ የባህል ማዕከል ያስፈልጋል፡፡ ኢንቨስትመንቱ ግን ከባድ ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ከደርግ ጀምሮ የነበሩ የስብሰባ አዳራሾችን ወደ ባህል ማዕከል በማዞር የባህል ቡድኖች እንዲጠቀሙባቸው እያደረግን ነው፡፡ በክልሉ ያሉት ከ80 በላይ የባህል ቡድኖች የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በክልሉ ያሉትን ፓርኮች ጨምሮ በአገሪቱ ያሉ ፓርኮች ከሕገወጥ የሰዎች ሠፈራ፣ ከእንስሳትና ደኖች ጥበቃ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች ተጋርጠውባቸዋል፡፡ ከነዚህ ፓርኮች የስሜን ተራራ ይጠቀሳል፡፡ ችግሮቹን ለመቅረፍ ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ልዑል፡- በክልሉ የፓርኮችና የአካባቢ ጥበቃ መሥሪያ ቤት አለ፡፡ ፓርኮች ከኛ ጋር የሚገናኙት ከፓርኮች የሚገኘውን ጥቅም ወደ ቱሪዝም በመቀየር በኩል ነው፡፡ የእንስሳቱን ህልውናና የፓርኩን ድንበር መጠበቅ የአካባቢ ጥበቃን ይመለከተዋል፡፡ ይህ አሠራር አንዳንዴ አለመናበብ ይፈጥራል፡፡ ሌላው ችግር በፓርኮችና በአካባቢው ኅብረተሰብ መካከል ያለው ግንኙነት ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በፊት ከፓርኩ ሲያገኝ የነበረውን ጥቅም በመምራት በኩል ክፍተት አለ፡፡ ስለ ፓርኮች አስፈላጊነት በሚገባ ካለመሠራቱ ጋርም የተያያዘ ነው፡፡ ሆኖም የተሻለ ህልውና ያላቸው ፓርኮች የሚገኙት በክልሉ ነው፡፡ ስሜን  ተራራ ከነበረበት የምዝገባ የመሰረዝ አደጋ (ኢንዴንጀርድ ሊስት) እየወጣ ነው፡፡ አብዛኞቹን መስፈርቶች አሟልቷል፡፡ በቅርቡ የሚመዝን ኮሚቴ ይመጣል፡፡ የሠፈራ፣ የመልሶ ማልማትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በአገው ምድር፣ ወሎና ሰሜን ሸዋ ላይ አዳዲስ ፓርኮች ወጥተዋል፡፡ ችግሩ የፓርኮቹ መኖር ሳይሆን ለቱሪስት መስህብ ማድረግ አለመቻሉ ነው፡፡ ቱሪስቶቹ በፓርኮቹ በሚያደርጉ እንቅስቃሴ ከመሠረተ ልማት አለመዘርጋት ጋር የተያያዘ ችግር አለ፡፡ ፓርኮቹ ከተከለሉ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበት ጥያቄም ይነሳል፡፡ ተጠቃሚነቱ በዘገየ ቁጥር በፓርኩና በሰዎቹ መካከል አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ ችግሩን ለመፍታት መዋቅሩን ማስተካከል እንዳለብን እየተነጋገርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ የነበረው አለመረጋጋት በቱሪዝም ዘርፍ ያሳደረውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የምታደርጉት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ልዑል፡- የከተሞች ፎረም በጎንደር ከተማ መካሄዱ በጊዜያዊነትም ቢሆን ገበያው ላይ መሟሟቅ ይፈጥራል፡፡ ትልቁና ዘላቂው ግን የፈጠረው የገጽታ ግንባታ ነው፡፡ የአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከተሞች ነዋሪዎች ወደ ጎንደር ሲመጡ ስለ ጎንደር ተመሳሳይ ዕይታ ይኖራቸዋል፡፡ ጎንደር በአገር ደረጃም አለ የሚባለው የቱሪስት መዳረሻ ነው፡፡ እንደ አገር የምንኮራባቸው ቅርሶችና የተሻለ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ያለበት አካባቢ ነው፡፡ የገጽታ ግንባታው የውጪ ቱሪስቶች እምነት እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡ እዚህ አካባቢ ያሉ ቅርሶች የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ቅርሶችም ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ የዓለም ሕዝብ ቅርሶች ናቸው፡፡ ሰዎች ወደዚህ ሲመጡ የሚያዩት የራሳቸውን ቅርስ ነው ማለት ነው፡፡ በቅርቡ የዓለም ቱሪዝም ዋና ፀሐፊ መጥተው ጎብኝተውን ነበር፡፡ የሳቸው መምጣት የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከዛ በፊት ሥልጠናዎችና ኮንፈረንሶችም ተካሄደዋል፡፡ ይህ ለኛ የተለየ ትርጉም አለው፡፡

Standard (Image)

ባለ ጥላው ስታዲየም

$
0
0

በዓይነቱና በይዘቱ ልዩ ሆኖና የዘመናዊ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል ሆኖ ብቅ ያለው በሼሕ መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ሙሉ ወጪ ከግማሽ ቢሊዮን ብር  በላይ የተገነባው የወልድያ ስታዲየም ነው፡፡ ‹‹ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ›› ተብሎ የሚጠራው ስታዲየምና የስፖርት ማዕከሉ ከከተማው በስተ ምዕራብ የሚገኘው በመቻሬ ሜዳ ሲገኝ፣ የቆዳ ስፋቱ 117 ሺሕ ካሬ ሜትር ነው፡፡ ከ25 ሺሕ በላይ ተመልካቾችን የሚያስተናግደው ስታዲየሙ በስፖርቱ ማዕከሉ የሜዳ ቴኒስ፣  የቅርጫት፣ የመረብ፣ የእጅ ኳስና ውኃ ስፖርትን አጠቃሎ ይዟል፡፡ ስታዲየሙ ከአራት ዓመታት በፊት ግንባታው ከመጀመሩ በፊት የመነሻ ንድፍ (ዲዛይን) የቀረበው የአማራ ክልላዊ መንግሥት በአልትሜት አርክቴክት አማካይ ያሠራው ሲሆን፣ ይህም ንድፍ ለገንዘብ ዕርዳታ ማሰባሰቢያ ተብሎ  የተሠራ መሆኑ ይወሳል፡፡ ሁለተኛውና ሦስተኛው የዲዛይን ማሻሻል ሥራው በሁዳ ሪል ስቴት መሐንዲሶች አማካይነት ሲሠራ፣ የስፖርት ማዕከሉ ዓለማቀፋዊ ይዘት እንዲኖረውና አስፈላጊ የሆነ አገልግሎት መስጫ ይዞታቸው እንዲያካትት መደረጉ ይጠቀሳል፡፡ የስታዲየሙ ፕሮጀክቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅና የዲዛይን ፕሮጀክት ቁጥጥር ኃላፊ አቶ ዮናስ ብርሃኔ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምሕንድስና የተመረቁት አቶ ዮናስ፣ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር ባለው ሁዳ ሪል  ስቴት በዋና ሥራ አስኪያጅ እየተሠሩ ነው፡፡ የስታዲየሙ ግንባታ ሒደትና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡-የስታዲየሙ የግንባታ አነሳስ እንዴት እንደነበር ከማስታወስ ብንጀምር፤

አቶ ዮናስ፡- የሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲን ስታዲዮም ለመገንባት የታቀደው የዛሬ  አራት ዓመት አካባቢ ነበር፡፡ በወቅቱም በሸራተን አዲስ በተደረገው ገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ላይ ሼሕ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲን ‹‹እኔ ሙሉ በሙሉ ወጪውን በመሸፈን እገንባዋለሁ›› በማለት በገቡት ቃል መሠረት ግንባታው ከወልዲያ አስተዳደር ወደ ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ እንዲዘዋወር ሲደረግ፣ ፕሮጀክቱን ዶ/ር አረጋ ይርዳው በበላይነት  እንዲመሩትና እንዲያስፈጽሙ ተደረገ፡፡ በተከታታይም  ዲዛይኑ ላይ ክለሳ በማድረግ ወደ ግንባታ ሥራው መግባት ቻልን፡፡

ሪፖርተር፡-የስታዲየሙን ዲዛይን በድጋሚ ክለሳ ማድረግ ለምን ተፈለገ?

አቶ ዮናስ፡-መጀመሪያ ዲዛይኑ የተቀበልነው ከአልትሜትስ ፕላን ኢንተርናሽናል ከሚባል ተቋም ነበር፡፡ ቀደም ብሎ የተሠራው ዲዛይን ለገቢ ማሰባሰቢያ ተብሎ የወጣ ነበር፡፡ ከዛም ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከተረከበ በኋላ ዲዛይኑን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ከቴክኒክ ባለሙያዎች ጋር ሁለት ጊዜ በድጋሚ በማጥናት ምን ዓይነት ግብዓቶች እንደሚያስፈልጉት በመወያየት ወደ ሥራው ገባን፡፡

ሪፖርተር፡-የግንባታው ሒደት ምን ይመስል ነበር?

አቶ ዮናስ፡- በግንባታው ወቅት ብዙ ችግሮች ገጥመውን ነበር፡፡ ዋንኛው ችግር የነበረው የአፈር መቁረጥ ሥራ ነው፡፡ ቢያንስ ከሁለት ሜትር ከ50 ርቀት በላይ የሚቆፈር አፈር ነበር፡፡ መሠረቱ ሲሰፋም እስከ 15 እና 20 ሜትር በመቆፈር ተስማሚ አፈር በመተካት ወደ ሥራው ገባን፡፡

ሪፖርተር፡-በኢትዮጵያ ውስጥ ቀድመው ከነበሩት ስታዲዮሞች ልዩ የሚያደርገው ምንድነው?

አቶ ዮናስ፡- ስታዲዮሙ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ያመጣና ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያሟላ ነው፡፡ በስታዲየሙ ውስጥ ሁለት ቡድኖች በተለያየ ሰዓት የሚያደርጉትን ጨዋታ ለማከናወን የዳኛዎችን ጨምሮ ወዲያው እንዲዘጋጁ ያደርጋል፡፡ የመጀመሪያው ቡድን ጨዋታውን አጠናቆ እስኪመለስ ሌላኛው መጠበቅ አይገባውም፡፡ ባለው ቀሪ የመልበሻ ክፍል ዝግጅቱን ማድረግ ያስችላል፡፡ ሌላኛው የፊዚዮቴራፒ፣ የጋዜጠኞች አዳራሽ፣ የእንግዳ ማረፊያ፣ የካሜራ ባለሙያዎች መቀመጫ ክፍል፣ እንዲሁም ዝናብ በመጣ ሰዓት ተመልካቹ ያለምንም ሥጋት እንዲመለከት የሚረዳ ሽፋን (ጥላ) አለው፡፡

በተጨማሪም በምሽት ጨዋታ ሲካሄድ ተጨዋቾች በመብራት አማካይነት የራሳቸውን ጥላ እንዳያሳስታቸው የሚረዳ በቴክኖሎጂ የረቀቁ አምፖሎች ተገጥመውለታል፡፡

ሪፖርተር፡-የወልድያ ስታዲየም ተገንብቶ የተጠናቀቀው በኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ብቻ እንዲገነባ መደረጉ ዋነኛ ምክንያት ምን ነበር?

አቶ ዮናስ፡- በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ብቻ እንዲገነባ የተደረገበት ምስጢር፣ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ሲገነባ ኢትዮጵያውያን ታዳጊ መሐንዲሶች እንዲማሩ በማድረግ ለቀጣይ ሥራዎች ትምህርት እንዲቀስሙ በማሰብ ነው፡፡ በተለይ የስታዲየሙን ሽፋን በምንሠራበት ወቅት አስቸጋሪ የግንባታ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ግን በሒደት ያለውን ችግር በመመካከርና በማጥናት ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም መገንባት ችለናል፡፡

በተለይ ጣራውን በተመለከተ ተመልካቾች ዝናብ በሚመጣበት ወቅት ጨዋታው በቀላሉ መከታተል ያስችላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ሜዳው ውኃ እንዳያሠርግ የማድረግ ሥራ፣ ፀሐያማ በሆነ ወቅት ተመልካቹ በሙቀት እንዳይጎዳ የሚረዳ ቴክኖሎጂን ስንሠራ ትልቅ ትምህርት አግኝተንበታል፡፡ ለምሳሌ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ሜዳው ላይ ያረፈ ዝናብ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ያለውን አፈር ይዞ ሳይሄድ ውኃው ብቻ ወደ ታች እንዲወርድ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ መጠቀም  ችለናል፡፡ ስለዚህ ጨዋታ ሳይቋረጥ ማከናወን እንዲያስችል የሚያደርገውን ቴክኖሎጂ እንዴት እንደሚገነባ ለማወቅ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከውጭ አገር ያስመጣችሁት ወይም የተጠቀማችሁት ግብዓት የለም?

አቶ ዮናስ፡- ከውጭ አገር  የተጠቀምነው ነገር የስታዲዮሙ ሽፋን ነው፡፡ ሽፋኑ ፖሊ ካርቡኒት ይባላል፡፡ እንደሳንድዊች ዓይነት ሲሆን፣ ብርሃን የሚያስተላልፍና ከፍተኛ ሙቀትን ማስቀረት አቅም ያለው ነው፡፡ ያም ቴክኖሎጂ በአገር ውስጥ ስለማይገኝ ከውጭ አስመጥተናል፡፡ ሌላው በስታዲየሙ 56 ፓውዛዎች ተገጥመውለታል፡፡ በእያንዳንዱ ፓውዛዎች  ውስጥ 146 አምፖሎች አሉ፡፡ ይኼም በሜዳው ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች ጥላ እንዳይኖር ለማድረግ በኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች የተገጠመ ሲሆን፣ እያንዳንዱ የመብራት ብርሃኑ የሰው ዓይን እንዳይጎዳ ብቻ ትክክለኛ አቅጣጫ ለማስያዝ ለሦስት ቀናት የውጭ አገር ባለሙያዎች መጥተው አስተካክለውታል፡፡

ሪፖርተር፡- ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ስታዲየሙን ለከተማው ካስረከበ በኋላ በውድድር ሒደት ለሚከሰቱ ችግሮች ምን ዓይነት ክትትል ለማድረግ  አቅዳችኋል?

አቶ ዮናስ፡- ግንባታውን አጠናቀን ከወጣን በኋላ የወልዲያ ከተማ መስተዳድር ተረክቦ በኃላፊነት የሚከታተል ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ ሁዳ ሪል ስቴት በወልድያ አካባቢ የተለያዩ  ግንባታዎችን ስለሚሠራ ቢሮውን ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ቢሮው የተከፈተው አንደኛ የወልድያ ስታዲየም ሲሠሩ የነበሩ ወጣት ባለሙያዎች እንዳይበተኑ በማሰብና በአካባቢው በመንግሥትም የሆነ በግል የሚወጡ የግንባታ ጨረታዎችን በመወዳደር ለመሥራት ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ስታዲየሙ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅርበት ለመርዳት ነው፡፡ ለዚህም ግንባታውን ስናከናውን የወልድያ ወጣት ባለሙያዎች በብዛት አሳትፈን ስለነበር የመብራት፣ የኤሌክትሪክ ወይም ተዛማጅ ችግሮች ቢያጋጥሙ በቅርበት እንዲያስተካክሉ መሐንዲሶቹን አዘጋጅተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የወልድያ ስታዲየም ሲገነባ ብዙ ባለሙያዎች ትምህርት እንደቀሰሙ ይታመናል፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ግንባታዎች እየተከናወኑ ሲሆን ሌሎች ግንባታዎችን ተረክቦ ለመሥራት ምን ዓይነት እንቅስቃሴ እያደርገችሁ ነው?

አቶ ዮናስ፡-የወልድያ ስታዲየምን 90 በመቶውን ወጣት ኢትዮጵያን ባለሙያዎች ናቸው የገነቡት፡፡ ስታዲየሙ ሲገነባ ብዙ ልምድ አግኝተናል፡፡ በቀጣይ የበለጠ ለመሥራት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በዘርፉ ላይ መሳተፍ የሚቻለው በጨረታ ስለሆነ፣ አዲስ አበባ ውስጥ የሚሠሩ ሁለት ግንባታዎች ላይ ጨረታ ብንሳተፍም ሊሳካልን አልቻለም፡፡ ችግር ኖሮብን ከሆነ በሒደት የምናስተካክለው ይሆናል፡፡ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የግንባታ ጨረታውን ማሸነፍ ባንችልም ጥረታችንን ግን አናቆምም፡፡

Standard (Image)

‹‹እኛ የሚያሳስበን የአንድ ሰው ሕይወት ነው››

$
0
0

ዶ/ር ተስፋዬ ተፈራ፣ በአሜሪካ ሎሳንጀለስ ከተማ በተቋቋመው ኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን (ኤኤችኤፍ) የኢትዮጵያ የሜዲካል ዳይሬክተር

ዶ/ር ተስፋዬ ተፈራ እ.ኤ.አ. በ1987 በአሜሪካ ሎሳንጀለስ ከተማ የተቋቋመው ኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን (ኤኤችኤፍ) የኢትዮጵያ የሜዲካል ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ፋውንዴሽኑ ስለ ኤድስ የነበረው መረጃ እምብዛም በነበረበት፣ ለታማሚዎች እንክብካቤ መስጠት ባልተጀመረበት ወቅት በግለሰቦች የተቋቋመ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በሚገኙ 37 አገሮች በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ መሥራት የጀመረው ከዛሬ አሥር ዓመታት በፊት ቢሆንም፣ ራሱን ችሎ መሥራት የጀመረው  የዛሬ ሦስት ዓመት ነው፡፡ ፋውንዴሽኑ ሰሞኑን የኤችአይቪ ሕክምናን በተመለከተ ለጋዜጠኞች የግማሽ ቀን ዓውደ ጥናት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ የድርጅቱን  እንቅስቃሴና በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለውን የኤችአይቪ ሥርጭት በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን ዶ/ር ተስፋዬን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡-የኤድስ ኬር ፋውንዴሽን ራሱን ችሎ በተቋቋመበት ወቅት በአገሪቱ የነበረው የኤችአይቪ ሥርጭት የቀነሰበት ወሬውም የተቀዛቀዘበት ጊዜ ነበር፡፡ ብዙ በኤችአይቪ ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶችም ፊታቸውን ወደ ሌላ ማኅበራዊ ችግሮች ያዞሩበት ወቅትም ነበር፡፡ በዚያ ወቅት እናንተ ራሳችሁን ችላችሁ እንድተቋቋሙ ያነሳሳችሁ ምን ነበር?

ዶ/ር ተስፋዬ፡-ኤኤችኤፍ በኢትዮጵያ ከዛሬ አሥር ዓመታት ጀምሮ በቀጥታም ባይሆን ሲሠራ ነበር፡፡ ራሱን ችሎ መቋቋም የፈለገበት አንዱ ምክንያት አብሮት ይሠራ የነበው ድርጅት ሊዘጋ ሲል ነፃ ሕክምናን የሚሰጡ የኤኤችኤፍ ክሊኒኮች አብረውት እንዳይዘጉ በመስጋትነው፡፡ የኤችአይቪ ኤድስ ፕሮግራም መቀዛቀዙና የዛኛው ፕሮግራም መዘጋት በአጋጣሚ መገጣጠሙ እንጂ ይህ ብቻ አልነበረም፡፡ ምክንያቱ የፋውንዴሽኑ ዋና ዓላማ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ ተደራሽነቱን እያስፋፋ መሄድ ነው፡፡ የሚሠራውም ሁለት ነገሮች ላይ ትኩረት አድርጎ ነው፡፡ አንደኛው መከላከል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የሕክምና ዕርዳታ መስጠት ነው፡፡ መከላከል ላይ በሁለት ፕሮግራሞች ማለትም ኮንዶም የማሠራጨትና ትምህርት በመስጠት ሰዎችን የማስተባበር ሥራ እንሠራለን፡፡ ራሳቸውን እንዲያውቁ እናደርጋለን፡፡ የሕክምና አገልግሎትም እንሰጣለን፡፡ በእርግጥ በአገሪቱ የኤችአይቪ መድኃኒት በአብዛኛው በመንግሥት የሚሸፈን ነው፡፡ ኤኤችኤፍም ከመድኃኒት ውጪ ያሉትን ሕክምናዎች በነፃ ያቀርባል፡፡ 

ሪፖርተር፡-የፀረ ኤድስ መድሀኒት መደበኛ ባለሆኑ መንገዶች የሚገባው እንዴትና በምን አጋጣሚ ነው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡-  በእርግጠኝነት ለመናገር መረጃ ያስፈልጋል፡፡ ግን አንዳንድ ግለሰቦች የኤችአይቪ መድኃኒቶችን ከውጭ በግላቸው ያመጣሉ፡፡ ዘመዶቻቸውም ከውጭ የሚልኩላቸውም አሉ፡፡ በተለይ ሕክምናቸውን በውጭ አገር ሲከታተሉ የነበሩ ወደዚህ ሲመጡ የጀመሩትን መድኃኒት በዘመዶቻቸው አልያም በሌላ መንገድ ይገባላቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡-በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙት የፀረ ኤድስ መድኃኒቶች የፈዋሽነት አቅም ዝቅተኛ ስለሆነ ነው ከውጭ መድኃኒት የሚያስገቡት ወይስ ሌላ ምክንያት አላቸው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡-  አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ወደ 25 የሚደርሱ የፀረ ኤድስ መድኃኒቶች አሉ፡፡ እኛ አገር ቀላል የሆነ ልኬት ተዘጋጅቶለታል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውን መርህ ነው የምንከተለው፡፡ በዚህ መሠረት በጣም ጥቂት ለሆኑ ግለሰቦች ካልሆነ በስተቀር ወደ 99 በመቶ የሚሆነው ሕክምና የኢትዮጵያን ሕግ የተከተለ ነው፡፡ በሌላ አገር ለምሳሌ በአሜሪካ እንደኛ አገር ፊክስድ ዶዝ ኮምቢኔሽን አይደለም የሚጠቀሙት፡፡ ጂን ሬዚስታንስ ቴስቲንግ የሚባል ምርመራ አለ፡፡ መድሀኒት የሚሰጡአቸው ይህን ምርመራ ሠርተውላቸው ይህ ቫይረስ ከዚህኛው ዓይነት መድኃኒት ጋር ይጣጣማል ወይ አይጣጣምም የሚለውን ካረጋገጡ በኋላ ነው፡፡ እኛ አገር ፊክስድ ኮምቢኔሽን የሆነ በፓኬጅ የተዘጋጀ ነው የሚሰጣቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ውጭ አገር የሚኖሩ ከሆኑ ከኢትዮጵያ አንዱን የተቀረውን ደግሞ ከውጭ በተለያዩ መንገዶች የተቀሩትን መድኃኒቶች ያገኛሉ እንጂ እኛ ጋር ስለሌለ አይደለም፡፡ እኛ ጋር በደንብ ያልገቡ ብዙ አዳዲስ መድኃኒቶች አሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ያሉት መድኃኒቶች ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኤችአይቪ እንደገና እያገረሸ እንደሚገኝ እየተገለጸ ይገኛል፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

ዶ/ር ተስፋዬ፡-አሁን ኤችአይቪ ወደነበረበት ተመልሷል ለማለት ጥናት ያስፈልገናል፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ኤችአይቪ ኤድስን በመከላከል ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡ አገሮች አንዷ ነች፡፡ ይህ የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ መረጃዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ2001 በኢትዮጵያ የነበረው የኤችአይቪ ሥርጭት መጠን 3.4 በመቶ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2011 በኋላ ግን የሥርጭት መጠኑ ወደ 1.4 በመቶ ዝቅ ለማለት ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኤችአይቪ ሥርጭት 1.07 በመቶ ሆኗል፡፡ ይህም የሥርጭት መጠኑ በየጊዜው እየቀነሰ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡ በየዓመቱ በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር እንኳ ብንመለከት በኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ መቀነስ ተችሏል፡፡ ሆኖም በአንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ በስፋት የሚገኝበት፣ አገር አቀፍ ሥርጭቱም ከክልል ክልል፣ ከገጠር ከተማ የሚለያይ ሆኗል፡፡ በፊት ሁሉንም የማጥቃት ነገር ነበረው፡፡ አሁን የተወሰኑትን ተጋላጭ የኅብረተሰቡን ክፍሎች ነው የሚያጠቃው፡፡ ስለዚህም ኤች አይቪን ለመከላከል በፊት የምንከተላቸው እስትራቴጂዎች አሁን አይሠሩም ማለት ነው፡፡ የተሻለ እስትራቴጂ ያስፈልገናል፡፡

ሪፖርተር፡-ምን ዓይነት እስትራቴጂ ነው የሚያስፈልገው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡-በኢትዮጵያ ለኤችአይቪ ተጋላጭነት ካላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴተኛ አዳሪዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ከከተማ ከተማ ይለያይ እንጂ እስከ 23 በመቶ የሚሆኑት ሴተኛ አዳሪዎች ኤችአይቪ ኤድስ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የሕክምና አገልግሎት የማያገኙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙም ተጋላጭ ናቸው፡፡ ኢንቨስትመንት የሚስፋፋባቸው ቦታዎች የሚኖሩ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው፡፡ እነዚህ ክፍሎች ላይ ትኩረት አድርገን መሥራት ከቻልን በሽታው ቀድሞ ወደነበረበት እንዳይመለስ ማድረግ እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡-እነዚህ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ላይ ትኩረት ተደርጎ አልተሠራም ነበር እያሉ ነው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡-በዚያ ጊዜ የወረርሽኙ ሁኔታ እንደ አጠቃላይ ስለነበር የሚተላለፈው መልዕክት፣ የኤችአይቪ ምርመራ ለሁሉም ሰው ነበር፡፡ በዚህ ትልቅ ለውጥ መፍጠር ተችሏል፡፡ ይህን በአሁኑ ሰዓት ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑት ኅብረተሰቦች ብናደርገው በቀላሉ ለውጥ መፍጠር እንችላለን ለማለት ነው እንጂ ሌላው ማኅበረሰብ ትምህርት አያስፈለገውም፣ ምርመራ አያስፈልገውም ለማለት አይደለም፡፡ ተጋላጭነት ባላቸው የኅብረተሰቡ አካላት ላይ ትኩረት ብናደርግ ውጤቱ የላቀ ስለሚሆን ነው፡፡

ሪፖርተር፡-የኤችአይቪ መከላከያና የሕክምና አገልግሎትን በተመለከተ የተለያዩ  ችግሮች ይስተዋላሉ? ከመመርመሪያ መሳሪያዎች አቅርቦት ጀምሮ ችግሮች እንዳሉ ይሰማል፡፡ በዚህ ላይ ምን ታዝበዋል?

ዶ/ር ተስፋዬ፡-መንግሥትን ወክዬ መናገር አልችልም፡፡ እኛ ግን በወረዳዎች ላይ በምንሠራበት ወቅት የታዘብናቸው ነገሮች አሉ፡፡ ኤችአይቪ እንደገና እያገረሸ ነው ለማለት ጥናት ማድረግ ያስፈልጋለ፡፡ ነገር ግን አሁንም አርፈን የምንተኛበት ጊዜ ላይ አልደረስንም፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ከ21,000 ሰዎች በላይ በኤችአይቪ ይያዛሉ፡፡ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር የሥርጭት መጠኑ አነስተኛ ይሁን እንጂ በመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ አንድ በመቶ የሥርጭት መጠን እንኳ ብዙ ነው፡፡ እኛ የሚያሳስበን የአንድ ሰው ሕይወት ነው፡፡ አንድ ሰው በበሽታው እንዳይያዝ ማድረግ እንችላለን:: አሁን ይህንን ማድረግ የምንችልበት አጋጣሚም አለን፡፡ በየዓመቱ 26,000 ሰዎች በኤችአይቪ ኤድስና በተያያዥ ጉዳዮች ይሞታሉ፡፡ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒትና ሕክምና እያለ ይህንን ያህል ሰው መሞቱ ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለዚህ እንዳይያዙ አስቀድሞ መከላከል፣ ከተያዙ በኋላ ደግሞ በሕክምና እንዳይሞቱ ማድረግ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡-በመከላከሉ ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወተው ኮንዶም፣ የመመርመሪያ መሣሪያዎች እንዲሁም የመድኃኒት አቅርቦትን በተመለከተ ክፍተቶች እንደሚያጋጥሙ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት ይሰጣሉ?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- የኢትዮጵያ የኤችአይቪ ኤድስ ፕሮግራም ውጤት የሚያመጣና ውጤት እያመጣም ያለ ነው፡፡ በ1998 ዓ.ም. ፖሊሲው ከተቀረፀ ጊዜ ጀምሮ መንግሥት በስፋት እየሠራ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ የኤችአይቪ ምርመራ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ማዕከላት ቁጥር በሺዎች የሚቆጠሩ ሆነዋል፡፡ የፀረ ኤድስ መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎችም 400,000 አካባቢ ደርሰዋል፡፡ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ይህ ግን ካልቀጠለ ወደኋላ የሚመልሱ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ የኮንዶም ተደራሽነት እንደሚታሰበው አይደለም፡፡ አንዳንድ ደንበኞቻችን እንደሚነግሩን ከሆነም የኮንዶም እጥረት ይታያል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ አንድ ፍሬ ኮንዶም እስከ 40 ብር የሚሸጥበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ እኛ እንደ ኤድስ ኬር ፋውንዴሽን ኮንዶም ገዝተን ለጤና ድርጅቶች፣ ለክፍለ ከተሞችና ለጤና ቢሮዎች እናሰራጫለን፡፡ ነገር ግን በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ይህ ኮንዶም ለተባለለት ዓላማ ሳይውል ወይም ደግሞ በነፃ መሰጠት ሲገባው ወደ ግዢ የተገባበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ እንግዲህ ባለው እጥረት የተከሰተ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ከጤና ቢሮዎች ጋር ምክክር እያደረግን ለኤችአይቪ መከላከያ የሚሆን ኮንዶም ለጤና ድርጅቶች ትሰጣላችሁ ወይ የሚል ጥያቄ አቀረብንላቸው፡፡ መልሳቸው ግን ‘ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከል ሳይሆን ለቤተሰብ ምጣኔ ብቻ ነው’ የሚል ነበር፡፡ እርግዝናን በሌላ መንገድ መከላከል ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሰዎች እርግዝናን ለመከላከል ኮንዶም እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ የኮንዶም ተደራሽነቱ ላይ መታሰብ አለበት፡፡ ሁለተኛው የኤችአይቪ መመርመሪያ መሣሪያዎችን በተመለከተ ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት አወዛጋቢ የነበረ ነገር ነው፡፡ አገሪቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሁለት ጊዜ የኤችአይቪ መመርመሪያ አልጎሪዝም ቀይራለች፡፡ በመንግሥት አማካይነት ነው የመመርመሪያ መሣሪያዎች እየመጡ ያሉት፡፡ መመርመሪያዎቹ ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ ነው፡፡ ይሁንና በሁሉም ቦታዎች በሚፈለገው መጠን ይገኛል ወይ? የሚለው አሁንም አጠያያቂ ነው፡፡ ኤችአይቪ ለመመርመር ሦስት ኪት ነው የሚያስፈልገው፡፡ እኔ ሦስት ኪት ሲኖረኝ ነው ኤችአይቪን የምመረምረው፡፡ የተመርማሪው ውጤት ፖዘቲቭም፣ ኔጌቲቭም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ምርመራውን ለማድረግ ሦስቱም ኪቶች ሊኖሩኝ ይገባል፡፡ በአንዱ ኪት እመረምራለሁ፡፡ ኔጌቲቭ ከሆነ እዚያ ጋር እቆማለሁ፡፡ የተቀሩትን አልጠቀምም፡፡ ፖዘቲቭ ከሆነ ግን ፖዘቲቭ ብዬ ከመናገሬ በፊት ሁለተኛ ጊዜ የማረጋገጫ (ኮንፈርማቶሪ) ምርመራ በሁለተኛው ኪት አደርጋለሁ፡፡ በመጀመርያው ምርመራ ፖዘቲቭ የሆነው በሌላ ምክንያት ይሆናል፡፡ ስለዚህም በትክክል ኤችአይቪ ነው የሚለውን ለማረጋገጥ ትክክለኛ ውጤቱን 99.8 በመቶ  ማሳየት በሚችለው ሁለተኛው ኪት ምርመራ አደርጋለሁ፡፡ ይህኛውም ፖዘቲቭ ከሆነ ደግሞ ሌላ ምርመራ ማድረግ ሳያስፈልገኝ ፖዘቲቨ ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡ ነገር ግን በሁለተኛው ምርመራ ኔጌቲቭ እንደሆነ የሚያሳይ ከሆነ ሁለቱን ውጤቶች የሚያስታርቅ ሦስተኛ ምርመራ አደርጋለሁ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንድን ሰው ከመመርመሬ በፊት ሦስቱ ኪቶች በእጄ ሊኖሩ ይገባል፡፡ ውጤቱን እርግጠኛ ሳልሆን መናገር የለብኝም፡፡ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ውስጥ አንድ ሰው በአንድ ሐኪም ተመርምሮ ኤችአይቪ ፖዚቲቭ ከተባለ በኋላ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት እንዲጀምር አይጠበቅም፡፡ የዓለም የጤና ድርጅትና የኢትዮጵያ ሕግ በሚያዘው መሠረት ሁለተኛ ምርመራ በሌላ ባለሙያ፣ በሌላ የደም ናሙና፣ በተመሳሳይ የምርመራ መሣሪያና አልጎሪዝም እንዲመረመር ይደረጋል፡፡ ሁለቱ ሰዎች ሲያረጋግጡ ብቻ ነው ፀረ ኤችአይቪ መጀመር ያለበት፡፡ ይህም አንድ ሰው በተሳሳተ የምርመራ ውጤት ዕድሜውን ሙሉ ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት እንዳይወስድ ለማድረግ ነው፡፡ ኤችአይቪ ምርመራን በተመለከተ ይህንን ያህል ኢንቨስትመንት ይጠይቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሦስቱም መመርመርያ ኪቶች በአንድ ላይ ላይገኙ ይችላሉ፡፡ የመቆራረጥ ሁኔታም ይታያል፡፡ ሌላው የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒትን አቅርቦት በተመለከተ ጥያቄ የለውም ተደራሽ ነው፡፡ ብዙ ሰዎችም እየወሰዱት ነው፡፡ ነገር ግን በጤና ድርጅት ውስጥ የሚሰጠው ሕክምና በፊት እንደሚሰጠው ዓይነት ደረጃ የለውም፡፡ ወይም ደግሞ ፓኬጅ የለውም፡፡ በፊት የመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ የጤና ድርጅቶች ሁለት ዓይነት መድኃኒቶች ከመንግሥት ያገኛሉ፡፡ አንደኛው የፀረ ኤችአይቪ ሕክምናውን ነው፡፡ ሁለተኛው የተጓዳኝ በሽታዎች መድኃኒቶች ናቸው፡፡ ፀረ ኤችአይቪው በአሁን ሰዓት በበቂ አለ፡፡ ብዙ ችግር አያጋጥምም፡፡ የተጓዳኝ በሽታዎች ሕክምና መድኃኒቶች በፊት በተገቢው መጠን ይገኙ ነበር፡፡ አሁን ግን እየቀነሱ እየቀነሱ መተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ለምን ሆነ?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- ይኼን መንግሥት ነው የሚያቀርበው፡፡ በእኛ በኩል ግን እነሱን መድኃኒቶች በዕርዳታ የምናገኝበት የራሳችን መንገድ ስላለን መድኃኒቶቹን እናቀርባለን፡፡ እኛ ጋር እንኳን መድኃኒቶቹ ባይኖሩ ከሌሎች ጋር በመተባበር በነፃ እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ ዉጪ ያሉ ሰዎች ግን መድኃኒቶቹ በሚፈለገው መጠን እየቀረቡ ባለመሆናቸው ለግዢ ይዳረጋሉ፡፡ እኛ ግን በራሳችን መንገድ ለማካካስ እንሞክራለን፡፡ ሌላኛው የአገልግሎትን ጥራት በተመለከተ ያለው ነው፡፡ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቱ በጣም ጥሩ ለውጥ ያመጣና እስከ 96 በመቶ የሚሆነውን ኤችአይቪ መከላከል የሚያስችል መድኃኒት ነው፡፡ መከላከል የሚችለው በትክክል ሲወሰድ ነው፡፡ በትክክል ካልወሰዱ ፀረ ኤችአይቪው የመሥራት ዕድሉ አነስተኛ ይሆናል፡፡ መድኃኒት ወስደው የሚያቋርጡ ሰዎች በመኖራቸው መድኃኒት የተላመደ ቫይረስ እንዳይሠራጭ እንሠጋለን፡፡ በሌላ በኩል አንድ ሰው መድኃኒቱን በአግባቡ ሲከታተል ነው ቫይረሱን ወደ ሌላ የማስተላለፍ ዕድሉ ዝቅተኛ የሚሆነው፡፡ በትክክል ካልወሰደ ግን የማስተላለፍ እድሉ ይጨምራል፡፡ እዚህ ላይ አደጋው የሚያስተላልፈው ቫይረስ መድኃኒት የለመደ ሊሆን ስለሚሆን ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  በአገሪቱ ለተላመደ ቫይረስ የሚሆን  የመድኃኒት  አቅርቦት ምን ይመስላል?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- እንዳልኩሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ስታንዳርዳዝድ የሆነ አሠራር ነው ያለው፡፡  የተላመደ ቫይረስን የምንለይበት የምርመራ አካሄድ ጄኖታይፒንግ የለንም፡፡ ለየትኛውም መድኃኒት ሬዚስታንት እንደሆነ እንኳን አናውቅም፡፡ ስለዚህ አሁን ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ የዓለም የጤና ድርጅትም በ2030 ኤችአይቪን ለመቆጣጠር አንዱ ብሎ ያስቀመጠው በሰውነት ውስጥ ያለውን ቫይረስ መጠን መቀነስ ነው፡፡ ይህ ማለት መድኃኒት ከሚወስዱ ሰዎች መካከል 90 በመቶ በሚሆኑት ሰዎች የደም መጠን ውስጥ የሚገኘውን ቫይረስ መጠን መቀነስ ከቻልን የመቆጣጠርና የማጥፋት ተስፋ ይኖረናል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ነገሮች ይበልጥ ይወሳሰባሉ፡፡

 

Standard (Image)

‹‹የታወቅንበትን እንግዳ አቀባበል በሆቴል አገልግሎት ላይ ብናውለው ትልቅ ለውጥ ይመጣል››

$
0
0

 

አቶ አንዱዓለም ታደሰ፣ የሆቴል አስተዳደር ባለሙያ

ሆቴሎችን፣ ሪዞርቶችንና ሬስቶራንቶች በማደራጀት ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ አንዱዓለም ታደሰ የተወለዱት በያቤሎ ከተማ ሲሆን፣ ዕድገታቸውና ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሐዋሳ ከተማ ነው፡፡ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለምረቃ የበቁበት የሆቴል አስተዳደር (ማኔጅመንት) ትምህርት መከታተላቸው ባደጉባትና በተማሩባት ሐዋሳ ከተማ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎች በሙያቸው ለመሥራት አስችሏቸዋል፡፡ በሥራቸው ዙሪያ ታምራት ጌታቸውአነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሆቴል ማደራጀት ሥራ ጋር እንዴት ተገናኙ?

አቶ አንዱዓለም፡-ሐዋሳን አውቃታለሁ፤ ከ15 ዓመት በፊት ገና ምንም ያልነበራት ከተማ ነበረች፡፡ ብዙም ሆቴል ስላልነበራትም ሰዎች ተዝናንተው ወደ ሻሸመኔ አደራቸውን ይመለሱ ነበር፡፡ ገና ግንባታ ላይ ነበረች፡፡ ወደዚህ ሥራ የገባሁት ፈልጌው አልነበረም፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ራቅ ብዬ መማር ነበር የምፈልገው፡፡ በአጋጣሚ ደግሞ ማንኛውም ተማሪ በአካባቢው ባለ ዩኒቨርሲቲ ይማር የሚል ሕግ በመውጣቱ እሱን ተቀብዬ ስገባ በህልሜም በውኔም የሌለ ከመረጥኩት የትምህርት ዓይነት ውጪ ሆቴል ማኔጅመንት እንደደረሰኝ በጋዜጣ ተመለከትኩ፡፡ ምንም ምርጫ ስላልነበረኝ ትምህርቴን በመቀጠል ለዩኒቨርሲቲውም ሁለተኛ ባች ሆኜ ተመረቅሁ፡፡ ትምህርቱ ለዩኒቨርሲቲውም ለእኔም በዚህ ሥራ ላይ ለተሰማሩም አዲስ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ቀጥታ ወደ ማናጀርነት ነው የገባሁት፡፡ ከተማዋም ትልልቅ ሆቴሎች እየተገነቡባት እንዲሁም አገልግሎት መስጠት የጀመሩም ነበሩባት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ሌዊ ሪዞርት ሐዋሳ ፒያሳ ያለውን ማናጀር በመሆን ነው ሥራዬን የጀመርኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ሆቴል ማደራጀት ማለት ምን ማለት ነው?

አቶ አንዱዓለም፡-ሆቴል ማደራጀት ማለት ራሱን የቻለ ሳይንስ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ባለሙያ በሆቴሉ ባለቤት አቅም ልክ፣ ይህን ያህል ሰው የሚይዝ የስብሰባ አዳራሽ፣ ይህን ያህል የመኝታ ክፍሎች ወዘተ… ብሎ ዲዛይን ይሠራል፡፡ በተሠሩት ላይ ደግሞ አደራጁ አዳራሹ ከመኝታ ክፍሉ፣ ኪችኑ ከመመገቢያ አዳራሹ እንዲሁም ሌሎችም የሆቴሉ ክፍሎች እንዴት እርስ በርስ ተቆላልፈውና ተመጋግበው ይሠራሉ የሚለውን ዲዛይን ይሠራል፡፡ ከዛ ግንባታው ካለቀ በኋላ ደግሞ ሰዎችን ያሠለጥናል፣ ሥርዓት ይዘረጋል፡፡ ለማኔጅመንት የሚያገለግሉ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም ሲስተም መዘርጋት፣ ያንን ለማይችሉ ደግሞ በማንዋል እንዲሠሩ ማዘጋጀት፣ በጥቂቱ ሲሆኑ በአጠቃላይ ሕንፃው ላይ ነፍስ በመዝራት ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል እንዲሆን ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስንት ሆቴል አደራጅተዋል?

አቶ አንዱዓለም፡-ሥራውን የጀመርኩት ፒያሳ በሚገኘው ሌዊ ሪዞርት ነው፡፡ ከዛም ሐይቁ ዳር ሪዞርት ሲገነባ ያንን በማደራጀትና በማናጀርነት እየሠራሁ ኃይሌ ሪዞርት መጣ፡፡ ከኃይሌ ጋር መሥራት ደግሞ ዕድሉ ስለገጠመኝ በጣም ደስተኛ ነበርኩ፡፡ የሱንም ለሁለት ዓመት በማደራጀትና በማናጀርነት ከሠራሁ በኋላ ራሴን ሳየው የማደራጀቱን ሥራ አሁን ባለኝ አቅም ሙሉ በሙሉ መሥራት እንደምችል በማመኔ የራሴን ቢሮ በመክፈት የማደራጀቱን ሥራ በስፋት ጀመርኩ፡፡ የቢዝነስ ፈጠራ በውስጤ እንዳል ያላሰብኩት ትምህርት አውጥቶልኛል፡፡ ከሆቴሉ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲ ስማር የተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆኜ ለትምህርት ቤቱ የሚቀርበው እንጀራ ከየመደብሩ የሚገዛው በከፍተኛ ወጪ ነበር፡፡ ግዢውን በከተማ የሚኖሩ ደካማ እናቶች 200 የሚሆኑ በማደራጀት ከጤፍ ግዢ ጀምሮ እንጀራ አቅርቦት ድረስ ለዩኒቨርሲቲው እንዲያቀርቡ አደረግኩ፡፡ ለእነዚህ እናቶች የተፈጠረው የሥራ ዕድል ዛሬ ለሆቴሎች ጭምር አቅርቦት ማድረግ ችለዋል፡፡ ሌሎችም በርካታ የቢዝነስ ፈጣራዎችንም በከተማ ላሉ ነዋሪዎች ሠርቻለሁ፡፡ ከአደራጀኋቸው በርካታ ሆቴሎች ለምሳሌ ጎንደር ላንድ ሆቴል፣ ሐዋሳ ኃይሌ ሪዞርት፣ ሌዊ፣ ሴንትራል ኬርድ ይገኙበታል፡፡ አሁን በማናጀርነት እየሠራሁ ያለሁበት ባለ አምስት ኮከብ የሆነው ሮሪ ሆቴል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያሉ ሆቴል ገንቢዎች ወደእናንተ የመምጣት ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ አንዱዓለም፡-የሆቴል ኢንዱስትሪውና ባለሙያ በአገራችን የቅርብ ጊዜ ዕድገት ነው ያላቸው፡፡ ለምሳሌ እኔ ሥራ ከጀመርኩበት ከአሥር ዓመታት በፊት በባለሙያ እየተመሩ ይሠሩ የነበሩት ታላላቅ ሆቴሎች የነበሩትን ያህል የሆቴል ልምድ በሌላቸው በኮንስትራክሽን ባለሙያ ብቻ ተመርተው ወደ ሥራ የገቡም አሉበት፡፡ ከነችግሩ የተገነባው ሆቴል ደግሞ ባለቤቱ ለወደደው ሰው ነበር እንዲያስተዳድር የሚሰጠው፡፡ ይህ ደግሞ ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያ የዕድሜውን ያህል ለውጥ ማምጣት እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ኢንተርናሽናል ሆቴሎች መምጣት በዛው ልክ ዩኒቨርሲቲዎችም ለኢንዱስትሪው የሚሆን ባለሙያን ማፍራት በመጀመራቸው ለውጥ እየታየ ነው፡፡ ከትክክለኛ የሆቴል ባለሙያ ጋር መመካከር፣ አስተያየት መጠየቅ፣ አምኖ መቀበል ይታያል፡፡ ስለዚህ ከኮንስትራክሽን ባለሙያ ወደ ሆቴል ባለሙያ እየተቀየረ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው የሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት የኤሌክትሪክ ዝርጋታ የውኃ መስመር እንዲሁም የአንድ ሆቴል ግንባታ ምን መምሰል እንዳለበት ጥቂት ስለሚማር ቢያንስ ፕላኑን በማጥናት መስተካከል ያለበትን አስተያየት መስጠት ይችላል፡፡ እንግዲህ ለአሁኑ ጊዜ ባለሙያና ባለሀብት በጥምረት የሠሩት ማሳያ ይሆናል ብዬ የማስበው ሮሪ ሆቴልን ነው፡፡ ከሐሳቡ ጀምሮ አሁን እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ በርካታ የሆቴል አማካሪዎችን በመቅጠር፣ አስተያየት በመጠየቅ የአገሪቱን የአምስት ኮከብ ደረጃን ባከበረ መልኩ ተገንብቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ሆቴሎች በብዛት እየተገነቡ ቢሆንም የአገልግሎት (ሰርቪስ) አሰጣጣቸው ግን ገና እንደሆነ ይነገራል፤ ችግሩ ምንድነው?

አቶ አንዱዓለም፡-ያው አሁንም ኢንዱስትሪው ዕድገት ላይ ነው፡፡ ትንሽ ግን መሻሻሎች ይታዩበታል እላለሁ፡፡ ቢያንስ አሁን ባሉ ትምህርት ቤት ከራስ ንጽሕና አጠባበቅ ጀምሮ የእንግዳ አቀባበል መስተንግዶው ትምህርቱ ይሰጣል፡፡ በዚህም ባለሙያው ቢሆን ለውጥ ሲያመጣ ይታያል፡፡ ግን ይኼ የእነሱ ችግር ብቻ አይደለም እንደ አገርም መታየት ያለበት ነው ደረጃውን የሰጣቸው አካል ቁጥጥር ካላደረገ መመለሳቸው አይቀርም፡፡ በቁጥጥሩ ወቅትም ጉድለት የታየባቸውን ቅጣት በመጣል ቀሪውም ተስተካክሎ ይሠራል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ሌላው ምናልባት በየዓመቱ ማን ምን ዓይነት ደረጃ እንዳገኘና እንዳለው ለኅብረተሰቡ ማስተዋወቅ ተጠቃሚው ከየትም ቢመጣ ወጥ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኝ ይረዳዋል፡፡ ሆቴሉም ደረጃውን እንደጠበቀ ሊሠራ ያስችለዋል፡፡ የታወቅንበትን እንግዳ አቀባበል በሆቴል ላይ ብናውለው ትልቅ ለውጥ ይመጣል፡፡

ሪፖርተር፡- በሆቴል ማደራጀት ወይም ማናጀርነትህ እንደ ትልቅ ችግር የሚነሳው ምንድነው?

አቶ አንዱዓለም፡-ዋነኛ ችግሩን መመለስ ነው፡፡ የሆቴል ሥራ ደግሞ ወጥነት ይፈልጋል፡፡ በየትኛውም አገልግሎት የሚዋወቅ ከሆነ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ በሚገባው መልኩ አደራጅተህ ስትሄድ፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እነሱ በሚመቻቸው መልኩ መልሰውት ታገኘዋለህ፡፡ ማናጀር ስትሆንም እንደዚህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደፊት ሆቴሎች ሲገነቡ ምን መደረግ አለባቸው ይላሉ?

አቶ አንዱዓለም፡-ዘመኑ የውድድር ነው፡፡ ትላልቅ ስም ያላቸው ሆቴሎች እየመጡ ነው፡፡ ውድድሩ የሚሆነው ልምድ ባለውና በሌለው ነው፡፡ ስለዚህ ሆቴል መሥራት የሚያስብ ሰው ከመሬት መረጣ ጀምሮ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም እንኳን ከባለሙያ መለየት የለበትም፡፡ ምክንያቱም ቢዝነሱ ዛሬ ተሽጦ የሚመለስ አይደለም፡፡ ቀስ እያለ የጥራት ስሙን መጠበቅ ይገባዋል፡፡ 

Standard (Image)

‹‹የአሜሪካውን ተምች በነቂስ መልቀም ቢቻል ከየአካባቢው ማጥፋት ይቻል ነበር››

$
0
0

አቶ ተስፋዬ መንግሥቴ፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ፣ የግብዓት አቅርቦትና አጠቃቀም ያለበትን ደረጃ እንዲሁም በቀጣይ በትኩረት መሠራት ስለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችና በበልግና በመኸር ሰብሎች ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ የሚገኘውን የአሜሪካ ተምች አስመልክቶ ሰኔ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡ መግለጫውን የሰጡት የእርሻ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ መንግሥቴ ናቸው፡፡ መግለጫውን የተከታተለችው ምሕረት ሞገስእንደሚከተለው አቀናብራዋለች፡፡

ጥያቄ፡- የመኸር እንቅስቃሴ ምን ደረጃ ላይ ነው?

አቶ ተስፋዬ፡- የዘንድሮውን በጀት ዓመት ዕቅድ ለመንደፍ መነሻ ያደረግነው የዓምናውን አፈጻጸም ነው፡፡ ዓምና 12 ሺሕ ሔክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ተሸፍኗል፡፡ ከዚህም በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የመረጃ አሰባሰብ ሥርዓት መሠረት ወደ 290 ሚሊዮን ኩንታል ምርት አግኝተናል፡፡ ጉድለቶች ቢኖሩም የተሻለ አፈጻጸም ነበር፡፡ የዘንድሮ ዕቅድ 13.8 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለመሸፈን ሲሆን፣ ከምርትም አንፃር 345 ሚሊዮን ኩንታል ይገኛል ተብሎም ታቅዷል፡፡

ጥያቄ፡- ይህንን ዕቅድ እንዴት ማሳካት ይቻላል?

አቶ ተስፋዬ፡- ይህንን ለማሳካት የአቅም ግንባታ ሥራውን ከዚህ ቀደም ከነበረው አጠናክረን መግባት አለብን ብለን ተነስተናል፡፡ በዋናነት ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ የንቅናቄ መድረክ በተደራጀ መልኩ እንዲካሄድ የሚል ነበር፡፡ የዘንድሮ የሰብል ሥራችን ከዚህ ቀደም የነበረውን ችግር የሚያካክስ፣ ያለንን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ የሚጠቀም፣ ወደፊት የሚፈጠሩ ችግሮችን የሚያስወግድ መሆን አለበት በሚል መግባባት እንዲፈጠርና ንቅናቄው እንዲሳካ ተሠርቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ያጋጠሙ የዕውቀትና ክህሎት ችግሮችን ለይተን ስለገባን ዘንድሮ ተግባር ተኮር ሥልጠናዎችን ለመስጠት ጥረት ተደርጓል፡፡ ተግባር ተኮር ሥልጠናው በአርሶ አደሩ ዘንድ ከዚህ ቀደም ከነበረው ሥልጠና የተሻለ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ጥያቄ፡- ሥልጠናው ከዚህ ቀደም ከነበረው ምን ይለየዋል?

አቶ ተስፋዬ፡- ሰብል ተኮር ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ ለምሳሌ በቆሎ ብቻ የሚያመርቱ አካባቢዎች ስለበቆሎ ብቻ የበለጠ የሚሠለጥኑበት፣ ስንዴ በክላስተር የሚያመርቱ አካባቢዎች ስንዴ ላይ የበለጠ ትኩረት እንዲያደርጉና በየአካባቢው ተለይቶ በብዛት የሚበቅል ሰብል ለገበያ፣ ለምግብና ለኢንዱስትሪ ወሳኝ ተብለው የተለዩ ሰብሎች ካሉም ሥልጠናው ያተኮረው በተለዩት ላይ መሆኑ ይለየዋል፡፡ ይህ ዓምናም በተለያዩ ክልሎች ጅምሩ ቢኖርም፣ ዘንድሮ በአራቱ ዋና ዋና ክልሎች ሰብል ተኮር ሥልጠና በተቀናጀ መንገድ ተሰጥቷል፡፡ በሞዴል፣ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙና ግፊት የሚፈልጉ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ አርሶ አደሮች አሉ፡፡ ለሦስቱ ዓይነት አርሶ አደሮች የሚሰጠው ሥልጠናም እንደየክፍተቶቻቸው የተለያየ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ዓምና በኦሮሚያ ክልል ሥልጠናው በስፋት ተሰጥቷል፡፡ በአማራ ክልል በተወሰኑ አካባቢዎች ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ ዘንድሮ በሁሉም አካባቢዎች የሥልጠና ቁሳቁስ በማዘጋጀት ተግባር ተኮር ሥልጠናው ተሰጥቷል፡፡ የአቅም ግንባታው ሥራ ከዓምናው የዘንድሮው የተሻለ ስለሆነ ለመኸር ሥራው ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ 345 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ለመሰብሰብ የባለፈውን መንገድ ብቻ በመከተል ውጤታማ ልንሆን አንችልም፡፡ የተለየና አዲስ አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይጠይቃል፡፡

ጥያቄ፡- ከአሠራር አንፃር ምን ታሳቢ ተደርጓል?

አቶ ተስፋዬ፡- የግብርና ሜካናይዜሽን ክላስተር ልማትን በተጠናከረ መንገድ ማካሄድ ታሳቢ የተደረገ ሥራ ነው፡፡ የግብርና ሜካናይዜሽን ሥርዓትን የማልማት ሥራ ማከናወንን ታሳቢ አድርገናል፡፡ በአራቱ ዋና ዋና ክልሎች ዓምና ሥራው ቢጀመርም ሰፊ አልነበረም፡፡ ያነጣጠረውም በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን ስናስብ ኩታ ገጠም በሆነ ሥፍራ ላይ ብቻ ያተኮረ አልነበረም፡፡ በአካባቢው ፀጋ የተመረጠ ሰብል ስንዴ፣ ገብስ ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል፣ የቦታውና የኤክስቴንሽን ሥራው ስፋት ታይቶ ተሠርቶበታል፡፡ ከገበያ አኳያ ዋጋ ያለው ሰብል በክልሎች አካባቢ እንዲለይ ተደርጓል፡፡ ዘንድሮ ይህ በሁሉም አካባቢዎች ይሠራል ተብሎ ታሳቢ የተደረገ ሲሆን፣ ይህ አርሶ አደሩ በአስተሳሰብ ደረጃ አንድ የሚሆንበትን መንገድ ይፈጥራል፡፡ ምን እናመርታለን? እንዴት እናመርታለን? መሬቱን ምን እናደርገዋለን? የሚሉ ጥያቄዎችን በጋራ የሚመልሱበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ የአመራርነት ሥርዓት ላይ እርስ በርስ እንዴት መደጋገፍ ይችላል? በሚለው ላይ እንዲሠሩ ያግዛል፡፡ እያንዳንዱ ሞዴል አርሶ አደር ሁለትና ሦስት ሞዴል አርሶ አደር ይዘው እንዲወጡ ዕቅድ ተሰጥቷል፡፡ ይህ በክላስተር ልማቱ ውስጥ ያሉ ሞዴል አርሶ አደሮች ሌሎቹን አርሶ አደሮች ደግፎ የማውጣት አሠራርን እንዲከተሉ ያደርጋል፡፡ ከግብርና ኢኮኖሚ አኳያ ያሉ ክፍተቶች  በተባይ መከላከልና በበሽታ ዙሪያ ያሉ ችግሮ በጋራ እንዲመለሱ ያደርጋል፡፡ ዕውቀት ለሁሉም አርሶ አደር የሚደርስበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ የክላስተር ልማት ገበያ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ካመረትን በኋላ ወደ ገበያ መሄድ ሳይሆን፣ ቀድመን የምናመርተው ምርት ገበያ አለው? የለውም? የሚለውን ለይተን የምናውቅበት ሥርዓት ዘርግተናል፡፡ አርሶ አደሩ የሚመረተው ሰብል ገበያ አለው? ወይስ የለውም? ብሎ ወስኖ እንዲገባ ይደረጋል፡፡ ወደዚህ ሥራ ሲገባ ግብርናን ለማዘመን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ አካሄዶች ይፈጠራሉ፡፡ የግብርና ሜካናይዜሸን ለመጠቀምም አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ የግብርና ሜካናይዜሽን ስንል የግድ ትራክተርና ኮምባይነር ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ሌሎች የግብርናውን ሥራ የሚያግዙ የግብርናና የእርሻ መሣሪያዎች ለመጠቀም አቅም ይፈጥራል፡፡ ይህ የሥራ ዕድልንም ይፈጥራል፡፡ በማረስ፣ በማጨድ፣ በመውቃት፣ በግብይት ሥርዓት ውስጥ በመግባት የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል፡፡ ይህ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ብቻ ሳይሆን ግብርናን ለማዘመን ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ይህ ዘንድሮ አቅደን የገባንበት ሥራ ነው፡፡ 

ጥያቄ፡- ከአቅም ግንባታ ጎን ለጎን ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ተስፋዬ፡- ግብዓትና ቴክኖሎጂን በስፋት ማቅረብ እየተሠራበት ነው፡፡ ግብዓትና ቴክኖሎጂን መጠቀም ያልቻለ ግብርና ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ ከግብዓት አኳያ በአግባቡና በመጠን ከተጠቀምን ግባችንን እናሳካለን፡፡ ከግብዓት አኳያ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ማዳበሪያ ነው፡፡ የከረመ ያልተጠቀምንበት እንዲሁም አዲስ የሚገዛ ተደምሮ 14 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ማቅረብ አለብን ብለን ዕቅድ ይዘናል፡፡ ይህ የዘንድሮ ዕቅድ ነው፡፡ የዓምናው በመጠን 12 ሚሊዮን ኩንታል ነበር፡፡ ዘንድሮ 14 ሚሊዮን ኩንታል ደርሷል፡፡ በማዳበሪያ ዓይነትም ዓምናና ከዚያ በፊት ዩሪያና ዳፕ እንጠቀም ነበር፡፡ ዘንድሮ አምስት ዓይነት ማዳበሪያዎች እንጠቀማለን ብለን ገብተንበታል፡፡ አምስቱም ዓይነት ከዩሪያና ከኤንፒኤስ በስተቀር ተቀነባብሮ አልቆለት የመጣ ነው፡፡ 11.5 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ በእጃችን ገብቷል፡፡  ከዕቅድ አኳያ 80 በመቶ የሚሆነውን አሳክተናል፡፡ በክልል ደረጃ ሲታይ ማዳበሪያ የሚጠቀሙ ዋና ክልሎች አማራና ኦሮሚያ ናቸው፡፡ ሁለቱም ከዕቅዳቸው 84 በመቶ ማዳበሪያ ደርሰዋል፡፡ ደቡብ በባህሪ ከሌሎች ክልሎች ስለሚለይና የበልግ ተጠቃሚም ስለሆነ ከዕቅዱ 71 በመቶ ደርሶለታል፡፡ ትግራይ በመጠኑ ዝቅተኛ ሲሆን፣ የሚያቀርብለትም ሙሉ ለሙሉ የግብርና ሥራዎች ድርጅት ስለሆነ መቅረብ ያለበት ቀርቦለታን ብለን እናስባለን፡፡ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀሪ 20 በመቶውን ለማሳካት እየተሠራ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ማዳበሪያ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች አሉ ይባላል?

አቶ ተስፋዬ፡- በዚህ ዙሪያ ክፍተት እንዳለ ለይተናል፡፡ አንደኛውና ትልቁ ከዕቅድ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አርሶ አደሩ ማዳበሪያ እንዲወስድ ለማድረግ ሰፊ ሥራ ጠይቋል፡፡ የተመቻቸ ሁኔታም ስላልነበረ በየጊዜው መሠራት ነበረበት፡፡ ፍላጎት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ማዳበሪያ ቀድመው የሚወስዱ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው? የሚለው ዕቅዱም ሲሠራ ክፍተት ነበረበት፡፡ ቀድመው በቆሎ፣ ስንዴና ጤፍ   የሚዘሩ ድንች የሚጥሉ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው? ተብሎ ዕቅዱ ላይ ሲቀመጥ ክፍተት ነበር፡፡ እጃችን ላይ ያለው ማዳበሪያ አርሶ አደሩ ከወሰደው ጋር ልዩነት አለው፡፡ አሁን የማይጠቀሙ፣ ወደፊት የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች መጋዘናቸው ውስጥ ማዳበሪያ አለ ማለት ነው፡፡ ወቅቱን የጠበቀ ሥርጭት ከማድረግ አኳያ ክፍተት ስለነበር፣ የተፈጠረውን ስህተት ማረም አለብን ብለን ይዘናል፡፡ ሥርጭቱም ሲታይ አንዳንድ አካባቢ ማዳበሪያ መወሰዱ እንጂ የቱ መቅደም አለበት? የሚለው አልታየም፡፡ ይህም ክፍተት ፈጥሯል፡፡ ችግሩን ባወቅንበት ጊዜ ግን ለመፍታት ጥረት ተደርጓል፡፡ እስካሁን ወደ 5.1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ አርሶ አደሩ ገዝቶ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡ ከሜትሮሎጂ ኤጀንሲ በቅርቡ ባገኘነው መሠረት መረጃ ዝናብ ቀድሞ መምጣቱ ጥሩ ቢሆንም፣ ወደ መጨረሻ አካባቢ ቀድሞ ሊወጣ ይችላል የሚል ትንበያ አለ፡፡ በመሆኑም አርሶ አደሩ ቀድሞ እንዲዘራ እየመከርን ስለሆነ በዚህ ላይ ተመሥርቶ የማዳበሪያ ፍላጎቱ ቀድሞ መጥቷል፡፡

ጥያቄ፡- የዘር አቅርቦትስ ምን ይመስላል?

አቶ ተስፋዬ፡- በሙያተኞች ግምገማ እስከ 45 በመቶ የምርት ጭማሪ የምናገኘው በምርጥ ዘር ነው የሚል እምነት አለ፡፡ ከዚህ አኳያ ከክልሎች ፍላጎት አንፃር ወደ 1.8 ሚሊዮን ኩንታል የተለያዩ ምርጥ ዘሮች እናቀርባለን ብለን ነው ያቀድነው፡፡ እስካሁን በእጃችን የገባው 1.4 ሚሊዮን ኩንታል ሲሆን፣ ከዕቅዱ አንፃር 78 በመቶ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ የብዕርና የአገዳ ሰብሎች ላይ ችግር የለም፡፡ የጥራጥሬና የቅባት እህል ምርጥ ዘሮችን ግን በበቂ አቅርበናል የሚል እምነት የለንም፡፡ ቴክኖሎጂውን ከማግኘት ጀምሮ አርሶ አደሩ እንዲጠቀም እስከማድረግ ክፍተት አለ፡፡

ጥያቄ፡- እስካሁን ያለው የመኸር ሥራ ምን ይመስላል?

አቶ ተስፋዬ፡- 345 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እናገኛለን ብለን አቅደናል፡፡ በሰብል የሚሸፈነው መሬት 12.8 ሚሊዮን ሔክታር ሲሆን፣ እስካሁን 10.7 ሚሊዮን ሔክታር ላይ የእርሻ ሥራ ተካሂዷል፡፡ በዘር የተሸፈነው 3.5 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ነው፡፡ ከዕቅዳችን አኳያ 33 በመቶ ላይ ነን፡፡ ይህ ከወቅቱ አኳያ ማለትም ሰኔ ላይ ስለሆንን በተለይ ቀድመው ከሚዘሩ ሰብሎች አኳያ ሲታይ ጥሩ ደረጃ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ የተዘራውም የብዕርና የአገዳ ሰብል ነው፡፡ በቆሎ በዋናነት ሲሆን፣ ቀጥሎ ገብስ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ከተዘራው ውስጥ ከማዳበሪያና ከምርጥ ዘር ውጭ አዲስ የሚባሉ ቴክኖሎጂዎች ተጠቅማችኋል?

አቶ ተስፋዬ፡- ከተዘራው መሬት 2.6 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነው ወይም 75 በመቶው በመስመር የተዘራ ነው፡፡ ይህ አዘራር ተባይ ለመከላከል፣ ለአሠራርና ግብዓት ለመጠቀም ምቹ ነው፡፡ ምርትና ምርታማነትንም ያሳድጋል፡፡ ሆኖም 75 በመቶ በቂ ነው አይባልም፡፡ እዚህ ላይ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡

ጥያቄ፡- ባሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ምን ችግር ገጥሟችኋል?

አቶ ተስፋዬ፡- ጎልቶ የሚወጣውና ፈታኙ ችግር የአሜሪካ ተምች (Fall armywarm) ነው፡፡ ተምቹ ከመከሰቱ በፊትም ቀድመን አውቀናል፡፡ ለኢትዮጵያም አዲስ ነው፡፡  በመሆኑም ከተለያዩ ሙያዎች የተውጣጣ ግብረ ኃይል አቋቁመን መረጃ ሰብስበን ነበር፡፡ ሥልጠና ለመስጠት ስንዘጋጅ ተምቹ ቀድሞ በአገሪቱ ቤንች ማጅ ዞን ተከስቷል፡፡ የአሜሪካ ተምች መሆኑ ሲረጋገጥ በስፋት ግንዛቤ ማስጨበጡ ተጀመረ፡፡ ግንዛቤውን በተለይ ችግሩ ላለባቸው ዋና ዋና አካባቢዎች ፈጥረናል፡፡ ለመከላከል ኬሚካልና በባህላዊ በእጅ መልቀም የሚቻል ቢሆንም፣ የምንመርጠው ባህላዊውን ነው፡፡ ከአቅም በላይ ካልሆነ ኬሚካል አንመክርም፡፡ ለመከላከሉ በጀት አስመድበን ኬሚካልና መርጫ መሣሪያ የመግዛት ሥራ ተከናውኗል፡፡ ክልሎችም ካለው ነባራዊ ሁኔታ እያዩ መከላከሉ ላይ እየሠሩ ነው፡፡ የአሜሪካ ተምቹ በተከሰተባቸው ቤንሻንጉል፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ አማራ፣ ትግራይና ጋምቤላ የተዘራው በቆሎ አንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 135 ሺሕ ሔክታር ላይ ችግሩ ተከስቷል፡፡ የመከላከል ሥራው ከተሠራበት 83 ሺሕ ሔክታር መሬት 43 በመቶው በባህላዊ መንገድ በመልቀም የተከናወነ ነው፡፡ ይህ ግን ኬሚካል ላይ ማተኮርን ያሳያል፡፡ ትልቅ ክፍተትም ነው፡፡ ከኬሚካል አኳያ ያለውን ሁኔታ ማስወገድ አለብን፡፡ ኬሚካል የመጨረሻ አማራጭ መሆን አለበት ብለናል፡፡ ተምቹ ኬሚካሉን ከተለማመደ በኋላ መወጣት አንችልም፡፡ አጠቃቀም ላይም ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ባህላዊ መንገድ ላይ ስናተኩር በሕዝቡ ላይ ያለው ንቅናቄ ክፍተት አለበት፡፡ ባህላዊ ለቀማ በአርሶ አደሩ ወይ በቤተሰቡ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ሥራው ዘመቻን የሚፈልግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ብዙ መሥራት አለብን፡፡ ምክንያቱም ተምቹ ከደቡብ ተነስቶ ትግራይ ደርሷል፡፡ ስለዚህ ተምቹን ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም ማጥፋት አለብን፡፡ ደቡብ ቢታይ ተምቹ ከታየ አራት ወራት ሆነውታል፡፡ መጀመርያ ተምቹን በነቂስ መልቀም ቢቻል ከየአካባቢያችን ያለውን ማጥፋት ይቻል ነበር፡፡ ይህንን ተባይ መከላከልና ማጥፋት የሚቻለውም ጊዜ ሳይሰጡ ነው፡፡ ዘመቻውን በአጭር ጊዜ ማከናወን ከቻልን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጥፋት እንችላለን፡፡

 

 

 

 

Standard (Image)

አዲሱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ሙዚየም

$
0
0

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ እንዲህ ተጀመረ የሚለን የብሔራዊ ኦሊምፒክ መዝገብ ነው፡፡ ስምንተኛው የኦሊምፒክ ጌምስ እ.ኤ.አ. ከግንቦት 4 ቀን እስከ ሐምሌ 27 ቀን 1924 በፓሪስ ሲካሄድ፣ እንዳጋጣሚ ሆኖ ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኰንን አውሮፓን ይጎበኙ ስለነበር የወቅቱ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ፕሬዚዳንት ፒየር ዴ. ኩበርቲን አልጋ ወራሹ ከተከታዮቻቸው ጋር በክብር እንግድነት በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ጋብዟቸዋል፡፡ ራስ ተፈሪ በበዓሉ አከባበርና በውድድሮቹ ድምቀት ተማርከው ስለነበር ኢትዮጵያ የአይኦሲ አባል በምትችልበት ሁኔታ ላይ ከኩበርቲን ጋር ተመካከሩ፡፡ የፕሬዚዳንቱ ፍላጎት የኦሊምፒክ ፍልስፍናን በመላው ዓለም ማስፋፋት ስለሆነ የአልጋ ወራሹን ሐሳብ በደስታ ተቀበሉ፡፡ ልዑል አልጋ ወራሽ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ ኢትዮጵያ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል በመሆን በ1928 በዘጠነኛው አምስተርዳም ኦሊምፒክ እንድትካፈል ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ኩበርቲንን የተኩ ቤልጅጋያው ሄኔሪ በባይላት ቱር ኢትዮጵያ የአባልነት መስፈርትን አታሟላም በማለት ጥያቄዎቿን ውድቅ አደረጉ፡፡ በአይኦሲ አባልነት የወቅቱ ዋነኛ መስፈርቶች ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴን ምርጫ ማካሄድና ቢያንስ፣ አምስት አገር አቀፍ ፌዴሬሽኖችን በመመሥረት የኢንተርናሽናል ፌዴሬሽን አባል መሆን ነበር፡፡ በኦሊምፒክ ለመካፈል ያቀረበችው ጥያቄዋ ውድቅ በሆነ በ28 ዓመቱ እ.ኤ.አ. በ1956 በሜልቦርን በተዘጋጀው 16ኛው ኦሊምፒያድ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስና በብስክሌት ተሳተፈች፡፡ ለመጀመሪያው ተሳትፎዋ ውጤታማ መሆን ባትችልም ከአራት ዓመት ቆይታ በኋላ 17ኛው ኦሊምፒያድ በሮም ሲካሄድ በማራቶን በጥቁር አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ በአበበ ቢቂላ ለማግኘት ችላለች፡፡ ከሜልቦርን እስከ ሪዮ በስድሳ ዓመታት ውስጥ ከተከናወኑት ኦሊምፒኮች አውራዎች አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ ኢትዮጵያ በአልጋወራሽዋ፣ በመሳፍንትና መኳንንቷ አማካይነት ከኦሊምፒክ ጋር ከተዋወቀችበት ከ93 ዓመታት፣ የኦሊምፒኩ አካል ከሆነችበት ከ60 ዓመታት ወዲህ ያላትን ቅርስና ውርስ ለአሁንና ለመጪው ትውልድ ለማስተዋወቅ ይረዳ ዘንድ ከስድስት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ሙዚየም አቋቁሟል፡፡ በሙዚየሙ እቅስቃሴ ዙሪያ የኦሊምፒክ ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያውን አቶ ዳንኤል አበበን ሔኖክ ያሬድአነጋግሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- የኦሊምፒክ ሙዚየም ምንድነው? ብሔራዊ የኦሊምፒክ ሙዚየምስ ለምን ተቋቋመ?

አቶ ዳንኤል፡- የኦሊምፒክ ሙዚየም በስብስቡ የኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ለማስተዋወቅ የሚረዳ ሁነኛ መሣሪያ ነው፡፡ የስፖርትና የኦሊምፒክ እሴቶችና ባህል በኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲሠርፅ ያደርጋል፡፡ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአገልግሎት ላይ የዋሉ ጨዋታዎችን ጨምሮ ሳንቲሞችና የመታሰቢያ ቴምበሮች አማካይነት የኦሊምፒዝምን መልዕክት፣ ታሪክና ቅርስ ለማስተላለፍ ሙዚየም ጠቀሜታ አለው፡፡ ይህን መሠረተ ሐሳብ ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ሙዚየም የተቋቋመው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ባጭሩ የተቋቋመበት ዓላማውም የኦሊምፒክ ፍልስፍናና የኦሊምፒክ እንቅስቃሴን በአገራችን ውስጥ ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት ነው፡፡ በኦሊምፒዝም ፍልስፍና ውስጥ ያሉትን ትምህርቶች ለማስፋፋት ሙዚየሙ አንዱ ትልቅ የኮሙዩኒኬሽን መሣሪያ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኦሊምፒክ ሙዚየሙ ስብስብ ምን ይመስላል?

አቶ ዳንኤል፡- ቅርሶቹ በአብዛኛው የተሰበሰቡት ቀደም ብሎ አገራችን የተሳተፈችባቸው ኦሊምፒከ ላይ ባለድል ያደረጓትንና የተሳተፉትን የስፖርተኞች ፎቶዎች ከስፖርተኞቹ ቤተሰቦችና ስፖርት ወዳዶች በመጠየቅና ቀደም ብለው ከታተሙ መጽሔቶችና ጋዜጦች ሲሆን፣ ሌሎች ቁሳቁሶች በየአገራቱ ከሚገኙ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች በስጦታ የተበረከቱ ናቸው፡፡ ከነዚህም መካከል አንድ የጃፓን ኩባንያ የአበበ ቢቂላ ቀኝ እግር ቅርፅ ይገኝበታል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በፕሬዚዳንትነት የመሩ የሁሉም ፎቶዎች በሙዚየሙ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከቀድሞ አትሌቶችና ከሌሎች ባለሙያዎች ከኦሊምፒክ ጋር የተያያዙ በስጦታ ያገኛችኋቸው አሉ?

አቶ ዳንኤል፡- የአትሌቶችና የዘርፉ ባለሙያዎች ሜዳሊያዎችንና ሌሎች የክብር ስጦታዎች ለመስጠት ያላቸውን ግንዛቤ አነስተኛ ነው፡፡ በእርግጥ እኛም ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሄድንበት ርቀት አመርቂም አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የኦሊምፒክ ሙዚየሙ አደረጃጀት ምንን መሠረት ያደረገ ነው?

አቶ ዳንኤል፡- የሙዚየሙ አደረጃጀትን በተመለከተ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር  ማንዋሎችን አግኝተናል፡፡ ሲሆን የቅርሶቹ አቀማመጥ ቅደም ተከተል ኦሊምፒክ መሳተፍ ከጀመርንበት እ.ኤ.አ 1956 የሜልቦርን ኦሊምፒክ ጀምሮ ባለድል የሆኑትን አትሌቶች በቅደም ተከተል ከነሙሉ መግለጫው አስቀምጠናል፡፡ ጎብኝዎች በሚመጡበት ወቅት እያንዳንዳቸው መግለጫ የተለጠፈባቸው በመሆኑ ለገለጻው የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ሌሎች የስጦታ ዕቃዎች አቀማመጥ የአቀማመጡ ቅደም ተከተል ድብልቅ አንድ የስፖርት ሙዚየም ሲገነባ አደረጃጀቱ በተቻለ መጠን ራሱን ችሎ በባለሙያዎች ብቻ እንዲመራ ብሎም በቂ በጀት ሊበጀትለት ያስፈልጋል፡፡ የስፖርተኞች የሕይወት ታሪክና በተለይም በየስፖርቱ የተገኙ ውጤቶችንና አንጸባራቂ ድሎች ለመጪው ጊዜ በታሪክነት እንዲዘከር ለማድረግ በጽሑፍ፣ በፎቶግራፍ፣ ተንቀሳቃሽ ፊልምና በድምፅ ተቀርፀው ቢቀመጡ፣ የስፖርተኞችን አልባሳት፣ መጫሚያ፣ ልዩ ልዩ ሽልማቶች የያዙና ሰፋ ባለ ክፍልና ብርሃን ባለበት ክፍል ቢሆንና ለዕቃዎች ማስቀመጫና ጥበቃ እንዲያመች የመስታወት ሼልፍ ቢኖሩት ይመረጣል፡፡ ይህንንም ለማድረግ እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡-  ሙዚየሙ ለጎብኝዎች ክፍት ነው ወይ?

አቶ ዳንኤል፡ ሙዚየሙ ወሎ ሰፈር አይቤክስ ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የሚገኝና ሳምንቱን በሙሉ በሥራ ሰዓት ክፍት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከውጭ አገር ተቋማት ጋር  ግንኙነት አላችሁ?

አቶ ዳንኤል፡- ከሙዚየሙ አኳያ ያለን ግንኙነት እጅግ ውስን ነው፡፡ የጠበቀ የሥራ ግንኙነት ያለን ሙዚየማችንን ከማበልጸግ አኳያ ሎዛን ከሚገኘው ከዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሙዚየም ጋር ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድን ነው?

አቶ ዳንኤል፡- የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ሙዚየምን የተሻለ ለማድረግ በጣም በርካታ ሥራዎች ወደፊት ይጠብቁናል፡፡ በሌሎች መሰል ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ሙዚየም የኦሊምፒዝም ማስተማሪያ፣ ታዳጊና ወጣት አትሌቶች የሚነቃቁበት መሠረታዊ መዋቅር ነው፡፡ ሰለሆነም እንደ ኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሙዚየሙን ዳግም በማደራጀትና እንደ ሙዚየም መያዝ ያለበትን ቅርሶች እንዲይዝ ዕቅድ ተይዟል፡፡ በያዝነው የአራት ዓመት ስትራቴጀክ ዘመን ሙዚየማችንን አንድ ዓይነተኛ ዕርምጃ (ለውጥ) እንዲያመጣ እንሠራለን፡፡

 

 

       

 

 

Standard (Image)

‹‹በጋምቤላ ማማረጥ ካልሆነ ሥራ ተፈልጎ የሚታጣባት አይደለችም››

$
0
0

በ​ ታምራት ጌታቸው

አቶ ኦካኔ ኡጋዳ ኡፓዲ፣ የጋምቤላ ከተማ ዋና ከንቲባ

በጋምቤላ ከ345 ሺሕ በላይ ስደተኞች በተለያዩ የስደተኛ ካምፖች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ከተማዋ በመሠረተ ልማት ለውጥ እያስመዘገበች ቢሆንም፣ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ አለመግባባቶች ክልሏን በተለያዩ ጊዜያት ለፀጥታ ችግር ሲያጋልጧት ተስተውለዋል፡፡ አቶ ኦካኔ ኡጋዳ ኡፓዲ የጋምቤላ ከተማ ዋና ከንቲባ ናቸው፡፡ ጋምቤላ ስላለችበት ሁኔታና በክልሉ የተጠለሉ ስደተኞች ስላሳደሩት ተፅዕኖ ታምራት ጌታቸውከንቲባውን አቶ ኡካኔ አነጋግሯቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ጋምቤላ በምን ያህል ወረዳዎችና ቀበሌዎች የተከፋፈለች ናት? የሕዝቦች አሠፋፈርስ ምን ይመስላል?

አቶ ኦካኔ፡- ጋምቤላ ትንሿ ኢትዮጵያ ነች ማለት ይቻላል፡፡ ከሁሉም ክልል የመጡ ነዋሪዎች ከተወላጁ ጋር የሚኖርባት ነች፡፡ ይህም ለየት ያደርጋታል፡፡ አኗኗሯርን በተመለከተ ይህን ያህል የተደራጀና ዘመናዊ አሠፋፈር የተከተለ አይደለም፡፡ ጋምቤላ ከተማ በአምስት ቀበሌዎች የተከፋፈለች ስትሆን በቅርቡ ግን ወደ ሦስት ወረዳዎች ለማሳደግ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከመሠረተ ልማት አኳያ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ኦካኔ፡- ጋምቤላ ከዚህ በፊት ምንም ያልነበራት ከተማ ነበረች፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች የአስፋልት መንገድ፣ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች አለመኖር ብዙም እንቅስቃሴ የማይታይባት ከተማ አድርጓት ቆይቷል፡፡ ከሆቴል አቅም እንኳን የዛሬው ባሮ ሆቴል ብቻ ነበር ያለው፡፡ እንግዲህ ከተማዋ ትልቅ ለውጥ ያመጣችው 11ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በክልሉ እንዲከበር ከተወሰነ በኋላ ነው፡፡ በተሰጠን በስምንት ወር ጊዜ ውስጥ ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን ጠንካራ አመራር በመፍጠር ስታዲየም፣ የመሰባሰቢያ አዳራሽ፣ የመንግሥት ቢሮዎች፣ የአስፋልት መንገዶች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ በመንግሥትና በግል የተገነቡ ሲሆን ዛሬ እንደ ሌሎች ከተሞች መሆን ጀምራለች፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ የነበረው ከተማዋን የማልማት እንቅስቃሴ ዛሬ ቀዝቅዟል ይባላል፡፡ ለምንድነው?

አቶ ኦካኔ፡- 11ኛ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በክልሉ መከበሩ ካስተማረን አንዱ በአጭር ጊዜ የተለያዩ ማኅበረሰቦችን በማስተባበር አገር መለወጥ እንደሚቻል ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ግን ቁርጠኛ አመራር፣ ሠርቶ የሚያሠራ ያስፈልጋል፡፡ ዝም ብሎ ሊሠራ አይችልም፡፡ በመሀል የተፈጠረው ችግር፣ የአመራሮች እየተዳከሙ መምጣትና በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው ችግር ጋምቤላም ውስጥ በመታየቱና አመራሮች በዚህ ችግር ውስጥ በመዘፈቃችን ሊቀዘቅዝ ችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- በከተማዋ ከፍተኛ የወጣት ሥራ አጥ መኖር እንደ ችግር ይነሳል፡፡ እዚህ ላይ ምን እየሠራችሁ ነው መንግሥት በመደበው ፈንድ እየተጠቀማችሁ ነው?

አቶ ኦካኔ፡- የወጣት አጀንዳ የሞት ሽረት አጀንዳ ነው፡፡ በቅርቡም በተደረገው የተሃድሶ ለውጥ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየሠራንበት ነው፡፡ በከተማዋ የሚገኙትን ከ2,111 በላይ ሥራ አጥ ወጣቶች ቤት ለቤት በመሄድ መዝግበን ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ እነዚህን ወጣቶች ወደ ሥራ ካስገባናቸው ትርፍ እናገኝበታለን፡፡ ሥራ ካልሰጠን ደግሞ ኪሳራ ነው፡፡ በከተማዋ ተመዝግበው የነበሩ ሥራ አጦችን በማኅበር በማደራጀት እስከ አራት ሚሊዮን ብር ብድር በመስጠት በኮብልስቶንና በተለያዩ መስኮች ሥራ ላይ እንዲሰማሩ አድርገናል፡፡ ከአራት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ወጣት አባወራዎች በከተሞች የምግብ ዋስትና ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ክልሉም በመደበው በጀት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከተማዋ ሥራ ፈልገህ የምታጣባት አይደለችም፡፡ ምናልባት አሁን የሚታየው የሥራ ማማረጥ ካልሆነ በስተቀር ሥራ አጥ አለ ለማለት ያስቸግረኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከተማዋ የጎርፍ ተጠቂ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ አምና የተከሰተው ጎርፍ የሰው ሕይወት እስከመንጠቅ ደርሷል፡፡ ዘንድሮስ ይህን ለመቀነስ ምን ሠርታችኋል?

አቶ ኦካኔ፡- ከተማዋን የሚያጠቃት ጎርፍ በሁለት ይከፈላል፡፡ አንደኛው ቀድሞ የጎርፍ መውረጃ የነበሩ ቦታዎች ላይ ሰዎች ግንባታ ማካሄዳቸው፣ ሁለተኛው ደግሞ ቀድሞ የተሠሩ የፍሳሽ ቱቦዎች በመዘጋታቸውና ውኃው መንገዱን ለቆ በመውጣቱ በከተማዋ ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ ከዚህም ችግር በመነሳት በተለይ በባሮ ወንዝ ዳርና ዳር ሕገወጥ ግንባታ ሠርተው ለአደጋ ተጋላጭ የነበሩ ከ400 በላይ እማወራዎችና አባወራዎችን በማንሳት ወደ ሌላ ሥፍራ አስፍረናል፡፡ የከተማው አስተዳደርም ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተዘጉ ቱቦዎችን ከመክፈት ጀምሮ አዳዲስ የጎርፍ መውረጃ ቱቦዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ ሌላው ማኅበረሰቡ ወንዝ ዳር ግንባታዎችን እንዳያካሂድ ቁጥጥር በማድረጋችንና ቆሻሻዎችን በአግባቡ እንዲጥል ትምህርት እየተሰጠ በመሆኑ በዘንድሮ ችግሩ ይቃለላል ብለን እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- የባሮ ወንዝ ብክለቱ እየጨመረ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ መንስዔው ምንድነው?

አቶ ኦካኔ፡- ባሮ ወራጅ ወንዝ ስለሆነ በባህሪው ሊበከል አይችልም፡፡ ተበከሉ የሚባሉት መጋቢዎቹ ናቸው፡፡ በከተማዋ ካሉ አምስቱም ቀበሌዎች ባሮን የሚቀላቀሉ ወንዞች አሉ፡፡ በተለይ ከአራት ኪሎ ሜትር አካባቢ የሚመጣው ጀጀባ ወንዝ የሚባል አለ፡፡ ይህ ወንዝ ሰዎች በብዛት የሚኖሩበት በመሆኑ፣ የሞቱ እንስሳት ከመኪና ማጠቢያዎች የሚወጣው ዘይት፣ ቆሻሻና ሌሎች በርካታ በካይ ነገሮችን ይዞ ባሮን ይቀላቀላል፡፡ ባሮ ለሰውና ለከብቶች መጠጥ ይውል የነበረ ቢሆንም አሁን ከባድ ሆኗል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ከአካባቢ ጥበቃና ከከተማ ግብርና ቢሮዎች ጋር በመተባበር ባሮን በሚመግቡት ወንዞች ላይ ጉዳት የሚያደርሱትን ችግሮች ማስወገድ በመሆኑ ከነዋሪዎቹ ጋር እየሠራንበት ይገኛል፡፡ ከከተማ ግብርና ቢሮ ጋር በመሆን ደግሞ የከተማ ግብርናን ለወጣት የሥራ ዕድል ፈጠራ በማዋል በወንዞቹ ዳርቻ የመስኖ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ሠፋሪዎች በተነሱበት ቦታ ደግሞ ችግኞችን በመትከል ችግሩን ለመቀነስ እየተሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በከተማዋ እየጨመረ በመጣው የቤት ኪራይ ክፍያ ነዋሪዎች እየተማረሩ ይገኛሉ፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ኦካኔ፡- በእኛ በኩል ለጊዜው ቤት የመሥራት ፕሮግራም የለም፡፡ ነዋሪዎች እየኖሩበት ያለው መኖሪያ ቤት ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን በማኅበር ተደራጅተው ቢመጡ መሬት እናቀርባለን፡፡ ሌላው ከተማዋ እንደ ዕድል ሆኖ ለመኖሪያ ምቹ የሚያደርጋት በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ከተማዋን ለሁለት የሚከፍለው ባሮ ወንዝ ነው፡፡ ይህ በራሱ ውበት ነው፡፡ ባደጉት አገሮች እንደምናየው የጀልባ ትራንስፖርትና ሌሎች መዝናኛዎችን የአካባቢውን ሥነ ምኅዳር በመጠበቅ መሥራት ይቻላል፡፡ ያለንን ምቹነት በማስተዋወቅ የሪል ስቴት አልሚዎች እንዲገቡ በማድረግ ችግሩ እንዲቀረፍ እኛም የጀመርነው ሥራ አለ፡፡ እዚህ ላይ የግል ባለሀብቶች እንዲሳተፉበት እያበረታታን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጋምቤላ የፀጥታ ጉዳይ ሥጋት መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ ችግሩ ምንድነው?        

አቶ ኦካኔ፡- ጋምቤላ የድሮዋ ከተማ አይደለችም፡፡ ከቀን ቀን እየጨመረ የመጣ የከተማ ነዋሪዎች ብዛት አለ፡፡ ይህም ችግሮች ይዞ ይመጣል፡፡ ችግሩ በሁለት መንገድ የነበረ ነው፡፡ ከጥልቅ ተሃድሶው በፊት የነበረው አንድ ሰው ሲጣላ ችግሩን ከብሔር ጋር በመውሰድ ብሔር ለብሔር እንዲጋጭ ማድረግ አመራሩ ጭምር የሚሳተፍበት ነበር፡፡ ከተሃድሶው በኋላ ግን አንድ  ሰው ከሌላ ጋር ቢጋጭ ተጠያቂው ሰውየው ብቻ እንዲሆን በመደረጉ ይህ አሁን ተቀርፏል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከተሞች ሲስፋፉ አብሮ የሚመጣው የመዝናኛ ቦታዎች መስፋፋት ነው፡፡ በዚህ የሚደረጉ ፀቦች፣ የመንገዶች ጉራንጉር መሆን፣ የውስጥ ለውስጥ መብራት ባለመኖሩ ጨለማን ተገን በማድረግ ዘረፋ ማካሄድ፣ ሞባይል መንጠቅና  ሌሎች ችግሮች ይታዩ ነበር፡፡ እነዚህ በተደራጀ መልኩ ሳይሆን ዕለታዊ ነበሩ፡፡ ችግሮቹ ላይ ኅብረተሰቡን በማወያየትና መፍትሔዎችም ራሱ ኅብረተሰቡ እንዲሆን በማድረግ፣ የከተማ አስተዳደር ደግሞ የውስጥ ለውስጥ መብራቶችን በማስተካከል ከአጎራባቻችን ኦሮሚያ ክልል ጋርም በመተባበር ችግሮችን መፍትሔ በማስቀመጥ ችግሩ ቀንሷል፡፡

ሪፖርተር፡- ከጎረቤት ደቡብ ሱዳን ከ345 ሺሕ በላይ ስደተኞች በክልሉ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ይህ በከተማዋ ላይ ጫና አልፈጠረም?

አቶ ኦካኔ፡- ስደተኞች በከተማዋ ስለማይኖሩ ይህ ጥያቄ በእርግጥ እኛን አይመለከትም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከተማዋ ተጠቃሚ ነኝ ነው የምትለው፡፡ በአጎራባች ወረዳዎች አኝዋ፣ ጃዊ፣ ያሉ አሉ፡፡ እነዚህ ስደተኞች በታሪክ አጋጣሚ በብሔር ደረጃ በከተማዋ የሚኖሩ፣ በዜግነት ደረጃ ደግሞ የደቡብ ሱዳን ስደተኛ በመሆን የተሰደዱ ናቸው፡፡ ባህላችንና አኗኗራችን አንድ በመሆኑ ምንም ዓይነት የባህል መበረዝ አይመጣም፡፡ ምግባችንም አንድ ነው፡፡ ለከተማዋ ትልቅ አጋጣሚም ናቸው፡፡ እነዚህ ስደተኞች በተቀመጡበት ቦታ ኑሮአቸውን ለማሻሻል አንዳንድ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ለምሳሌ ምግብ ቤት ከፍተው በብዛት ይሠራሉ፡፡ ለእነዚህ ደግሞ ሸቀጥ የሚቀርበው ከከተማ ነው፡፡ በተፈቀደላቸው ጊዜና ሰዓት ከተማዋ ውስጥ መጥተውም ተዝናንተው፣ አልባሳት ሸምተው ይመለሳሉ፡፡ ይህም ከተማ ያሉትን እየጠቀመ ነው፡፡ ፀጥታን በተመለከተ ግንኙነታችን ቤተሰባዊ ነው፡፡ እንደነገርኩህ አብዛኛው ነገሮቻችን ይመሳሰላሉ፡፡ ወደ ከተማ ምን ያህል ሰው እንደመጣ ስለሚታወቅና የሚመጣበትም ሰዓት ውስን በመሆኑ በእነሱ ምክንያት የፀጥታ ችግር አይታይም፡፡ በአጠቃላይ በእነሱ ተጠቃሚ ነን እንጂ ጫና አልተፈጠረብንም፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይነት ምን መሥራት አስባችኋል?

አቶ ኦካኔ፡- ጋምቤላ ሥራ እየተጀመረባት ያለች ከተማ ነች፡፡ በሁሉም መስክ ገና ጅማሮው ነው ያለው፡፡ በርካታ ሥራዎች ይጠበቁብናል፡፡ እንደ ቅድሚያ የሰጠነው ማስተር ፕላን በማዘጋጀት ከተማዋን ከተማ አድርጎ ለማስጀመር ነው፡፡ ከፍተኛ የመንገድ ችግር አለ፡፡ በሚቀጥሉት ጊዜያት ሰፋፊ መንገዶች ለመገንባት አቅደናል፡፡ አረንጓዴ ልማትን ማስቀጠልም ሌላው ሥራ ነው፡፡ ጋምቤላ እንደሚታየው አረንጓዴ ነች፡፡ በርካታ ወንዞች ያሉባትም ነች፡፡ ስለዚህ ከአካባቢ ብክለት ነፃ ሆና የምታድግበትንም እየሠራን ነው፡፡ 

Standard (Image)

ዘመነኛው የኪነ ጥበብ መገበያያ

$
0
0

ፊልም ኢቲ በቅርቡ የተመረቀ ድረ ገጽ ሲሆን፣ ፊልሞች፣ ዘፈኖች፣ ቀልዶች እንዲሁም ልዩ ልዩ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ይገኙበታል፡፡ የጥበባዊ ሥራዎቹ ባለቤቶች ሥራዎቻቸውን የሚሸጡበት ድረ ገጽ ከመሆኑ በተጨማሪ ተጠቃሚዎች አካውንት ከፍተው የሚፈልጉትን የሚመለከቱበትና ምልከታቸውን የሚያንሸራሽሩበት ነው፡፡ ድረ  ገጹ ከያዝነው ሳምንት ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ ስለአጠቃቀሙና ለኪነ ጥበብ ስለሚኖረው አስተዋጽኦ የታፊ አድቫንስ ኮምፒውተር ሲስተምስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ተፈራ አያሌውን ምሕረተሥላሴ መኰንንአነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ በቅርቡ ያስመረቀው ፊልም ዶት ኢት (ፊልም ኢቲ) ድረ ገጽ እንዴትና ለምን ተቀረፀ?

አቶ ተፈራ፡- ድርጅታችን ከዚህ በፊት በቫት ሲስተምና ሶፍትዌር ዴቨሎፕመንቶች ዙሪያ ሠርቷል፡፡ በቫት ሲስተም የምንሠራው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ሲሆን፣ 8678 የሚባል የስልክ ቁጥር አለ፡፡ መጀመርያ የለቀቅነው ሄሎ አድራሻን ሲሆን፣ ሄሎ አድራሻ በአጭር የፅሑፍ መልዕክት (ኤስኤምኤስ) የሚፈለገው አድራሻ በቀላሉ የሚገኝበት ነው፡፡ እስካሁን ወደ 1.5 ሚሊዮን መረጃዎች አሉን፡፡ መረጃ የምንሰበስበው ከመንግሥት አካላት ጋር ተጻጽፈን በሕጋዊ መንገድ ነው፡፡ በሄሎ አድራሻ ሥር ካሉት አንዱ በቅርቡ ያስመረቅነው ፊልም ኢቲ ነው፡፡ አሁን አገልግሎት ባይጀምሩም ከፊልም ኢቲ ጋር አብረው የሚሠሩ ኢቨንትኢቲን የመሰሉ ድረ ገጾችም አሉ፡፡ ፊልም ኢቲ የድረ ገጽ፣ የኤስኤምኤስና የሞባይል ባንኪንግ ወይም ኢኮሜርስ ሲስተምን ያካትታል፡፡ በኤስኤምኤስ አንድ ነገር መግዛት የሚቻልበት ሲስተም ፈጥረናል፡፡ በድረ ገጽ ረገድ ፊልም ኢቲ የማኅበራዊ ሚዲያ ባህሪ አለው፡፡ ሰዎች የኔነት ስሜት እንዲሰማቸው የወደዱትን ላይክ እንዲያደርጉ፣ አስተያየት እንዲሰጡ፣ መረጃ ከሌሎች ጋር እንዲጋሩ (ሼር እንዲያደርጉ) ያስችላል፡፡ ሰዎች የመውደዳቸውን መጠን የሚገልጹበት (ሬቲንግ) እና የተቃውሞ መግለጫም አለ፡፡ በፌስቡክና ሌሎች ሚዲያዎች ያሉትንና የሌሉትንም በራሳችን ፈጠራ ጨምረን ዲዛይን አድርገነዋል፡፡ ባሙያው ማን ላይክ እንዳደረገ፣ ማን እየተከተለው (ፎሎወሩ እንደሆነ) ያውቃል፡፡ ሁለተኛው የኦንላየን ግብይት ባህሪ ነው፡፡ ማንኛውም ኦንላየን መቀመጥ የሚችሉ ይዘቶች ፖስት ይደርጋሉ፡፡ ሥዕል፣ ሙዚቃ ወይም ማንኛውም በኤሌክትሮኒክ ሲስተም መቀመጥ የሚችሉ ይካተታሉ፡፡ ያስቀመጠው ሰው ማነው? አድራሻው የት ነው? የሚለው መረጃ አብሮ ይካተታል፡፡ ፊልም ከሆነ ሲሠራ የተሳተፉ ተዋናዮችና ሌሎችም ባለሙያዎች ይመዘገባሉ፡፡ ፕላትፎርሙ ነፃ ስለሆነ ማንኛውም ሰው ያለውን ማቅረብ ይችላል፡፡ ግብይቱ የሚፈጸመው በሦስት መንገድ ነው፡፡ አንደኛው ባለቤቱ በሚያገኘው የላይክ መጠን የምንከፍለው ክፍያ ነው፡፡ ሁለተኛው በተጎበኘለት መጠን የምንከፍለው ሲሆን፣ ሦስተኛው ሲሸጥ የሚያገኘው ገቢ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያነቱና የግብይቱ መድረክነቱ ተጣጥሞ እንዲሄድ የተፈጠረ ድረ ገጽ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በተለያየ መንገድ የተሞከሩ ድረ ገጾች አሉ፡፡ ፊልምኢቲ ይዟቸው ከመጣው የተለዩ ነገሮች መካከል ዶት ኢቲ መጠቀሙ ይጠቀሳል፡፡ አገራዊ ቃና ያለው ነገር ስለፈለግን ዶት ኢቲን መርጠናል፡፡ ፊልም ኢቲ፣ ሚዩዚክ ኢቲ፣ ኢቨንት ኢቲና ላይብረሪ ኢቲ በሚልም ሥራውን እናከናውናለን፡፡ ፊልም ኢቲ ማንም ሰው ሊጫወትበት የሚችል ሜዳ ወይም ፕላትፎርም ነው፡፡ በተሰጠው ወሰን ውስጥ እየተሽከረከረ ለተጠቃሚዎች አማራጭ ያቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኪነ ጥበብ ሥራዎች ሽያጭና ባለሙያዎች ከሕዝቡ አስተያየት የሚያገኙበት መንገድ ከማመቻቸት አንፃር ፊልም ኢቲ አሁን ያለውን ክፍተት ይሞላል?

አቶ ተፈራ፡- በበለፀጉ አገሮች ሁሉም ነገር የሚገለጸው በቁጥር ነው፡፡ የሰው ማንነት፣ ሽያጭና ሁሉም ነገር በቁጥር ይገለጻል፡፡ እኛ አገር በቁጥር መግለጽ ገና እየተጀመረ ነው፡፡ አንድ ነጋዴ የሚገዛውና የሚሸጠው በቲን ነምበር (ቁጥር) ቢሆንም፣ ምርቶችና አገልግሎቶች በቁጥር አይሸጡም፡፡ በቁጥር ማሰብ እስከምንችል ድረስ ሲስተሙን ማምጣት አንችልም፡፡ ሲስተሙ እንዲመጣ ትንንሽ ድርጅቶች የሚያድጉበት ሜዳ መዘርጋት አለበት፡፡ አሁን ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ተቋቁመው ገበያ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ጠንካራ ናቸው፡፡ ካሉት ድርጅቶች ጋር ለመወዳደር አዳዲስ ሐሳብ ማምጣት አለብን፡፡ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከተፈለገ መንግሥትና ሁሉም አካል በቁጥር ማሰብ አለበት፡፡ ፊልም ኢቲ በዚህ ረገድ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ አንድን ነገር ፖስት የሚያድረገው አካል ተጠያቂነት አለው፡፡ ፖስት ማድረግ፣ መሸጥ፣ የሚገዛውን ሰው ማወቅ፣ ፖስት የተደረገውን በማውረድ መቆጣጠር ስለሚችል ግልጽነት አለው፡፡ በኦንላየን ግብይት ሲስተም አንድ ሰው ኤስኤምኤስ ሲልክ እኛ ኪውን ጄነሬት አድርገን ግዥ ይፈጸማል፡፡ ቴሌ የራሱ አሠራር አለው፡፡ እኛም የቴሌ የቢዝነስ አጋር ነን፡፡ ከባንኮች ጋርም በቀላሉ የኦላየን ሽያጭ ስለሚካሄድበት መንገድ እያወራን ነው፡፡ አንድ ሰው የገዛቸው ነገሮች ባጠቃላይ ሚዲያው ላይ ስለሚመጡለት በፈለገበት ሰዓት ያጫውታቸዋል፡፡ የሚፈልገውን ሲያወርድ በሲግኔቸር ማለትም የገዥውና የሻጩ መለያ ተካቶ ስለሆነ ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ሻጩ አንድ ሰው ያልገዛውን ነገር ሲጠቀም ካየ መክሰስም ይችላል፡፡ ሲስተሙ እኛ የፈጠርነው ሳይሆን በዓለም ያለ ነገር ነው፡፡ ሲግኔቸር መጠቀም የማይችሉ ነገሮችን አፕሎድ ለማድረግ ሲስተሙ ስለሚከለክል መረጃው ደኅንነቱ በተጠበቀ ፎርማት መቅረብ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ኢኮሜርስ ባልተስፋፋበት የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ድረ ገጹን ስታዘጋጁ የኪነ ጥበብ ባለሙያችን እንዲሁም ሕዝቡን ምን ያህል ታሳቢ አድርጋችኋል? የሐሳቡ አለመስፋፋትስ በድረ ገጹ ትግበራ ክፍተት አይፈጥርም?

አቶ ተፈራ፡- ክፍተት አለ፡፡ ለምሳሌ የባንኮች ሲስተም ኦንላየን ግብይት ማድረግ ቢያስችልም ከቴክኖሎጂ እጥረት፣ ካለመሞከር ወይም ከፍራቻ የተነሳ ሲስተሙ ክፍት አይደለም፡፡ ባንኮች ኤፒአይ በተባለ ሲስተም ከተለያዩ ድረ ገጾች፣ የገበያ ማዕከሎች ጋር መገናኘት ይችላሉ፡፡ አሁን ባለው የባንኮች ኔትወርክ ሲስተም መሠራትም ይችላል፡፡ አማራጩ ስላለ እንሥራ ብለን የባንኮችን በር እያንኳኳን ነው፡፡ ጭላንጭል ብናይም ያገኘነው ምላሽ አጥጋቢ አይደለም፡፡ ባንኮች የሚሠሩት ከውስን ድርጅቶች ጋር ከሆነ ቢዝነሱ አያድግም፡፡ ሕዝቡ የሚጠቀመው ሁሉም ድርጅት መሳተፍ ሲችል ነው፡፡ ውድድሩ ሲሰፋ የተሻለ ነገር ያለው ድርጅት በገበያው ይቆያል፡፡ ሕዝቡ በድረ ገጹ እንዲጠቀም የተለያዩ ማበረታቻዎች በማዘጋጀት ለማስተዋወቅ እየሞከርን ነው፡፡ አንዱ ማበረታቻ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. 100 ሺሕ ላይክ ለሚያገኝ ሰው 10 ሺሕ ብር እንሰጣለን፡፡ ጉግልና ዩቲዩብ ከሚከፍለው ጨምረን ክፍያ የምናካሂደው ድርጅቱ ያን ያህል አትራፊ ይሆናል ብለን ሳይሆን ድረ ገጹ መታወቅ ስላለበት ነው፡፡ ሲስተሙ ጋባዥ እንዲሆን አድርገናል፡፡ አንዱ ላክይ ሲያገኝ ሌሎች ላይክ ያገኙትን ይጋብዛል፡፡ እነ ፌስቡክና ዩቲዩብ እንደታወቁት ፊልም ኢቲም ቀስ በቀስ ያድጋል፡፡ ሕዝቡ ቴክኖሎጂ እየገባው መምጣቱ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ እኛም ለማትረፍ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰባዊ ዋጋውንም እናያለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ያላችሁ ስምምምነት ምንድነው?

አቶ ተፈራ፡- ከባንኮች ጋር መሥራት ካልቻልን ያለን አማራጭ ከቴሌ ጋር መሥራት ነው፡፡ ባንኮች ወደ ቴክኖሎጂው እየሄዱ ያሉት በቀስታ ነው፡፡ እነሱን አሳምኖ አብሯቸው መሥራት ከባድ ነው፡፡ እነሱ ፈልገው ሳይሆን ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር አብሮ መሥራት ግዴታቸው ነው፡፡ አገሪቱ እንድታድግ ከተፈለገ በቴክኖሎጂው መሠራት ያለበት ነገር ያለ ገደብ መሠራት አለበት፡፡ በኦንላየን ግብይት ረገድ ከባንኮች ጋር መሥራት ለሚፈልግ ተቋም መፈቀድ አለበት፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የራሱ ውስንነት አለው፡፡ ያላግባብ በርካታ ብር ይወስዳል፡፡ አንድ ሥራ በሦስት ብር ተሽጦ ባለቤቱ 40 በመቶ፣ ኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ይወስዳል፡፡ እኛ የምንወስደው 20 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ የኛ ትልቅ ገቢ ከማስታወቂያ የምናገኘው ነው፡፡ ሥራው አትራፊ ነው፡፡ አቅሙ ያላቸው ድርጅቶች ወደ ቢዝነሱ እንዲገቡ ግን ብዙ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ጥበባዊ ሥራዎቹ ለገበያ የሚቀርቡበት ዋጋ ተተምኗል?

አቶ ተፈራ፡- ማንኛውም ሰው ሲስተሙን መጠቀም ይችላል፡፡ የሚሸጠው ሰው ከሦስት ብር ጀምሮ የፈለገውን ዋጋ ያስቀምጣል፡፡ በእርግጥ የኢትዮ ቴሌኮምን ኔትወርክ ስለምንጠቀም ገደብ አለው፡፡ ሻጩ በነፃ ማድረግ፣ ፖስት ያደረገውን ማውረድም ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የኮፒራይት መብታቸው እየተጣሰ ከሥራዎቻቸው ተገቢውን ጥቅም ባለማግኘታቸው ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ በድረ ገጹ ከሥራዎቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሽያጩን የሚቆጣጠሩበት መንገድ አለ?

አቶ ተፈራ፡- አንድ ሙዚቃ ቁጥር ተሰጥቶት ሽያጩ ሲካሄድ የገዛው አካልም በቁጥር ይታወቃል፡፡ ይህንን የሚቆጣረው የመንግሥት አካል ነው፡፡ በቁጥር ማሰብ እንዲኖር ከዚህ በፊት ድርጅታችን ለንግድ ሚኒስቴር ይህን ሐሳብ አቅርቦ ፈቃድ አግኝተን ነበር፡፡ በየጊዜው አዋጅ ይታወጃል፤ ማኅበራትም ይቋቋማሉ፡፡ የችግሩ መሠረት ግን አልተገኘም፡፡ መንግሥት ተገቢውን ታክስ እንዲሰበስብና ትክክለኛውን የገበያ ሥርዓት እንዲቆጣጠር ከተፈለገ ወደ ቁጥር አስተሳሰብ መምጣት አለብን፡፡ ገበያው የሚተዳደረው በአይደንቲፊኬሽን ነምበር (የመለያ ቁጥር) ከሆነ ትርፍና ኪሳራውን መንግሥት ያውቃል፡፡ አንድ ባለሙያ ፊልሙን ፖስት ሲያደርግ ማን በምን ያህል እንደገዛ በኛ ሲስተም ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ሲስተምም ይታያል፡፡ እኛ ሱቅ የማከራየት ዓይነት ሚና ነው ያለን፡፡ የምንቀበለው የሱቅ ኪራይ ነው እንጂ ዕቃው የባለቤቱ ንብረት ነው፡፡ ባለቤት ነኝ ብሎ ሥራውን ፖስት ሲያደርግ ተጠያቂነቱን አዘጋጅተንለታል፡፡ የገዛው ግሰለብ ማን እንደሆነ እንዲያውቅም ሲስተሙን አዘጋጅተናል፡፡ ያዘጋጀነውን ሜዳ ደኅንነት በአንደኛ ደረጃ መንግሥት መጠበቅ አለበት፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከቴክኖሎጂው ዓለም ሰዎች ጋር መነጋገር አለባቸው፡፡ ሌላው ዓለም ላይ እንዴት እየተሠራ ነው? የሚለው መታየት አለበት፡፡ የኪነ ጥበቡ ባለሙያዎች ሲጎዱ ለምን ይኼ ሆነ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ትክክል ናቸው፡፡ ችግሩን ሲስተሙ ራሱ ይቀርፈዋል፡፡ አደጉ የሚባሉ አገሮች መቆጠጣሪያ መንገዳቸው ቁጥር ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ አሜሪካ ዕቃ ለማስገባት ቁጥር መሰጠት አለበት፡፡ አገልግሎት ሲሰጥም ቁጥር ይሰጠዋል፡፡ ሰውም በሴክዩሪቲ ነምበር ይለያል፡፡ እኛ ጋም ይህ መጀመር አለበት፡፡ የፊልምና ሌሎችም የሙያ ማኅበራት ሐሳብ እንዲተገበር ከተፈለገ የቴክኖሎጂ ሒደቱ መፋጠን አለበት፡፡ ማኅበራቱም በቴክኖሎጂው ረገድ አሠራሩ የሕግ ማዕቀፍ እንዲያገኝ መንግሥትን መገፋፋት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በድረ ገጹ በዋነኛነት የሚጠቀሙት የኪነ ጥበቡ ባለሙያዎች እንደመሆናቸው ሥራችሁን በሙያተኞች ዘንድ ምን ያህል አስተዋውቃችሁታል?

አቶ ተፈራ፡- ባለሙያዎችን እንዲህ አድርጉ ብለን መንገር ባንችልም፣ ባለን ዕውቀት ድረ ገጹን አዘጋጅተናል፡፡ ለፊልም ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ዘርፎች እንዲውል አድርገናል፡፡ ችግሮች እንዲቀረፉ ከተፈለገ ባለሙያዎቹ ከሌሎች ዘርፎች ባለሙያዎች ጋር እጅና ጓንት ሆነው መሥራት አለባቸው፡፡ ሲስተሙ እንዳለ አሳውቀናል፡፡ በእርግጥ ሥራ የጀመረውም በቅርቡ ነው፡፡ ባለሙያዎች የሥራውን አብዛኛውን ፐርሰንት የሚወስዱ ግማሽ አካሎቻችን ስለሆኑ በቀጣይም አብረን እንሠራለን፡፡  

ሪፖርተር፡- እናንተ ከምትሰጡት አገልግሎት ጋር ተቀቀራቢ ሥራ ከሚሠሩ ተቋሞች በተለየ ምን ይዛችሁ መጥታችኋል?

አቶ ተፈራ፡- በመካከላችን ጤናማ ውድድር መፈጠር አለበት፡፡ ያሉት ድርጅቶች አስፈላጊ ናቸው፡፡ ከኛ በፊት ያሉት መስመሩን ባይቀዱት ይህን ማድረግ አንችልም ነበር፡፡ ባለው የኢትዮጵያ ገበያ ኦንላየን ግብይት ማድረግ ስለማይቻል የኤስኤምኤስ መንገድን እንደ አማራጭ ወስደናል፡፡ ማኅበራዊ ድረ ገጽን ከቢዝነስ ጋር ማዋሃዳችንም የተለየ ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ድረ ገጹ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጠ ነው? ተጠቃሚዎችስ ምን ማሟላት ያስፈልጋቸዋል?

አቶ ተፈራ፡- ከተመረቀበት ሐምሌ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ማንኛውም ሰው አካውንት መፍጠርና ፖስት ማድረግ ይችላል፡፡ አንድ ሰው ወደ ፊልም ዶት ኢቲ ገብቶ የሚፈልገውን ዓይቶ ብቻ መውጣት ይችላል፡፡ ላይክ ማድረግና ሼር ማድረግ እፈልጋለሁ ካለ መመዝገብ አለበት፡፡ መሸጥ እፈልጋሁ ካለ ኮንፈርሜሽን (ማረጋገጫ) ይጠየቃል፡፡ እያንዳንዱ ነገር ደረጃ አለው፡፡ ሕዝቡ መርሳት የሌለበት ለጊዜው ኮንፈርሜሽኑን አለመጀመራችንን ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ሰዎች ስለ ድረ ገጹ እንዲያውቁና እንዲገቡ እንፈልጋለን፡፡ በሒደት አውተንትኬሽን እንጀምራለን፡፡ የምንፈልገው ተጠቃሚ ቁጥር ሲሞላ ለእያንዳንዱ ነገር አውተንትኬሽን እንጠይቃለን፡፡ አሁን ባለው ሲስተም የሚታወቁት ገዥና ሻጭ ናቸው፡፡ ሰው ማድረግ ያለበትና የሌለበት (ተርምስ ኤንድ ኮንዲሽንስ) አሉ፡፡

 

 

 

 

Standard (Image)

‹‹በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የበላይነት በባህልና በሌሎችም መገለጫዎች ላይ ተፅዕኖ ሊያመጣ ይችላል››

$
0
0

ወጣት ብርሃኑ ወልደሰንበት፣ የኢንተርናሽናል ትሬድ ሃንድቡክ አዘጋጅ

ወጣት ብርሃኑ ወልደሰንበት ይባላል፡፡ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ ዲፕሎማ ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ የመጀመሪያ ሥራውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጀመረው ወጣት ብርሃኑ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በግል ባንኮች በተለያዩ ቅርንጫፎች በተለይ በውጭ ንግድ ዘርፍ (አስመጪና ላኪ) ከአሥር ዓመታት በላይ ሠርቷል፡፡ ወጣቱ በሠራባቸው ዓመታት በአስመጪና ላኪነት ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች ዘርፉን አጥርቶ ከማወቅ ጋር በተገናኘ ሲቸገሩ በማየቱ፣ መፍትሔ ይሆን ዘንድ International Trade Handbook (ኢንተርናሽናል ትሬድ ሃንድቡክ) የተባለ መጽሐፍ በእንግሊዝኛ አዘጋጅቷል፡፡ በመጽሐፉ ዙሪያ ታምሩ ጽጌወጣት ብርሃኑን አነጋግሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንተርናሽናል ትሬድ ሀንድቡክ በሚል ያሳተምከው መጽሐፍ ለማዘጋጀት ምን አነሳሳህ?

አቶ ብርሃኑ፡- መጀመሪያ ላይ መጽሐፍ ለመጻፍ አላሰብኩም ነበር፡፡ ወይም የመጽሐፍ ዓላማም አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን አንድ ባህሪ አለኝ፡፡ ሁልጊዜ ከምሠራው የሥራ ባህሪ ጋር የሚገናኙ መጻሕፍት ካሉ ማንበብ እወዳለሁ፡፡ ይህ ደግሞ ዝም ብዬ ለማንበብ ሳይሆን፣ አንድ ሥራን ለማሻሻልና ሥራውንም ለማሳደግ ጠቃሚ መንገድ በመሆኑ ነው፡፡ እኔ ሥራ የጀመርኩት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ እንደአጋጣሚ ሆኖ ቀጥታ የሥራ ግንኙነቴ በውጭ ንግድ ማለትም መላክ (ኤክስፖርት) እና ማስመጣት (ኢምፖርት) ላይ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት አንድን የአገር ውስጥ ምርት ወደ ውጪ ለመላክና የውጭ አገሮችን ምርት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ግልጽ የሆነ መመርያ ያስፈልጋል፡፡ በወቅቱ እኔ ያገኘሁት ሁለት ዓይነት መመርያዎችን ብቻ ነው፡፡ አንደኛ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያና ከኢንተርኔት የሚገኙ የተለያዩ ከውጭ ንግድ ጋር የሚገናኙ መጣጥፎችን ብቻ ነው፡፡ ሥራውን የተቀላጠፈ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ለማድረግ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ አሰብኩ፡፡ እሱም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶችንና መጻሕፍትን መፈለግ፡፡ በዚህም የተነሳ ድረ ገጾችን መፈተሽ ጀመርኩኝ፡፡ በአገራችን የውጭ ንግድን በሚመለከት መንገድ የሚሰጥ ወይም አብራርቶ የሚያስረዳ መጽሐፍ ማግኘት አይቻልም፡፡ በመሆኑም በአማዞን ላይብረሪ በመግባት የውጭ አገር መጻሕፍትን በመፈለግና ከዓለም አቀፍ ንግዱ ጋር ተስማሚ የሚሆኑትን በመውሰድ ለመጽሐፍ ግብዓት ተጠቅሜያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- መጽሐፉን ለመጻፍ በዋናነት ምክንያት የሆነህ ተመድበህ ትሠራበት የነበረው መላክ (ኤክስፖርት) እና ማስመጣት (ኢምፖርት) የሥራ ዘርፍ ላይ ችግር ገጥሞህ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለህ?

አቶ ብርሃኑ፡- በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስቸግሩ ነገሮች ነበሩ፡፡ በሥራ ላይ ይገጥሙኝ የነበሩትን ችግሮች መፍታት የሚቻለው ልምድ ካላቸውና በሥራው ላይ ብዙ ጊዜ ካሳለፉ ሰዎች እንጂ በመጻሕፍት ላይ ወይም በሥራ መመርያ ላይ ማግኘት አይቻልም ነበር፡፡ በዘርፉ ላይ ዕውቀት ቢኖርም በተበታተነ ቦታ ላይ ነበር፡፡ ማለትም በዘርፉ ላይ ተሰማርተው ረዥም ዓመታት ካገለገሉ ሰዎች ፈልገህ ወይም በስልክ ንግግር በማድረግ ነበር ያጋጠመህን ችግር መረዳት የምትችለው፡፡ የተዘጋጀና በሥራ ላይ ለሚያጋጥምህ ችግር እንደ መፍቻ ቁልፍ ተደርጎ በመጽሐፍ መልክ የተዘጋጀ ነገር አታገኝም፡፡ ዕውቀቱ ወይም መፍቻ ቁልፉ የሚገኘው በሰዎች አዕምሮ ውስጥ እንጂ፡፡ በሌላ በኩል ሰዎች ልምድ ሊኖራቸው የሚችለው እንደ አጠቃላይ ከተማሩት የትምህርት ዘርፍ በተጨማሪ በሥራ ላይ የሚያገኙት ልምድ ነው፡፡ በውጭ ንግድ ላይ ተሰማርቶ የሚሠራ ሰው ዕውቀቱን የሚያገኘው በሥራ ላይ ከነበሩ ሰዎች ከሆነ፣ የሰው ልጅ ዕውቀት ወይም ልምድ ደግሞ እንደየሰው ሊለያይ ይችላል፡፡ ይህ ማለት ደረጃውን የጠበቀና አንድ መስመር የያዘ ዕውቀት ማግኘት ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት እኔ በሥራ ዘርፉ ላይ እያለሁ የሚያጋጥሙኝን ችግሮች ለመፍታት ‹‹እስከመቼ ነው ሰዎችን እያስቸገርኩ የምኖረው?›› የሚለው ጥያቄ ቀድሞ ከነበረኝ በዘርፉ ያለውን የዕውቀት ችግር ከመፍታት ራዕይ ጋር ተደምሮ በዘርፉ ያሉ መጻሕፍትንና የተለያዩ ግብዓቶች በማንበብ ያገኘኋቸውን ግብዓቶች የመጽሐፌ አካል አድርጌያቸዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በአስመጪና ላኪነት ዘርፍ ላይ የሠሩ ልምድ ያላቸውን ሰዎች ሐሳብና አስተያየት በመጽሐፉ አካተሃል?

አቶ ብርሃኑ፡- አንዳንድ አስተያየቶችን ለማካተት ሞክሬያለሁ፡፡ የሚገርመው ነገር ልምድ ያላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ስትጠይቃቸው ቁንጽል ነገር ነው የሚሰጡህ፡፡ እኔ ግን ቀን በምሠራበት ወቅት የሚገጥሙኝን የሥራ ላይ ችግሮች ማታ ወደ ቤት ስገባ በማስታወሻ ላይ አሰፍራቸዋለሁ፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች ግን በቅንነት ‹‹ይህ ቢገጥምህ ይህንን አድርግ›› ብለው ዕውቀታቸውን ሳይደብቁ የሚነግሩህና ልምዳቸውን የሚያካፍሉህ አሉ፡፡ እነዚህን ሰዎች እከሌ ከእከሌ ሳልል በጅምላ አመሰግናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሰዎች በአንድ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው የሚያገኙትን ዕውቀት ወይም ልምድ በቅንነት ለሌላው የማያስተላልፉት ለምን ይመስልሃል?

አቶ ብርሃኑ፡- እንግዲህ አንዳንዶች ፈቃደኛ የማይሆኑበት ምክንያት ሙሉ ዕውቀት ስለሌላቸው ይመስለኛል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎችም ሆነ በሌላ ቦታዎች ዓለም አቀፍ ንግድ እንደ አንድ ኮርስ የሚሰጥ ቢሆንም፣ በመጻሕፍት የታገዘ አይደለም፡፡ እኔ ይህንን መጽሐፍ ለመጻፍ ያልረገጥኩበት ቦታ የለም፡፡ ምንም ዓይነት የተደራጀ መጽሐፍ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ከብሔራዊ ባንክ መመርያ ውጪ ለመመርያና ማስተማርያ የሚሆኑ መጻሕፍትን አላገኘሁም፡፡ ይህ ባለመኖሩ በዘርፉ ትንሽ ዕውቀት ያላቸውም ቢሆን ለማስረዳት ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ምናልባት የጻፍኩት መጽሐፍ ይህንን ሁሉ ችግር ይቀርፋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ችግሮች እንዴት መፈታት እንዳለባቸውና አንድ በዘርፉ የተሰማራ ነጋዴ ከጅማሮ እስከ መጨረሻው ምን ማድረግ እንዳለበት መጽሐፉ ምላሽ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፍ ንግድ ሲካሄድ ዓለም አቀፍ ሕግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሥራ ሲሠራ ችግርም ሊከሰት ስለሚችል፣ ችግሩን መፍቻ መሣሪያ ያስፈልጋል፡፡ መጽሐፍህ እነዚህን ነገሮች አካቷል?

አቶ ብርሃኑ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ንግድ ሲሠራ ችግር ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ችግሮች ቢገጥሙህ እንዴት ሊፈቱ ይችላሉ? ለሚሉት ጥያቄዎች መፍትሔ የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ሕግጋትንም በመጽሐፉ አካትቻለሁ፡፡ እያንዳንዱ በዘርፉ የተሰማራ ምን ዓይነት ፎርማት መከተል እንዳለበት? ችግሮች ቢገጥሙት እንዴትና በምን ሁኔታ መፍታት እንደሚችል በመጽሐፉ ዝርዝር ከመገለጹም በተጨማሪ ምሳሌዎች ተያይዘዋል፡፡ አንድ የውጭ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ ሰው አንብቦና ተረድቶ ሊተገብረው በሚችለው ሁኔታ መጽሐፉ በመዘጋጀቱ ጠቀሜታው ሰፋ ያለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዋናነት በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ያጋጥማሉ የሚባሉት ችግሮች ምንድናቸው?

አቶ ብርሃኑ፡- ችግሩን በሁለት እከፍለዋለሁ፡፡ ገበያን ከማግኘት በፊት የሚያጋጥም ችግርና ገበያው ከተገኘ በኋላ የሚያጋጥም ችግር በሚል፡፡ ከገበያ በፊት የሚያጋጥም ችግር ገበያውን የማፈላለግና የማግኘት ችግር ነው፡፡ እንዴት ገበያውን መፈለግና ማግኘት እንደሚቻል የሚያጋጥም ችግር ነው፡፡ ገበያን በቀላሉ ለማግኘት እንደሚቻል አመላካች ወይም መፈለጊያ ዘዴዎች ባለመኖራቸው የሚያጋጥሙ ችግሮች ናቸው፡፡ የጻፍኩት መጽሐፍ ግን የሚያተኩረው ወደ ገበያው ከተገባ በኋላ ያሉ ሒደቶች ላይ ነው፡፡ አንድ በንግድ ላይ የተሰማራ ሰው ከውጭ አገር ዜጋ ጋር የንግድ ግንኙነት ይፈጥራል፡፡ የኤልሲ፣ የሰነድ ድርድርና የመሳሰሉ ነገሮች ያጋጥሙታል፡፡ እነዚህ የድርድር ዓይነቶች የንግድ ስምምነቶች ምንና ምን ዓይነት እንደሆኑ በመጽሐፉ በደንብ ተገልጿል፡፡ አንድ ሰው በየትኛው በኩል ልደራደር ብሎ ሲያስብ፣ እያንዳንዱን ድርድር የሚያካሂድበት መንገድ በመጽሐፉ ተቀምጧል፡፡ ድርድሮቹ የራሳቸው ጥቅምና ጉዳት አላቸው፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ሒደቶች ችግር እንዳይገጥም በድርድር ወቅት ምን መደረግ እንዳለበት በደንብ የሚያስረዱ ነጥቦች ከመጽሐፉ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፡፡ ከድርድሩ በኋላ በሚደረስ ስምምነት መሠረት በቀጣይ የሚኬደው ወደ ጭነት ስምምነት ነው፡፡ የተጫነው ዕቃ በሚጓጓዝበት ወቅት አደጋ ቢደርስበት የማን ወጪ ነው? የሻጭ ወይስ የገዢ? ይህንንም ችግር እንዴት መፍታት እንደሚቻል፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መጽሐፉ ምላሽ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- መጽሐፉ እንደነገርከኝ በተለይ በአስመጭነትና ላኪነት ንግድ ላይ ለተሰማሩ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በሌላው የንግድ ዘርፍ ለተሰማሩትስ?

አቶ ብርሃኑ፡- አንድ ሰው ወደ ንግድ ለመግባት መጀመሪያ የሚያስፈልገው ዕውቀት ነው፡፡ ቢያንስ ይህን መጽሐፍ ካነበበ በኋላ፣ በውጭ ንግድ ዙሪያ ያለውን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ሊያውቅ ይችላል፡፡፡ እኔም ትኩረት ሰጥቼ በመጽሐፉ ላይ ያሰፈርኩት የሥራው እንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡ በሥራው ላይ ያሉት ነጋዴዎች በተለያየ ባለሙያ እየታገዙ ቢሆንም የሚመጣውን አደጋም ለመቀበል ወስነው ነው፡፡ ይህንን መጽሐፍ ቢያነቡት ግን ለእነሱ በቀላሉ አደጋን እንዴት እንደሚቀንሱና ሥራውን በተቀላጠፈ ሁኔታ መሥራት እንደሚችሉ ተጨማሪ ግብዓት ይሆንላቸዋል፡፡ ለጀማሪዎች ደግሞ ተጨባጭ ዕውቀት ይዘው በቀጥታ ሥራቸውን መጀመር እንዲችሉ የሚያስችል ትልቅ መሣሪያ ይሆናቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ተቋም (WTO) አባል እንድትሆን ግፊት እየተደረገባት ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ እንደ አገር የሚያስበውና መስተካከል አለበት በሚለው ላይ ገና እየሠራ መሆኑን በመግለጽ ምላሽ እየሰጠ ነው፡፡ በዋናነት በዕውቀት የበለፀጉ አገሮች በአገር ውስጡን ንግድ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ የሚል እምነትም ስላለው ነው፡፡ ያንተ ሥራ ለንግዱ ማኅበረሰብ አስተዋጽኦ በማድረግና ነጋዴውን ማኅበረሰብ ከሌላው ዓለም አቀፍ ነጋዴ ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን ምን ሚና ይኖረዋል? በዚህ ዙሪያ የሚሠሩ ባለሙያዎችን አማክረሃል?

አቶ ብርሃኑ፡- መጽሐፉን ለመጨረስ ስድስት ዓመታት ፈጅቶብኛል፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚሠሩ ባለሙያዎችን ለማግኘትና ለማማከር ዕድሉን አላገኘሁም፡፡ ነገር ግን በመጽሐፉ ውስጥ የተቀመጡ ነጥቦች በሙሉ የዓለም አቀፍ ንግድ እንዴት እንደሚሠራ፣ ጥቅሙ፣ ጉዳቱና የሚያስከትለው ችግር ጭምር የተካተቱበት በመሆኑ የአገር ውስጥ ነጋዴው መጽሐፉን አንብቦና ራሱን በደንብ አዘጋጅቶ ወደ ገበያው ከገባ፣ ተወዳዳሪ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ የዓለም አቀፍ ንግድ ተቋም አባል መሆን የሚያስፈልገው በዕውቀትና በልምድ ብልጫ ያላቸው የውጭው ዓለም ንግድ ማኅበረሰብ፣ በአገር ውስጥ የንግድ ማኅበረሰብ ላይ ብልጫ በመውሰድ የበላይነትን ይይዛሉ የሚል ነው፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የበላይነት ደግሞ በባህልና በሌሎችም አገራዊ መገለጫዎች ላይ ተፅዕኖ ሊያመጣ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያም ፍርሃት ከዚህ የዘለለ አይደለም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ጥሩ የሚሆነው በየዘርፉ የሚዘጋጁ መጻሕፍትን በማንበብና ዕውቀትን በማዳበር ብቁና ተወዳዳሪ መሆን ነው፡፡ የእኔ መጽሐፍ በአንዱ ማለትም በአስመጪና ላኪ የሥራ ዘርፍ ለተሰማሩ ዕውቀትና መረጃ ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩልም ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ሞጆ ደረቅ ወደብ፣ መቐለ፣ ኮምቦልቻና ድሬዳዋ ደረቅ ወደቦች ትልቅ የውጭ ንግድ አካል የሆኑ መሥሪያ ቤቶችን ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተጨባጭ ለማስተማር እስካልቻልን ድረስ፣ የውጭ ንግድ አካል መሆናቸውን የሚያውቁበት መንገድ የለም፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በተጨባጭ የአገራችንን ኤክስፖርትና ኢምፖርት አሠራር ማስተማር የሚችሉ መጻሕፍትን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መጽሐፌ በተቻለ መጠን ይህንን ግንዛቤ በሚያስጨብጥ መልኩ አድርጌ ነው የጻፍኩት፡፡

ሪፖርተር፡- መጽሐፉን ስትጽፍ በዘርፉ ለተሰማሩ የንግዱ ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን ዩኒቨርሲቲዎችንም ታሳቢ በማድረግ ጭምር መሆኑን ገልጸሃል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ትምህርቱን የሚሰጡ መምህራንን አነጋግረህ እንደ ግብዓት የተጠቀምክበት ነገር አለ?

አቶ ብርሃኑ፡- መጽሐፉን በሚመለከት ለማነጋገር የሞከርኩት ሁለት ጫፎችን ይዤ ነው፡፡ አንደኛ ጭራሽ ዕውቀቱ የሌለው ሰው ስለመጽሐፉ አስተያየት እንዲሰጥ አድርጌዋለሁ፡፡ የውጭ ንግድ ዕውቀቱ የሌለው ሰው ይህንን መጽሐፍ አንብቦ የመረዳት ችሎታው ምን ይመስላል? የሚለውን አይቻለሁ፡፡ ሁለተኛው ስለ ውጭ ንግድ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች የሰጡኝን ግብዓት በመጽሐፉ አካትቻለሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያሉ መምህራንን ለማናገር ብሞክርም ከምፈልገው ጊዜ ጋር ሊራመድልኝ ባለመቻሉ ሊሳካልኝ አልቻለም፡፡ ነገር ግን ይህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ከመሆኑ አንፃር በቀጣይ ሌሎች ግብዓቶችንና አዳዲስ አሠራሮችን ጨምሬ መሥራቴ ስለማይቀር፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የመጀመሪያዎቹ አስተያየትና ግብዓት ሰጪዎቼ እንደሚሆኑ ከወዲሁ መናገር እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- መጽሐፉን በአገር ውስጥ ቋንቋዎች ተርጉሞ ለማቅረብ ዕቅድ አለህ?

አቶ ብርሃኑ፡- ከተለያዩ ሰዎች ጋር እየተነጋገርኩ ነው፡፡ በአማርኛና ኦሮምኛ ቋንቋዎች መተርጎም እንዳለበት እየተነጋገርን ነው፡፡ 

Standard (Image)

የጎንደሩ ሳይንስ ማዕከል

$
0
0

ጎንደር ሳይንስ ማዕከል ከአራት ዓመት በፊት የተቋቋመ ማዕከል ሲሆን፣ በጎንደር ከተማ ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎችን ያስተናግዳል፡፡ ተማሪዎች በሳይንስ በንድፈ ሐሳብ የተማሩትን በተግባር የሚያጤኑባቸው ቤተ ሙከራዎችና የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው ታዳጊዎች ችሎታቸውን የሚያዳብሩባቸው ወርክሾፖች ይገኙበታል፡፡ ባለፉት ዓመታት በሳይንስ ዘርፍ ተስፋ ሰጪ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎች በማዕከሉ ሠልጣኞች ተሠርተዋል፡፡ ማዕከሉ በጎንደር ከተማ እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ የጎንደር ሳይንስ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ግርማ ወርቄን ምሕረተሥላሴ መኰንንአነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ጎንደር ሳይንስ ማዕከል መቼና ምን ዓላማ አንግቦ ተመሠረተ?

አቶ ግርማ፡- ማዕከሉ የተመሠረተው እ.ኤ.አ. በ2013 ማርክ ገልፈንድ በተባለ አሜሪካዊ እስራኤላዊ ዕርዳታ ሰጪ አማካይነት ነው፡፡ ተማሪዎች በንድፈ ሐሳብ ያገኙትን ትምህርት በተግባር የሚያዩበት ማዕከል ነው፡፡ በተግባር ካሳየናቸው በኋላ የፈጠራ ሥራዎች እንዲሠሩ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችም ወደ ማዕከሉ ሲመጡ ደስተኛ ናቸው፡፡ ከማዕከሉ በራቁ አካባቢዎች የሚኖሩ ተማሪዎች ዕድሉን ለማግኘት ስለሚቸገሩ በየትምህርት ቤታቸው የመስክ (አውትሪች) ፕሮግራም እናካሂዳለን፡፡ ዋና ዓላማችን ተማሪዎች በንድፈ ሐሳብ የተማሩትን በተለያዩ ሳይንሳዊ ቁሳቁሶች በመታገዝ እንዲረዱ ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከሉ ለተማሪዎች ምን ዓይነት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል?

አቶ ግርማ፡- ማዕከሉ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት የኦፕቲክስ፣ የኤሌክትሮኒክስ፣ የመካኒክና የአይቲ (ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ) ቤተ ሙከራዎች ናቸው፡፡ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት ወርክሾፕ አለ፡፡ የባዮሎጂና ኬሚስትሪ፣ ፕላንት ሳይንስ ለወደፊት የሚሟሉ ቤተ ሙከራዎች ናቸው፡፡ ተማሪዎች አሁን ባሉት ቤተ ሙከራዎችና ወርክሾፖች እየተጠቀሙ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከሉ የሚያስተናግደው በየትኛው የትምህርት ደረጃ ያሉ ተማሪዎችን ነው? የሥልጠናው አካሄድስ ምን ይመስላል?

አቶ ግርማ፡- ከመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ማለትም ከአምስተኛና ስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ጀምሮ ያሉትን እናካትታለን፡፡ ለወደፊት ከኬጂ (አፀደ ሕፃናት) ጀምሮ ተማሪዎች በሕፃንነታቸው የሳይንስ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለመሥራት ሥርዓተ ትምህርት ነድፈናል፡፡ አሁን ከአምስተኛ ክፍል በታች ያሉ ተማሪዎች ለጉብኝት ብቻ ወደ ማዕከሉ ይመጣሉ፡፡ ተማሪዎችን የምንመርጠው ለሚመለከተው አካል ደብዳቤ በመላክ ነው፡፡ በሒሳብና በሳይንስ ትምህርቶች ከፍተኛ ውጤት ያላቸውና የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው  ተማሪዎች እንዲላኩልን እንጠይቃለን፡፡ መጀመርያ ሲመጡ ደኅንነታቸውን እንዲጠብቁ (ሴፍቲ ሩል) እናሳያቸዋለን፡፡ ወደ ቤተ ሙከራ ሲገቡ ቅደም ተከተሉን ጠብቀው ነው፡፡ የምናሳያቸው ነገር ከሚማሩት ጋር አብሮ የሚሄድ መሆን አለበት፡፡ እያንዳንዱ ቤተ ሙከራ ማንዋል ያለው ሲሆን፣ የተወሰነ መመሪያ ከሰጠናቸው በኋላ ራሳቸው እንዲሠሩ እናደርጋለን፡፡ ተማሪዎቹ በግላቸው እንዲመራመሩ ይጠበቃል፡፡ የሠሩትንም ሪፖርት ያደርጉልናል፡፡ ተማሪዎቹ በየሴሚስተሩ ሲመጡ በስም ዝርዝራቸው መሠረት እንከታተላለን፡፡ የማይከታተል ተማሪ ካለ ሌላ ተማሪ እንዲተካ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በማዕከላችሁ ሠልጣኞች ከተሠሩ የፈጠራ ሥራዎች መካከል ለዘርፉ ዕድገት አስተዋጽኦ ያበረክታሉ የሚሏቸውን ቢጠቅሱልን?

አቶ ግርማ፡- አንዱ ፈጠራ አውቶማቲክ ስትሪት ላይት (የመንገድ መብራት) ነው፡፡ መብራቱ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ ሲሆን ሰው ሳይቆጣጠረው ጨለማ ሲሆን በርቶ ቀን ላይ ይጠፋል፡፡ አውቶማቲክ ስለሆነ ኃይል ይቆጥባል፡፡ በተግባር ውሎ አገልግሎት የሚሰጥበት መንገድ እንዲፈጠር ለሚመለከታቸው አሳውቀናል፡፡ ሌላው ፓርኪንግ ሎት ነው፡፡ በተለምዶ በሆቴሎች፣ በቢሮዎችና በግለሰብ ቤቶች መኪና ፓርክ ለማድረግ ጥበቃዎችን ጠይቀን በር አስከፍተን ነው፡፡ ፈጠራው በፓርኪንግ አካባቢ ያለውን ክፍት ቦታ በመቁጠር ያለሰው እገዛ ክፍት ቦታ ካለ ለመግባት ያመቻል፡፡  በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደ ውድድር ከ78 ፕሮጀክቶች መካከል አንደኛ የወጣ ሲምፕል ሮቦቲክ ካር አለን፡፡ ፈጠራው ዕቃዎችን በቀላሉ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚያስችል መኪና ሲሆን፣ አማኑኤል ደምሴ የተባለው ፈጣሪው ላፕቶፕ ተሸልሟል፡፡ መኪናውን በምን መልኩ በተግባር እናውለው? የሚል ጥያቄ በዞን ደረጃ ተነስቶም ነበር፡፡ የትራፊክ መብራት፣ ስሞክ ኤክስራክተር፣ ሞባይል ዲተክተርም ከፈጠራዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ሞባይል ዲተክሩ ስብሰባ በሚኖር ወቅት ወይም በትምህርት ቤት አካባቢ የሞባይል ድምፅ እንዳይረብሽ በተወሰነ አካባቢ ብቻ ሞባይል እንዳይሠራ የሚያደርግ ነው፡፡ ስሞክ ኤክስራክተሩ ቤታችን ውስጥ ጭስ በሚበዛበት ወቅት በቀላሉ የሚያስወግድ ነው፡፡ ተማሪዎች የፈጠራ ፕሮቶታይፕ (ሞዴል) ማዘጋጀት እንጂ ትልቅ ሥራ አይጠበቅባቸውም፡፡ ወደሚቀጥለው ደረጃ ለመሸጋገር በጀትም ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከፈጠራ ሥራዎቹ መካከል ከሞዴል በተግባር ላይ የዋሉና ኅብረተሰቡ የሚገለገልባቸው አሉ?

አቶ ግርማ፡- በፕሮቶታይፕ የሚገኙ እንጂ በተግባር የዋሉ አይደሉም፡፡ እኛ የምንጠቀምበት ሶላር ኦቨን (በፀሐይ ብርሃን የሚሠራ ምድጃ) አለ፡፡ አንድ ወቅት በባዮጋዝ ወተር ፓምፕ ለማሠራት ሞክረን ወደ መኪና ማንቀሳቀሻነት ቀየርነው፡፡ የፈጠረውን ልጅ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር አገናኝተነው ባዮጋዙን በሞተር ቦታ ዳማስ በምትባል መኪና እንዲገጥም ተደረገ፡፡ መኪናዋ ስሊንደር ተገጥሞላት በባዮጋዝ ከተማ ውስጥ እየተንቀሳቀሰችም ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለልጁ ነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠትና መኪናዋ በተግባር እንድትውል በማድረግ ተባብሮናል፡፡ ልጁ መኪናዋን የሠራው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ሲሆን፣ ከተማ ውስጥ ይነዳት ነበር፡፡ አሁን ወደ ውጪ አገር ለትምህርት ሄዷል፡፡ የመድኃኒት መርጫ አውሮፕላን ዲዛይን አድርጎ ጨርሶ ወደ ውጪ የሄደም ልጅ አለ፡፡ ለአውሮፕላኑ (ማረጋገጫ) አፕሩቫል የሚሰጠን ግን አላገኘንም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጠይቀን ነበር፡፡ ከጊዜ እጥረት ነው መሰለኝ አልመጡልንም፡፡ አውሮፕላኑ በአልሙኒየም የተሠራ ሲሆን፣ አንድ ሰው ጭኖ መድኃኒት የሚረጭ ነው፡፡ አሁን ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይገኛል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ድጋፍ የሚያደርግላችሁ አካል አስተዋጽኦ ምን ድረስ ነው?

አቶ ግርማ፡- ዕርዳታ የሚያደርግልን ማርክ ገልፈንድ ከልጅነቱ ጀምሮ የሳይንስ ሰው ነው፡፡ ብዙ የራሱ ፈጠራዎች ያሉት ሲሆን፣ ሳይንስን በአገሪቱ ለማስፋፋት ተነሳስቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጎንደር በተጨማሪ ደብረ ዘይት፣ ባህር ዳር፣ መቐለ፣ አዳማና ሐዋሳ የሳይንስ ማዕከሎች አቋቁሟል፡፡ በማዕከሉ ከሚሠሩ ፕሮጀክቶች መካከል ያመነባቸውን ይደግፋል፡፡ የሳይንስ ፌር (መድረክ) ስናዘጋጅና በሌሎች አጋጣሚዎችም እየመጣ ይጎበኛል፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጅማሮ ደረጃ ከሚገኙ አገሮች መካከል እንደመሆኗ፣ ማዕከሉ በዚህ አካባቢ ያሉ ታዳጊዎችን በሳይንስ ዘርፍ በማብቃት ረገድ ስላለው አገራዊ አበርክቶ ቢገልጹልን?

አቶ ግርማ፡- ትልቅ ለውጥ እያመጣን ነው፡፡ ተማሪዎች ንድፈ ሐሳብ ብቻ ሲማሩ ሳይንስ ምናባዊ ብቻ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ተማሪዎች ዲፍራክሽን ምንድነው? ሲባሉ ንድፈ ሐሳቡን ብቻ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን በቤታቸው የሚተገብሩት ነገር ነው፡፡ አትክልት ውኃ ሲጠጣ የትቦ ጫፍ በእጅ ሲያዝ ዲፍራክሽን እየተሠራ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ሲቀርብላቸው ደስ ስለሚላቸው ለሳይንስ ያላቸው ፍላጎት ይጨምራል፡፡ ማዕከሉ እየታወቀ ሲመጣ ብዙ ቤተሰቦች ልጆቻቸው እንዲገቡ እየጠየቁን ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ለሳይንስ ባለው አመለካከትና በተማሪዎች ላይም ለውጥ እየታየ ነው፡፡ ልዩ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች በትርፍ ጊዜያቸው እየመጡ ይጠቀማሉ፡፡ ኅብረተሰቡ የሳይንስ ማዕከል መኖሩን ሲያውቅና ፈጠራዎቹ አገር ውስጥ መሠራታቸውን ሲያይ የአነሳሽነት ባህሪ አለው፡፡ ተማሪዎች የተወዳዳሪነት ባህሪ እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል፡፡ ሰዎች የፈጠራ ሥራዎቹን ሲያዩ አገር ውስጥ መሠራታቸውን ማመን እስኪያቅታቸው ይገረማሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ፈጠራዎች የማኅበረሰቡን ችግር ከግምት በማስገባት መፍትሔ ለመስጠት ቢሠሩም፣ ፈጠራዎች ከሞዴልነት ባለፈ እምብዛም በተግባር ሲውሉና በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ሲቀርቡ አይስተዋልም፡፡ ይህን ውስንነት ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት?

አቶ ግርማ፡- የተባለው ውስንነት አለ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና መንግሥትም መሳተፍ አለበት፡፡ ብዙ ሰው የሆነ ነገር ፈጥሮ በአቅም ማነስ የተነሳ ወደ ተግባር አይቀይረውም፡፡ ፈጣሪው አቅም ካለው ሰው ጋር ላይተዋወቅ ወይም ማሳመን አይችል ይሆናል፡፡ የፈጠራ ሰዎች በብዛት ዕድሉን አያገኙም፡፡ ፈጠራዎቻቸው ወደ ተግባር የማይመጡትም ለዚህ ነው፡፡ እኛ ፈጠራዎችን ወደ ተግባር ለማስገባት ከብዙ አካሎች ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ መንግሥት ለሳይንስ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ ያሉት ችግሮች ተቀርፈው አገሪቱ በሳይንስ ከፍተኛ ደረጃ የምትደርስበት ጊዜም ቅርብ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከከተማ ቀመስ አካባቢዎች በዘለለ አብዛኛው ማኅበረሰብ ወደሚኖርበት ገጠራማው አካባቢ ሳይንስን ለማስፋፋት ጥረት ታደርጋላችሁ?

አቶ ግርማ፡- ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡ እኛም እንዴት ማዳረስ እንደምንችል ዕቅዶች ይዘናል፡፡ በ2010 ዓ.ም. በጀቱን ካገኘን በወረዳዎች ለመሥራት ዕቅድ አለን፡፡ ገጠር ውስጥ በጣም ጎበዝ ልጆች አሉ፡፡ እነሱን ለመደገፍ ፕሮግራሞች ይዘናል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ በየገጠሩ የትራንስፖርት፣ የኤሌክትሪክና ሌሎችም የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ባለመኖራቸው ለሳይንስ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ትምህርት የሚሰጠው ዋጋ አነስተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ብዙ ፕላዝማዎች ከዓመታት በፊት ከውጪ መጥተው እስካሁን አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመሩ በሚዲያ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ ማለት የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት አለ ማለት ነው፡፡ ኃይል በሌለበት ሳይንስን ማስፋፋት አስቸጋሪ ነው፡፡ መንግሥት በየገጠሩ የመብራት አገልግሎት እየዘረጋ ስለሆነ ሳይንስንም አብሮ ማስፋፋት ይቻላል፡፡ ተማሪዎች ወደ ሳይንስ የሚያዘነብሉት በመጽሐፍ ከሚያነቡት ንድፈ ሐሳብ ባለፈ በቴሌቪዥን፣ በኢንተርኔትና በሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሲታገዙ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ምን ያህል ሠልጣኞች አሏችሁ?

አቶ ግርማ፡- በዚህ ዓመት 830 ተማሪዎችና በአውትሪች ፕሮግራም ከ2,000 በላይ ተማሪዎች ተካተዋል፡፡

 

 

 

 

 

Standard (Image)

‹‹ኢትዮጵያ የጃፓን ኩባንያዎችን ለመሳብ ትልቅ አቅም አላት››

$
0
0

 

አቶ ሐሰን ከድር፣ በጃፓን ኮቤ ከተማ የአፍሪካ ኮቤ አገናኝ ባለሙያ

ሐሰን ከድር እድሪስ ይባላሉ፡፡ ከወንዶ ገነት ዩኒቨርሲቲ በናቹራል ሪሶርስ ማኔጅመንት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያገለገሉ ሲሆን በቀድሞው የግብርና ሚኒስቴር በአፈርና ውኃ ጥበቃ ባለሙያነት አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 ወደ ጃፓኗ ሰባተኛ ግዙፍ ከተማና ዓለም አቀፍ የባህር ትራንስፖርት መናኸሪያ ኮቤ በማቅናት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የኮቤ ከተማ መስተዳድር ከተማዋንና ኩባንያዎችን ከአፍሪካ አገሮች ጋር የማስተሳሰር ከፍተኛ ኃላፊነት ሰጥቷቸው ተቀጥረዋል፡፡ ዮሐንስ አንበርብርበቅርቡ በጃፓን የተለያዩ ከተሞች ባደረገው የሥራ ጉብኝት ወቅት ከኢትዮጵያዊው ባለሙያ አቶ ሐሰን ከድር ጋር በኮቤ ከተማ ከንቲባ ስለተሰጣቸው ተልዕኮ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኮቤ ከተማ መስተዳደር የተሰጡት የሥራ ተልዕኮ ምንድነው?

አቶ ሐሰን፡- በአሁኑ ወቅት የጃፓን መንግሥት ለአፍሪካ ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ የጃፓን ኩባንያዎች ወደ አፍሪካ እንዲገቡ በስፋት ይፈለጋል፡፡ ይህንን ለማስፈጸም የተለያዩ የፖሊሲ መሣሪያዎች በአገሪቱ መንግሥት ተቀርጿል፡፡ የኮቤ ከተማ አስተዳደርም በከተማዋ የሚገኙ ኩባንያዎች ወደ አፍሪካ ገበያ እንዲያተኩሩ እያበረታታ ይገኛል፡፡ የኔ ኃላፊነትም ይህንን የመስተዳደሩ ጥረት መደገፍ ነው፡፡ የጃፓን ኩባንያዎች የቆየ ልማድ አላቸው፡፡ ይኸውም ከአገራቸው ወጥተው በንግድ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት ቀልባቸው ስለተሳበበት አገር አጠቃላይ ሁኔታ፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አዝማሚያዎች አጥንተው ስለምቹነቱ እርግጠኛ ሲሆኑ ነው የሚገቡት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመረጡት አገር ውስጥ ያሉ አገር በቀል ኩባንያዎችን አቅም በመመዘን ከእነሱ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም ስለመሆኑ እርግጠኛ ካልሆኑ በስተቀር አንድ ዕርምጃ አይራመዱም ነበር፡፡ ይህ ከፍተኛ ጥንቃቄ አሁን መቀየር እንዳለበት አምነዋል፡፡ ቢሆንም መጠነኛ ዕውቀት እንዲኖራቸው አሁንም ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑም የኮቤ ከተማ ኩባንያዋች ከተሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ጋር መጣጣም የሚችሉ የአፍሪካ ኩባንያዎችን በማጥናትና በመመዘን ለኮቤ ከተማ ኩባንያዎች መረጃ ማቅረብና ማበረታታት ነው ዋነኛ የሥራ ኃላፊነቴ፡፡

ሪፖርተር፡- የሥራ ኃላፊነቶን ከወሰዱ ጀምሮ ያደረጉት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎ ምን ይመስላል? በየትኞቹ የአፍሪካ አገሮች ነው ቅድሚያ ትኩረት የሰጣችሁት?

አቶ ሐሰን፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የኮቤ አፍሪካ ሊያዘን ኦፊሰር ሆኜ እየሠራሁ ነው፡፡ ሥራውን የጀመርኩት በዚህ ዓመት ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ነው፡፡ የሥራ ኃላፊነቴ አህጉር አቀፍ ወሰን ያለው ሲሆን የኮቤ ከተማ ኩባንያዎችን በሚሰጠኝ አቅጣጫ ወሠረት ከአፍሪካ ኩባንያዎች ጋር ጥምረት መመሥረት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ የአፍሪካ አገሮችን ዕምቅ አቅም በመገምገም ለኮቤ ከተማ ኩባንያዎች መረጃ ማቅረብና ወደ አፍሪካ እንዲገቡ ማበረታታት ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ የሚያስቀምጠው አቅጣጫ ይኖራል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ተስማሚ ሆኖ ቅድሚያ የተሰጠው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከአፍሪካ አገሮች ኩባንያዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር የኮቤ ኩባንያዎችን ወደ አፍሪካ እንዲገቡ ማበረታታት ነው፡፡ በግብርናና የትምህርት ዘርፎችም እየሠራን ነው፡፡ ቅድሚያ በተሰጠው የአይሲቲ ዘርፍ ባደረግነው እንቅስቃሴ የሩዋንዳ ኩባንያዎችን የተሻለ አቅም በመለየት የኮቤ ኩባንያዎችን ወደ ሩዋንዳ እንዲገቡ ያደረግነው ጥረትም ውጤት እየታየበት ነው፡፡ በኮቤ ከተማ የሚገኙ ኩባንያዎች በዚህ በአይሲቲ ዘርፍ ላይ በስፋት ይሠራሉ፡፡ በጃፓንና በአፍሪካ መካከል ያለውን ርቀት በዚህ ዘርፍ በመስበር መቀራረብን መፍጠር የሚቻል በመሆኑ በከተማ አስተዳደሩም ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ የሩዋንዳ መንግሥት ፖሊሲ ትልቅ ትኩረት ለአይሲቲ የሰጠ ሆኖ መገኘቱና በርካታ የሩዋንዳ ኩባንያዎችም በዚህ ዘርፍ በመንቀሳቀስ ላይ ሆነው መገኘታቸው ቅድሚያ ዕድሉን እንድታገኝ አድርጓታል፡፡ ሩዋንዳ እንደ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ የፈጠረባትን የግንኙነት መሰናከል በአይሲቲ ዘርፍ ለመቅረፍ እየሠራች ከመሆኑም ባሻገር የመጪው ጊዜ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ የጀርባ አጥንት አድርጋ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የኮቤ ከተማ ኩባንያዎችም ከፍተኛ ፍላጎትን አሳይተዋል፡፡ በእስካሁኑ ጥረት ብቻ ሁለት የኮቤ ከተማ ኩባንያዎች ወደ ሩዋንዳ በመግባት ከሩዋንዳ ኩባንያዎች ጋር ጥምረትን ፈጥረዋል፡፡ ሩዋንዳ በተራራማ መልክዓ ምድር ላይ የምትገኝ በተደጋጋሚ በመብረቅ የምትመታ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ይህንን ችግር በአይሲቲ ለመቅረፍ በመንቀሳቀስና አፕሊኬሽኖችን በማልማት ለኢኮኖሚ ገበያው ማቅረብን ትኩረት አድርገዋል፡፡ በኮቤና በሩዋንዳ ኪጋሊ ከተማም በቅርቡ የትብብር ስምምነት ተፈርሟል፡፡ ጃፓኖች ለቴክኖሎጂ ቅድሚያ ይሰጣሉ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች መሪ አንቀሳቃሹ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በሰው ኃይል ቅጥር ላይ ብዙ ትኩረት አያደርጉም፡፡ በጥቂት ባለሙያዎች ነው ሥራዎቻቸውን የሚመሩት፡፡ በመሆኑም ሩዋንዳ ለአይሲቲ ትኩረት የሰጠች አገር መሆኗ ቀዳሚ ምርጫቸው ሆናለች፡፡ ጥቂት ባለሙያዎቻቸውን ሩዋንዳ ላይ በማድረግ ሥራዎችን ለሩዋንዳ የጥምረት ኩባንያዋቻቸው በሰብ ኮንትራት በመስጠትና በሩዋንዳ ያለውን ፍላጎት በማጤን ለመሥራት የሚመቻቸው በመሆኑ በዚህ መንገድ ለመንቀሳቀስ ሩዋንዳን በአሁኑ ወቅት መርጠዋል፡፡ ይህንን ተሞክሮ መሠረት በማድረግ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ማስፋፋት ሌላው አቅጣጫ ነው፡፡ በእስካሁኑ እንቅስቃሴ በጃፓን የሚታወቁት አይሲቲ ኩባንያዎች አቶዋ ዳንኪ እና ዋየርድ ኢን በሩዋንዳ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ አይሲቲ ዘርፍ የኢትዮጵያ ኩባንያዎችና በኢትዮጵያ ያሉ ሁኔታዎች በጃፓን ኩባንያዎች ተመራጭ የመሆን አቅም አላቸው ብለው ያምናሉ?

አቶ ሐሰን፡- በአይሲቲ ዘርፍ ኢትዮጵያ በስፋት ባትንቀሳቀስም ጅምር መሣሪያዎችና ፍላጎቶች እንዳሉ እገነዘባለሁ፡፡ ትልቅ ክህሎትና ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያውያንም ብቅ እያሉ ነው፡፡ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ለአይሲቲ ዘርፍ ትልቅ ገበያ መፍጠር እንደሚችልም ይታወቃል፡፡ የጊዜ ሁኔታ እንጂ ኢትዮጵያ በአይሲቲ ዘርፍ ዕምቅ የሆነ የቢዝነስ ዕድልና ገበያ እንዳላት ይታወቃል፡፡ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢንጂነሮች እየተመረተባት ያለች አገር በመሆኗ አቅም አላት፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ኩባንያዎች እንደዚህ ዓይነት ዕድል እንዳያመልጣቸው ምን ይመክራሉ?

አቶ ሐሰን፡- ቀደም ብዬ እንዳልኩት የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት በራሱ ትልቅ የገበያ ዕድል ነው፡፡ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢንጂነሮች የሚመረቱበት አገር ነው፡፡ በሩዋንዳ እንዳየሁት ከሆነ አዲስ ምሩቆች የራሳቸውን ትንሽ ቢዝነስ አቋቁመው የውጭ ኩባንያዎችን መሳብ ችለዋል፡፡ የራስህ የሆነ ትንሽ አቅም የውጭ ኩባንያን እንዴት መሳብ እንደሚያስችል በተግባር ተመልክቻለሁ፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥም እንደዚህ ዓይነት ተሞክሮዎች ቢለመዱ እጅግ ጠቃሚ ነው የሚሆነው፡፡ እንዲሁም የማርኬቲንግ ሥራና ራስን ማስተዋወቅ ላይ ብዙ መሠራት ይጠይቃል፡፡ ምን ያህል አቅም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ እያስተዋወቅን አይደለም፡፡ እኛ ስለራሳችን በተናገርነው ልክ ነው ሰዎች የሚቀበሉን፤ ስለዚህ በዚህ ላይ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ዌብሳይቶችን አልምቶ መሥራት ብቻ በቂ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የኮቤ ከተማ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በአይሲቲ ዘርፍ መግባት የሚችሉበት አቅም አለ?

አቶ ሐሰን፡- በትክክል፡፡ በተለይ መንግሥት እያቋቋመ ነው የተባለው የአይሲቲ መንደር ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ 

Standard (Image)

‹‹ታካሚዎች በኢትዮጵያ ሐኪሞች ላይ እምነት ሊኖራቸው ይገባል››

$
0
0

ዶ/ር ብሩክ ላምቢሶ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአጥንት ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊና ተባባሪ ፕሮፌሰር

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአጥንት ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊው ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ብሩክ ላምቢሶ ናቸው፡፡ በሆስፒታሉ ስፔሻሊስት ሐኪም ከመሆናቸው ባሻገር የአጥንት ሕክምናም አማካሪ ናቸው፡፡ ስለ አጥንት ሕክምና እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአጥንት ሕመም እንዴት ይከሰታል?

ዶ/ር ብሩክ፡- የአጥንት ሕመም በስፋት የሚከሰተው በአደጋ ጊዜ ነው፡፡ አሁን በአገሪቷ ያለው የተሽከርካሪ አደጋ ደግሞ የበለጠ ቁጥሩን እየጨመረ አንዲመጣ አድርጎታል፡፡ በዚህም መሠረት የእኛ ባለሙያዎች ያለ ዕረፍት ዕርዳታቸውን እያደረጉ ነው፡፡ ሌላኛው የአጥንት በሽታ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ የሚከሰት  ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ውጭ አገር አምርተው የአጥንት ሕክምና እንዲደርጉ ውሳኔያችሁን ያገኙ ታካሚዎች ባገር ውስጥ መፍትሔ ያላገኙበት አጋጣሚ ምን ነበር?

ዶ/ር ብሩክ፡- ወደ ውጭ አገር ሄደው እንዲታከሙ ጉዳያቸው የታየላቸው ታካሚዎች አሉ፡፡ በሽታው በጣም ውስብስብ ሲሆንና ሕክምናው በአገር ውስጥ የማይሰጥ ሲሆን ብቻ ወደ ውጭ ይጻፍላቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የታካሚዎች ፍላጎትን በማከል መልኩ ይከናወናል፡፡ ግን ቀደም ብለን ክትትል ስናደርግላቸው የሚሄድ የማይሄደውን እንለያለን፡፡ እሱም ደግሞ በባለሙያዎች ከፍተኛ ድጋፍ ነው የሚታየው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ እምብዛም ከሌላው ዓለም ያነሰ ሕክምና እያደረግን ነው ማለት አያስደፍርም፡፡

ሪፖርተር፡- በአገር ውስጥ ሕክምናውን የሚከታተል የአጥንት ሕመም ታካሚ ውጭ አገር ሄዶ እንዲታከም ውሳኔ የሚሰጠው በምን ዓይነት መንገድ ነው?

ዶ/ር ብሩክ፡- ውጭ ሄዶ እንዲታከም ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት የታካሚው ሁኔታ በጥልቀት መታየት አለበት፡፡ ታካሚው የሚያስፈልገው ሕክምና ለማግኘት ያጋጠመው ሕመም ከተፈጥሮ ነው ወይስ በሒደት የመጣ? ወይንም ደግሞ በአደጋ የሚለው ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ከዛም በኋላ በሽታው በአገር ውስጥ ሕክምና የማይቻል መሆኑና አገር ውስጥ ካለው የሕክምና  አቅም በላይ ከሆነ ወደ ውጭ ሄዶ እንዲታከም ይወሰናል፡፡ የውሳኔው ሒደት አምስት አባላት ያሉበት ኮሚቴ አለው፡፡ ባለሙያዎቹ ጉዳዩን ከተከታተሉትና ከተወያዩበት በኋላ ውሳኔ ላይ ደርሰው ታካሚው ወደ ውጭ ሄዶ ሕክምና እንዲያደርግ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ቀድሞ ከነበረው የአጥንት ሕክምና ባለሙያ አንፃር አሁን ላይ ያለው ምን ዓይነት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ብሩክ፡- አሁን ላይ ያሉት የአጥንት ሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር በጣም ጨምሯል፡፡ በቅርቡ ራሱ ከ100 በላይ ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ከ13 በላይ ንዑስ ስፔሻላይዝድ ክፍሎች አሉ፡፡ እንዲሁም የሕፃናት የአጥንት ሕክምና ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች አሉን፡፡ ከአገራቸውም ተርፈው ወደ ተለያዩ አገሮች በማምራት ግልጋሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን ማፍራት እየቻልን ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹም ብቃት ያላቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ መሆን የሚችሉ ባለሙያዎች እያፈሩ ነው፡፡ አንዳንዴ ተማሪዎቹ ካላቸው አቅምና የትምህርት ውጤት አንዱን ከአንዱ ለማስቀረት ራሱ አዳጋች የሚሆንበት ወቅት አለ፡፡ ካሉን የአጥንት ባለሙያዎች አንፃር ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ቀዳሚ መሆን እየቻልን ነው፡፡ ስለዚህ ብቁ የሆኑና ቁጥራቸው ወደፊት የበለጠ የሚጨምር ባለሙያዎች ይኖሩናል ማለት ያስችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ታካሚዎች አስፈላጊውን  ሕክምና እና ዕርዳታ ከመስጠት አንፃር እንቅስቃሴያችሁ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ብሩክ፡- እውነት ለመናገር ባለሙያዎች ታካሚዎችን ለመርዳት በማንኛውም ጊዜ ዝግጁ ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው በአገሪቷ በየቀኑ የሚያጋጥመው የተሽከርካሪ አደጋና ባለሙያዎቹ ምን ዓይነት ዕርዳታ እንደሚሰጡ አንድ ቀን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አድሮ መመልከት ይቻላል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ በአጠቃላይ ከ2,500 በላይ ከፍተኛ ቀዶ ሕክምናዎችን ማከናወን ችለናል፡፡ በቀን ከዘጠኝ በላይ ኦፕራሲዮን እናደርጋለን፡፡ 

ሪፖርተር፡-  የአጥንት ሕክምና ቀድሞ ከነበረው አንፃር ሲታይ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ብሩክ፡- በአጠቃላይ ሕክምና ሲባል በማንኛውም አጋጣሚ የታመመ ሰውን የማዳን ሥራ ነው፡፡ ሁሉም ሰው በተለያዩ በሽታዎች ሕይወቱ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን የሁሉም ሰው በሽታ ተመሳሳይ ነው ማለት አይቻልም፤ የእያንዳንዱ ሰው በሽታ የራሱ የሆነ ባህሪ አለው፡፡ ስለዚህ በባለሙያዎች አስፈላጊው ክትትል ከተደረገለት በኋላና ጉዳዩ በጥልቀት ከታየ በኋላ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ ቀደም ብሎ በአጥንት ሕክምና ዙሪያ ባለው የባለሙያ ዕጥረትና አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ዕቃ ያለመኖር የተወሰኑ ታካሚዎች ወደ ውጭ አገር ሄደው እንዲታከሙ ተደርገዋል፡፡ ግን ቀድሞ ከነበረው አሁን ላይ ቁጥሩ በጣም ቀንሷል፡፡ በፊት በዓመት እስከ 115 ታካሚዎች ወደ ውጭ አገር አምርተው እንዲታከሙ ተደርጓል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የዘንድሮውን ቁጥር ብንመለከት 56 ታካሚ ብቻ ነው የተላከው፡፡ ለዚህም በግማሽ የመቀነሱ ምክንያት  በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ይሰጥ የነበረው የአጥንት ሕክምና በሁሉም መሰጠት ስለተጀመረ ነው፡፡ በተጨማሪም ዓለም የደረሰበትን የሕክምና መሣሪያ በአገራችን ማስገባት ስለቻልን እንዲሁም የባለሙያዎች ቁጥር መጨመር ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በቅርቡ እንዲያውም የውጭ አገር ዜጎች በእኛ አገር ሕክምናው እያገኙ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ወደ ውጭ አገር ሄደው ሕክምና የሚያደርጉ ታካሚዎችን መሉ በሙሉ እናስቀራለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ግን ታካሚዎች በኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎች ላይ እምነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ስላለው የሕክምና ማሻሻያ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ብሩክ፡- በቅርቡ መንግሥት የሕክምና መሣሪያ አስገብቶልናል፡፡ በፊት አንድ ታካሚ ለአጥንት መገጣጠሚያ እስከ 150 ሺሕ ብር ያወጣ ነበር፡፡ አሁን ግን 67 በመቶ በነፃ እንዲታከም አስችሎታል፡፡ ሌላው በኢትዮጵያ ውስጥ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ የሕክምና ጣቢያዎች እየተስፋፉ መምጣታቸው ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ እየታየ ያለው የአጥንት ሕክምና ዕድገት ችግሮችን በአገር ውስጥ በቀላሉ ለመፍታት ያስችላል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ላይ ታካሚዎች ከሚያጋጥማቸው ድንገተኛ በሽታ አኳያ የገንዘብ ዕጥረት እያጋጠማቸው በየመንገዱ ሕዝቡን ሲማጸኑ ይታያል፡፡ ለዚህ መፍትሔው ምንድነው ይላሉ?

ዶ/ር ብሩክ፡- ማንኛውም ሰው እንዴትና መቼ በሽታ እንደሚያጋጥመው እርግጠኛ መሆን አይችልም፡፡ ችግሩ ሲያጋጥመው ደግሞ ቅድሚያ ሕክምና ማግኘት ይኖርበታል፡፡ አሁን ግን በበሽታው መጎዳቱ ሳይቀር የሚታከምበት ገንዘብ ፍለጋ የሰው ፊት ለመመልከት ይገደዳል፡፡ ስለዚህ በእኛ አገር የጤና ዋስትና መስፋፋት ይኖርበታል፡፡ ከሚገኘው የቀን ገቢ ለጤና ዋስትናው የመቆጠብ ባህልን መልመድ ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች አገሮች የጤና ዋስትና አላቸው፡፡ በደህና ጊዜ ገንዘብ የመቆጠብ ዘዴ መለመድ ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡      

Standard (Image)

‹‹ለፖሊስ ፈታኙ ጊዜ አሁን ነው››

$
0
0

 

ረዳት ኮሚሽነር አበበ ለገሰ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር

ረዳት ኮሚሽነር አበበ ለገሰ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ በዕጩ መኰንንነት ተመርቀዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት የመጀመሪያ፣ እንዲሁም ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ሕግ ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በሥራ ዓለምም የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንን በማደራጀትና በአምቦ ሰንቅሌ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ እንቅስቃሴና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ዋና ዳይሬክተሩን ታምራት ጌታቸውአነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሌጁ መቼ ነው የተቋቋመው? ዓላማውስ ምን ነበር

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- ኮሌጁ እንደ ኮሌጅ ከመመሥረቱ በፊት የኦሮሚያ ፖሊስ ማሠልጠኛ ማዕከል በሚል መጠሪያ በ1984 ዓ.ም. በጅማ ዞንና በአዳማ ከተማ ተመሠረተ፡፡ ከዚያም በ1985 ዓ.ም. አምቦ ሰንቅሌ ማሠልጠኛን በማዋሃድ አምቦ ሰንቀሌ በሚባል ቦታ ላይ ኦሮሚያ ፖሊስ ማሠልጠኛ በመባል አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በዚህ ግን መቀጠል አልቻለም፡፡ ምክንያቱም በየጊዜው እያደገ የመጣው የኅብረተሰቡ የፖሊስ አገልግሎት ፍላጎት በዘመናዊ መልክ መስጠት በማስፈለጉ እንዲሁም የምናሠለጥነው ፖሊስ ከዘመኑ ጋር መራመድ እንዲችል ከማሠልጠኛ ወደ ኮሌጅ ማሳደግ ግድ ሆኗል፡፡ በዚህም የተነሳ ቀድሞ ናዝሬት ሕፃናት ማሳደጊያ ይባል በነበረው ቦታ ላይ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅን በ2002 ዓ.ም. ለማቋቋም ተችሏል፡፡ ኮሌጁ በርካታ ዓላማዎች ያሉት ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ጥናትና ምርምር ማካሄድ ተደጋጋሚ ወንጀሎችን የሚፈቱበትን ጥናት ማድረግ፣ ወንጀሎች ከመከሰታቸው በፊት ምርምር ማካሄድና መፍትሔዎችን ማበጀት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኮሌጁ የሚገባ አንድ ሠልጣኝ ምን ምን መሥፈርት ነው ማሟላት ያለበት? ኮሌጁስ በምን መስክ ሥልጠና ይሰጣል? የመቀበል አቅሙስ ምን ያህል ነው?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- ወደ ኮሌጁ የሚገባ አንድ ሠልጣኝ በሁለት ዓይነት መንገድ ነው፡፡ አንደኛው ከትምህርት ቤት ጀምሮ በትንሹ አሥረኛ ክፍልን ያጠናቀቀ፣ ሙሉ ጤንነቱ በሕክምና የተረጋገጠ፣ ዕድሜው ከ18 እስከ 25 ዓመት የሆነና የፀባዩ ሁኔታ ምንም ወንጀል እንደሌለበት ከቀበሌ ጀምሮ ትምህርት ቤቱ የተመሰከረለት መሆን ይገባዋል፡፡ ለዚህም በኦሮሚያ ክልል ባሉ ከ7,000 በላይ ቀበሌዎች ማስታወቂያዎችን በመለጠፍ በመመልመል ብቁ የሆኑት የሚገቡበት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከፖሊስ ሠራዊት ውስጥ የሚመለመሉ ሲሆን፣ ይህም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና ወይም በመሰናዶ ትምህርት መልቀቂያ ፈተና ውጤታቸው ቢያንስ 2.2 ለወንድ፣ ለሴት ደግሞ 2 ነጥብና ከዚያ በላይ ያላቸው፤ የአገልግሎት ዘመናቸው ከአምስት ዓመት በላይ የሆናቸውና የመግቢያ ፈተናውን ያለፉ በዲፕሎማ ፕሮግራም በመመልመል የፖሊስ ሳይንስ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ኮሌጁ የሚሰጣቸው የትምህርት ዓይነቶች በርካታ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ የመደበኛ ፖሊስ፣ ትራፊክ፣ አድማ ብተና፣ የወንጀል ምርመራ፣ በፖሊስ ሾፌርና እንዲሁም በየጊዜው በሚቀያየረው የፖሊስ ሳይንሳዊ ትምህርቶችን ይሰጣል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የመቀበል አቅሙም ከ6,000 እስከ 7,000 ደርሷል፡፡   

ሪፖርተር፡- ኮሌጁ ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ፖሊስ በማፍራት ደረጃ ምን እየሠራ ነው?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- የፖሊስ አገልግሎት በአሁኑ ሰዓት በጣም ፈታኝ ሥራ ውስጥ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም ወንጀል በተለምዶ የሚከናወን አይደለም፡፡ ዛሬ ደግሞ ዘመኑ የረቀቀ ወንጀል በረቀቀ መሣሪያ የሚፈጸምበት ነው፡፡ ማኅበረሰቡንም ከነዚህ የረቀቁ ወንጀሎች ለመጠበቅ ፖሊስ ከሁሉም ቀድሞ መገኘት መቻል ግዴታ ነው፡፡ ለፖሊስ ፈታኙ ጊዜ አሁን ነው፡፡ ይህንን ካልተወጣን የሕግ የበላይነት ይጠፋና የኅብረተሰብ ያለመረጋጋት ይመጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም በተመሠረተው የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ለሠልጣኞቻችን በቴክኒክ ሙያ፣ በኮምፒውተር ጥቃት ላይ እየሠራን ሲሆን፣ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በአመራር፣ በኮምፒውተር ላቦራቶሪ፣ በረቂቅ ወንጀሎች አፈታት ዙሪያ ከውጪ ባለሙያዎችን በማስመጣት ሥልጠና እንጀምራለን፡፡ ይህም ሆኖ ግን ኅብረተሰቡ በሚፈልገው ልክ ዘመናዊ ፖሊሲ የማውጣት ሥራ ሠርተናል ማለት ግን አንችልም፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ከ10,000 በላይ የሚሆኑ የፖሊስ አባላትን በመቀበል ችግሩን ከተጠቀሰው ቁጥር ለመቀነስ ግብ ጥለን እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሌሎች የትምህርት ተቋማት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- በዚህ ዙሪያ ጥሩ ሥራ እየሠራን እንገኛለን፡፡ እነሱ ከእኛ የሚፈልጉት አለ፡፡ እኛም ከነሱ የምንፈልገው አለ፡፡ ለምሳሌ እነሱ የጥበቃ አገልግሎት የትምህርት ቤቶች ደኅንነት እንዴት እንደሚጠበቁ እንዲሁም ከሌሎች ጉዳይ ልምድ ይፈልጋሉ፡፡ እኛ ደግሞ አንድ ሠልጣኝ በፖሊስ ሳይንስ ትምህርት ብቻ በቂ ይሆናል ብለን አናምንም፡፡ ለምሳሌ በሕግ፣ በኮምፒውተር፣ በዲሲፕሊንና በድኅረ ምረቃ አስተማሪዎቻችን እንዲያሠለጥኑልን እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም በአንድ ተቋም ብቻ ፖሊስ አሠልጥኖ ማውጣት ስለማይቻል በጋራ መሥራት የግድ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በክልሉ ካሉ 15 ዩኒቨርስቲዎች ጋር ለመሥራት ደብዳቤ እየተጻጻፍን ሲሆን፣ ለጊዜው ከአርሲ፣ ከአምቦና ከአዳማ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሥራ ጀምረናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ፖሊስ ኮሌጅ ሰሞኑን የቀድሞ ፖሊሶች (በሥራ ላይ የነበሩትን) እየጠራ እንደ አዲስ እያሠለጠነ ይገኛል፡፡ ለምንድነው? ባለፈው ረብሻ የታዩ ክፍተቶች ስለነበሩ ነው?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- በእርግጥ መነሻው እሱ ባይሆንም በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የተከሰተው ችግር በእኛም ክልል ነበር፡፡ ለምሳሌ በዚህ ወቅት በፖሊስ ሠራዊቱ ላይ የታየው ክፍተት በጥናት ስናይ ሕዝቡ በፖሊስ አባላት ላይ የነበረውን ችግር፣ እንዲሁም በክልሉ የትራፊክ አደጋ ለምን እንደሚጨምር ለየንና እንዚህንና ሌሎች በአጠቃላይ በፖሊስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በተደረገው ጥናት የተገኘው ውጤት የፖሊስ አባሎቻችንን እንዲሁም በየትኛውም እርከን ያሉ አመራሮች እንደ አዲስ መሠልጠንና ተሃድሶ ማግኘት እንዳለባቸው በመታመኑ ነው ሥልጠና እንዲገቡ የተደረገው፡፡

ሪፖርተር፡- በጥናቱ የተገኘው ውጤት ምንድነው?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- በመሠረቱ አንድ የፖሊስ አባል በፖሊስ ሳይንስ ተመርቆ ወጣ ማለት ሁሌም ብቁ ሆኖ ነው የሚሠራው ማለት አይደለም፡፡ በየዘመኑ ከኅብረተሰቡ ፍላጎት አንፃር እየታየ መታደስ ያስፈልገዋል፡፡ እኛ ይህንን ሳናደርግ ቆይተናል፡፡ በዚህም በፖሊስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከታየው የግንዛቤ ክፍተት፣ ፖሊሳዊ ዲሲፕሊኖች መጥፋት፣ በተወሰኑ አባሎች ላይ ደግሞ የኪራይ ሰብሳቢነት መፈጠር፣ የተደራሽነት ችግር እንዲሁም ሕዝቡ ያነሳቸው የነበሩ የመርማሪዎች ማነስ ከተለዩት ችግሮች በጥቂቱ ሲሆኑ፣ በፖሊስና በፍትሕ አካላት ላይ በሕዝቡ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ የተሰጠ ሥልጠና ነው፡፡ ሥልጠናው የሚሰጣቸው እንደየሥራ ክፍሎቻቸው ሲሆን፣ በተከታታይም የማብቃት ሥራ በየደረጃው ኮሌጁ በአምቦ ሰንቅሌ፣ በአዳማ እንዲሁም በትውስት በወሰድነው አላጌ ግብርና ባሉት ካምፖች ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- በኮሌጁ ውስጥ እንደ ችግር የሚያነሱት ምንድነው?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- ኮሌጁ ያለበትን ችግር በማጥናት ለመንግሥት አቅርበን መልስ እየጠበቅን ቢሆንም፣ በአሁን ሰዓት ከፍተኛ የአቅርቦት ችግር አለበት፡፡ የቅበላ አቅማችን ከዓመት ዓመት እያደገ ቢመጣም ያሉት የመማሪያ ክፍሎች፣ በከባድ ሁኔታ ደግሞ የመኝታ ክፍሎች እጥረት፣ ቀድሞ ሜዳ የነበሩ በአሁኑ ሰዓት ባሉን ኮሌጆች አካባቢ ሁሉ ከተማ መስፋፋት፣ ኢላይብረሪ፣ አለመኖር አጋዥ የሆኑ የመማሪያ ቁሳቁሶች እጥረት እነዚህ ከፍተኛ ችግሮቻችን ናቸው፡፡ በትንሹ እነዚህ ችግሮች ቶሎ መፈታት ካልቻሉ ለሚቀጥለው ዓመት ለምንቀበላቸው ሠልጣኞች ጋር እንኳን ከባድ ነው የሚሆንብን፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሌጁ በሚቀጥሉት ዓመታት ምን ለመሥራት አስቧል?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- ኮሌጁ ሲቋቋም ዓላማ እና ተልዕኮ አለው፡፡ ከተልዕኮው ደግሞ ዕቅዱ ይመነጫል፡፡ በዚህም ከ2010 ዓ.ም. የፖሊስ ሳይንስ ትምህርት በትንሽ ተማሪዎች የዲግሪ ፕሮግራም መጀመር፣ የቅበላ አቅሙን በማሳደግ 10,000 አዳዲስ የፖሊስ አባላትን ለማሠልጠን ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ በክልሉ የሚታየውን የመረጃ ሰብሳቢ ባለሙያ እጥረትን ለመቅረፍ የሚሠራ ይሆናል፡፡ ሌላው በአባሎች ላይ የሚታየውን የሕክምና አገልግሎት ችግር ለመቅረፍ በአቅራቢያቸው ቀላል ሕክምና የሚሰጧቸውን ባለሙያዎች በሚቀጥለው ዓመት ማስተማር ለመጀመር ለመንግሥት ያቀረብነው ጥያቄ ቃል በተገባልን መሠረት ቶሎ የሚፈጸም ከሆነ በክልሉ ያሰብነውን ዘመናዊና ተደራሽ የፖሊስ እንዲሁም የፍትሕ አሰጣጥ አገልግሎት በሰፊው ለመሥራት ዝግጁ ሆነን እየጠበቅን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀን ለሁለተኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡ ለእርሶ ምን ስሜት ይሰጥዎታል?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- ፖሊስ 365ቱንም ቀን በሥራ ነው የሚያሳልፈው፡፡ ከዚህ ቀን ውስጥ ደግሞ አንዱ ፖሊስ የሚታሰብበት ቀን ሲሆን፣ ለሞራልም ለሥራም ተነሳሽነት ደስ ይላል፡፡ ሌላው ፖሊስ ማለት ሕዝብ ነው፡፡ ወንጀልን የሚፀየፍ ሕዝብ ፖሊስ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ይህ ባህል የሁላችንም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መልካም በዓል ለሁላችንም ለማለት እወዳለሁ፡፡ ግሮጠ

 

Standard (Image)
Viewing all 290 articles
Browse latest View live