Quantcast
Channel: ርዕሰ አንቀጽ
Viewing all 290 articles
Browse latest View live

‹‹የማዳበሪያ ተፅዕኖን ለማየት ቅድሚያ በአፈርና ውኃ ጥበቃ ላይ መሠራት አለበት››

$
0
0

ዶ/ር ጠና ዓላምረው፣ የወተር ኤንድ ላንድ ሪሶርስ ሴንተር ምክትል ዳይሬክተር

ዓመታት እየቆጠረ ኢትዮጵያን ከሚያጋጥማት የድርቅ ችግር መከላከል ከሚያስችሉ ተግባራት መካከል የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ይገኝበታል፡፡ አርሶ አደሩም ከራሱ ፍጆታ አልፎ ገበያ ተኮር የሆነ ምርት ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ማበረታታት ሌላው ተግባር ነው፡፡ የወተር ኤንድ ላንድ ሪሶርስ ሴንተር በእነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ይሠራል፡፡ ዶ/ር ጠና ዓላምረው የወተር ኤንድ ላንድ ሪሶርስ ሴንተር ምክትል ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግራቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ የተቋቋመው መቼ ነው? እንቅስቃሴውስ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ጠና፡-ማዕከሉ የተቋቋመው በአገሪቱ ውኃና መሬት ሀብት ዙሪያ ያለውን መረጃ ለማሰባሰብና ጥቅም ላይ ለማዋል ታስቦ ነው፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ሶይል ኤንድ ወተር ኮንሰርቬሽን ፕሮግራም በ1973 ዓ.ም. ነበር የተጀመረው፡፡ በ2003 ዓ.ም. ደግሞ ማዕከሉ በኢትዮጵያና በሲውዘርላንድና መንግሥታት መካከል በሁለትዮሽ ፕሮጀክት መልክ እንደገና ተቋቋመ፡፡ ከ2008 ዓ.ም. መጀመሪያ ወር ጀምሮም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንዱ አካል ሆኗል፡፡ ሁለት ዓብይ ሥራዎችንም ያከናውናል፡፡ አንደኛው መረጃዎችን ማመንጨት ወይም ምርምር መሥራት ነው፡፡ ምርምሩ የሚሠራው የተራቆተው የአገሪቱን መሬት መልሶ ለማበልፀግ ነው፡፡ ሁለተኛው ዓይነት በደለል የሚሞሉ የውኃ አካላትን ለመጠበቅ የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ከምርታማነት ጋር የተገናኙ ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ በሰሜን ጎንደር ከሰሜን ተራራ ጀምሮ ጎጃም፣ ደጀንና ደምበጫ አካባቢዎች፤ በሐረሪ ክልል፣ ኢሊአባቦራ መቱ አካባቢ ያሉትን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ወደ 11 የሚጠጉ ነባር የአፈርና ውኃ ምርምር ጣቢያዎች አሉን፡፡ ከዚህም ሌላ አዳዲስ ጣቢያዎችን በቅርቡ አቋቁመናል፡፡ እነሱም የሚገኙት በባሌ ዞን ዲንሾ፣ በደሎመናና አንፈቶ ደሀዋ አካባቢዎች ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከሉ በመሬትና በውኃ ሀብት ዙሪያ መረጃ ያሰባስባል፡፡ ከዚህ አኳያ መረጃዎቹ ምን ያሳያሉ?

ዶ/ር ጠና፡-በመሬትና በተጠቃሚው መካከል ያለውን ሁኔታ ማስታረቅ ብንችል መሬት የሰጠናትን ነገር እጥፍ አድርጋ ልትመልስ ትችላለች፡፡ በመራቆት ደረጃ ሲታይ በምርታማነት ላይ ከአፈር መሸርሸር ጋር በተገናኘ ከባድ የሆነ ችግር አለ፡፡ ነገር ግን በትግራይና በአማራ ክልሎች መሻሻሎች ይታያሉ፡፡ በተረፈ በተለይ የአፈር መሸርሸርና የደለል ችግራችን የከፋ ነው፡፡ አንድ ሐይቅ በደለል መሞላቱ ውኃ የመቋጠር አቅሙን ይቀንሰዋል፡፡ በደለል መሞላትን ለመከላከል በተወሰኑ አካባቢዎች የሚታየው እንቅስቃስ ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም እንደ አገር ሲታይ ለረዥም ጊዜ ብዙ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ባልተከናወነበት ቦታ ላይ ማዳበሪያ መጨመር ትርጉም የለውም፡፡ ማዳበሪያ በምርታማነት ላይ ያለውን ተፅዕኖ ለማየት መጀመሪያ መሠራት ያለበት የአፈርና የውኃ ጥበቃ ላይ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እዛው ያለው አፈር ተከልቶ  ማዳበሪያውንም ይዞት ይሄዳል፡፡ ስለዚህ ማዳበሪያ በምርታማነት ላይ ያለውን ለውጥ ለማየት መጀመሪያ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ላይ መሥራት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት ይካሄድ የነበረው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ምን ይመስላል? የበፊቱ አሠራር የሚፈለገውን ለውጥ ያላመጣው ለምንድነው?

ዶ/ር ጠና፡-የቀድሞው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ከላይ ወደታች ወይም የእዝ አካሄድ ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ሕዝቡ አተገባበሩን በአግባቡ በባለቤትነት እንዲቀበለው አላስቻለም ተብሎ ይነገራል፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ ሥራው ከላይ ወደታች ከሚሆን በሚል ‹‹ኢንተግሬትድ ፓርቲሲፖቶሪ ወተር ሼድ ማኔጅመንት›› ማለትም ማኅበረሰቡን ያሳተፈና የተቀናጀ ውኃ ገብ ሥፍራዎችን ማስተዳደርና መጠበቅን ማስተዋወቅ ተጀመረ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው ለውጥ መምጣት የጀመረው፡፡ ነገር ግን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሥራት ከተጀመረ በኋላ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራው አገር አቀፍ እንቅስቃሴ ሆኗል፡፡ በምግብ ለሥራ ሳይሆን እያንዳንዱ ገበሬ የራሱን መሬት መጠበቅ አለበት ወደሚለው እየተሄደ ነው፡፡ ለምሳሌ አማራ ክልል ተፋሰሶችን በጋራ የማልማትና የመጠበቅ ሕግ በቅርቡ አውጥቷል፡፡ በዚህ ለውጥ እየታየ ነው፡፡ ብዙ ቦታዎች ላይ ግጦሽ ቀርቷል፡፡ ልቅ ግጦሽ ሲከለከል በጓሮ የከብት መኖ የሚለማበትን መንገድ ማመቻቸት ግድ ይላል፡፡ በዚህ መልኩ ከቀጠለ የአገሪቱ የግብርና ሥነ ምህዳር ይቀየራል፡፡ ፈጣን ለውጦችም ሊታዩ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በክትትል ረገድ የማዕከሉ ሚና ምን ይመስላል?

ዶ/ር ጠና፡-የምርምር ውጤቶች ከኤክስቴንሽን ሥራዎች ጋር እንዲሠሩ እናደርጋለን፡፡ ቴክኒሽያንም እንመድባለን፡፡ ተፋሰስን የማልማት፣ ከንክኪ ነፃ የሆኑ መሬቶችን የመንከባከብ ሥራው የማኅበረሰቡ ድርሻ ነው የማዕከሉ ሚና የቀሩ ቴክኖሎጂዎች አሉ ሲባል ይዞ ለመግባት ወይም ለማቅረብ መሞከር ነው፡፡ አነስ ያለ አቅም ያላቸውን ትራክተሮችንና በአንድ ከብት በመሳብ አገልግሎት የሚሰጡ የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን እንሞክራለን፡፡ ትልቁ ዓላማችን ግን በተፈጥሮ ሀብቱና በሰው መካከል ያለውን ግንኙነት ጤናማ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የማዕከሉ ዋናውና ትልቁ ሳይት የትኛው ነው?

ዶ/ር ጠና፡-ትልቁ ሳይታችን የዓባይ ተፋሰስ ነው፡፡ ፕሮጀክቱም ዓባይ ተፋሰስ ላይ ነው ትኩረት ያደረገው፡፡ ወደ ገናሌ ዳዋ ተፋሰስ የተንቀሳቀስነው በ2006 ዓ.ም. ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ድርቅን ለመከላከልና አርሶ አደሩ ምርታማ እንዲሆን ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ዶ/ር ጠና፡-ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝቦች 85 ከመቶ ያህሉ አርሶ አደር ነው፡፡ ይህም አርሶ አደር የሚያመርተው ብዙውን ጊዜ ለራሱ ፍጆታ ያህል ነው፡፡ በአየር ለውጥ ሳቢያ እርሻው ቢስተጓጎል ችግር ውስጥ ነው የሚገባው፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ችግር ለመላቀቅ ከፍጆታው በላይ ማምረት ይኖርበታል፡፡ ይህ ዓይነቱ አመራረት ለገበያ የሚያወጣውና በጎተራ የሚያስቀምጠው እንዲኖረው ያስችላል፡፡ ድንገት ድርቅ ቢከሰት ዕርዳታ እስከሚደርስለት ድረስ በጎተራ ያከማቸውን በመጠቀም ለተወሰነ ጊዜ ችግሩን ለመቋቋም ያስችላል፡፡ ትልቁ ነገር ግን አርሶ አደሩ እየተበረታታ ወደ ገበያ ተኮር ምርታማነት እንዲሄድ ካስቻለ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ፈር ቀዳጁ ትምህርት ነው፡፡ የጤናና የትምህርት ሥርዓቶቹ ከተጠናከሩ ቢያንስ ማንበብና መጻፍ የሚችልና ሌላውን ዓለም በተሻለ መረዳት የሚችል ማኅበረሰብ መፍጠር ይቻላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ አሁን ያለንበትን ችግር በአንድ ወይም በሁለት ትውልድ ጊዜ ውስጥ የመቀየር ተስፋ ይኖራል፡፡

Standard (Image)

‹‹ሆስፒታል ያቋቋምኩት ከሕዝቡ በመጣ ጉትጎታ ነው››

$
0
0

ጤና መኮንን ዮሐንስ ፈንታዬ፣ የሞጆ ሳማ ሰንበት የግል ሆስፒታል መሥራች፣ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ

ጤና መኮንን ዮሐንስ ፈንታዬ የሞጆ ሳማ ሰንበት የግል ሆስፒታል መሥራች፣ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ጎጃም አዊ ዞን አዲስ ቅዳሜ በተባለው ከተማ ተወለዱ፡፡ በእንጅባራ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን፣ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ደብረማርቆስ ከተማ መጨረሳቸውን ይናገራሉ፡፡ በወቅቱ ደብረብርሃን መምህራን ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት በመምህርነት፣ በጎንደር ጤና አጠባበቅ ኮሌጅ (ጎንደር ዩኒቨርሲቲ) በጤና መኮንንነት ሠልጥነዋል፣ በዕድገት በኅብረት ዘመቻም ተሳትፈዋል፡፡ በሥራ ዓለም ኢሊአባቦራ ውስጥ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት አገልግለዋል፣ በአቃቂ ጨርቃ ጨቅርና በቆቃ ቆዳ ፋብሪካዎች በሕክምና ሙያ ሠርተዋል፡፡ ባለትዳርና የስድስት ልጆች አባት የሆኑትን ጤና መኮንን ዮሐንስ ፈንታዬን፣ በሆስፒታሉ ምሥረታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የሞጆ ሳማ ሰንበት ሆስፒታልን ለማቋቋም ያነሳሳዎት ምንድነው?

ጤና መኮንን ዮሐንስ፡-ቆዳ ፋብሪካ ተቀጥሬ ስሠራ፣ ፋብሪካው በአዳማ ከተማ ቤት ተከራይቶልኝ እኖር ነበር፡፡ በዛን ዘመን በሞጆ ከተማ ምንም ዓይነት የመንግሥትም ሆነ የግል ክሊኒክ አልነበረም፡፡ ከመኖሪያ ቤት ለሥራ ወደ ፋብሪካው ስመላለስ ሞጆ ላይ ወባ ተንሰራፍቶ ለአጨዳ የሚመጣ ሰው በአብዛኛው ይሞት ነበር፡፡ በአራት ክሎሮኪን መድኃኒት ሕይወቱ ሊተርፍ ይችል የነበረው ሁሉ በወባ ረግፎ መገኘቱ ልቤን ነካው፡፡ እገሌ የት ሄደ? ብዬ ስጠይቅ ‹እሱ እኮ ሞተ› ይሉኛል፡፡ ምን ሆኖ? ስላቸው ‹በወባ› የሚል መልስ የተለመደ ነበር፡፡ ሰው የሕክምና አገልግሎት ያገኝ የነበረው ወይ ቢሾፍቱ አለበለዚያም አዳማ ሄዶ ነው፡፡ ሁኔታዎች በእንዲህ ላይ እንዳሉ ከመኖሪያ ቤቴ ወደ ፋብሪካው ከዚያም ወደ ቤቴ ያመላልሰኝ የነበረው ሰርቪስ ቆመ፡፡ በዚህም የተነሳ ከአዳማ እየተመላለሱ መሥራት አድካሚ ሆኖ ስላገኘሁት፣ ኑሮዬን ሞጆ ከተማ ላይ አደረኩ፡፡ እንደገባሁም በተከራየሁበት ቤት ግቢ ውስጥ መንደርተኛው በወባ በሽታ ለሕልፈተ ሕይወት እየተዳረገ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ የሕክምና ባለሙያ ሆኜ ሰው በወባ በየጊዜው ሲሞት ዝምብዬ ከማየት ይልቅ ለምን አንድ አነስተኛ ክሊኒክ አልከፍትም የሚል ሐሳብ አደረብኝና ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ ጀመርኩ፡፡ በዚህም የተነሳ ቀበሌ አስፈቅጄ ቦታ ሰጠኝ፡፡ አንድ ጤና ረዳት፣ አንድ ላቦራቶሪ ቴክኒሺያንና እኔ ሆነን ሁለት ክፍሎች ያሉት ክሊኒክ ከፈትን፡፡ የምርመራ አገልግሎት የምንሰጠውም ለካርድ ሁለት ብር ብቻ በማስከፈል ሲሆን መድኃኒቱን ግን ታካሚዎቹ ከየትኛውም ፋርማሲ ይገዛሉ፡፡ ቀስ በቀስ በዚሁ ክሊኒክ መርፌ መውጋት ጀመርን፡፡ ቁስለኛም ሲመጣ ማከምን ተያያዝነው፡፡ በዚህም የተነሳ በከተማው የሚገኙ ወደ አራት የሚጠጉ ፋርማሲዎች ለወረዳው ጤና ጽሕፈት ቤት ከሰውን ለጊዜው አስቆሙን፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተስ ምን ዕርምጃ ወሰዳችሁ?

ጤና መኮንን ዮሐንስ፡-ዞን መስተዳደር ጤና መምሪያ ሄድኩና ሰው በወባ በሽታ እያለቀ ነው፡፡ ፋርማሲዎቹ ያቀረቡት ክስ አግባብ አይደለም ብዬ አመለከትኩ፡፡ የመምሪያ ኃላፊውም ክሊኒክ አቋቁመህ የሕክምና አገልግሎት መስጠት ከጀመርክ ጥሩ ነው ብለው የተዘጋው ክሊኒኬ ተከፈተ፡፡ ቀን ሁላችንም መደበኛውን ሥራችንን ስለምንሠራ ሦስታችንም የሕክምና አገልግሎት እንሰጥ የነበረው ማታ ማታ ብቻ ነው፡፡  ማታ ማታ ብቻ በሰጠነው አገልግሎት ብዙ የወባ ሕሙማንን ረዳን፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ ግን የታካሚው ቁጥር እየበዛ ስለሄደ፣ በአግባቡ ማስተናገድ ተሳነን፡፡ በዚህም የተነሳ ቦታ ይሰጠኝና ትንሽ ቤት ልሥራ ብዬ አመለከትኩ፡፡ 588 ሜትር ካሬ ቦታ ሰጡኝ፡፡ በዚህም ቦታ ላይ በሳማ ሰንበት ስም የሚጠራ መካከለኛ፣ ቀጥሎ ደግሞ ባለ አንድ ፎቅ ከፍተኛ ክሊኒክ አቋቋምኩ፡፡ በዚህም ክሊኒክ ለመስተናገድ የሚመጡት ሕሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ፣ በአንጻሩ ደግሞ ከፍተኛ ክሊኒኩ እየጠበበ ሲመጣ፣ ሰፋ ባለ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል ሆስፒታሉን ገነባሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሞጆ ሳማ ሰንበት ሆስፒታልን ለማቋቋም ምን ያህል ገንዘብ እንደፈጀና የሕክምና ባለሙያዎችን ስብጥር በተመለከተ ቢያብራሩልን?

ጤና መኮንን ዮሐንስ፡-ለሆስፒታሉ ግንባታ የተሰጠኝ ቦታ ከ9270 ሜትር ካሬ በላይ ነው፡፡ የሆስፒታሉ ዲዛይን የተሠራው በሦስት ምዕራፎች በመከፋፈል ነው፡፡ ይህም ማለት አንደኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ (ፕራይመሪ) ደረጃ፤ በሁለተኛው ምዕራፍ አጠቃላይ (ጄኔራል)፤ በሦስተኛው ምዕራፍ ሪፈራል ሆስፒታል እንዲሆን ተደርጎ ነው፡፡ ከቦታው ውስጥ አንድ ሦስተኛ በሆነው ስፍራ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ገንብተናል፡፡ ሆስፒታሉም ባለ አንድ ፎቅ ሲሆን በፎቁ ላይ ያሉትን ክፍሎች የምንጠቀመው ለአስተዳደር ሥራ ነው፡፡ በምድር ያሉትን ክፍሎች ለታካሚዎች አድርገናል፡፡ በእነዚህም ክፍሎች 44 አልጋዎች አሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜም የጥርስ፣ የቆዳ፣ የማሕፀን፣ የውስጥ ደዌና የክስሬይ ራዲዮሎጂስቶች ስፔሻሊስቶች ያሉን ሲሆን፣ ሆስፒታሉ ተጨማሪ 73 ልዩ ልዩ የሕክምና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችንም ይዟል፡፡ በየክፍሉ ያሉት አልጋዎችና የኃይል ማመንጫው ጄኔሬተር በሙሉ ዲጂታል ናቸው፡፡ ታካሚው ነርስ ወይም ሌላ አስታማሚ ሳይጠይቅ አጠገቡ ባለው የርቀት መቆጣጠሪያ አማካይነት አልጋውንና ትራሱን ከፍና ዝቅ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ድንገት የኃይል መቋረጥ ቢያጋጥም ጄኔሬተሩ ሰኮንድ ሳይቆይ ኃይል ማስተላለፍ ይጀምራል፡፡ ሆስፒታሉን ለማቋቋምና በዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎች ለማደራጀት ወደ 30 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ተመርቆ የተከፈተው ሰኔ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. ሲሆን፣ የተሟላ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ደግሞ ካለፈው ዓመት ወዲህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የትኞቹን የሕክምና አገልግሎቶች ትሰጣላችሁ? ለሕክምና ከሚመጡ ሕሙማን መካከል በአብዛኞቹ ምን ዓይነት በሽታ ያደረባቸው ናቸው?

ጤና መኮንን ዮሐንስ፡-በሰብ ስፔሻሊስት ወይም በኒሮሎጂስት የሚሠሩ ካልሆነ በስተቀር በጄኔራል ሆስፒታል ደረጃ የሚሰጡ የሕክምና አገልግሎቶችን ሁሉ እንሰጣለን፡፡ ሆስፒታሉ ከተቋቋመ ሁለት ዓመቱ ነው፡፡ የመጀመሪያውን ዓመት በአብዛኛው ልዩ ልዩ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን በማሟላት አሳልፈናል፡፡  ወደ ሕክምና ሥራ በሙሉ አቅማችን ከገባን አንድ ዓመት ሆኖናል፡፡ እስካሁን ለሕክምና ከሚመጡት ሕሙማን መካከል አብዛኞቹ ተላላፊ በሽታዎች ያደረባቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ታይፎድና የተቅማጥ በሽታዎች ይበዛሉ፡፡ የመተንፈሻ አካል ችግርም በሁለተኛ ደረጃ ጎልቶ ይታያል፡፡ ወባና የሥራ ላይ አደጋም በርከት ይላል፡፡ በከተማው ወደ 15 የሚጠጉ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ የሕክምና ኮንትራታቸው በዚህ ሆስፒታል ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በአራት አቅጣጫዎች ከተማውን አቋርጦ በሚያልፈው አውራ ጎዳና የትራፊክ አደጋ ሲደርስ፣ የሚመጣው ወደዚሁ ሆስፒታል ነው፡፡ በተለይ የክፍያ ወይም ፈጣን መንገድ ከተሠራ ወዲህ የሚደርሰው የመኪና አደጋ ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ከአደጋው ባሻገር የአደጋው ክብደት ወይም ግዙፍነት በጣም ከባድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን በመወጣት ረገድ ምን እየሠራችሁ ነው?

ጤና መኮንን ዮሐንስ፡- ሆስፒታላችን ገና በክሊኒክና በከፍተኛ ክሊኒክ ደረጃ እያለ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በወባና በኤችአይቪ/ኤድስ ዙሪያ ሕዝቡን ለማንቃትና ራሱን ከበሽታዎች እንዲከላከል ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በሳማ ሰንበት ከፍተኛ ክሊኒክ ስም 12 አባላት ያሉት የኤችአይቪ ክበብ በማቋቋም፣ ለዚሁ ሥራ የሚያገለግል በየወሩ አምስት ሺሕ ብር በመመደብ፣ አምፕሊፋየርና ስፒከር በመግዛት በከተማው፤ በየእምነት ተቋማት፣ በየፋብሪካዎችና በየትምህርት ቤቶች ተዘዋውረን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተናል፡፡ ከሞጆ ከተማ ወጣ ብለን መቂ፣ ዓለም ጤናና ምንጃር ሸንኮራ ድረስ ተጉዘን ተመሳሳይ ሥራ አከናውነናል፡፡ በአሁን ደረጃ ደግሞ ከሌሎች ጤና ጣቢያዎችና ክሊኒኮች አልትራሳውንድና ኤክስሬይ የሚያስፈልጋቸው ሕሙማን በአቅም ማነስ ምክንያት ተቸግረዋል የሚል መረጃ በደረሰን ቁጥር፣ ወደ ሆስፒታሉ መጥተው አገልግሎቱን በነፃ እንዲያገኙ እንዲሁም የአረጋውያን ማኅበር አባል የሆኑና ሕክምና የሚያስፈልጋቸው አረጋውያን በነፃ እንዲታከሙ እያደረግን ነው፡፡ የደሃ፣ ደሃ ከሆኑ ደግሞ የመድኃኒትም ዕርዳታ ይደረግላቸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዕርዳታ የሚደረግላቸው ከማኅበሩ ወይም ከቀበሌ አስተዳደር የአቅም ማነስ ችግር አለባቸው የሚል ደብዳቤ ሲያመጡ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የግል ሆስፒታል እንደመሆኑ መጠን ሁሉንም አገልግሎት የሚሰጠው በክፍያ ነው፡፡ ክፍያው የአካባቢውን ነዋሪዎች አቅም ያገናዘበ ነው?

ጤና መኮንን ዮሐንስ፡- በመጀመርያ ደረጃ ይህን ሆስፒታል ያቋቋምኩት ከሕዝቡ በመጣ ግፊትና ጉትጎታ ነው፡፡ የእኔ ጥረት ቢኖርም ሕዝቡ ሆስፒታል ለምን አታቋቁምም? እያለ ይገፋፋኝ ነበር፡፡ ግንባታውን ስጀምር ለምን ቶሎ አያልቅም? እያሉ ይጉተጉቱኝ ነበር፡፡ ሕዝቡም ጎትጉቶኝ ያቋቋምኩት ሆስፒታል የሚጠይቀው ክፍያ የሕዝቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ነው፡፡ በአነስተኛም ሆነ በከፍተኛ ከተማ በአንድ ስፔሻሊስት ለመመርመር ከፍ ሲል 100 ብር አነሰ ሲባል ደግሞ 50 ብር ለካርድ ይከፈላል፡፡ ከዚህ በታች የትም እንደሌለ ግልጽ ነው፡፡ በሆስፒታላችን ግን ለምርመራ ካርድ ለማውጣት በቅርቡ ነው 40 ብር ያደረግነው፡፡ ቀደም ሲል ግን 30 ብር ነበር፡፡ ሌሎቹም የላብራቶሪ፣ ኤክስሬይና የአልትራሳውንድና ክፍያዎች ከሌሎች የሕክምና ተቋማት ሲነፃፀሩ ዝቅተኛ ናቸው፡፡ በአልትራሳውንድ ልዩ የልብ ምርመራ 250 ብር ነው የምናስከፍለው፡፡ ለስኳር ሕሙማን ምርመራ 10 ብር ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለሆስፒታሉ መቋቋም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትና ከአንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተደረገልዎት እገዛና ትብብር አለ?

ጤና መኮንን ዮሐንስ፡- የከተማው አስተዳደር ሳያመላልሰኝ ቦታ በመስጠት፣ ላቅ ያለ እገዛና ትብብር አድርጎልኛል፡፡ የዞኑ መስተዳደር ደግሞ ሆስፒታሉን እንድገነባ በማበረታታት ከጎኔ ቆሟል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮም ሥራውን ለመጀመር የሚያስችል ፍቃድ በወቅቱ በመስጠት ትብብር አድርጎልኛል፡፡ ቲቢና ኤችአይቪ/ኤድስን ለመከላከል ባካሄድነው እንቅስቃሴ ዩኤስኤአይዲ 30 ሺሕ ብር የሚያወጣ ዘመናዊ ማይክሮስኮፕ፣ እንዲሁም ስዊድን ውስጥ የሚገኘውና ሂውማን ብሪጅ የተባለ ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት ልዩ ልዩ የሕክምና መገልገያዎችና ሌሎችንም ቁሳቁሶች በነፃ በመስጠት ከፍተኛ ድጋፍ አበርክተውልኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ የሚገኙ ሆስፒታሎች ደረጃ ወጥቶላቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ያልተሟላና ለታካሚው የማያመች ሆስፒታል ቀይ ቀለም ያለው ፍቃድ፣ የተወሰነ ጉድለት የሚታይበት ሆስፒታል ቢጫ፣ የተሟላና ለታካሚዎች ምቹ ሆኖ የተገኘው ሆስፒታል ደግሞ አረንጓዴ ቀለማት ያላቸው ፍቃድ ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ እርስዎ ያቋቋሙት ሆስፒታል በየትኛው ደረጃ ተካቷል?

ጤና መኮንን ዮሐንስ፡- አረንጓዴ ቀለም ባለው ፍቃድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያለውን ፕራይመሪ ሆስፒታል ወደ ጠቅላላ ሆስፒታል ለማሳደግ ምን እየሠራችሁ ነው?

ጤና መኮንን ዮሐንስ፡- አሁን ባለው ደረጃ መሠረት አንድ ጄኔራል ሆስፒታል ለመባል፣ እኛ ካሉን ስፔሻሊስት ሐኪሞችና አልጋዎች መጨመር አለብን፡፡ ከዚህ አኳያ አሁን በሥራ ላይ ያለውን ሆስፒታላችንን ወደ ጠቅላላ ሆስፒታል ከፍ ለማድረግ አንድ የሕፃናት ስፔሻሊስትና ስድስት ተጨማሪ አልጋዎች ያስፈልጉታል፡፡ ይህንንም በቅርቡ አሟልተን ወደ ጠቅላላ ሆስፒታል ለማሳደግ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የደርግን ሥርዓት በመቃወም በረሃ ገብተው ነበር፡፡ ሆኖም እስከመጨረሻው አልዘለቁም፡፡ ምክንያቱ ምን ነበር?

ጤና መኮንን ዮሐንስ፡- ጎንደር ጤና አጠባበቅ ኮሌጅ የአራተኛ ዓመት ትምህርቴን አቋርጨ ነበር በረሃ የገባሁት፡፡ ከ1969 እስከ 1973 ዓ.ም. ድረስ በለሳ፣ ጠልመት፣ ወልቃይትና ጋይንት ድረስ እንቀሳቀስ ነበር፡፡ በግና ፍየል ነጋዴ ሆኜ መንግሥት በሚያስተዳድርበት ሥፍራ እየገባሁ መረጃ እሰበስብ ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ በሕክምና ሙያም ሳገለግል ቆይቼአለሁ፡፡ በ1973 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የኢሕአፓ ዕርምት እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ የአንድ ሳምንት ስብሰባ ተካሄደ፡፡ በዚህም ስብሰባ ኢሕአፓ መስመሩን ስቶ የከተማ ትግል ማካሄዱ ልክ አይደለም፣ በዚህም በርካታ ወጣቶችን አስጨርሷል ተብሎ ተነቀፈ፡፡ ከስብሰባውም በኋላ መከፋፈል ተፈጠረ፡፡ የተወሰኑት እዛው በረሃ እንቆያለን አሉ፡፡ ሌሎችም ወደ ትግራይ ሄደው ከሕወሓት ጋር ተቀላቀሉ፡፡ እኩሉ ሱዳንና አሜሪካ ሲወጣ፣ ከፊሉ ደግሞ እጁን ለደርግ በሰላም ሰጥቶ ገባ፡፡ ከሰጡት ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- እጅዎን በሰላም ሰጥተው ከገቡ በኋላ ምን ገጠመዎት?

ጤና መኮንን ዮሐንስ፡- እንደገባሁ የሁለት ወር ተሃድሶ ተሰጠኝ፡፡ የጤና መኮንንነት ትምህርቴን ልጨርስ ሦስት ወራት ሲቀረኝ ነበርና ለትግል በረሃ የገባሁት፣ ትምህርቴን ለመቀጠል ብጠይቅ አምስት ዓመት ከትምህርት ተለይቼ በመክረሜ ችግር ገጠመኝ፡፡ በኋላም በእያንዳንዱ ዲፓርትመንት ለሦስት፣ ሦስት ወራት ያህል በመቆየት ለአንድ ዓመት እንደገና የትምህርት ላይ ልምምድ አድርጌ እንድመረቅ ተወሰነልኝ፡፡ ትምህርቴንም ጨርሼ ለመመረቅ በቃሁ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከልጆችዎ መካከል የእርስዎን ሙያ የተከተለ አለ?

ጤና መኮንን ዮሐንስ፡- ሁለቱ ሐኪሞች ናቸው፡፡ ሌሎቹ ሁለቱ ደግሞ ፋርማሲስትና ነርስ ናቸው፡፡

 

 

Standard (Image)

‹‹የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ አስተዳደራቸውን ማስተካከል፣ ሕጉን ማወቅና በደንብ መተግበር አለባቸው››

$
0
0

ወ/ሮ ፋንታዬ ገዛኸኝ፣ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር
ወ/ሮ ፋንታዬ ገዛኸኝ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉት የመጀመርያና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተከታተሉት ጉሬ ከተማ ሲሆን፣ በመምህርነት ሙያ ሠልጥነዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በሕግ የመጀመርያ ዲግሪ፣ በከተማ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያችውን ሠርተዋል፡፡ በሥራ ዓለምም በመምህርነት ከአሥር ዓመት በላይ አገልግለዋል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለተኛና ሦስተኛው ዙር ተመርጠው ለአሥር ዓመታት ያህል ሠርተዋል፡፡ በእነዚህም ዓመታት በምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ መከላከያና ደኅንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል፣ እንዲሁም የሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ፋንታዬን ታደሰ ገብረማርያም በበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ማኅበራትና ኅብረቶች እንቅስቃሴና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ምን ያህል የበጎ አድራት ድርጅቶች፣ ማኅበራትና ኅብረቶች እንዳሉ፣ የገቢ ምንጮቻቸውና የሚያከናውኑትን የተግባር በጥቅሉ ቢገልጹልን?
ወ/ሮ ፋንታዬ፡- በመላ አገሪቱ ከ3,000 በላይ የሚሆኑ ልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ማኅበራትና ኅብረቶች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል 2,109 ያህሉ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሲሆኑ፣ 371ቱ ደግሞ የውጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ናቸው፡፡ ሌሎች 333 የኢትዮጵያ ማኅበራት፣ 107 የኢትዮጵያ በጎ አድራት ድርጅቶች፣ 89 የኢትዮጵያ ነዋሪዎች ማኅበራት፣ 53 ኅብረቶች (ኮንሰርቲየም) እና 46 የውጭ ጉዲፊቻ ድርጅቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅቶችን ያቋቋሙት ወይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወይም ኢትዮጵያውያን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ገቢያቸው በውጭ በጀትና እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ ይኽም ማለት 90 እና ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን ገቢያቸውን ከውጭ ማግኘት ይችላሉ፡፡ የሚደግፉትም ልማትን ብቻ ነው፡፡ የመብት ጉዳይ ላይ ሊሠሩ አይችሉም፡፡ በተረፈ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ ማኅበራት፣ የኢትዮጵያ ብዙኃን ማኅበራትና የኢትዮጵያ የሙያ ማኅበራት ከውጭ የሚያገኙት የገቢ መጠን አሥር በመቶ ያህሉን ብቻ ሲሆን፣ ቀሪው 90 በመቶ የሚሆነውን ገቢ የሚያገኙት ግን ከአገር ውስጥ ነው፡፡ ከልማት ሥራ ባሻገር በመብት ጉዳይ ላይም ይሠራሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ለምሳሌ ወላጅ አልባና ጎዳና ተዳዳሪ ልጆችን የሚያሳድግ ድርጅት በፈንድ እጥረት ቢዘጋ የልጆቹ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?
ወ/ሮ ፋንታዬ፡- ቤተሰብ አካባቢ ያሉት ልጆች ለጊዜው ላይቸገሩ ይችላሉ፡፡ በእጁ ያሉትን አሰባስቦ በማዕከል ደረጃ የሚያሳድግ ድርጅት ከሆነ ግን እንዲያው በቀላሉ ወደ ተጠቀሰው ውሳኔ አይሄድም፡፡ የመዘጋት ውሳኔ ላይ ሲደረስ በቅድሚያ ለኤጀንሲው ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ደግሞ ኤጀንሲው የራሱን ቅድመ ዝግጅት ማከናወን ይኖርበታል፡፡ በዚህም ቅድመ ዝግጅት ልጆቹን ከነቀሪ ገንዘቡና ከነንብረቱ ሊቀበሉ የሚችሉ ሌሎች የጉዲፈቻ ማዕከላት እንዲረከቡ ይደረጋል፡፡ የምናስተላልፈውም ዝም ብለን ሳይሆን በማወዳደር ነው፡፡ ይኽ ማለት ተቋሙን ከነልጆቹ፣ ከነንብረቱና ከነገንዘቡ ጭምር ተረክበው ልጆቹን በጥሩ ሁኔታ እየተንከባከቡ የማሳደጉን ሥራ ማስቀጠል የሚፈልጉ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በማስታወቂያ ይጠራሉ፡፡ በማስታወቂያው መሠረት ፍላጎት ያላቸው ድርጅቶች እየቀረቡ ይመዘገባሉ፡፡ ከተመዘገቡትም መካከል ጥሩ አያያዝ፣ አፈጻጸምና በጀት ያላቸው በግምገማ ይጣራሉ ወይም ይመረጣሉ፡፡ በምርጫው ላሸነፈ ድርጅት ልጆቹን ከነገንዘቡና ከነንብረቱ እናስተላልፋለን፡፡ ማስታወቂያ ወጥቶ የሚጠፋ ወይም የሚቀርብ ድርጅት ከታጣ ቁጭ ብለን እንመካከራለን፡፡ በዚህ ልጆቹን ከፋፍለን ለተለያዩ ድርጅቶች እንሰጣለን አለበለዚያ ሌላ መፍትሔ እንፈልጋለን እንጂ በተአምር ልጆቹ ችግር ላይ አይወድቁም፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፈው ወር መጨረሻ አዳማ ውስጥ ኤጀንሲው ከልማት አጋር አካላት ጋር ባካሄደው ምክክር ላይ 108 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በተለያዩ ምክንያቶች እንደተዘጉ ተገልጿል፡፡ እስኪ በዚህ ዙሪያ ትንሽ ማብራሪያ ቢሰጡበት?
ወ/ሮ ፋንታዬ፡- በዳግም ምዝገባና ከዛም በኋላ ዝም ብለው በስሜት ወይም የበጎ አድራጎት ድርጅትን ዓላማና ግብ ሳይገነዘቡ የተመዘገቡ ብዙ በጎ አድራጎት ድርጅቶች አሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ኮሚቴ አዋቅረን ፋይሎችን የማጥራት ሥራ አከናወንን፡፡ በዚህም ከ95 በመቶ በላይ ይሚሆኑ ዝም ብለው የተመዘገቡና ምንም ሥራ ያልሠሩ ወይም ወደ ተግባር ያልገቡ ድርጅቶች ተገኝተዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ሥራዎቻቸውን እየሠሩ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ዓላማቸውን ማስቀጠል ያልቻሉም በራሳቸው ጥያቄ የተዘጉ ናቸው፡፡ በጣም ጥቂት በሚባል ደረጀ ደግሞ ኤጀንሲው ባካሄደው ክትትል ሥራቸውን በተገቢ ባለመሥራታቸው የተዘጉ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንድ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በልማት ፕሮግራሞቻቸው ሃይማኖትን ጣልቃ እያስገቡ ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል ይባላል?
ወ/ሮ ፋንታዬ፡- እኛ ክትትል እናደርጋለን፡፡ የበጎ አድራጎት ሥራ የሚያከናውኑ የፖለቲካና የሃይማኖት ሥራ ማከናወን አይችሉም፡፡ ሃይማኖት ራሱን የቻለ አደረጃጀት ያለውና በአዋጅም ለሌላ አካል የተሰጠ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የበጎ አድራጎት ሥራ ለመሥራት የሚፈልጉ ኤጀንሲው ዘንድ፤ በሃይማኖት ዙሪያ ለመሥራት የሚፈልጉ ደግሞ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ነው የሚመዘገቡት፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በአዋጅ 621/2001 ይገዛሉ፡፡ እነዛ ደግሞ በወጣው አዋጅ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ነው የሚገዙት፡፡ በበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ አምልኮ የሚያካሂዱም አልፎ አልፎ አግኝተን ማስጠንቀቂያ የሰጠናቸው አሉ፡፡ ሃይማኖት ነክ ሆነው የመጡ የልማት ድርጅቶች ለብቻ ጠርተናቸው ሕጉን በሥርዓት አውቀው ሕጉን ተከትለው የጠራ ሥራ እንዲሠሩ እያደረግን ነው፡፡ እስካሁን ያለው አካሄድ ጥሩ ነው፡፡ እንነጋገራለን፡፡ መተዳሪያ ደንባቸውን እንዲያሻሽሉ አድርገናል፡፡ በፊት ቅይጥ የነበረው መዋቅር ለየብቻ እንዲወጣ አድርገናል፡፡
ሪፖርተር፡- የዓላማ ማስፈጸሚያና አስተዳደራዊ ውጪ ምጣኔ ወይም 30/70 መሠረት ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሳሉ?
ወ/ሮ ፋንታዬ፡- አዋጁ ሲወጣ የተለያዩ አገሮች ልምድ ተወስደው ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣሙ ተደርጓል፡፡ 70/30 የሚጠቀሙ አገሮች እንዳሉ ሁሉ 20/80 የሚጠቀሙ አገሮችም አሉ፡፡ የእነዚህን አገሮች አጠቃቀም ከእኛ አንፃር ስናየው 70 በመቶ ለሕዝብ ጥቅም ማለትም ተቋሙ ለተቋቋመለት ዓላማ የሚያውለው ነው የሚሆነው፡፡ ይኽም ማለት አንድ ተቋም በትምህርት ላይ እሠራለሁ፣ የትምህርት ሽፋኑ ይህን ያህል እንዲደርስ አደርጋለሁ፣ ይህን ያህል ትምህርት ቤት እገነባለሁ ለሚለው 70 በመቶውን እንዲያውል ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ሌላ ምንም የተለየ ነገር የለውም፡፡ ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ የአስተዳደር ጉዳይ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ለዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ደግሞ 30 በመቶ ያህሉን ማዋል አለበት፡፡ አሁን በተቋማት እየታየ ያለው ችግር ግን ሕጉን በደንብ ያለመረዳት ነው፡፡ በደንብ አሠራሩን አውቆ ከመተግበር ይልቅ እንዲሁ አያስኬድምና አይሠራም የሚሉ አሉ፡፡ ወደ ተግባር ገብተው ሥራውን እያካሄዱት ካሉት ተቋማት መካከል ግን አይደለም 70 ከመቶ ያህሉን 80 እና 90 ከመቶ ያህሉን ለዓላማ ማስፈጸሚያ ያዋሉ አሉ፡፡ አዋጁን ተወካዮች ምክር ቤት፣ ደንቡን ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲያወጡ ኤጀንሲው ደግሞ ዘጠኝ መመርያዎችን አውጥቷል፡፡ መመርያዎቹን በዝርዝር አውቆ መጠቀም ይገባል፡፡ ዓላማ ማስፈጸሚያ ምንድነው? የአስተዳደር ወጪ ምንድነው? የሚለው መመርያው ውስጥ ተለይቶ ተቀምጧል፡፡ ይህን አውቆ ያለመፈጸምም አለ፡፡ ዓላማ መሆን የሚገባው አስተዳደር ውስጥ፣ አስተዳደር መሆን ያለበትን ዓላማ ውስጥ ከትተው የሚሠሩ ድርጀቶችም አሉ፡፡ መመርያው ከወጣ ጀምሮ የግንዛቤ ችግሮች እንዳሉ ይታያል፡፡ እንግዲህ በቀጣይ መድረኮችን እያሰፋን ብዥታዎችን የማጥራት ሥራ ማከናወን ግድ ይላል፡፡
ሪፖርተር፡- ኤጀንሲው ባለሙያዎችን የማቆየት ችግር ወይም የአቅም ማነስ እንዳለበት ይታያል፡፡ ይህ በአፈጻጸም ላይ እንቅፋት አይሆንም?
ወ/ሮ ፋንታዬ፡- አዎ፡፡ በአፈጻጸም ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው፡፡ በሥነ ምግባር መከላከያና ቅሬታ ማስተናገጃ ዳይሬክተር በኩል ችግሩ ምንድነው? በሚለው ዙሪያ ያተኮረ ጥናት እንዲካሄድ አድርገናል፡፡ አንድ ሠራተኛ ሲለቅ ዳይሬክቶሬቱ መጠይቅ ሰጥቶ እንዲያስሞላ አድርገናል፡፡ በዚህ መልክ ባካሄድነው የዳሰሳ ጥናት ምንም እንኳን የአስተዳደር ችግር አይኖርም ተብሎ ባይታሰብም አብዛኛው ሠራተኛ ሌላ የተሻለ ደመወዝ እያገኘ እንደሚሄድ ነው የተረዳነው፡፡ ሠራተኛውም እየፈለሰ ያለው የተሻለ መዋቅር ሠርቶ አቅሙን ወደ የሚያበለጽገው የመንግሥት ተቋም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የእኛም ኤጀንሲ በዚህ መንገድ እንዲቃኝ ወይም ከሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የደመወዝ ስኬል ጋር እንዲስተካከል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ጥረት ከተሳካ ደግሞ ትንሽ የተረጋጋ ነገር ሊኖር ይችላል ብለን እናስባለን፡፡ ከዚህ ባለፈ አሁን እያደረግን ያለው ነገር ቢኖር ማስታወቂያዎችን በየጊዜው እያወጣን ክፍተት በታየው ቦታ ላይ የሰው ኃይል መተካት ነው፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 50 ሠራተኞች ለቅቀው በምትካቸው 47 አዳዲስ ሠራተኞችን ቀጥረናል፡፡ አዳዲስ ሠራተኛ ሲገባ ደግሞ ስብሰባ አድርገን በአዋጁ፣ በደንቡና በመመርያዎቹ ላይ ያተኮረ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ከዛ በተረፈ ደግሞ በቡድን ሲሠሩ እየተመካከሩና እየተደጋገፉ እንዲሠሩ እናደርጋለን፡፡ በዚህ ዓይነቱ አካሄድ አንዱ ለሌላው ዕውቀቱን ያካፍላል፡፡ በዚህም ዘንድሮ የተሻለ አፈጻጸም ነው ያለው፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንድ ድርጅቶች ለፕሮጀክቶቻቸው ማስፈጸሚያ የሚያገኙን ገንዘብ በሁለት ይከፍሉና ለራሳቸው አስቀርተው ለእናተ ትንሽ ገንዘብ እንዳገኙ አስመስለው ያቀርባሉ ይባላል? ይህንን የምታጣሩበትና የምትቆጣጠሩበት ዘዴ አለ?
ወ/ሮ ፋንታዬ፡- ፕሮጀክቶች በመጀመርያ በዘርፉ አስተዳዳሪዎች ማለትም ትምህርት ከሆነ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ጤና ነክ ከሆነ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ በአካባቢ ዙሪያ ከሆነ ከአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ጋር መስማማቱ ከተረጋገጠ በኋላ ነው ወደ እኛ የሚመጣው ወይም ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር ስምምነቱን ተፈራርመው ሲመጡ ነው እኛ የምንቀበለው፡፡ እኛ ደግሞ ተቀብለን በአዋጁ መሠረት የሚሄድ ከሆነ ሥራ ላይ እንዲውል እናደርጋለን፡፡ ለዚህም የተበጀተውን በጀት እናውቃለን፣ እንመዘግባለን፣ እንከታተላለን፡፡ ያልከው ነገር ሊኖር ይችል ይሆናል፡፡ በጥቆማና በተለያየ መንገዶች ሲመጣ የምናገኛቸው ነገሮችም ይኖራሉ፡፡ ቢሆንም ግን የሚሾልኩ ነገሮች የሉም አይባልም፡፡
ሪፖርተር፡- በውጭ በጎ አድራጎ ድርጀቶች የሚመደቡ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ሠራተኞች ከ60 ሺሕ እስከ 70 ሺሕ ዶላር የሚጠጋ ደመወዝ ያገኛሉ፡፡ በዛ ላይ ደግሞ የቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርትና የልጆቻቸው ትምህርት ቤት ወጪ ይሸፈንላቸዋል፡፡ ለቤታቸው ጥበቃና ለአትክልተኛ ሁሉ ይከፈልላቸዋል ይባላል፡፡ ይህ ጉዳይ በሕዝብ ስም የሚመጣውን ገንዘብ መልሶ መቀራጨት አይሆንም?
ወ/ሮ ፋንታዬ፡- በዚህ ዙሪያ ኤጀንሲው ከፍተኛ ትግል ነው እያካሄደ ያለው፡፡ ወጪው በጣም የተጋነነ ከሆነ አንቀበልም፡፡ አስተካክላችሁ ኑ እንላቸዋለን፡፡ በተወሰነ መልኩ ከአገሪቷ የመክፈል አቅም ጋር እንዲሆን፣ የሚሰጡ ነገሮች እንዲስተካከሉ እናደርጋለን፡፡ ከወሰዱ በኋላም እንዲመልሱ የምናደርጋቸውም አሉ፡፡ ለደመወዝ ሳይሆን በጎ ፈቃደኞች ነን ብለው ለሚመጡት የምግብ፣ የቤት ኪራይና ሌሎችም ወጪዎች የሚከፈላቸው ሲታይ ከደመወዝ በጣም የሚበልጥበት ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በጎ ፈቃደኛ ነን ብለው ታክስ ያለመክፈል ሁኔታም ይታያል፡፡ ሕጉ ደግሞ ማንም ሰው ካገኘው ገቢ ላይ ለመንግሥት ታክስ እንዲከፍል ያዛል፡፡ ይህንን ሁሉ ላለመክፈል ሲጥሩ ይታያል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ አገራቸው የሚከፈላቸው ደመወዝ እዛው አገራቸው ባንክ ተቀማጭ ይደረግላቸዋል፡፡ ይህንን በተመለከተ አንዳንድ የውጭ ድርጅቶች የሚሉት ነገር ቢኖር በጎ ፈቃደኛው በአገሩ የሚያገኘው የጡረታውን ብቻ ነው፡፡ እዚህ ግን የሚሰጠው ለምግቡና ለወጪዎች መሸፈኛ ያህል ብቻ ነው የሚል ነው፡፡ እኛ ደግሞ ይህንን ብታደርጉም የሚያገኙት ታክስ መደረግ አለበት ነው የምንለው፡፡ በዚህና በሌሎችም ዙሪያ እየታገልን ነው፡፡ አንተ እንዳልከው ግን የተጋነነ ደመወዝ የሚያቀርቡ፣ ለጥቅም ብለው ከዛም በላይ የሚያቀርቡ አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በመላ አገሪቱ የተሰማሩ የበጎ አድራጎት ድርጀቶች ሁሉ በየተሰማሩበት የልማት መስኮች የሚያከናውኗቸው ተግባራት ውጤታማነት እንዴት ነው?
ወ/ሮ ፋንታዬ፡- እያንዳንዱ ድርጅት እየተገመገመ ነው፡፡ በዚህም ደረጃ ማውጣት ጀምረናል፡፡ ማነው ውጤታማ? ማነው ጥሩ ሥራ የሠራ? ያገኘውን ገቢ በትክክል ለሕዝቡ ያዋለና ሕጉን የሚያከብር ማን ነው? በሚሉት ዙሪያ በመነሳት ደረጃ ለማውጣት ዘንድሮ ሞክረናል፡፡ ይህም ሙከራ የተወሰነ ነገር ሊያሳየን ይችላል፡፡ የመጀመርያ ጅምራችን ስለሆነ ዕውቅና ለመስጠት ተቆጥበናል፡፡ ነገር ግን መቶ በመቶ ወይም ሙሉ በሙሉ ውጤታማ ናቸው? አይደሉም? የሚለውን ለማወቅ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ በእኔ ግምገማ ግን ካሁን በፊት ሕግ ካልነበረበት ጊዜ ይልቅ አሁን የተሻለ ነገር አለ ማለት እችላለሁ፡፡ አዋጅ 621 ከመውጣቱ በፊት የነበረውና አሁን ያለው አንድ አይደለም፡፡ በተወሰነ መልኩ በሥውርና በድብቅ የሚደረጉ ነገሮች እንዳሉ ሆነው የተገኙ ነገሮች ሥራ ላይ እንዲውሉ ወይም ለሕዝብ እንዲውሉ ለማድረግ የሚያችል ክትትል አለ ጥሩ ነው፡፡ ይህ ሲባል ደግሞ የተፈለገውን ያህል ተደርሷል ተብሎ የሚጋነንም ነገር አይደለም፡፡ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ተችሏል ወይ? የሚለው ቀጣይ ሥራ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ድሮ ያሉበት ቦታ አይደሉም፡፡ የተፈለገው ቦታ ደግሞ አልደረሱም፡፡ አገር ይለውጣል ማለት ሳይሆን በመጡበትም ዓላማ ላይ ትንሽም ጠብታ ማዋል ይገባቸዋል ማለት ነው፡፡ የተቻለውን ያህል ክትትል እየተደረገ ወደ ተግባር እንዲገቡ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከአምና ጀምሮ በደንብ አጥብቀን ይዘናል፡፡ እንዲማሩና በሚቀጥለው እንዲሻሻሉ የማድረግ ብቻ ሳይሆን ካሁን በፊት የነበረውን ማስጠንቀቂያ ለመስጠትና ዕርምጃ ወደ መውሰድ እንገኛለን፡፡ ኤጀንሲው እየደፈገም እያስተማረም አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ካሁን በኋላ ግን የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማኅበራትና ኅብረቶች አስተዳደራቸውን ማስተካከል፣ ሕጉን ማወቅና በደንብ መተግበር አለባቸው ወደሚል እየተሸጋገርን ነው ያለነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ ከአገር ውስጥና ከውጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በተካሄደው የምክክር መድረክ ምን ተገኘ?
ወ/ሮ ፋንታዬ፡- በዚህ ዙሪያ ለመገምገም የሚያስችል አጠቃላይ ሪፖርት እየተዘጋጀ ነው፡፡ ለማንኛውም በመድረኩ ላይ ያየነው ነገር ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ ክፍተት እንዳለ ነው፡፡ ክፍተቶቹ የት ላይ እንዳሉ እየተረዳን እንድንሠራ አቅጣጫ አሳይቶናል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ታዳሚዎቹ ለማወቅ ያላቸውን ጉጉት አይተናል፡፡ ከነሱም ያገኘነው ግብረ መልስ ተረዳድተንና ተቀራርበን ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ወይም ጥሩ መነሳሳት እንዳላቸው ነው፡፡ ከክልሎች፣ ከዘርፉ አስተዳደሮችና ከተገልጋዮም ጋር የበለጠ ተቀራርበን መሥራት እንዳለብን ተገንዝበናል፡፡ በዚህ ዙሪያ በፊት የጀመርናቸው አሁንም የተጀመሩ አሠራሮች አሉ፡፡ እነሱን አጠናክሮ መሥራት እንዳለበን አይተናል፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ አኳያ እንዲህ ዓይነቱ ስብሰባ በየዓመቱ ይካሄዳል ማለት ነው?
ወ/ሮ ፋንታዬ፡- መደበኛ ሆኖ በየዓመቱ ይካሄዳል፡፡ አምናም አድርገናል፡፡ ዘንድሮም ይኼው ነው የሆነው፡፡ ተገልጋዮቻችንን በሁለት ደረጃ ለይተናቸዋል፡፡ ገቢያቸው አገር ውስጥ የሆነ ወይም 90 በመቶ ከአገር ውስጥ ማግኘት አለባቸው ያልናቸውና መብትም ላይ ልማትም ላይ የሚሠሩ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት፣ ሙያ ማኅበራትና ብዙኃን ማኅበራት እንደ ሕዝብ ክንፍ ነው ያየናቸው፡፡ ከነሱ ጋር በጣም መቀራረብ አለብን፡፡ መብትም ላይ ይሠራሉ፣ ዴሞክራሲያዊ ግንባታ ላይና ልማቱም ላይ ይሠራሉ፡፡ ስለዚህ ወሳኝ አካላት ብለን እንደ ሕዝብ ክንፍ ለይተናቸዋል፡፡ ከእንደነዚህ ዓይነቱ አካላት ጋር በየሦስት ወሩ ወይም በዓመት አራት ጊዜ በዕቅዳቸውና በአፈጻጸማቸው ላይ እንወያያለን፡፡ አሁንም ጀምረናል፡፡ ከኢትዮጵያ ነዋሪዎችና በጎ አድራጎት ድርጅቶችም ጋር እንዲህ ዓይነቱን ተሞክሮ የማስፋት ሥራ በሚቀጥለው ዓመት እንጀምራለን፡፡
ሪፖርተር፡- በተለያዩ ምክንያት የሚዘጉ እንዲሁም በሥራ ላይ እያሉ ንብረት ይወገድልኝ ጥያቄ የሚያቀርቡ ድርጅቶችን ንብረቶች ኤጀንሲው እየተቀበለ በሐራጅ በመሸጥ የተገኘውን ገንዘብ በድርጅቶች ስም ባንክ በዝግ ሒሳብ እንደሚያስቀምጥ፣ ከፊሉን ንብረት ደግሞ በሥራ ላይ ላሉ ለሌሎች ድርጅቶች ገቢ እንደሚያደርግ ተረድተናል፡፡ ይህን ሥራ ድርጅቶቹ ራሳቸው ቢሠሩ የሚል ጥያቄ ይነሳል?
ወ/ሮ ፋንታዬ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ እየተነጋገርንበት ነው፡፡ ድርጅቶቹም በአዳማው መድረክ ላይ ባነሷቸው ጥያቄዎች አንዱ ይኼው ነበር፡፡ ንብረትን በተመለከተ አንደኛ ድርጅት ሲፈርስ ነው ሁለተኛ ደግሞ ንብረቱ ተርፎ ወይም አገልግሎቱ አብቅቷል ብለው እንዲወገድላቸው ሲጠይቁ ነው፡፡ በዚህ በኩል ያየነው ነገር ቢኖር ለትንሽም ሆነ ለብዙም ዕቃ፣ ለሚጠቅመውም ለማይጠቅመውም ኤጀንሲው መቸገር የለበትም የሚል እኛም መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ ስለዚህ ምንድነው መደረግ ያለበት? የሚለውን እያየን ነው፡፡ በዚህም መሠረት አሠራሩን ለመዘርጋት መነሻ ነገር አይተናል፡፡ እሱን አብረን ለወደፊት ሥራ ላይ እናውላለን፡፡ በተወሰነ ደረጃ በጎ አድራጎ ድርጅቶቹ ሊያስወግዱ የሚችሉበትና አስወግደው ሪፖርት የሚያቀርቡበትን አሠራር በማመቻቸት ላይ ነን፡፡ በዚህ መልኩ በኤጀንሲው ላይ የሚደርሰውን ጫና ማቃለል ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- በየክልሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎች አሏችሁ?
ወ/ሮ ፋንታዬ፡- እኛ ውክልና የሰጠነው ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የፋይናንስ ቢሮዎች ውስጥ የበጎ አድራጎ ድርጅቶቹን ሥራ የሚከታተሉና በቢሮ ምክትል ኃላፊች የሚመሩ ዲፓርትመንቶች አሉ፡፡ የበጎ አድራጎ ድርጅቶች ንብረትን በተመለከተ አንድ ነገር ሲከናወን ዲፓርትመንቶቹ ለእኛ እንዲያሳውቁ የምናደርግበት ሥርዓት አለ፡፡

Standard (Image)

አዲሱ የትግራይ ቋንቋዎች አካዴሚ

$
0
0

በትግራይ ብሔራዊ ክልል በሚገኙ ሦስት ቋንቋዎች ሳሆ (ኢሮብ)፣ ኩናምኛና ትግርኛ ዙርያ በተለያዩ የቋንቋና ባህል ዘርፎች ሳይንሳዊ ጥናቶች የሚያከናውን፣ ቋንቋዎቹም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጽንሰ ሐሳብ የመግለጽ አቅም እንዲኖራቸው የሚያስችል የትግራይ ቋንቋዎች አካዴሚ ሥራውን ባለፈው ኅዳር ወር ጀምሯል፡፡ አካዴሚው በክልሉ ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 249/06 መሠረት ያቋቋመው በ2006 ዓ.ም. ነበር፡፡ አካዴሚው ሐቻምና ከመቋቋሙ በፊት በ1988 ዓ.ም. ያለ አዋጅ ተቋቁሞ በሥራ ላይ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በላይ ማለፍ አልቻለም፡፡ ዘንድሮ እንደ አንድ መንግሥታዊ አካል በተለይም ለክልሉ ርእሰ መስተዳደር ተጠሪ ሆኖ፣ ዳግም የተቋቋመው የትግራይ ቋንቋዎች አካዴሚን በዋና ዳይሬክተርነት የሚመሩት ዶ/ር ዳንኤል ተኽሉ ናቸው፡፡ በተግባራዊ ሥነ ልሳንና ግንኙነት (አፕላይድ ሊንጉስቲክስና ኮሙዩኒኬሽንስ) የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ዶ/ር ዳንኤል፣ ከትግርኛ ቋንቋና ባህል እንዲሁም ሥነ ጽሑፍ ጋር የተያያዙ 19 መጻሕፍት አሳትመዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የትግርኛ እንግሊዝኛ፣ የእንግሊዝኛ ትግርኛ መዛግብተ ቃላት፣ የሰዋስው (ግራመር)፣ የሥነ ጽሑፍና የሥነ ግጥም፡፡ የሥነ ቃልና የሕፃናት መጻሕፍት ይገኙባቸዋል፡፡ ከ1,300 በላይ ገጾች ያሉት የትግርኛ በትግርኛ መዝገበ ቃላትም አዘጋጅተዋል፡፡ የሕትመቱን ብርሃን እየጠበቀ ነው፡፡ በአካዴሚው እንቅስቃሴ ዙሪያ ዋና ዳይሬክተሩን ዶ/ር ዳንኤልን ሔኖክ ያሬድ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የአካዴሚው ምሰሶዎች ምንድን ናቸው?
ዶ/ር ዳንኤል፡- አካዴሚው የተቋቋመበት መሠረታዊ ነገሮች አሉት፡፡ አንደኛው መነሻ ሦስቱ ቋንቋዎች የሳይንስና የቴክኖሎጂ ቋንቋዎች እንዲሆኑ ስለተፈለገ ነው፡፡ ዘመኑ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቋንቋ ነውና ለኅብረተሰቡ በሌሎች ቋንቋዎች ጽንሰ ሐሳቡን አምጥተህ ሊረዳ አይችልም፡፡ ጽንሰ ሐሳቦቹን ተረድቶ ተግባራዊ ሊያደርግ፣ ሕይወቱንም የሚያሻሽልበት ሁኔታ ለማመቻቸት አይችልም፡፡ ስለዚህ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጽንሰ ሐሳቦች በራሱ ቋንቋ ከቀረበለት ይበልጥ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው በተለያዩ ምክንያቶች እነዚህ ቋንቋዎች የተጎዱ ነበር ማለት ይችላል፡፡ በመማር ማስተማር ላይ አልነበሩም፡፡ በተለይ ሳሆኛና ኩናምኛ ስንወስድ፡፡ ትግርኛም ቢሆን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው ያለው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ገባ ወጣ ያለበት ሁኔታ ቢኖርም ኅብረተሰቡን ሙሉ በሙሉ ለማገልገል ብቃት እያለው ሳይሆን የቀረበት ነው፡፡ ቋንቋዎቹ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በሰዋስውም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ተጠንተው አገልግሎት በሚሰጡባቸው አካባቢዎች ያሉ ክፍተቶች ለመሙላት ታስቦ አካዴሚው ተቋቁሟል፡፡
ሌላው ከዚሁ ጋር በተያያዘ መልኩ የተወሰኑ ጥረቶች ቢኖሩም በቋንቋዎቹ ዙርያ የተለያዩ መዛግብተ ቃላት የሉም፡፡ ስለዚህ ይሄ አካዴሚ በዋናነት እነዚህ ነገሮች ይዞ ለመሥራት ተነስቷል፡፡ ቋንቋዎቹ በፍትሕ፣ በትምህርት፣ በሚዲያ እንዲሁም በጽሕፈት ቤት እየተገለገልንባቸው ቢሆንም ክፍተቶች ስላሉ ችግሮቹ በጥናት ተለይተው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆነን መፍትሔ የምንሻበት አጋጣሚው ይፈጠራል ብለን እናስባለን፡፡
ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ በቋንቋዎቻችን ላይ እንደ ክፍተት የሚነሳው ጥያቄ ሰዋስውን (ግራመር) የተመለከተ ነው፡፡ ተጠቃሚዎች በአግባቡ አይጠቀሙም ይባላል፡፡ በክልሉ ያሉት ሦስት ቋንቋዎች ከሰዋስው ጥናት ጋር ያላቸው ቁርኝት እንዴት ይገለጻል?
ዶ/ር ዳንኤል፡- ከሦስቱ ቋንቋዎች ሰዋስውን በተመለከተ በደንብ ተጠንቷል ብለን የምናስበው ትግርኛ ላይ የተሠሩትን ነው፡፡ ፈረንጆችም የተወሰነ ሒደውበታል፡፡ ርሱ በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ሳሆ አካባቢ የተወሰኑ ጥረቶች አሉ፡፡ ኩናምኛ ግን ብዙ ነገር ይቀረናል፡፡ አካዴሚው ሲቋቋም ዓላማዬ ካላቸው አንዱ የሦስቱ ቋንቋዎች ሰዋስው በስፋት በሳይንሳዊ መንገድ እንዲጠና ማስቻል ነው፡፡ አጠቃቀም ላይ ስንመጣ ጽሑፍና ንግግር ብለን ብንለየው የተሻለ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ በርግጥ አንዳንድ ጊዜ የምንናገረውን ስለምንጽፈው ችግር አለ፡፡ የምንናገረው ደግሞ በቃላቱ፣ በሰዋስው፣ በዕርባታው በሌሎች ቋንቋዎች የተበረዘ ነው፡፡ ለምሳሌ በመዋቅሩ ትግርኛ በአማርኛ የሚዘነበልበት (ዶሚኔት የሚደረግበት) ሁኔታ አለ፡፡ የተጻፉ መጻሕፍት፣ የተሠሩ ጥናቶች ቢኖሩም በመማር ማስተማር ሒደት፣ በሚዲያና በመሥሪያ ቤቶች አካባቢ ውጥንቅጥ አካሄድ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የግንዛቤ ችግር የፈጠረው መሆኑን ተረድተን በሒደት የምናስተካክለው ይሆናል፡፡ ችግሩና ክፍተቱ በሰዋስው ብቻ አይደለም፡፡ ትግርኛ የመግለፅ ብቃቱ የለኝም ሳይል የትግርኛ ቃላትን እየተውን ቃላትን እየቀላቀልንና በሌሎች እየተካን ነው፡፡ በሳሆና በኩናምኛም ተመሳሳይ ነገር አለ፡፡ ስለዚህ እነዚህን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት አካዴሚው የራሱ የሆነ ሚና ይኖረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- አደረጃጀቱ እንዴት ነው?
ዶ/ር ዳንኤል፡- አካዴሚው ተጠሪነቱ ለክልሉ ፕሬዚዳንት ነው፡፡ አደረጃጀቱም በውስጡ ሦስት ክንፎች አሉት፡፡ አንደኛው ክንፍ የሰዋስውና የመዛግብተ ቃላት ጥናት ነው፡፡ ሁለተኛው ሥነ ቃል፣ ሥነ ጽሑፍና ትርጉም የሚል ሲሆን ሦስተኛው የፋይናንስ ዘርፍ ሆኖ ተዋቅሯል፡፡ እያንዳንዱ ዘርፍ በተለይ በሥነ ጽሑፍና በሥነ ልሳን አካባቢ የሦስቱም ቋንቋዎች ክፍሎች ይኖራሉ፡፡ በሥነ ቃልና በትርጉምም እንዲሁ፡፡ አደረጃጀቱ ለጊዜው እንጂ ቋሚ ላይሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የሰው ኃይሉ ታይቶም በቢፒአር ጥናት መሠረት ሊሰፋ ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- በባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተመሳሳይ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ተደራራቢነት አይኖርም? መተሳሰርስ ይኖራል?
ዶ/ር ዳንኤል፡- በባህልና ቱሪዝም ቢሮ በቋንቋ ጉዳይ፣ በሥነ ቃልና በመዛግብተ ቃላት ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ይኸ ማለት ያለ መናበብ ችግር ይፈጥራል ወደሚል የሚወስድ አይመስለኝም፡፡ ከዚያም በተጨማሪ በአዲስ አበባ፣ በመGለና በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች፣ በዓድዋና በዓቢይ ዓዲ የመምሀራን ትምህርት ኮሌጆች የትግርኛ ትምህርት ክፍል አለ፡፡ የትግራይ ባህል ማኅበርም በጠቀስናቸው ዘርፎችም ይሠራል፡፡ መንግሥት እነዚህን እንቅስቃሴዎች አድንቋል፡፡ ግን አካሄዳቸው የተበተነ በመሆኑ አካዴሚው እንዲመሠረት ትልቅ መነሻ የሆነው እነዚህ በተለያዩ ቦታዎችና ባለሙያዎች የሚደረጉ ጥረቶች በማማከል እየተናበቡ እንዲሄዱ ለማመቻቸት ነው፡፡ አብረን ነው የምንሠራው፡፡ አካዴሚው በማስተባበርና በመምራት ሙሉ ድርሻ ይኖረዋል ብለን እናስባለን፡፡
ሪፖርተር፡- ትግራይ የጥንት የኢትዮጵያ ሥልጣኔ መገኛ ነች፡፡ በዘመነ አክሱም ሆነ ቅድመ አክሱም፣ በደኣማት ቅርስና ውርሶችን የሚያሳዩ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች በግእዝ፣ በሳባ፣ በግሪክ ይገኙበታል፡፡ እንዲሁም ሄይሮግራፊክስም መገኘቱም የሚያወሳ ጥናትም አይቻለሁ፡፡ በተለይ አካባቢው የግእዝ ሥነ ጽሑፍ የ1,500 ዓመታት ታሪክም ዐቢይ አካል ነው፡፡ ከአክሱም እስክ ናዝሬን/ናዝሬት (ደቡብ ትግራይ) ጉንዳጉንዶን ጨምሮ በርካታ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ሀብት አለ፡፡ አካዴሚው ከዚህ አንፃር ምን ሥራ ይኖረዋል? በአካዴሚው አዋጅ ላይ ስለ ግእዝና ስለ ሌሎች ጥንታዊ ቋንቋዎች የሚያነሳው ነጥብ የለም፡፡ አካዴሚው ይኼን እንዴት ያየዋል?
ዶ/ር ዳንኤል፡- ለጊዜው በክልሉ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ያገኙት ሦስቱ ቋንቋዎች ናቸው፡፡ ይኸ ማለት ግን በግእዝ ላይ የምንሠራው ሥራ አይኖርም ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ሦስቱ ቋንቋዎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቋንቋዎች እንዲሆኑ ይፈለጋሉ፡፡ ወደ ትርጉም ስንመጣ ግን የግድ ወደ ግእዝ እንሄዳለን፡፡ ወደ ሌሎችም የአገራችን ቋንቋዎችም እንዲሁ እንመለከታለን፡፡ በቋንቋዎቻችን የመዋዋስ ነገር አለ፡፡ ከግእዝ የሚወስዱት ብዙ ነገር ይኖራል፡፡ የግእዝ ህልውና ያስፈልጋል፡፡ አካዴሚው ጥናቱን ሲያጠቃልል የዶክመንቴሽን ማዕከል ይኖረዋል፡፡ ሦስቱ ቋንቋዎች ከምን ተነስተው እምን ደረሱና ምን ላይ ይገኛሉ? በሚል የዶክመንተሽን (ስነዳ) ማዕከል ይኖረዋል፡፡ ጎን ለጎን የግእዝ ስነዳ ማዕከል ይኖራል ብለን እናስባለን፡፡ ከግእዝ እንዋሳለን ስንል ሰነዶች ያስፈልጉናል፡፡ ማዕከሉ የሚያስፈልገን ሰነዶቹን የምናሰባስብበት ስለሚሆን ነው፡፡ ለትግርኛ፣ ኩናምኛና ሳሆኛ የምንጠቀምበት ይሆናል፡፡ የኅብረተሰቡ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሥነ ልቦናዊ የሆኑ ሀብቶች፣ እንዲሁም ታሪክ ለማጥናትም ግእዝ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በትርጉም ዙሪያ ደግሞ በስፋት እየሄድን እናጠናዋለን ብለን እናስባለን፡፡
ሪፖርተር፡- ከሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት ጋር ያላችሁ ወይም የሚኖራችሁ ግንኙነትስ እንዴት ይገለጻል?
ዶ/ር ዳንኤል፡- አካዴሚያችን ገና በጅምር ላይ ነው ያለው፤ ተሞክሮ እናገኝበታለን ብለን ከምናስበው ተቋም ጋር አብረን መሥራት እንፈልጋለን፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ፣ ከብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር)፣ ከኦሮሚኛ ቋንቋና ባህል ማዕከል፣ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ማበልፀጊያ ማዕከል፣ ወደ ደቡብ ሲኬድ የሀዲያን ተሞክሮ በስፋት እንዳስሳለን፡፡ አብረንም እንሠራለን፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ውጭ ካሉት ከሩሲያ የቋንቋዎች አካዴሚ፣ ከጀርመን ሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲ፣ ከስዊድን ጋርም ግንኙነት ጀምረናል፡፡ ምክንያቱም ትግርኛ የተጠናበትና እየተጠናበት ነው፡፡ ለአካዴሚው ግብአት ይኖረዋል እስካልን ድረስ ከተቋማት ሌላ ከግለሰቦች ጋርም አብረን ለመሠራት ዝግጁ ነን፡፡
ሪፖርተር፡- ትግርኛ በኤርትራም የሚነገር ቋንቋ እንደመሆኑ ትስስር አለ፡፡ በዚህስ ረገድ ምን ታስባላችሁ?
ዶ/ር ዳንኤል፡- ኤርትራ አካባቢ የሚነገረውና እዚህ የሚነገረው ቋንቋ አንድ ነው፡፡ አሜሪካና እንግሊዝ የተለያዩ አገሮች ናቸው፡፡ በሁለቱም እንግሊዝኛ ይነገራል፡፡ በመካከላቸው የቋንቋ ድንበር አናበጅም፡፡ እንግሊዝኛ ነው ብለን ነው የምንቀበለው፡፡ በሁለቱም ያለው ትግርኛ ነው፡፡ ስለዚህ በሁለቱ መካከል የፖለቲካ ልዩነት ሊኖር ይችላል፡፡ ቋንቋው ግን እዚያም ሆነ እዚህ ሲነገርም ሆነ ሲጻፍ ተደጋግፈው ቢሄዱ ቋንቋውን ይበልጥ ያበለፅጉታል፡፡ በኤርትራ የሚጻፉ ለምሳሌ መዛግብተ ቃላት ያስፈልጉናል፤ እንጠቀምባቸዋለን፡፡ እዚህ የሚጻፉ እነሱም ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በኤርትራ የተሠሩ የተለያዩ ጥናቶችም እያየን ነው፡፡ በትግራይ ተወላጆች የተጻፉ የትግርኛ ጽሑፍን አጣቅሰው (ሪፈር አድረገው) ጥናቶችን የሚያቀርቡበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ የምናወራው ስለ ትግርኛ ነው፡፡ ፖለቲካው ሌላ ነገር ነው፤ ለትግርኛ ቋንቋ ዕድገት የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ እንጠቀምበታለን፡፡
ሪፖርተር፡- የፊደል አጠቃቀምን በተመለከተ በመGለና በአስመራ በተለይ ሁለቱ ‹‹ፀ›› እና ‹‹ጸ›› ላይ ልዩነት አለ፡፡ አስመራዎች ‹‹ጸ››ን ሲጠቀሙ መGለዎች ‹‹ፀ››ን ይጠቀማሉ፡፡ አንዳቸው አንዱን ጥለዋል፡፡ ትርጉም ላይ ልዩነት ያሳያል፡፡ ለምሳሌ በአስመራ ‹‹ጸሓይ›› በመGለ ‹‹ፀሓይ›› ተብሎ ይጻፋል፡፡ የመGለው ታዳጊ የአስመራውን ሲያነብ ‹‹ጸ››ን ስለማያውቃት ‹‹ደ›› ብሎ ሲያነባት፣ የአስመራው በበኩሉ ‹‹ፀ›› ን ስለማያውቃት ‹‹ዐ›› ብሎ ስለሚያነባት አለመግባባት ይፈጥራል፡፡ በዚህ ረገድ ምን ማለት ይቻላል?
ዶ/ር ዳንኤል፡- ሁለት ነገሮችን እናንሳ፡፡ አንደኛው በትግርኛ ፊደላት ሞክሼነት የለም፡፡ ሁሉም ራሳቸውን ችለው በየድምፃቸው የቆሙና አገልግሎት የሚሰጡት፡፡ ምናልባት ‹‹ፀ›› ጸሐዩና፣ ‹‹ጸ›› ጸሎቱ፣ ‹‹ሠ›› ንጉሡና ‹‹ሰ›› እሳቱ አካባቢ ችግር ሊኖር ይችል ይሆናል፡፡ እንደ ችግርም ላይነሳ ይችላል፡፡ ትልቁ ችግር እየተፈጠረ ያለው ተማሪዎች ሕፃኖቻችን ሲማሩ የአማርኛ ፊደል ገበታን መጠቀማቸው ነው፡፡ ለምሳሌ አፀደ ሕፃናት (ኬጂ) ብትሄድ አማርኛ ለማስተማር በተቀረፁ የፊደል ገበታ ትግርኛን ይማራሉ፡፡ በትግርኛና በአማርኛ መካከል በአጠቃቀም ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ ለምሳሌ ‹‹በርሀ› የመጀመርያው [ኸ] ነው፡፡ ‹‹አብርሃ›› አራተኛው (ሃ ራብዕ) ነው፡፡ የአማርኛ ተጽዕኖ ነው ወደ ትግርኛ መጥቶ ችግር የፈጠረው፡፡ ያነሳኸው ልዩነት በኤርትራና በትግራይ ያለው የሁለቱ ፊደላት አጠቃቀም ሥነ ዘዴያዊ (ሜቶዶሎጂካል) ዕይታ አለው፡፡ እኛ ‹‹ፀ›› ፀሓዩን ለመጠቀም የወሰንነው በጥናት ነው፡፡ ምናልባት ሌላ ተጨማሪ ጥናት ያስፈልጋል ቢባል ያስኬዳል፡፡ ግን አንዳንዱ የፊደል አወሳሰዱ ጥናት ላይ የተመሠረተ አይደለም የሚለውን አስተሳሰብ አልደግፈውም፡፡ ለግእዝ ሁለቱም ‹‹ፀ›› እና ‹‹ጸ›› የተለያዩ ናቸው፡፡ በትርጉም ደረጃ የሚያስተላልፉት መልዕክት አለ፡፡ እንደ ‹‹ሠረቀ›› እና ‹‹ሰረቀ››፡፡ በትግርኛ ግን አንድ ‹‹ሰ›› ብቻ እንጠቀማለን፡፡ እሳቱ ‹‹ሰ›› የሆነበት ምክንያት ፊደል ስናስተምር ‹‹በ›› ብለን እንጀምራለን፡፡ አናቱ ላይ ጭረት አድርግ ካልነው አንድ ፊደልን በቀላሉ ተማረ ማለት ነው፡፡ ሌላ ‹‹ሠ›› ከሆነ ግን እናበዛበታለን፡፡ ሸክም ነው፡፡ ‹‹በ››ን ተምሮ ‹‹ሰ››ን ከዚያ በ‹‹ሰ›› ላይ አግድም ሲያደርግበት ‹‹ሸ›› ይሆናል፡፡ ስለዚህ አንድ ልጅ ፊደልን ለማጥናት ስለሚያቀላጥፍለት፣ ለትምህርት ዕድገት በጎ አስተዋጽኦ ስላለው በዚህ ተመረጠ፡፡ ‹‹ፀ›› እና ‹‹ጸ›› ላይ ስንሄድም ተመሳሳይ ነው፡፡ በትግርኛ ‹‹ዐ›› አስተምረን ስንጨርስ መሀል ላይ ሠረዝ አድርግና ‹‹ፀ›› አድርገው፡፡ በቀላሉ እንዲገነዘበው ለማድረግ ነው፡፡ ጸሎቱ ‹‹ጸ›› ግን ከ‹‹ደ›› ጋር ይምታታል፡፡
ስለዚህ አካሄዳችን ከትምህርት ሥነ ዘዴ አኳያ ተቀባይነት ያለውና በጥናት ላይም የተመሠረተ ነው፡፡ ከቅርስ ጋር ተያይዞ የሚነሳ አስተያየት አለ፡፡ የቅርስ ጉዳይ እኛንም ያገባናል፡፡ ሥርዓተ ጽሕፈታችን ይዞ ያመጣቸው ሁለቱ ‹‹ጸ ፀ›› መጥፋት የለባቸውም የሚለውን እንደግፋለን፡፡ በቅርስነታቸው ለመቀበል ሁለት ዓይነት አማራጭ አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ አንዱ አማራጭ ግእዝ ቋንቋን ማዳን ነው፡፡ እርሱን ማዳን ካልተቻለ ቢያንስ ቢያንስ ድሮ የተጻፉ በመጻሕፍት መልክ ያሉትን ሰነዶች ሰንዶ ለትውልድ ማቆየትና ማስተላለፍ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአካዴሚው ማቋቋሚያ አዋጅ አማካሪ ቦርድ አባላት ብሎ ከዘረዘራቸው ውስጥ ከትግርኛም ሆነ ከሳሆ እና ኩናማ ቋንቋዎች ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራ የሠሩ የሃይማት ተቋማት ለምን እንዲካተቱ አልተደረገም? ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ ከኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክና እስልምና ተቋማት የተወከሉ ሊቃውንትን በቦርድ አባልነት አቅፏል፡፡ ከነርሱ ልምድ መቅሰም አይቻልም? ለአካዴሚያችሁስ አይበጅም?
ዶ/ር ዳንኤል፡- በሁለት መልኩ እንየው፡፡ አማካሪው ቦርድ አቅጣጫ የሚሰጥ ነው፡፡ አካዴሚው የራሱን ዕቅድ እየነደፈ አቅጣጫ እያስቀመጠ ለቦርዱ ያቀርባል፡፡ አማካሪው ቦርድ በሚቀርብለት ጉዳይ ሐሳብ ይሰጣል፡፡ ሁለተኛው የጠቀስካቸው የሃይማኖት ተቋማት በጣም ጠቃሚ ናቸው፡፡ የሃይማኖት ተቋማቱን ብቻ ሳይሆን ግለሰቦች ጭምር ከአካዴሚው ጋር እንዲሠሩ የሚደረግበትም አሠራር ይኖረናል፡፡ ስለዚህ የሃይማኖት ተቋማት፣ ከቋንቋና ባህል ጋር የተያያዙ ባለሙያዎች፣ ምሁራን ይኖሩበታል፡፡ ሙያዊ ሥራ የሚሠራ አካልም ከሁሉም የሚውጣጣ ስለሚኖር ተቋማቱ የሚተው አይደሉም፡፡

Standard (Image)

‹‹የከተማ ጤና ችግሮች ለጤና ዘርፍ ብቻ መተው የለባቸውም››

$
0
0

ዶ/ር ሚርጊሳ ካባ፣ የከተማ ጤና አማካሪ ቡድን መሪ

ዶ/ር ሚርጊሳ ካባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ክፍል ባልደረባ ናቸው፡፡ ሶሲዮሎጂ ከዚያም አንትሮፖሎጂ አጥንተዋል፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲም መምህር ነበሩ፡፡ ሲሠሩ የነበረው በጤና ዘርፍ ስለነበር የጥናት ትኩረታቸውን ጤና ላይ በማድረግ ፒኤችዲያቸውን በማኅበረሰብ ጤና ዘርፍ ሠሩ፡፡ በአጠቃላይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ከአሥር ዓመት በላይ ሲያገለግሉ በአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሥራት ከጀመሩ ደግሞ ከሦስት ዓመት በላይ ሆኗል፡፡ ከዚህ ባሻገር ደግሞ በቅርብ የተቋቋመው የከተማ ጤና አማካሪ ቡድን (Urban health think tank) መሪ ሆነው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በአማካሪ ቡድኑ እንቅስቃሴና በከተማ ጤና ጉዳዮች ዙሪያ ምሕረት አስቻለውከዶ/ር ሚርጊሳ ካባ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡ 

ሪፖርተር፡- የከተማ ጤና አማካሪ ቡድን የማቋቋሙ እንቅስቃሴ እንዴት ተጀመረ?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- መንግሥት ልክ የገጠር ጤና ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደተነሳው የከተማ ጤና ላይም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ደግፎ ይመስለኛል እ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮ እንቅስቃሴ ጀምሮ ነበር፡፡ ለዚህ ዩኤስኤአይዲ ድጋፍ ሰጪ፣ ጄኤስአይ በሚባል ተቋም ተግባሪነት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ሆነው ይሠራሉ፡፡ ይህ ፕሮግራም ሲጀመር አማካሪ ነበርኩና ፕሮግራሙ ሲገመገም የተረዳነው ነገር በእርግጥ የተሠሩ ጥሩ ሥራዎች ቢኖሩም የከተማ ጤና እንደገጠሩ በኤክስቴንሽን ፕሮግራም ሊሠራ የሚችል አለመሆኑን ነበር፡፡ ይልቁንም በቀጣይ እንደገጠሩ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ሳይሆን ሰፋ ብሎና የከተማ ቅርፅ ይዞ መተግበር አለበት የሚል ነገር ላይ ነበር የደረስነው፡፡  

ሪፖርተር፡- እዚህ ሐሳብ ላይ የተደረሰው እንዴት ነበር?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- የከተማ ጤና የአንድ ተቋም ጉዳይ ባለመሆኑ የተወሳሰበ ነው፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች እንደገጠሩ ቤት ለቤት ሊዞሩ አይችሉም፣ የከተማ ኗሪ እንደ ገጠሩ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት ችግርም የለበትም ምክንያቱም የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በየቦታው ይገኛሉና፡፡ ጤናን የሚመመለከት መረጃ እጥረትም በገጠሩ ደረጃ የለም፡፡ አንዱ የሐሳቡ መነሻ ከከተማ ጤና ጋር በተያያዘ የሚሰጠው አገልግሎት ከገጠሩ የተለየና የተሻለ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው በከተማ ጤና እንደ ግንባታ ዘርፍ፣ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ የትምህርትና ሌሎችም ዘርፎች የሚመለከታቸው መሆኑ ነው፡፡ የከተማ ጤና ጉዳይ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ የገጠሩ ጤናም ቢሆን በተወሰነ መልኩ ዘርፈ ብዙ ነው ስለዚህም የጤናው ዘርፍ ሊሠራ የሚችለው ሥራ በጣም ሰፊ ነው፡፡ በንፅፅር ሲታይ ከተማ ላይ ሌሎች ዘርፎች ከጤና ተቋም ጋር ሆነው ሊሠሩ የሚገባቸው በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ በዚህ ረገድ ጄኤስአይ ከጤና ጥበቃ ጋር በመሆን በሁለተኛ ዙር በተጠቀሰው መልክ መንቀሳቀስ ሲጀምር የአዲስ አበባ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤትም የእንቅስቃሴው አካል ሆነ፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የትምህርት ቤቱ ኃላፊነት የሚያተኩረው የከተማ ጤናን በሚመለከት የመረጃ ችግር አለ የለም የሚለውን ማጥናት፣ የከተማ ጤናን የሚመለከት መረጃስ የሚገኘው የት ነው? የከተማ ጤናን በሚመለከት የምርምር ሥራዎችና ፖሊሲ ግንኙነት አላቸው ወይ? በማሉት ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ የመጨረሻውን ለምሳሌነት ብንመለከት ብዙ ጥናቶች የምርምር ሥራዎች ይካሔዳሉ በተለያየ መንገድም ይሠራጫሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሥራዎች ፖሊሲና ፕሮግራም ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩት በጣም ውስን በሆነ ደረጃ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የምርምር ውጤቶችና ፖሊሲዎች አይነጋገሩም ለከተማ ጤናም የተፈጠረ ነገር የለም የሚል ግምት ያስወስዳል፡፡ ስለዚህ በምርምርና በፖሊሲ መካከል ድልድይ የሚፈጠረው እንዴት ነው የሚለው ታሳቢ ተደርጓል?

ሪፖርተር፡- በከተማ ጤና ላይ የተሠሩ ጥናቶች አሉ?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- ከተማ ጤና ላይ ምን ምን ተሠርቷል የሚለውን ስንመለከት ይህ ነው የሚባል የተሠራ ነገር አይገኝም፡፡ በተሠሩ ሥራዎች ላይም ከተሞች በጥቅሉ እንደ ከተማ ባህርዳር፣ አዲስ አበባና ሐዋሳ እየተባሉ ነው የታዩት፡፡ በጥቅል ሳይሆን በከተሞች ውስጥ ያለው ልዩነት መታየት ይኖርበታል፡፡ በከተማ ውስጥ የአገልግሎት አሰጣጥ ልዩነቶች አሉ፡፡ አንዳንድ የከተማ ክፍሎች ላይ ከሞላ ጐደል ከገጠር ጋር የሚመሳሰል ነገር ይታያል፡፡ በከተማ ውስጥ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች አሉ በእነዚህ ቦታዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ለበርካታ የጤና ችግሮች ይበልጥ የተጋለጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች አሁን እየተጠኑ ነው፡፡ የከተማ ጤና አገልግሎት ጥራት ምን ይመስላል ጥራትን አዳጋች ያደረጉ ነገሮችስ ምንድን ናቸው? ጥራትስ እንዴት ነው የሚለካው ኅብረተሰቡስ ረክቷል ወይ በሚሉት ነገሮች ላይ ይሔ ነው የሚባል የተሠራ ሥራ የለም፡፡ እዚህ ላይ አሁን ጥናት እየተሠራ ነው፡፡ ትልልቅ የከተማ ችግሮች የሚባሉት የትኞቹ ናቸው የሚያያዙትስ ከምን ጋር ነው የሚሉ ነገሮችም በጥናቱ እየታዩ ነው፡፡ ጥናቶቹ በተማሪዎቻችንና በመምህራን የሚሠሩ ናቸው፡፡ በሌሎች አካላት የከተማ ጤና ላይ የተሠሩ ሥራዎችን መሰብሰብም ሌላው ኃላፊነታችን ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- የመረጃ ማዕከል አቋቁማችኋል?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- የከተማ ጤና ላይ ያሉ መረጃዎችን ሰዎች ማግኘት ቢፈልጉ በሚል የመረጃ ማዕከሉን አቋቁመናል፡፡ ማዕከሉ በዓለም አቀፍ፣ በአፍሪካና በኢትዮጵያ ደረጃ የከተማ ጤና ላይ የተሠሩ ጥናቶችን አደራጅቶ ለተመራማሪዎች፣ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለጋዜጠኞችና ለሌሎችም ያስቀምጣል፡፡ መረጃዎቹ ኦንላየንም እንዲገኙ መንገድ ፈጥረናል፡፡ ማዕከሉ የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅዶች አሉት ሥልጠናዎችን መስጠት፣ የዲግሪ ፕሮግራም መጀመር ይገኙበታል፡፡

ሪፖርተር፡- አማካሪ ቡድኑ እንዴት ተቋቋመ?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- በአገሪቱ የኅብረተሰብ ጤና ላይ ረዥም ጊዜ የሠሩና አንቱ የተባሉ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ አማካሪ ቡድኑ ተቋቋመ፡፡ ዓላማው በፖሊሲና መሬት ላይ ባለው እውነታ መካከል የለውን ቅርበት ማጐልበት ነው፡፡ የቡድኑ ሥራ የሚሆነው ለፖሊሲና ፕሮግራም አውጪዎች ይሔ ጉዳይ እንደዚህ ነው ብሎ ማማከር ነው፡፡ ቡድኑ ከተቋቋመ ወራቶች የተቆጠሩ ሲሆን፣ ሦስተኛውን ዙር ስብሰባ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ድጋፍን መጠቀም አለመጠቀም የተጠቃሚው ውሳኔ ሲሆን፣ የቡድኑ ዋና ዓላማ በከተማ ጤና ላይ በመረጃ የተደገፈ ድጋፍ መስጠት ነው፡፡ አማካሪ ቡድኑን ለማቋቋም የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ወደ ዘጠኝ ወር ገደማ ወስደዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከጊዜው አንፃር የአማካሪ ቡድኑ መቋቋም አስፈላጊነት ምን ያህል ነው?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- ኢትዮጵያ ወደ ከተሜነት እየሔደች ነው፡፡ እንደሚታየው 18 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ከተሜ ነው፡፡ በ2050 ደግሞ 38 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተማ ውስጥ ይኖራል ተብሎ ይገመታል፡፡ ስለዚህ የከተማ ኗሪ ቁጥር እንዲህ እየጨመረ የሚሔድ ከሆነ የከተማ ጤና ጉዳይም ውስብስብ እየሆነ ይሔዳል ማለት ነው፡፡ እነዚህን ውስብስብ ችግሮች እንደፀባያቸው መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው አማካሪ ቡድኑ ያስፈለገው፡፡ ለምሳሌ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ብንመለከት በአመጋገባችን ከአጠቃላይ የአኗኗር ዘዬአችን ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ እነዚህ በሽታዎች አንዳንዶቹ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች መከላከል የሚቻሉ ናቸው፡፡ ከውጥረትና ከጭንቀት፣ ከመኪና አደጋ ጋርም የተያያዙ አሉ፡፡ እነዚህ ውስብስብ የከተማ ጤና ችግሮች ለጤና ዘርፍ ብቻ መተው የለባቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- የትኞቹ ዘርፎች በአማካሪ ቡድኑ ተወክለዋል?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- ጤና ጥበቃ፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የከተማ ልትና ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ በአማካሪ ቡድኑ ተወክለዋል፡፡ ከግል ዘርፉ እንዲሁም እንደ ዓለም ጤናና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት መርጃ ድርጅት፣ ዓለም ባንክ፣ ዩኤስኤአይዲና ጄኤስአይ የመሰሉ ተካትተዋል፡፡ ከግሉ ዘርፍ እንደ ባለሙያ በግላቸው የአማካሪ ቡድኑ አባል የሆኑም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አማካሪ ቡድኑ የተነጋገረበትን ነገር፣ ምክረ ሐሳቦችንስ እንዴት ነው የሚያሠራጨው?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- ፖሊሲ ብሪፎች፣ ዜና መዋዕሎች ይዘጋጃሉ፡፡ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በመተባበር የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀትም ሌላው መንገድ ነው፡፡ አማካሪ ቡድኑ የከተማ ጤና ጉዳይ ከአንድ ዘርፍ በላይ ነው ይላል፡፡ እዚህ ላይ አስምሮ ሌሎች ዘርፎች በጋራ ሆነው የሚሠሩበትን መንገድ መቀየስም ኃላፊነቱ ነው፡፡ የአማካሪ ቡድኑ እንቅስቃሴ በአጠቃላይ የከተማ ጤናን አንድ ዕርምጃ ወደፊት መውሰድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአማካሪ ቡድኑ የአጭር ጊዜ ዕቅድ ምንድን ነው?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- የተለያዩ ዘርፎች የከተማ ጤና ጉዳይ ይመለከተኛል ብለው እንዲመጡና ከጤናው ዘርፍ ጋር እንዲሠሩ ማስቻል፡፡ በከተማ ውስጥ በተለየ መልኩ የተጐዳ ቦታ የተለየ ችግር ያለበት አለ ካልን ይህን በመረጃ አስደግፎ የሚመለከታቸውን አካላት ማሳመንም በቅርብ በተጨባጭ እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች መካከል ነው፡፡ በከተማ ጤና የዲግሪ ፕሮግራም መጀመር ደግሞ የረዥም ጊዜ ዕቅዳችን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በከተማ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ይህን ያን ያህል ነው በማለት ቁጥር ሲቀመጥ ይታያል፡፡ የዚህ ዓይነቱ መረጃ እንዴት ይታያል?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- ትክክል ነው በከተማ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ይህን ያህል ነው ተብሎ ይቀመጣል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው የሚለው ግን ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም የሚቀመጠው ቁጥር በከተማ ውስጥ የለውን ልዩነት የሚያሳይ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞግራፊክ ሔልዝ ሰርቬይን ብንወስድ አንድም ቦታ በከተማ ውስጥ ያለውን የአገልግሎት ተደራሽነት ልዩነት አያስቀምጥም፡፡  እንዲሁ ይሔን ያህል ሽፋን አለ ተብሎ ነው የሚቀመጠው፡፡ መንግሥትንም እዚህ ጋር ስህተት አለ ስንል በመረጃ መሆን ስላለበት መረጃውን መያዝ የእኛ አንዱ ሥራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በእስካሁኑ ጉዟችሁ አስቸጋሪ የነበረው ምን ነበር?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- የከተማ ጤና ሲባል ምን የተለየ ነገር አለው የሚል አመለካከት በብዙዎች ዘንድ ነበር፡፡ የከተማ ጤና ይለያል ኢፍትኃዊነም አለ የሚለውን በመረጃ አስደግፎ ብዙዎችን ማሳመን ራሱን የቻለ ሥራ ነበር፡፡ አማካሪ ቡድኑ እንደ ፕሮጀክት ሳይሆን እንደ ፕሮግራም ለረዥም ጊዜ እንዲቀጥል ነው የምንፈልገው፡፡ አሁን የገንዘብ ምንጫችን ዕርዳታ ነው፡፡ ይህም አንደኛው ችግራችን ነው፡፡

Standard (Image)

‹‹የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ትልቁ ክፍተት የተፈጥሮ ቱሪዝሙ በጣም እየሞተ መሆኑ ነው››

$
0
0

አቶ ንጉሤ ቶዬ፣ የአዲስ አበባ የአስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት

የአዲስ አበባ የአስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ከተመሠረተ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ 36 አስጎብኚ ድርጅቶችን በሥሩ የያዘው ማኅበሩ፣ በቱሪዝም ዘርፍ ከሚንቀሳቀሱ የግል ማኅበሮች አንዱ ነው፡፡ በቅርቡ የማኅበሩ አባላት በሆኑ አስጎብኚዎች የተነሱ ፎቶግራፎች ዓውደ ርዕይ በብሔራዊ ሙዝየም ተዘጋጅቷል፡፡ ስለ ማኅበሩ እንቅስቃሴ እንዲሁም ስለ ዓውደ ርዕዩ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ንጉሤ ቶዬን ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ድርጅቱ አመሠራረትና ስለምታደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ቢገልጹልን?

አቶ ንጉሤ፡-ማኅበራችን የተመሠረተው መስከረም 29 ቀን 2004 ዓ.ም. ነው፡፡ ሲመሠረት የኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪን አንድ ዕርምጃ ለማራመድ ነው፡፡ ሁሉም አባላቱ ማለት ይቻላል ከቱሪዝም ኮሌጅና ከዩኒቨርሲቲ በቱሪዝም የተመረቁና ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ወደ 80 በመቶ የሚሆኑት አባሎች ወጣቶች ናቸው፡፡ አንደኛው የማኅበሩ ዓላማ የአባላትን ጥቅም ማስከበር ነው፡፡ ከብቃት ማረጋገጫና ከመዳረሻ ልማት ጋር ተያይዞም ከመንግሥት ጋር መወያየት ሌላው ነው፡፡ ዓላማችን ብዙ ቢሆንም ለአባላት በተለያየ የቱሪዝም ዘርፍ ሥልጠና መስጠት ይገኝበታል፡፡ እንደ በርድ ዋቺንግና ዋይልድ ላይፍ የመሰሉትን እንዲያውቁ ስለጉዳዩ ዕውቀት ያላቸው አባሎች ለሌሎች አባላት ሥልጠና ይሰጣሉ፡፡ እንደ ባለድርሻ አካልነታችን በኢትዮጵያ ቱሪዝም የሚጠበቅብንን ለማድረግ ከመንግሥት ጋር በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ አብረን እንሠራለን፡፡ በየጊዜው አስፈላጊ በሆኑ ሐሳቦች ዙሪያ ከክልልና የፌዴራል ቢሮ ጋርም አብረን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ያዘጋጃችሁት የፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይ የቱሪስት መስህብ አካባቢዎችን በማሳየት የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለመሳብ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ አለመሠራቱ በተደጋጋሚ ይጠቀሳልና ዓውደ ርዕዩ ምን ያህል ለውጥ ያመጣል ብለው ያምናሉ?

አቶ ንጉሤ፡-እኛ የምናስጎበኘውና ለአገሪቱም የውጪ ምንዛሬ የምናስገባው ከውጪ ገበያ በማምጣት ነው፡፡ ወደ አገር ውስጥ ስንመለስ ግን ሕዝባችን ያለውን የቱሪዝም ሀብት ብዙ አያውቀውም፡፡ የዓውደ ርዕዩም ዓላማ ኅብረተሰቡ ስለቱሪዝም ሀብቱ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ነው፡፡ እያንዳንዱ አካባቢ ተደራሽ ሆኖ ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆንና ስለመንከባከብም ግንዛቤ እንዲወስድ ነው፡፡ ከዐውደ ርዕዩ በጣም ትልቅ ነገር አግኝተናል፡፡ መቶ በመቶ ባይባልም የመጣው ሕዝብ አድንቆታል፡፡ ብዙ አስተያየት መጻፊያ አጀንዳ አልቋል፡፡ በዐውደ ርዕዩ ሰው ቁጭት እንዲሰማውና አገሩን ለማወቅ እንዲነሳሳ አድርገናል፡፡ ቀድሞ ዝም ብለው የሚያዩዋቸው ወፎች የቱሪስት መስህብ ስለመሆናቸው ግንዛቤ አስጨብጠናል ብዬ እገምታለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አስጎብኚዎችን በተለያየ ዘርፍ እንደምታሠለጥኑ ገልጸውልናል፡፡ አስጎብኚዎች ስለቱሪስት መዳረሻዎች ያላቸው መረጃ ላይ ጥያቄ የሚያነሱም አሉ፡፡ በማኅበሩ የምትሰጡት ሥልጠና የመረጃ ክፍተትን በማጥበብ ረገድ ፋይዳው ምንድነው?

አቶ ንጉሤ፡-በቅርቡ የምንጀምረው ሥልጠና አስጎብኚዎቹን ወደማያውቁት ቦታ በመውሰድ ይሆናል፡፡ ወደ ሰሜን ሸዋ እስከ ጋቸኒ፣ አንኰበርና መልካ ጀብዱ በመሄድ ከቦታዎቹ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች ጋር ማስተዋወቅ ነው፡፡ ብዙ አባሎቻችን በተፈጥሮ ቱሪዝም በተለይም በርድ ዋቺንግ ብቻ ይሠራሉ፡፡ ሌሎች ድርጅቶችም ስለዚህ ቱሪዝም ዕውቀት መጨበጥ አለባቸው፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት በሚመጣው ወር 15 ለሚሆኑ የድርጅት ባለቤቶች ማለትም ቱር ኦፕሬተሮች የአሥር ቀን የመስክ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ምን አላችሁ ቢባል ይህ መረጃ አለን ብለው መናገር መቻል አለባቸው፡፡ ቱሪዝሙ በታሪካዊና በብሔር ብሔረሰቦች ባህል ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ዘርፍም መሆን አለበት፡፡ ያለውን ክፍተት ለማጥበብ በታሪክ፣ በባህልና ሌሎችም ዘርፎች ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች ሥልጠናውን ይሰጣሉ፡፡ ሁሉም አባሎች የአስጎብኚ ድርጅቶች ባለቤት ይሁኑ እንጂ፣ አስጎብኚዎች የነበሩ ናቸው፡፡ መስክ ላይ ሥልጠና ከሚሰጡ አባላት አንዱም እኔ ነኝ፡፡ አባላቱ ለሥልጠናው ምንም አይከፍሉም፡፡ የየዕለቱን የራሳቸውን ወጪ ብቻ ይችላሉ፡፡ በአንድ ጊዜ ማሠልጠን ስለማይቻል በሁለት ከፍለን እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- ቱሪዝም ዘርፈ ብዙ ኢንዱስትሪ በመሆኑ ስፖርት፣ ኮንፈረንስና ሌሎችም ክንውኖችን መሠረት ያደረገ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ በአገራችን ያለው አካሄድ የተለያዩ አማራጮችን ከመከተል በአንድ ዘርፍ የተወሰነ ይመስላል?

አቶ ንጉሤ፡-አንድ ሰው ከሚኖርበት ከ24 ሰዓት በላይ ከሄደ ወይም እስከ አንድ ዓመት በሄደበት ቦታ ከቆየ ቱሪስት ይባላል፡፡ ቱሪዝምን በብዙ መልኩ ማስኬድ ቢቻልም እኛ በባህላዊ፣ ታሪካዊና የተፈጥሮ ቱሪዝም ውስን ነገሮች ላይ አተኩረናል፡፡ በስፖርት፣ በኮንፈረንስና በብዙ መልኮች ቱሪስትን መሳብ ይቻላል፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን ለአክሱም፣ ለጎንደር፣ ላሊበላ፣ ለሰሜን ፓርክ፣ ለባሌ፣ ለቀይ ቀበሮ፣ ለጭላዳና ለብሔር ብሔረሰቦች ብለው በመምጣት ተወስነዋል፡፡ እዚህ ላይ የእኛ የባለሙያዎቹ ድክመት ይመስለኛል፡፡ የተገኘችውን ብቻ ይዘን ስለምንሄድ ስህተቱን ራሳችንን በመውቀስ መቀበል አለብን፡፡ እኛ ያለንን አላስተዋወቅንም፡፡ ከእኛ ቀጥሎ ደግሞ በዚህ መንገድ ሂዱ በማለት አቅጣጫ ማሳየት ያለበት ኢንዱስትሪውን የሚመራው አካል ሌላውን ድርሻ ይወስዳል፡፡

ሪፖርተር፡- ከማኅበሩ ግቦች አንዱ የአባላቱን ማለትም የአስጎብኚዎችን ጥቅም ማስጠበቅ እንደመሆኑ አስጎብኚዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች የምትፈቱት በምን መንገድ ነው?

አቶ ንጉሤ፡-በብዛት የሚፈትነን ከመንሥት ጋር ያለው ቢሮክራሲ ነው፡፡ ሌላው መስክ ላይ የሚገጥመውና አስጎብኚዎች በግላቸው የሚወጡት ችግር ነው፡፡ ከመንግሥት ጋር በተያያዘ ከብቃት፣ የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ጋር የሚገናኙ ነገሮች አሉ፡፡ እንግዶች ላይ የሆነ ችግር ቢጠፈር ወይም ቱሪስቶች ላይ አንዳች ጉዳት ቢከሰት እነዚህን ከመንግሥት ጋር እናወራለን፡፡ ዘርፉ የተረጋጋ እንዲሆን አስጎብኚዎች ስለችግሮቻቸው በተናጠል ከሚጠይቁ በማኅበር ቢሆን ይመረጣል፡፡ በየመዳረሻው ሰላማዊ የሆነ የቱሪስት ፍሰት እንዲኖር እንዲሁም ቱሪዝም ነክ መረጃዎች ከመንግሥት ወደታች እንዲወርዱ  በማድረግ እንሠራለን፡፡ በማኅበር ከምንጠይቃቸው አንዱ ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ ነገሮች ናቸው፡፡ የማኅበራችን አባል የሆኑ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንጠይቃለን፡፡ ማነቆ ስለሆኑ ነገሮችን ለመወያየት 36 ድርጅት ከሚሄዱ የነሱን ድምፅ የሚያስተጋባና መብታቸውን የሚያስጠብቅ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዕድገት ተብሎ በሚሠራው ሥራ ብዙ ችግሮች ቀርፈናል ማለት እችላለሁ፡፡ ቀድሞ ከመንግሥት ጋር መገናኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ዛሬ ከሚኒስትሮች ጋር እኩል ቁጭ ብለን ስለ አገር እናወራለን፡፡ የምንሰጣቸው ሐሳቦች እንደ አንድ ግብዓት ይቆጠራሉ፡፡ ብዙ የተስተካከሉ እንዳሉ ሁሉ፣ የሚቀሩም አሉ፡፡ ከአገሪቱ ዕድገትና ከቱሪዝም ልማት ጋር በሒደት የሚቀረፉ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ አንዳንዴ የሚመደበው ሰው በተቀያየረ ቁጥር ግብ የሚላቸው ነገሮች ቢቀያየሩም፣ ከዛሬ አሥር ዓመት ወዲህ የመጡት ኃላፊዎች ብዙ ነገር ስላወቁ በተለሳለሰ መንገድ እየሄደ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አለመሟላት ዘርፉን ከሚፈታተኑ ችግሮች አንዱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ ንጉሤ፡-ከትንሹ ችግር ስንጀምር የዛሬ 17 እና 18 ዓመት ሌላው ቀርቶ የፕላስቲክ ውኃ ሳይቀር እዚህ ስለሌለ ከውጪ ይመጣ ነበር፡፡ መንገዶችም አልነበሩም፡፡ ዛሬ  በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች በአብዛኛው የሚያስደስቱ ለውጦች አሉ፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች ተሠርተዋል፡፡ ድሮ መኪና ቢበላሽ ሌላ መኪና ለማግኘት ሌላ ከተማ ይኬድ ነበር፡፡ ዛሬ በእጅ ባለ ስልክ ያሉበት ቦታ ድረስ መኪና ይመጣል፡፡ ቀድሞ በየቦታው ሆቴሎች አልነበሩም፡፡ ዛሬ አንድም ቢሆን ሁለት ሆቴሎች እየተሠሩ ነው፡፡ አሁንም ግን የሚሠሩት ሎጆችና ሆቴሎች በቂ አይደሉም፡፡ ወደ ደቡብ ምሥራቅ ለምሳሌ ወደ ነገሌ ቦረና ለበርድ ዋቺንግ ቢኬድ ሆቴል አለመኖሩ ያስቸግራል፡፡ ራቅ ያለ ቦታ የሚገነቡት ደግሞ የምግብ ችግር አለባቸው፡፡ ጥሩ አብሳይ የላቸውም፡፡ ችግሮቹ በሒደት ይቀረፋሉ በሚል ነው እንጂ አሁን ባለው መልክ የቱሪስት ፍሰቱ ከቀጠለ ችግር ይፈጠራል፡፡ በተለይ በደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ በተወሰነ መልኩ ችግር አለ፡፡ አንዳንዴ ያሉት ሆቴሎችም የማስተወቂያ ብቻ ይሆናሉ፡፡ አንዳንድ ሎጆች ሆቴል ተብለው ብዙ እየተከፈለባቸው ሰፈር ውስጥ እንዳለ ቦታ ይሆናሉ፡፡ ሲሠሩ ደረጃቸውን የጠበቁ ስለመሆናቸው ቁጥጥር ያስፈልጋል፡፡ የሰው ኃይል ችግር ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ የቤቶቹ ባለቤቶች በኩል በአነስተኛ ወጪ ሠርቶ ከፍተኛ ገቢ የማግኘት ነገር አለ፡፡ እስከተከፈለ ድረስ ጥሩ አገልግሎት መገኘት አለበት፡፡ ችግሮቹ ካልታሰበባቸው ትላንት ስናወራ እንደነበረው ለወደፊትም የምናወራበት ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በመዳረሻ ቦታዎች ያለውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ በማድረግ እንዲሁም የየአካባቢውን ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብት እንዲጠበቅ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ በምን መንገድ መስተካከል ይችላል?

አቶ ንጉሤ፡-ትክክል ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ ትልቁ ችግር የባህል ወረራ ነው፡፡ አንዳንድ አገሮች የቱሪስት ፍሰትን ቁጥር ይወስናሉ፡፡ ምክንያቱም ለታሪካቸውና ለተፈጥሮ ሀብታቸው ጥንቃቄ በመውሰድ ነው፡፡ ኖርዝ ፖል አካባቢ ያለችው ቡታን የምትባል አገር ውስን ቱሪስት ብቻ ትቀበላለች፡፡ የሰው እግር የተፈጥሮ ሀብት ይዘቱን ስለሚያበላሽ በዓመት የምትቀበለው ሰው ይወስናል፡፡ በኪሊማንጃሮ ተራራም ተመሳሳይ ነገር አለ፡፡ የሰው ኮቴ አፈር እንዳይሸረሽርና በአካባቢው ያሉ አትክልቶችን ሰው ሲታከክ እንዳይጎዱ ለመከላከል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች አንጻር ስትታይ የቱሪስት ፍሰቱ እንደዚህ አልበዛም፡፡ በመዳረሻ ቦታዎች የነበረው ማኅበረሰብ ቀድሞ በስፋት ተጠቃሚ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ አሁን በየትኛውም መዳረሻ ያለው ማኅበረሰብ በአስጎብኚነት ይሠራል፡፡ የስጦታ ዕቃ በመሸጥ፣ እንደሰሜንና ባሌ ፓርክ በመሰሉት ደግሞ ፈረስ ጫኝ፣ አከራይ፣ ስካውትና አስጎብኚዎችም በማኅበር ተደራጅተው ይጠቀማሉ፡፡ ገቢው ለማኅበራቸው ይሆናል፡፡ የተወሰነ ፐርሰንት ደግሞ የግል አበል ይሆናል፡፡ ከዚህ በፊት ለምሳሌ ቦረና ሲኬድ ሊቦን ላርክ የምትባል ወፍ ለማየት አይከፈልም ነበር፡፡ ዛሬ ግን የዛ አካባቢ ሰዎች በማኅበር ተደራጅተው በበርድ ላይፍ ኢንተርናሽናል ሠልጥነው ወፏን በመፈለግና ከብቶች እዛ አካባቢ እንዳይግጡ በመጠበቅ ይሠራሉ፡፡ በመኪና 25 ብር በሰው 50 ብር እያስከፈሉ ባንክ ያስቀምጣሉ፡፡ ገንዘቡን መከፋፈል ሳይሆን ሱቅ በመክፈት ወይም በሌላ መንገድ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ከዛ በኋላ ድርቅ ወይም ሌላ ችግር በሚመጣበት ጊዜ ድርጅቱ ይጠቀሙበታል፡፡ ለወርቅ አውጪዎች ማኅበርም አንዳንድ ዕርዳታ ያደርጋሉ፡፡ ከ21 ዓመት በፊት ሳይከፈልባቸው የማውቃቸው ቦታዎች ዛሬ ኅብረተሰቡ ይብዛም ይነስም እያስከፈለ ተጠቃሚ እየሆነ ነው፡፡ ትልቁ ችግር ከእኛ ጋር የመረጃ ልውውጥ አለማድረጋቸው ነው፡፡ ለአንድ አካባቢ ጉብኝት ማስከፈል ሲጀምሩ በደብዳቤ ወይም በስልክ አያሳውቁንም፡፡ አስጎብኚዎችን በምንልክበት ጊዜ የሚሰጣቸው ገንዘብና እዛ የሚጠየቁት ገንዘብ ሳይመጣጠን ይቀራል፡፡ ክፍያ መጀመሩ ጥሩ ቢሆንም መረጃ መሰጠት አለበት፡፡ ገንዘብ የሚከፈልባቸው ቦታዎች ላይ ማኅበረሰቡ ተፈጥሯዊ ሀብቱንም ይጠብቃል፡፡ አሁን አደጋ እያመጣ ያለው የተጥሮ ሀብት መጥፋት ነው፡፡ ለደን እንክብካቤ አለማድረግ የሚታይባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ አንዳንድ ቦታዎች የምንከፍለው የተፈጥሮ ሀብቶቹን ከጠበቁ ብቻ ስለሆነ፣ ለውጥ አላቸው፡፡ እየተከፈለም ሰው እንክብካቤ ያጎደለባቸው ቦታዎችም አሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንሞክራለን፡፡ ጎብኚና አስጎብኚም ተመልሶ የሚመጣው ሀብቶቹ እስካሉ ድረስ በመሆኑ ጠብቁ የሚል መልዕክት እናስተላልፋለን፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዲስትሪ ትልቁ ክፍተት የተፈጥሮ ቱሪዝሙ በጣም እየሞተ መሆኑ ነው፡፡ አካባቢዎች በሙሉ ወደ ግጦሽና እርሻ መሬትነት እየተቀየሩ ነው፡፡ ኅብረተሰቡና መንግሥትም ቆም ብሎ ከደን ጭፍጨፋ መታቀብ አለበት፡፡ ልማትም ሲስፋፋ ለተፈጥሮ ሀብት ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዝም ብሎ ከተለጠጠ ነገ ምንድንነው የሚመጣው? የዓለም ሙቀት መጨመር ከካርቦን ልቀትና ከደን መጥፋት የመጣ ነው፡፡ ይህ ወደፊት ለኢትዮጵያም አደጋ ያለው ይመስለኛል፡፡ በአንዳንድ ፓርኮቻችን ሕዝቡ ገቢው ወደእኔ ስለማይመጣ ምን አገባኝ የሚል ነገር አለው፡፡ አዋሽ፣ አቢያታና ነጭ ሳር ችግር ያለባቸው ፓርኮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ መጠበቅ ይቻላል፡፡ የመጠበቁ ነገር ላይ ጅማሮዎች ቢኖሩም ገና ብዙ ይቀራል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም መለዮ ‹‹ላንድ ኦፍ ኦሪጅንስ›› ተብሏል፡፡ ምን ያህል አገሪቷን ገላጭና ቱሪስት ሳቢ ነው?

አቶ ንጉሤ፡-‹‹ላንድ ኦፍ ኦሪጅንስ›› የኢትዮጵያን ተፈጥሮ፣ ባህልና ታሪክ ሦስቱን በአንድ ለመግለጽ ነው፡፡ የሉሲ፣ የቡና የራሷ ፊደል እንዲሁም ብዙ ለየት ያለ ነገር ያላት መሆኗን ያሳያል፡፡ መለዮው ገላጭ ነው፡፡ ለቱሪዝሙ አንድ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ስናስተዋውቅ የነበረው እነዚህን ሀብቶች በመሆኑ፣ መለዮው ተጨማሪ አስተዋዋቂ ይሆናል እላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ በቅርብ ርቀት ያከናውናቸዋል የሚሉትን ዕቅዶች ቢገልጹልን?

አቶ ንጉሤ፡-ለወደፊት አባላት በቱሪዝም ልማት ከኅብረተሰቡ ጋር የተቀናጀ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ አባላትን በመወከል እንደ አንድ ድምፅ በቱሪዝም ልማት ላይ መንቀሳቀስና ለአባላት ምቹ የገበያ ሁኔታ መፍጠርም ይገኝበታል፡፡ አባላት የመንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በሚያዘጋጇቸው ከቱሪዝም ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እናበረታታለን፡፡ በየጊዜው ለአባላት ሥልጠና በመስጠት ለአገራችን ቱሪዝም የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ማስቻል ለሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የያዝነው ዕቅድ ነው፡፡ በየጊዜው ከአገሪቷ ዕድገት ጋር እነዚህ ዓላማዎች ይዳሰሳሉ፡፡

 

Standard (Image)

‹‹የምፎካከረው በአፍሪካ በቅኝ ግዛት ከነበሩና ከገዥዎቻቸውም ዕርዳታ ካገኙ ሪዞርቶች ጋር ነው››

$
0
0

ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ የባቦጋያ ሐይቅ ሪዞርት መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ

 
 ባቦጋያ፣ ቢሾፍቱና ሆራ፣ በቢሾፍቱ በእሳተ ጎመራ የተፈጠሩ ሐይቆች ናቸው፡፡ ሐይቁን እንደቀለበት በከበበው ተራራ ሥር የተቋቋሙት ሪዞርቶች ደግሞ ለመስህብነቱ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በዚህ መልኩ ከተቋቋሙት ሪዞርቶች መካከል፣ የባቦጋያ ሐይቅ ሪዞርት አንዱ ነው፡፡ ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የሪዞርቱ መሥራች፣ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ታደሰ ገብረማርያም በሪዞርቱ እንቅስቃሴ፣ ለቱሪስት መስህብነት ባለው ፋይዳና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የባቦጋያ ሐይቅ ሪዞርትን ለማቋቋም ያነሳሳዎት ምንድነው?

ልጅ ዳንኤል፡-በእውነቱ ከሆነ ሪዞርት አቋቁማለሁ ብዬ አላሰብኩም፡፡ አዲስ አበባ ላይ አዲስ ሸክላ ፋብሪካን በጨረታ ገዝቼ ካርታ ወይም ባለቤትነት ለማግኘት በጣም ስለተቸገርኩና በዚህም የተነሳ ሥራ መፍታት ስላልፈለኩ ቢሾፍቱ ለመጦሪያዬ ያህል ትንሽ ነገር ልሥራ ብዬ አሰብኩ፡፡ ሐሳቤንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚስማማኝን ሥፍራ ለመማተር ባቦጋያ ሐይቅ ሄድኩ፡፡ ቦታውንም ካየሁ በኋላ ከሕዝቡ ጋር ሆኜ ማልማት አለብኝ የሚል ስሜት ተሰማኝና ባለቤቴን አማከርኳት፡፡ ‹ጥሩ ሐሳብ ነው፣ ግፋበት› ብላ አበረታታችኝ፡፡ በዚህም የተነሳ 18 ክፍሎች ያሉት ሎጅ ለመሥራት ከአርክቴክቸሮች ጋር ተነጋገርኩና ጥናቱን ተያያዝነው፡፡ በመካከሉ ከውጭ አገር የመጡ አንዳንድ ወንድሞቼ ሆቴል ብትሠራ ይሻላል አሉኝ፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሥራ ለመሰማራት ጉዳዩ የሚመለከተውን መንግሥታዊ አካል ስንጠይቅ፣ ‹አይ ሥፍራው ለሪዞርት እንጂ ለሆቴልና ለሌላ አይሆንም› አሉኝ፡፡ ብዙም ክርክር ውስጥ አልገባሁም፡፡ ያላችሁት ጥሩ ነው ብዬ እንደገና ወደ ጥናት ገባሁ፡፡ እኔ በሙያ ኢኮኖሚስት ነኝ፡፡ ጥናቱን በማከናውንበት ጊዜ፣ ኅብረተሰቡንም አገሩንም እየረዳን እንድንንቀሳቀስ ሰፋ አድርገን እንሥራው በሚል ቀና ሐሳብ ተነሳስቼ፣ የባቦጋያ ሪዞርትን ለማቋቋም በቃሁ፡፡ ይህን ሪዞርት ለማቋቋም አምስት ዓመት ያህል ፈጅቶብኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህን ያህል ዓመት የፈጀው ለምንድነው?

ልጅ ዳንኤል፡-ባቦጋያ ሐይቅና በዙሪያው ያለው ተራራ በእሳተ ጎመራ አማካይነት የተፈጠረ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ስምጥ ሸለቆ የሚያልፍበት ቦታ ነው፡፡ ይህን በመሰለ ቦታ ላይ ድንገት የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ቢከሰት ግንባታው የመንሸራተት፣ የመሰንጠቅና የመፈራረስ አደጋዎች እንደሚደርስ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ስለሆነም የሕንፃው መሠረት ሲገነባ የተጠቀሱትን አደጋዎች መቋቋም በሚችል መልኩ ነው፡፡ ለዚህም ከፍተኛ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ ሥፍራው በአገር በቀል ዛፎች የተሸፈነ ነው፡፡ ስለሆነም በመስኩ የበሰለ ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች የሰጡትን ምክረ ሐሳብ በመቀበል፣ 75 በመቶ ያህሉ ዛፎች ሳይቆረጡና ሳይጨፈጨፉ ነው ሕንፃው የተገነባው፡፡ ይህን የመሰለ ጥንቃቄ የተሞላበት ሕንፃ ለመገንባት ብዙ ወጪ የጠየቀ ሲሆን፣ ግንባታውም ጥራት ባለው መልኩ ተጠናቋል፡፡ ከዚህም ሌላ በሪዞርቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የሚገኙና ከ60 በላይ የሚሆኑት ልዩ ልዩ ዕፅዋቶች ከውጪ አገር የመጡ ናቸው፡፡ እነዚህን ዕፅዋቶች የበለጠ የሚያደንቋቸው ደግሞ ፈረንጆች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በባቦጋያ ሐይቅ የእርስዎን ጨምሮ ቢያንስ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ ሪዞርቶች ይኖራሉ፡፡ ውድድሩ እንዴት ነው?

ልጅ ዳንኤል፡-እንድትረዳልኝ የምፈልገው ይህንን ሪዞርት ስሠራ በዙሪያው ካሉትና በዚሁ መስክ ከተሰማሩ ወንድሞቻችን ጋር ለመፎካከር አይደለም፡፡ ኬንያ ውስጥ ቦምባሳና ናይሮቢ፣ ዛንዚባር፣ ደቡብ አፍሪካና ማሌዥያ ካሉት ሪዞርቶች ጋር ነው የምፎካከረው፣ የፉክክር አስተሳሰቤን ከኢትዮጵያ ውጪ ነው ያደረኩት፡፡ ይህም በመሆኑ ለሪዞርቱ የሚያስፈልጉትን ወጪዎች ሳወጣ አልደነግጥም፡፡ ምክንያቱም የምፎካከረው ከእኔ በላይ ካሉና ብዙ ልምድ ካላቸው ወይም በቅኝ ግዛት ከነበሩና ከቅኝ ገዥዎቻቸውም ብዙ ዓይነት ዕርዳታ ካገኙት ሪዞርቶች ጋር ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በትምህርትና በስደት ውጪ አገር በቆየሁባቸው ዓመታት ያየኋቸውን አሠራርና አካሄድ ነው እዚህ አምጥቼ ተግባራዊ ያደረኩት፡፡ መንግሥትም ይህንን ተገንዝቦ ከአንዴም ሁለቴ ሽልማት ሰጥቶኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕንፃውን ይዞታና የግቢው ስፋት እንዲሁም ለስንት ሰዎች የሥራ ዕድል እንደፈጠሩ ሊገልጹልኝ ይችላሉ?

ልጅ ዳንኤል፡-ሪዞርቱ በአሁኑ ጊዜ ከ100 በላይ ለሆኑ ወገኖች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ከእነዚህም መካከል እስከ 35 በመቶ ያህሉ የሪዞርቱ ሕንፃ በተገነባበት ወቅት በቀን ሠራተኝነት ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ናቸው፡፡ በልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች በቋሚነት ተመድበው እንዲሠሩ የተደረገውም ሥልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ነው፡፡ ከሠራተኞችም ጋር ያለኝ ግንኙነት በፍቅርና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሕንፃው የተለያየ ደረጃ ያላቸው በአጠቃላይ 50 መኝታ ክፍሎች አሉት፡፡ መኝታ ክፍሎች ውስጥ ሆኖ ሐይቁን ማየት መንፈስን ያረካል፡፡ እንደ ደንቡ ከሆነ በአገር ውስጥ አንድ ሪዞርት ጠቅላላ ግቢው ቢያንስ 25 ሺሕ ካሬ ሜትር መሆን አለበት፡፡ እንደ ኬንያ ከሆነ ደግሞ ከ100 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ ነው፡፡ ሪዞርት ሲባል የፈረስና የጎልፍ ሜዳዎች ይኖረዋል፡፡ አንድ ሰው በሪዞርቱ ግቢ ውስጥ ገብቶ የያዘው መኝታ ክፍል ወይም ካፊቴሪያው ዘንድ ለመድረስ ትንሽ መጓዝ ይኖርበታል፡፡ ሆኖም የእኛ ጠበብ ያለች ናት፡፡

ሪፖርተር፡- የባቦጋያ ሪዞርት ጠቅላላ ግቢ ስንት ሔክታር ነው?

ልጅ ዳንኤል፡-የሪዞርቱ ጠቅላላ ግቢ ስምንት ሺሕ ሔክታር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሪዞርቱ ቅጥር ግቢ ባለው ክፍት ቦታ ላይ የተጀመረው የማስፋፊያ ሥራ ለምን አገልግሎት የሚውል ነው?

ልጅ ዳንኤል፡-ተጨማሪ ሕንፃ ለመገንባት ያሳሰበን ሪዞርቱ የተሟላ ስላልሆነ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ 46 የመኝታ ክፍሎች፤ በአንድ ጊዜ 600 ሰዎችን ለማስተናገድ የሚችል ሁለገብ የስብሰባ አዳራሽ፣ 180 ሰዎችን መያዝ የሚችልና ራሱን የቻለ ሌላ ኮምፕሌክስ አዳራሽ፤ ትምህርታዊና ታሪካዊ ፊልሞች በሳምንት ሦስት ቀን የሚታይበትና ካስፈለገም ጉባዔ ሊካሄድበት የሚችል ሲኒማ ቤትና ካፊቴሪያ እንዲሁም የመዋኛ ሥፍራ የያዘ ባለሁለት ፎቅ የጉባዔ ማዕከል የሚኖረው ይሆናል፡፡ በዚህ ማዕከል ለሚስተናገዱ እስከ አንድ ሺሕ ለሚጠጉ ታዳሚዎች የተሟላ ምግብ የማቅረብ አቅም አለን፡፡ ሪዞርቱ አጠገብ ከሚገኘው 60 ሺሕ ሜትር ካሬ ክፍት ቦታ ውስጥ፣ ስምንት ሺሕ ሜትር ካሬ ያህል በደንቡ መሠረት እንዲሰጠን ጉዳዩ የሚመለከተውን መንግሥታዊ አካል ጠይቀናል፡፡ የመንግሥታዊው አካል ኃላፊዎችም ሪዞርቱ ድረስ መጥተው ቦታውንም ካዩ በኋላ ‹‹ይገባዋል›› ብለው ነበር፡፡ ነገር ግን እስካሁን በተግባር የታየ ነገር የለም፡፡ ጥያቄዬን አላቆምኩም፡፡ አሁንም እየወተወትኩ ነው፡፡ ይህንን ተጨማሪ ቦታ የጠየኩበት ምክንያት ለሜዳ ቴኒስ፣ ለልጆች መጫወቻና ለመኪና ማቆሚያ ለማዋል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለቱሪስት ማረፊያ ወይም መዝናኛ የሚሆኑ ቦታዎች ምን መሆን አለባቸው?

ልጅ ዳንኤል፡-የአንድ አገር ኢኮኖሚው ከፍ የሚለው በኢንዱስትሪ ነው እንላለን፡፡ ሐቁ ግን በቱሪዝም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ከባህል፣ ከሃይማኖትና ከአርኪዎሎጂ ጋር የተያያዘ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዕድገት የምታበረክተው በርካታ ሀብት አላት፡፡ ይህንን ሀብቷን በማሳየት ብቻ በርካታ ዶላር ማግኘት ትችላለች፡፡ አንድ ፋብሪካ ሲሠራ ግን ምናልባት ወደ 100 ሚሊዮን ብር ሊያወጣ ይችላል፡፡ በዚህም ፋብሪካ የሚቀጠረው ቢበዛ 200 ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ የሚገኘው ምርት ገበያ ላይ የሚውለው ከሌላው ዓለም ጋር በመፎካከር ነው፡፡ ቱሪዝም ግን እያንኳኳ ነው የሚመጣው፡፡ የሚሰጥህም ዶላር ነው፡፡ ሆቴልና ቱሪዝም የተያያዘ ነው፡፡ የሚመጣው ቱሪስት ደግሞ በአገሩ ከጠዋት እስከ ማታ ያለውን ጫጫታና ግርግር በመሸሽ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ለሚመጣው ቱሪስት የሚፈልገውን ፀጥታ የማቅረብ ግዴታ ይኖራል፡፡ በዚህም የተነሳ በማንኛውም ሪዞርት ከወፎች ጫጫታ በስተቀር የሙዚቃ ጩኸት ሊኖር አይገባም፡፡ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር ቱሪስት ፀጥታ በሰፈነበትና ነፋሻ አየር ባለበት ሪዞርት ተዝናንቶና አዕምሮውን አስደስቶ ነው መመለስ የሚፈልገው፡፡ በአንዳንድ ሪዞርቶች የሚታየው ግን ከዚህ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ለ24 ሰዓት ሙዚቃ የሚያስጮሁ አሉ፡፡ ዕረፍት አድራጊው ያልጠበቀው ነገር ሲገጥመው እያማረረ ይመለሳል፡፡ ከሌላ ወገን በሚስተጋባው የሙዚቃ ድምፅ ብክለት ሳቢያ የተበሳጩና በእኔ ሪዞርት አልጋ የያዙ ፈረንጆች ሌሊት ተነስተው ገንዘባችንን መልሱ ብለው የሄዱበት ጊዜ አለ፡፡ ይህ ሁኔታ ከአንዴም ሁለቴ፣ ሦስቴ ተደጋግሟል፡፡ ይህ የሚያሳየው የመኝታ ክፍሎቻችን ሳይከራዩ ማደራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ቱሪስቶቹ ይዘው የሚሄዱት አሉታዊ ገጽታ ነው፡፡ በድረገጽ ላይ ‹‹ዘ ቤስት ሆቴል፣ ዘ ቤስት ቤድ ሩም፣ ዘ ቤስት ፉድ፣ በት ሶ ኖይዚ፣ ዊ ካኖት ሬስት›› እያሉ ነው የሚጽፉት፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሙዚቃ ድምፅ ብክለት ባሉባቸው ቦታዎች ሁሉ ክልከላ መደረግ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ይህን መሰል የሙዚቃ ድምፅ ከሚያሰሙት ጎረቤቶቻችሁ ጋር በጉዳዩ ላይ አልተወያያችሁበትም?

ልጅ ዳንኤል፡-እነሱም የራሳቸውን ፍላጎት ነው የሚያዩት፡፡ በዚህ አካባቢ ከሚመጡት ሰዎች የሙዚቃ ድምፅ ለመስማት ፍላጎት ያላቸው አሉ፡፡ ስለሆነም ለሌላው የድምፅ ብክለት ሲሆን ለእነሱ ግን አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ሐይቁ ከብክለት የተጠበቀ እንዲሆን የምታደርጉት ጥንቃቄ እንዴት ይገለጻል?

ልጅ ዳንኤል፡-ሐይቁ ከብክለት የፀዳ እንዲሆን ለማድረግ የበኩላችንን ጥረቶች አድርገናል፡፡ ካደረግናቸውም ጥረቶች መካከል በጋዝ ወይም በቤንዚን የሚንቀሳቀስ ጀልባ ሥራ ላይ እንዳይውል ማገዳችን ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህንንም ያደረግንበት ምክንያት አንደኛ ድምፁ ዓሳዎችን ይረብሻል፡፡ በሐይቁም ዙሪያ የድምፅ ብክለት ይከሰታል፡፡ ዓሳ  እንቁላል ትፈለፍላለች፡፡ ለዚህም ፀጥታ ትፈልጋለች፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ዘይቱ ከጊዜ ብዛት ንፋስና ውኃው ይበከላል፡፡ በዚህም ብክለት የተነሳ ሐይቁ ውስጥ ያሉት ዕፅዋቶች ይሞታሉ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ዓሳ አይኖርም፡፡ ከዚህ ዓይነቶቹ ችግሮች ለመላቀቅ የሚቻለው በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎችን በመጠቀም ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በዚህ ሐይቅ ላይ በአሁኑ ጊዜ እየተንቀሳቀሱ ያሉት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ጀልባዎች ብቻ ናቸው፡፡ ሪዞርቱ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ሁለት ጀልባዎች አሉት፡፡ የባቦጋያ ሐይቅ ርዝመት አንድ ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ ጥልቀቱ ደግሞ 82 ሜትር ነው፡፡ ሐይቁን በጀልባ ለማቋረጥ ቢያንስ 25 ደቂቃ ይፈጃል፡፡

ሪፖርተር፡- ሪዞርቱ ውስጥ ለመዝናናት የሚመጣውን የመግቢያ ታስከፍላላችሁ?

ልጅ ዳንኤል፡-የመግቢያ ክፍያ አይጠየቅም፡፡ በነፃ መግባት ይቻላል፡፡ ማንም ሰው ውስጥ ገብቶ ሌሎችን ካልረበሸ በስተቀር ከፈለገ ማታ ድረስ ሊቀመጥ ይችላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን መብል ይዘን እንግባ ይላሉ፡፡ ምግብ ከውጭ ይዞ መግባት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ይሄ ፓርክ አይደለም፡፡ ሪዞርት ነው፡፡ በግቢው ውስጥ አንድ ሰው በልቶ ቢታመም ተጠያቂው እኛ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- በሪዞርቱ ለመጠቀም አዘውትረው የሚመጡት የትኞቹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው?

ልጅ ዳንኤል፡-በርካታ የአገራችን ሰዎች አዘውትረው ይመጣሉ፡፡ ዛሬ ደስ የሚያሰኘው፣ ሕዝቡ በዕረፍት ጊዜው መዝናናትን እንደባህል አድርጎ መያዙ ነው፡፡ ቅዳሜና እሑድ ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ ከተዝናና በኋላ ሰኞ በአዲስ መንፈስ ወደ ሥራው የሚሰማራ እየበዛ  ነው፡፡ መካከለኛ ገቢ ያለው ኅብረተሰብ እየተፈጠረ ነው፡፡ ይህ ዓይነት ገቢ ያለው ኅብረተሰብ ደገሞ ባንክ ለማስቀመጥ ያሰበውን ገንዘብ እየተዝናናበትም ነው፡፡ ልጆቹን ወስዶ አንድ ጥሩ ነገር ማሳየት ይፈልጋል፡፡ ልጆችም ወጣ ማለትንና መናፈስን እየፈለጉ ነው፡፡ አንዳንድ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለስብሰባ  እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ የውጭ አገር ቱሪስቶችም ያዘወትራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሪዞርቱን ለማቋቋም በተንቀሳቀሱበት ወቅት ከሚመለከታቸው አካላት የነበረውን ድጋፍ እንዴት ይገልጹታል?

ልጅ ዳንኤል፡-በጉምሩክ በኩል ትልቅ እገዛ ተደርጎልናል፡፡ የክልሉ መንግሥትም ያልተቆጠበ ድጋፍ አበርክቶልናል፡፡ ከዚህ በተረፈ በመሬትና በመስፋፋት ጥያቄዎች ላይ ችግሮች አሉ፡፡ በአንድ በኩል ልማት ማስፋፋት ይቻላል ይባላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለልማት የተባለው መሬት ከሌላ ሰው ላይ የሚወሰድ ከሆነ ያ የሚወሰድበት ሰው አስፈላጊው ካሳ ካልተሰጠው አልወጣም ይላል፡፡ ኢንቨስተሩ ደግሞ የቦታ ጥያቄ ጊዜ ወሰደብኝ የትናንት ዶላር ዛሬ ላይ አሻቅቧል ይላል፡፡ ከዚህ አንፃር በዚህ ዙሪያ ትንሽ መሠራትና መስተካከል አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በሪዞርቱ አገልግሎት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ቢያብራሩልን?

ልጅ ዳንኤል፡-የውኃና የኤሌክትሪክ መቋረጥ ትልቁ ችግራችንና ለኪሳራም የዳረገን ነው፡፡ ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ ወዲያውኑ ኃይል የሚሰጥ እንግሊዝ ሠራሽ የሆነና 150 ኬቪ ጄኔሬተር አለን፡፡ በናፍጣ የሚሠራ ሲሆን፣ አንዳንዴ ደግሞ ናፍጣ ይጠፋል፡፡  አዳማና አቃቂ ድረስ ሄደን የምንገዛበት ጊዜ አለ፡፡ ውኃም ላልተወሰነ ጊዜ ከመስመር ይጠፋል፡፡ በዚህ ጊዜ ተራ ገብተን በቦቴ እናስመጣለን፡፡ ለአንድ ቦቴ ውኃ እስከ 2,500 ብር እንከፍላለን፡፡ የጉድጓድ ውኃ ለማውጣት አስበን ነበር፡፡ በአቅም ማነስ ምክንያት ሐሳቡን ተግባራዊ ማድረግ አቅቶናል፡፡ ሌላ ችግራችን እንግዶቻችን ወደ ሪዞርታችን ሲመጡ፣ ጥቂት ልጆች መሀል መንገድ ቆመው በሩ ተዘግቷል፣ ውኃ የለውም የሚሉና ሌሎችም ከእውነት የራቁ የሐሰት መረጃ እየሰጡ እንግዶቻችን እየሰጡ እንዲመለሱ እያደረጉ ናቸው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ኬንያ ላይ እንደሚደረገው ዓይነት ሪዞርቱን እናሳያችሁ ይሉና መኪና ውስጥ ከገቡ በኋላ ተንቀሳቃሽ የኪስ ስልክ (ሞባይል) እና ካሜራ እየሠረቁ ይሰወራሉ፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ ቱሪስቶች መጥፎ ስም ይው እንዲሄዱ እያደረገ ነው፡፡ ይህንን እኩይ አድራጎት ለመከላከል የራሳችንን ሰው ለጥበቃ ብናቆም ተከለከልን፡፡ ሌላው ገና እንደተቋቋምን ለሪዞርቱ የተሰጠው መጠሪያ ‹‹ባቦጋያ ሐይቅ ሪዞርት›› የሚል ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ባቦጋያ ጁስ ቤት፣ ባቦጋያ ቪው ወዘተ የሚባሉ አሉ፡፡ በየትም ዓለም አንድ ስም ሦስት አራት ቦታ ላይ አይኖርም፡፡ ከፍ ብሎ የተዘረዘሩትን ችግሮቻችን ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል አሳውቀናል፡፡ ችግሩ ግን አሁንም እንዳለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሪዞርቱ ባለስንት ኮከብ ነው?

ልጅ ዳንኤል፡-እስካሁን አልሰጡንም፡፡ አሁን ባለን ይዞታ እስከ አምስት ኮከብ ከተቻለ ደግሞ ከአምስት ኮከብ በላይ ነው የምንጠብቀው፡፡

ሪፖርተር፡- በሐይቁ ዙሪያ ያሉት ሪዞርቶች ባለቤቶች በማኅበር ተደራጅታችኋል?

ልጅ ዳንኤል፡-ቀደም ሲል የሆቴል ማኅበር በሚል ተሰባስበን እንንቀሳቀስ ነበር፡፡ ማኅበሩን ለማጠናከር የሚያስችሉ አንዳንድ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ለማስተዋወቅ ተብሎም ገንዘብ አዋጥተን ነበር፡፡ ግን እንደተጠበቀው ሆኖ አልተገኘም፡፡ እንቅስቃሴውም ተዳክሟል፡፡

Standard (Image)

በአርብቶ አደሩ አካባቢ ትምህርትን ተደራሽ የማድረግ ተግዳሮቶች

$
0
0

ከአሳይታ 17 ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው በአፋምቦ ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎች አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ናቸው፡፡ በወረዳው 7 ቀበሌዎች ይገኛሉ፡፡ በአራቱ ቀበሌዎች የሚገኙት ነዋሪዎች አርብቶ አደር ሲሆኑ በሦስቱ ቀበሌዎች የሚኖሩት ደግሞ ከፊል አርብቶ አደር ናቸው፡፡ እነዚህ ቀበሌዎች ከሌሎቹ ቀበሌዎች በተለየ ብዙዎች ተረጋግተው የሚኖሩባቸውና አርሶ አደሮች የሚገኙባቸው በመሆኑ ትምህርትና ሌሎችም መሠረታዊ ፍላጐቶችን ለማዳረስ የተመቹ ናቸው፡፡ ይሁንና በሌሎቹ አራቱ ቀበሌዎች የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለመዘርጋት ነዋሪዎቹ ተረጋግተው የማይቀመጡ በመሆናቸው አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በተለይም ትምህርት ቤት ገንብቶ ማኅበረሰቡን መደበኛ ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ከባድ ነው፡፡ በወረዳው የትምህርት ተደራሽነትን በተመለከተ የወረዳውን ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱ ኑርን ሻሂዳ ሁሴን አነጋግራቸዋለች፡፡

 
ሪፖርተር፡‑ የአካባቢው ነዋሪዎች አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር በመሆናቸው ለትምህርት በቂ ጊዜ ላይኖራቸው እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ይህ በመማር ማስተማሩ ሒደት ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ እየፈጠረ ነው?

አቶ አብዱ፡‑ ከፊል አርብቶ አደርና አርብቶ አደር በሆኑት ሦስቱ ቀበሌዎች የተሻለ የትምህርት ሁኔታ አለ፡፡ ይህም ከትምህርት እንዳያግዳቸው በፈረቃ እንዲማሩ እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን በሌሎቹ አራት ቀበሌዎች ያሉት ሙሉ ለሙሉ አርብቶ አደር በመሆናቸው በአካባቢው ትምህርትን ተደራሽ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በብዛት ተበታትነው ውኃ ወደሚያገኙባቸው አካባቢዎች በመጓዝ ነው የሚኖሩት፡፡ ክረምት አልፎ ትምህርት ማስጀመር ብዙ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ትምህርት መስከረም 2 መጀመር ሲገባው እስከ መስከረም 20 ብሎም እስከ ጥቅምት የምንቆይበት ጊዜያትም አሉ፡፡ ይህ በመማር ማስተማሩ ሒደት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳይፈጥር ትምህርት የሚጀመርበትን ቀን ወደፊት ገፋ እናደርጋለን፡፡ ትምህርት ቤቶችን ሰኔ 30 ላይ ከመዝጋት ይልቅም ሐምሌ 15 የሚዘጋበት አሠራር አበጅተናል፡፡ ከብቶቻቸውን ተከትለው ውኃ ወዳለበት ሥፍራ ስለሚጓዙም የጀመሩት ትምህርት እንዳይቋረጥ ከእነሱ ጋር አብሮ የሚንቀሳቀስ ተለዋጭ ትምህርት ቤትና አንድ መምህር በማዘጋጀት ችግሩን ለመቋቋም ጥረት እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡‑ እነዚህን አማራጭ ትምህርት ቤቶች የምታደራጁት እንዴት እንደሆነ ቢያብራሩልን?

አቶ አብዱ፡‑ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በአራቱ ቀበሌዎች በተወሰኑ ቦታዎች ላይ አሉን፡፡ በመደበኛ ትምህርት ቤቶቹ እየተማሩ ነዋሪዎች በአጋጣሚ ወደ ሌላ ቦታ ሄደው በሚሰፍሩበት ወቅት የጀመሩት ትምህርት እንዳይቋረጥ ከእነሱ ጋር አብሮ የሚኖር የእነሱ ተወላጅ የሆነ አንድ መምህር አብሯቸው በመጓዝ ያስተምራቸዋል፡፡ ትምህርቱን የሚማሩት ልክ እንደመደበኛ ትምህርት ነው፡፡ ደረጃ አንድ፣ ደረጃ ሁለት፣ ደረጃ ሦስት በሚል በደረጃ የተከፋፈለ ሲሆን በአማራጭ ትምህርት ቤት እስከ ደረጃ 3 የተማረ አንድ ልጅ ወደ መደበኛ ትምህርት ለመቀላቀል ብቁ መሆኑን ለማረጋገጥ ተገቢውን የመመዘኛ ፈተና እንዲወስድ ይደረጋል፡፡ በፈተናው ጥሩ ውጤት አስመዝግቦ ካለፈ በመደበኛው የትምህርት ዘርፍ አራተኛ ክፍል ገብቶ ትምህርቱን እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ ይህ የአማራጭ ትምህርት ቤቶች በመላው በክልሉ እየተሠራበት የሚገኝም ነው፡፡

ሪፖርተር፡‑ በወረዳው ምን ያህል ሰዎች ይኖራሉ? ምን ያህል ትምህርት ቤቶችስ አሉ?

አቶ አብዱ፡‑ ባለን የስታትስቲክስ መረጃ መሠረት በወረዳው 32,000 የሚሆኑ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ 16 መደበኛ 10 አማራጭ ትምህርት ቤቶችም አሉ፡፡ አማራጭ ትምህርት ቤቶቹ በብዛት የሚገኙት ራቅ ባሉት ቀበሌዎች ሲሆን በቅርበት በሚገኙ ቀበሌዎችም የተወሰኑ አሉን፡፡ እነዚህን ትምህርት ቤቶች የሚጠቀሙትም ከመደበኛ ትምህርት ቤቶች በኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የሚኖሩ ረጅም ርቀት መጓዝ የማይችሉ ሕፃናት ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡‑ በአማራጭ ትምህርት ቤቶች የምትመድቧቸውን መምህራን እንዴት ነው የምትመለምሉት?

አቶ አብዱ፡‑ ከዚህ ቀደም ከትምህርት ቢሮ ጋር በመነጋገር ከአራተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ የተማሩ፣ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ፣ እንዲሁም አፋርኛ የማስተማር አቅም ያላቸው በአማራጭ ትምህርት ቤቶቹ አስተማሪ ሆነው ይቀጠሩ ነበር፡፡ አሁን ግን አሥረኛ ክፍል የጨረሱ በመምህርነት ሙያ ሠልጥነው ሰርተፊኬት ያገኙ ብቻ እንዲያስተምሩ እየተደረገ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በቀድሞ አሠራር ተቀጥረው ሲያስተምሩ የነበሩትም ትምህርታቸውን እንዲያሻሽሉ ተደርጓል፡፡ ለመምህራኑ በወር 1,300 ብር ይከፈላቸዋል፡፡ ይህ ፕሮግራም ከተጀመረ ከአሥር ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡

ሪፖርተር፡‑ በወረዳው ምን ያህል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችስ ይገኛሉ?

አቶ አብዱ፡‑ በወረዳው16 መደበኛ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ ሦስቱ ትምህርት ቤቶች እስከ ስምንተኛ ክፍል ያስተምራሉ፡፡ የተቀሩት አምስቱ ደግሞ እስከ ስድስትና ሰባተኛ ክፍል ድረስ የሚማሩ ተማሪዎችን ያስተናግዳሉ፡፡ ነገር ግን የተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ ስለነበር እስካሁን ድረስ በወረዳው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አልተገነቡም፡፡ በዓመት 80 የሚሆኑ ተማሪዎች ብቻ ነበሩ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚያልፉት፡፡ ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል ወደ ሌላ ወረዳዎች ሄደው ለመማር አቅሙ የሌላቸው አብዛኞቹ ትምህርታቸውን ያቋርጡ ነበር፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ግን ወረዳው በጀት መድቦ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ከ70 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን ቀለብና የቤት ኪራይ ከፍሎ እያስተማረ ይገኛል፡፡ እነዚህ ልጆች የሚማሩት በአሳይታ ከተማ በሚገኘው አህመድ አንፍሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ለአንድ ተማሪ በወር እስከ 400 ብር ተመድቧል፡፡ ከዚህ ቀደም በወረዳው የነበሩት ሁለት መደበኛ ትምህርት ቤቶች ብቻ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን 16 መደበኛ ትምህርት ቤቶች 10 አማራጭ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆኜ ስመጣ አጠቃላይ የነበረው የተማሪዎች ቁጥር 1,000 ብቻ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ቁጥር ከ3,000 በልጧል፡፡

ሪፖርተር፡‑ አማራጭ ትምህርት ቤቶቹ የሚያስፈልጓቸውን የትምህርት ግብአት የማሟላት ነገር ምን ይመስላል?

አቶ አብዱ፡‑ ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑ መጻሕፍት፣ ሰሌዳ እንዲሁም መቀመጫ አዘጋጅተን በየአማራጭ ትምህርት ቤቶቹ እንልካለን፡፡ ለተሽከርካሪ የሚሆን መንገድ ባለመኖሩ ግብአቶቹን የምንልከው በግመል ነው፡፡ ግብአቶቹን በግመል ለመጫን ደግሞ አስቸጋሪ ነው፡፡ በመሆኑም አመቺ በሆነ መልኩ አነስተኛ ሰሌዳዎችና መቀመጫ የሚሆኑ ትንንሽ ኩርሲዎች አዘጋጅተን ነው ምንልከው፡፡ ተማሪዎቹም ብዙ ጊዜ ጥላ ሥር ሆነው ይማራሉ፡፡ ፀሐይ በሚበረታበት ጊዜ ደግሞ አፈራሪ የሚባል ዳስ አላቸው፡፡ እሱን ዘርግተው ይማራሉ፡፡ በወረዳው ያለው የትምህርት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ማሻሻያዎች ለማድረግ ብዙ ድጋፎች ይፈልጋል፡፡ የተማሪዎች ቁጥር በ3,000 ብቻ መወሰን አልነበረበትም፡፡ ከዚህ በላይ መሆን ነበረበት፡፡ ባለው የመማሪያ ክፍሎች የመምህራንና የትምህርት ግብአቶች እጥረት በየዓመቱ 90 የሚሆኑ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡‑ ተማሪዎቹ ትምህርት እንዳያቋርጡ የሚደረግ ጥረት ካለ?

አቶ አብዱ፡‑ የተለያዩ ሙከራዎች አድርገናል ነገር ግን አልተሳካም፡፡ ለምሳሌ ልክ በሁለተኛ ደረጃ እንዳደረግነው ከወረዳው በጀት በመመደብ ተማሪዎቹ ወደ ማዕከል መጥተው ቤት ተዘጋጅቶላቸው እንዲማሩ ለማድረግ ተሞክሮ ነበር፡፡ ከአንድ ቀበሌ 10 የአራተኛ ክፍል ተማሪዎችን አሰባስበን ፕሮግራሙን ጀምረን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አልተሳካልንም፡፡ ቤተሰብ ናፈቀን እያሉ ሁሉም ተበታተኑ፡፡ ትልቁ መፍትሔ ብለን የያዝነው ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ አዳሪ ትምህርት ቤት መገንባት ነው፡፡ ከወረዳው ጋር በመነጋገርም ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ማስተማር የሚችል አዳሪ ትምህርት ቤት ለመገንባት ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች በማፈላለግ ላይ ነን፡፡

ሪፖርተር፡‑ በአማራጭ ትምህርት ቤቶቹ የታሰበውን ያህል ውጤት ማየት ተችሏል? አስፋፍቶ የመቀጠል ሐሳብስ አላችሁ?

አቶ አብዱ፡‑ ተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋት ሐሳብ የለንም፡፡ ጥረታችን ቁጥራቸውን ለመቀነስ ነው፡፡ ፍላጐታችን ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰውን የአፋር ማኅበረሰብ በአንድ ቦታ ተረጋግቶ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ አርብቶ አደር በመሆኑ የሚፈልገው ሣርና ውኃ ነው፡፡ ስለዚህም ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በአንድ ቀበሌ ውስጥ የገበያ ማዕከል በመገንባት፣ ውኃና ሣር የሚያገኙበትን ቦታ አዘጋጅተን በአካባቢው እንዲሰፍሩ ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ በ1 ሚሊዮን ብር በጀት የግጦሽ መሬት ተዘጋጅቷል፡፡ በመጪው ዓመት መጀመሪያ ላይም ሥራ ይጀምራል፡፡ ይህም በአንድ በተወሰነ ቦታ እንዲኖሩ የሚያደርግና በመደበኛ ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ የሚያስችል ነው፡፡ በአማራጭ ትምህርት ቤቶች ማኅበረሰቡ አርብቶ አደር ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ፊደል እንዲቆጥር ማድረግ ተችሏል፡፡ በአማራጭ ትምህርት ቤቶች ተምረው አስተማሪ የሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ በየዓመቱም 20 የሚሆኑ በአማራጭ ትምህርት ቤት የተማሩ ተማሪዎች ወደ መደበኛው የትምህርት ዘርፍ እየተቀላቀሉ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡‑ ተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤቶቹ ላይ ቁጥጥር የምታደርጉበት አሠራርስ አላችሁ?

አቶ አብዱ፡‑ በወረዳው አራት የክላስተር ማዕከላት አሉ፡፡ እነሱም በየወሩ ወደ ትምህርት ቤቶቹ እየሄዱ ግምገማ ያደርጋሉ፡፡ በተጨማሪም የወረዳው ካቢኔ አባላት በሥራቸው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን እየጐበኙ በየሳምንቱ ሐሙስ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ የዳጉ ሥርዓትም በየአካባቢው ያለውን እንቅስቃሴ በቀላሉ እንድናውቅና ለችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ እንድንሰጥ ያስችለናል፡፡

ሪፖርተር፡‑ በድርቁ ወቅት በትምህርት ቤቶች አካባቢ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? የመማር ማስተማሩ ሒደት እንዳይስተጓጐልስ ምን አድርጋችኋል?

አቶ አብዱ፡‑ አቢሀይክ በምትባል ቀበሌ ውስጥ አንድ ተለዋጭ ትምህርት ቤት ነበረን፡፡ በትምህርት ቤቱ ይማሩ ከነበሩ 58 ተማሪዎች መካከል 38 የሚሆኑት በድርቁ ተፈናቅለው ሄዱ፡፡ ስለሁኔታው አፋጣኝ መረጃ ደረሰን፡፡ ወዲያው ያሉበት ቦታ ድረስ በመሄድ መፍትሔ መስጠት ችለናል፡፡ በሁለት አካባቢዎች ላይም ከፍተኛ የውኃ ችግር አጋጥሞን ነበር፡፡ ቦታው ላይ ተረባርበን ውኃ በቦቴ በማስገባት፣ ምግብ በማቅረብ አንድም ተማሪ በድርቁ ከትምህርት እንዳይስተጓጐል ለማድረግ ሞክረናል፡፡

ሪፖርተር፡‑ ሥራችሁን ለመሥራት ፈታኝ የሆኑ ሌሎች ችግሮች ምን ምን ናቸው?

አቶ አብዱ፡‑ በአፋምቦ ወረዳ ከፍተኛ የሆነ የንፁህ ውኃ ችግር አለ፡፡ አንድን ቀበሌ ከሌላው የሚያገናኙ የገጠር መንገዶችም የሉም፡፡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ እስከ 70 ኪሎ ሜትሮች በእግር ለመጓዝ ግድ ነው፡፡ የግጦሽ መሬት እጦትም የወረዳዋ ትልቁ ችግር ነው፡፡    

Standard (Image)

‹‹ውበትን የሚመልስ ሕክምና እንሰጣለን››

$
0
0

ዶ/ር አንተነህ ተስፋዬ ሮባ፣ የዚኒያ ኤስቴቲክ ኤንድ አንታይ ኤጂንግ ክሊኒክ ሜዲካል ዳይሬክተር

ዶ/ር አንተነህ ተስፋዬ ሮባ የኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ በተለይ በጤናው ዘርፍ የተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ከሥራ ባልደረባቸው ወይዘሪት ሰብለ ነብየልዑል ጋር በመሆን አሜሪካ ያካበቱትን ዕውቀትና ሀብት ለኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ለማካፈል እየሠሩ ሲሆን፣ የሚያደርጓቸውን አትራፊ ያልሆኑ ሥራዎች ቀጣይና ራስን በራስ ለማገዝ ዚኒያ ኤስቴቲክ ኤንድ አንታይ ኤጂንግ ክሊኒክ ከፍተው ሰዎች በሕመም ወይም በአየር ንብረት ለውጥ ያጡትን የፊት ውበት መልሶ ለማላበስ፣ ውፍረትን ለማከም በውፍረት ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን ለመከላከል ወይም ለማቆም፣ ያለዕድሜ የሚመጣ እርጅናን በማከምና በስንፈተ ወሲብ ላይ ዘመን አመጣሽ የሕክምና ቴክኖሎጂ በጠቀም አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ዶ/ር አንተነህ የክሊኒኩ ሜዲካል ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ወይዘሪት ሰብለ ደግሞ ኦፕሬቲንግ ማናጀር ናቸው፡፡ በአገልግሎቱ ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚኒያ ኤስቴቲክ ኤንድ አንታይ ኤጂንግ ክሊኒክ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር አንተነህ፡‑ቁንጅናና ቁንጅናን የሚያበላሹ ከጤና እንዲሁም ከአየር ፀባይ አለመስማማት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ማከም ነው፡፡ ከዕድሜ፣ ከአኗኗር፣ ከአመጋገብ ከመጠጥና ከሲጋራ ከስኳር፣ ከካንሰር፣ ከደም ብዛትና ከሌሎች ሕመሞች ጋር ተያይዞ የደከመና የተጎዳ ቆዳን ማከም ነው፡፡ አንዳንዴ ከሆርሞን መዛባት ጋር ተያይዞ ሰዎች ካለዕድሜያቸው ያረጃሉ፡፡ ሆርሞኖች በተለያየ ምክንያት ያለጊዜያቸው የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠት ሲያቆሙ ፊትን ያስረጃሉ፡፡ ይህንን ሁሉ በሕክምና በማስተካከል የአንድን ሰው ጤናና ውበት ለመጠበቅ ይቻላል፡፡ ክሊኒካችንም ውበትን በመጠበቅ፣ ያለጊዜ የሚከሰት ዕርጅናን ለመከላከል ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በውፍረት ሕክምና ላይ እንሠራለን፡፡ የውፍረት ችግር ኢትዮጵያም፣ አሜሪካም ሆነ አውሮፓ አለ፡፡ ዓለም አቀፍ ችግርና ወደፊትም ኢኮኖሚን የሚጎዳ መሆኑ ታውቋል፡፡ በውፍረት ምክንያትም ብዙ በሽታዎች ይመጣሉ፡፡

ሪፖርተር፡‑ ውፍረትን ለመከላከል ምን ዓይነት ሕክምና አላችሁ?

ዶ/ር አንተነህ፡‑ኢትዮጵያ ከመጣን በኋላ የውፍረት ችግር አይተናል፡፡ የአላስፈላጊ ስቦች መከማቸትና ቦርጭ የብዙዎች ችግር ሆኗል፡፡ ውፍረትን በአመጋገብና አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ እንዲሁም በሕክምና መቀነስና ማስተካከል ብሎም የወደፊት ሕይወትን ከውፍረት ጋር ተያይዘው ከሚመጡ በሽታዎች መከላከል ይቻላል፡፡ ውፍረት ሲያስቸግር፣ ለጤና ጠንቅም ሲሆን በመድኃኒት መቆጣጠር የምንችልበትን ሕክምና ክሊኒካችን ይሰጣል፡፡ ቀድመን እንዴት መከላከል እንደምንችልም ጭምር አንድ ሰው ጮማው ወይም ስቡ አንድ ቦታ ላይ ሲበዛ እንቀንሳለን ወይም እናስተካክላለን፡፡ የተጨማደደ ቦታን ያለ ቀዶ ሕክምና ወይም በቀዶ ሕክምና እናክማለን፡፡ ወደፊት ለማምጣት የምንፈልገው ደግሞ ሪጀነሬቲቭ ሜድስን ነው፡፡

ሪፖርተር፡‑ ሪጀነሬቲቭ ሜድስን ምን ማለት ነው?

ዶ/ር አንተነህ፡‑ሴሎችን መልሶ አክሞ የተጎዳ የሰውነት ክፍልን ማከም ወይም መጠገን ማለት ነው፡፡ ሕክምናው አንዳንዴ በአንድ ጊዜ የሚያድን ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሕክምና አንድ በሽታ ከያዘ በሽታውን በመድኃኒት ማከም፣ እንዳይባባስ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ በሪጀነሬቲቭ ሜድስን ግን በቋሚ ደረጃ የማዳን ዕድል አለ፡፡ ዘርፉ አዲስ ቢሆንም፣ በሕክምናው ዘርፍ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡ በዚህ ሕክምና ስር ስቴም ሴልና ፒአርፒ የሚባሉ የሕክምና ቴክኖሎጂዎች አሉ፡፡ በስቴም ሴል ሕክምና የሞቱ ሴሌችን መተካት እንችላለን፡፡ የስቴም ሴል ሳይንስም የወደፊት ሕክምና ልቀት ነው፡፡ እስከዛሬ የምናደርገው ሕክምና በሽታን አያስቀለብስም፣ ይቀጥላል፡፡ ለምሳሌ ደም ብዛት ላለው ሰው ባለበት እንቆጣጠራለን እንጂ አናድንም፡፡ በስቴም ሴል ግን በሽታውን ማዳን ይቻላል፡፡ ይህ ሳይንስ ወደፊት የሚመጣ ነው፡፡ አሁን ላይ የተራቀቀ ስቴም ሴል ሕክምና ውስጥ ባንገባም የተወሰኑ ችግሮችን ለማከም እንጠቀምበታለን፡፡

ሪፖርተር፡‑ ምን ዓይነት ሕመሞችን?

ዶ/ር አንተነህ፡‑ አሜሪካ ውስጥ ያለው ዚኒያ ኤስቴቲክ ኤንድ አንታይ ኤጂንግ ክሊኒክ ስንፈተ ወሲብና ስኳር በሽታን ለማከም ፈቃድ አለው፡፡ እነዚህን አገልግሎቶች እንሰጣለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለውም ቅርንጫፍ፣ አሜሪካ ውስጥ የምንጠቀመውን ፕሮቶኮል አምጥተነዋል፡፡ እንደ ስቴም ሴል ሕክምና ባይራቀቅም ተመሳሳይ አሠራር የሆነውን ፒአርፒ እንተገብራለን፡፡ በዚህ ሕክምና የተጎዳ አካልን እናክማለን፡፡ ለምሳሌ ስንፈተ ወሲብን እያከምንበት ነው፡፡ ብዙዎችም ለውጥ ማምጣታቸውን ነግረውናል፡፡ ከዚህኛው በበለጠ ስቴም ሴልን ሙሉ ለሙሉ ስንተገብር ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ ለስኳር በሽታ የተራቀቀ መሣሪያ ስለሚፈልግና በእኛ በኩልም ገና ዝግጅት ላይ ስለሆንን ለጊዜው ባይኖረንም፣ ወደፊት አገልግሎቱን ለመስጠት እንፈልጋለን፡፡ ለዚህ መንግሥት ከተባበረን ብዙዎችን ከስኳር ሕመማቸው መታደግ እንችላለን፡፡ አሜሪካ ውስጥ የምንሰጠው የስቴም ሴል ሕክምና የስኳር ሕሙማን ሙሉ ለሙሉ ከሕመማቸው እንዲፈወሱ መድኃኒት ሳይጠቀሙ እንዲቆጣጠሩ፣ መድኃኒት እንዲቀንሱም አስችሏል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈቀደልን ራሴም ሥልጠናውን ወስጄና ሌሎች ባለሙያዎችንም አምጥቼ ልሠራው እችላለሁ፡፡ ስንፈተ ወሲብንም ሆነ ሌሎች በሽታዎችን ለማዳን ስቴም ሴል ሕክምና አዋጭ ነው፡፡ አሜሪካ ውስጥ በስንፈተ ወሲብ ላይ የሚደረገው የስቴም ሴል ሕክምና ከ90 በመቶ በላይ መፍትሔ ይሰጣል፡፡ ይህን ቴክኖሎጂ ወደፊት እናመጣዋለን፡፡ አሁን ላይ በመለስተኛ ቴክኖሎጂ አገልግሎቱን እየሰጠን ነው፡፡ ወደ ክሊኒካችን በብዛት የሚመጡት  የስንፈተ ወሲብ ችግር ያለባቸው ቢሆኑም፣ አጥንት፣ ፀጉር፣ ፊት ላይ ላሉ ችግሮች ሕክምናውን እንሰጣለን፡፡ ስንፈተ ወሲብን በተመለከተ የሚመጡት ወንዶች ናቸው፡፡ ሴቶች ከባህሉ ጋር ተያይዞም ሊሆን ይችላል እየመጡ አይደለም፡፡ ቫያግራ እየተጠቀሙ ስንፈተ ወሲብ ያለባቸውን ጨምሮ ሌሎችም በሰጠናቸው ሕክምና ለውጥ ማግኘታቸውን ነግረውናል፡፡ መገጣጠሚያ አካላት ላይ ያሉ ሕመሞችን ደግሞ በሕክምናው ሙሉ ለሙሉ ማዳን ይቻላል፡፡ የፀጉር መሳሳትን በማቆም ፀጉርን መልሶ ማበልፀግ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡‑ ስንፈተ ወሲብ ከውስጥ ሕመም፣ ከሱስ ወይም ከስነ ልቦና ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ የምትሰጡት ሕክምና የትኛውን ያገናዘበ ነው?

ዶ/ር አንተነህ፡‑ ለሕክምናው የሚመጡ ሰዎች ችግራቸው ከሳይኮሎጂ፣ ከሱስ ወይም ከውስጥ በሽታዎች ጋር መሆኑን ለማረጋገጥ የሚሞሉት መጠይቅ፣ በኋላም የሕክምና ምርመራ አለ፡፡ የሳይኮሎጂ ከሆነ ሊረዱ ወደሚችሉበት እንጠቁማለን፡፡ አንዳንዱ ከኮሌስትሮል ብዛትና ከሎሎች የውስጥ ችግሮች ጋር ተያይዞ ስንፈተ ወሲብ ያጋጥመዋል፡፡ ለምሳሌ በኮሌስትሮል የመጣ ከሆነ ኮሌስትሮሉ ወደ መደበኛ እንዲመለስ የሚያደርግ ሕክምና አለ፡፡ ከዚያ ስንፈተ ወሲቡ ይታከማል፡፡

ሪፖርተር፡‑ የፊት ውበት፣ የመገጣጠሚያ አጥንት ሕመም፣ ስንፈተ ወሲብ፣ ያለጊዜ የመጣ እርጅናም ሆነ የስብ መከማቸት ወይም ውፍረት ላይ ለምትሰጡት አገልግሎት ቅድመ ምርመራ አለ?

ዶ/ር አንተነህ፡‑ አዎ፡፡ የፊት ቆዳ ችግሮችን በሕክምና መርዳት ከመጀመራችን በፊት የተገልጋዩን የፊት ገፅ በፎቶ ወስደን ማሽን ላይ በተገጠሙ የተራቀቁ ሶፍትዌሮች እያንዳንዱ የፊት ቆዳ ያለበት ችግርና ምን ዓይነት ሕክምና እንደሚያስፈልገው እናያለን፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ሕክምና የሚጀመረው፡፡ አንድ ሰው ለመክሳት ቢመጣ፣ መጀመሪያ የክብደት መቀነስ ሕክምና ከመጀመሩ በፊት ለምን ውፍረት እንደተከሰተ እንመረምራለን፡፡ ውፍረት የሚቀነሰው ለውበት ብቻ ተብሎ አይደለም፡፡ ውፍረት ከውበት ማበላሸት ባለፈም የጤና ጠንቅ ነው፡፡ እኛም በሕክምና የታገዘ የክብደት መጠን ማስተካከል አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሠለጠነው ዓለም ውፍረትን እንደ ስኳርና ደም ብዛት በሽታ አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡ እኛም ውፍረትን የምናየው ከበሽታ አንፃር ነው፡፡ ሰውነት ውስጥ የተከማቸ ስብ በሽታ ሲሆን፣ ጡንቻ መኖሩ ለጤና ወሳኝ ነው፡፡ ያለጥንቃቄ መክሳት የሚጎዳው ጡንቻን ስለሆነ አይመከርም፡፡ የሐኪም ምክር ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው በዳይት የከሳ መስሎት ተመልሶ ወደመደበኛ ምግቡ ሲገባ፣ ሰውነቱ በጣም የሚጨምረው፣ በዳይቱ በሰውነቱ የተከማቸውን ስብ ሳይሆን ጡንቻ ስላቃጠለ ነው፡፡ ጡንቻ የሌለው ሰው ስብን ማቃጠል አይችልም፡፡ እኛ ጋር ክብደት ለመቀነስ የሚመጣ ሰው፣ ደሙን ይመረመራል፣ የሆርሞን መዛባት ካለ እንዲስተካከል ይደረጋል፡፡ የተዛባ ሆርሞን ያለው ሰው ቀን ሙሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቢያደርግ አይከሳም፡፡ ሰዎች ውፍረት ለመቀነስ ሕክምና ከመጀመራቸው በፊት በሰውነታቸው ውስጥ፣ ምን ያህል ውኃ፣ ስብ (ጮማ)፣ አጥንት፣ ስቡ ያለው በቆዳ ውስጥ ነው ወይስ ልብ፣ ኩላሊት ወይም ጉበት ላይ የሚሉት በምርመራ ይረጋገጣሉ፡፡ በምርመራው መሠረት የሚቀንሰው እንዲቀንስ፣ የሚጨምረው እንዲጨምር ሕክምናውን እንጀምራለን፡፡ በአካላዊ ብቃት የታገዘ ዳይት እንዲጀምሩ ሲደረግም፣ ስኳር፣ ደም ብዛትና ሌሎች ችግሮች ታይተውና ታሳቢ ተደርገው ነው፡፡ የተቀናጀ ክብደትን የመቀነስ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠን ነው፡፡ በየጊዜው እየተከታተልንም ስቡ እንዲጠፋ፣ ጡንቻ እንዲጠነክር እናደርጋለን፡፡ በጣም አደገኛው ስብ በልብ፣ በጉበት እንዲሁም በኩላሊት ላይ የሚከሰተው ነው፡፡ ይህ ሰዎችን ለተለያዩ በሽታዎች ይዳርጋል፡፡ እኛ እነዚህ ከተከሰቱ የሚወገዱበት፣ ካልተከሰቱ እንዴት ጠብቆ መቆየት እንደሚቻል ሕክምናውን ከአሜሪካ ይዘን መጥተናል፡፡ የተሟሉ ዘመናዊ መሣሪያዎችም አሉን፡፡ ክብደት መቀነስ በሕክምና የመታገዙ ጥቅምም ከስኳር፣ ከደም ብዛትና ከሌሎች ሕመሞች ለመታደግ ማስቻሉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡‑ ከምትሰጡት ሕክምና ጋር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አብሮ አለ?

ዶ/ር አንተነህ፡‑ ወደፊት ምኞታችን እሱ ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ችግር የራሱ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ ብረት ማንሳት ውፍረትን ለመቆጣጠር ወሳኝ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ ሴቶች አይመስላቸውም፡፡ ጡንቻን ማዳበር ውፍረትን ለመቆጣጠር፣ ጤነኛ ለመሆን፣ ወደፊት እርጅና ሲመጣ መገጣጠሚያ ላይ ችግር እንዳይፈጠር ያግዛል፡፡ እርጅና ሲመጣ ወገቤን አመመኝ፣ እግሬ አላስነሳ አለ የሚባሉት ሁሉ የሚመጡት መጀመሪያውኑ ጡንቻ ስላልጠነከረ ነው፡፡ የአካል ብቃት ሲደረግ ለማን ምን ዓይነት? ለምን ያህል ሰዓት? የሚሉት መለየት አለባቸው፡፡ ወደፊት የራሳችን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጊያ ይኖረናል፡፡ አሁን ላይ ጂም መሄድ ለማይችሉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንነግራለን፡፡ መሄድ የሚችሉት ደግሞ አሠልጣኛቸውን እንዲያገናኙን አድርገን፣ ምን ዓይነት እንቅስቃሴ ማሠራት እንዳለበት/ባት እንነጋገራለን፡፡

ሪፖርተር፡‑ ውፍረታቸው ቀንሶ ቆዳቸው ለሚንዘላዘል ሰዎች የምትሰጡት ሕክምና አለ?

ዶ/ር አንተነህ፡‑አዎ፡፡ የተንዘላዘለ ቆዳ ሲኖር ሬዲዮፍሪኩዌንሲ የተባለ የተሸበሸበ ቆዳን የሚያስተካክል ሕክምና አለን፡፡ ሆኖም ከትልቅ ኪሎ ወደ ዝቅተኛ የሚገባ ሰው የሚንዘላዘለው የሰውነት ክፍሉ ከበዛ በሬዲዮፍሪኩዌንሲ ማስተካከል አይቻልም፡፡ ቀዶ ሕክምና ነው፡፡ ሆኖም ቆዳቸው በተለያየ ምክያት የተለጠጠ ሰዎች ሲከሱ የተንዘላዘለው የቆዳ ክፍል ብዙ ካልሆነ በሬዲዮፍሪኩዌንሲ እናስተካክለዋለን፡፡ ይህን ሕክምና እየሰጠን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡‑ ሰውነት ላይ የተከማቸ ስብን ያለቀዶ ሕክምና የምታስወግዱበት መሣሪያ አላችሁ? ለምሳሌ ቦርጭ፣ በሰውነት ጎንና ጎን ተርፈው የሚመጡ ስቦችን እንዴት ያለቀዶ ሕክምና ታጠፋላችሁ?

ዶ/ር አንተነህ፡‑አሜሪካ ብዙዎቹ ሰዎች የተትረፈረፈ አካላቸውን ያለቀዶ ሕክምና ማስወገድ ይመርጣሉ፡፡ ለዚህም ኩል ስክራፕቲንግ ማለትም ያለቀዶ ሕክምና ስብን የሚያስወግድ መሣሪያ አለ፡፡ በክሊኒካችንም መሣሪያውን ተጠቅመን አገልግሎቱን እየሰጠን ነው፡፡

ሪፖርተር፡‑ የፊት ውበት የውስጥ ጤንነት መገለጫ ሲሆን፣ ውፍረትም አስከትሎ የሚመጣቸው የጤና እክሎች አሉ፡፡ እዚህ ላይ ያለው ግንዛቤ እንዴት ነው?

ዶ/ር አንተነህ፡‑ብዙዎቹ የውስጥ ሕመሞች ፊት ላይ ይገለጻሉ፡፡ ለዚህ ነው ክሊኒካችን ውበትን ለመጠበቅና ካለዕድሜ የሚመጣ እርጅናን ለመከላከል በሕክምና የታገዘ አገልግሎት እየሰጠ ያለው፡፡ ለምሳሌ ብጉር ፊት ያበላሻል፣ ውበትን ያጠፋል፡፡ በዛው ልክ መታከም ያለበት ሕመም ነው፡፡ ብጉርን አክመን ማዳን እንችላለን፡፡ ብጉሩ ታክሞ ሲድን፣ የተበላሸ ፊትም መልሶ ውበት ይላበሳል፡፡ ውበትና ሕክምናን አጣምረን ነው የምንሠራው፡፡ በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት የፊታቸው ቆዳ የተጎዳ ሰዎችንም እናክማለን፡፡ ሙሉ ለሙሉ ማዳን የማይቻልባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ ማሻሻል ይቻላል፡፡ በበሽታ ምክንያት የሰረጎዱና ወዛቸው ጠፍቶ የተበላሹ ጉንጮችንም ማስተካከል እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡‑ በውጭ ዓለም እናንተ የምትሰጧቸው የውበት ሕክምናዎች ውድ ናቸው፡፡ እዚህ ስታመጡት ዋጋው እንዴት ነው?

ዶ/ር አንተነህ፡‑ እዚህም ትንሽ ይወደዳል፡፡ ከመርፌ አንስቶ ያለን ማሽን በሙሉ ከአሜሪካ የመጣ ነው፡፡ እዛም በውድ የሚገዛ ነው፡፡ አገር ውስጥ ሲገባ ደግሞ የትራንስፖርቱ አለ፡፡ ከሁሉም በላይ 81 በመቶ ታክስ እንከፍላለን፡፡ ሥራችን ከኮስሞቲክስ ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከሕክምናና ከሕክምና መድኃኒቶች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሆኖም በሜዲካል ደረጃ የምንሰጠው አገልግሎት እንደኮስሞቲክ ተቆጥሮ ከፍተኛ ግብር እንከፍላለን፡፡ በሌላ በኩል አገልግሎት እየሰጠን እንጂ ለሕክምናው የሚውሉ መድኃኒቶችን እየሸጥን አይደለንም፡፡ በአሜሪካ ቀድመን ከተማርነው የሕክምና ትምህርት በተጨማሪ ለእያንዳንዷ ተጨማሪ ትምህርት ብዙ ሺሕ ዶላር ከፍለን ሥልጠና ወስደናል፡፡

ወይዘሪት ሰብለ፡- አሜሪካ ቆይተን አገራችን ለመሥራት ስንመጣ፣ አገር መርዳት አለብን ባልነው ዘርፍ እየረዳን ነው፡፡ ዚኒያ ኤስቴቲክ ኤንድ አንታይ ኤጂንግ ክሊኒኩን የከፈትነው ለትርፍ ብሎም ከሚገኘው ትርፍ ቀድመን የከፈትነውን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጀትና በትምህርት ቤት የተጀመረውን የተማሪዎች ምገባ ለማጠናከር ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም አብዛኛውን እገዛ ያደረግነው ከኪሳችን አውጥተን ነው፡፡ ከሌሎች ትንሽ እገዛ ቢኖርም በተለይ ዶ/ር አንተነህ አሜሪካ እየሠራ፣ የሠራበትን እዚህ እያወጣ ነው፡፡ ይህ ለአገራችን የምናደርገው ስጦታ ነው፡፡ በአገር ውስጥ የተጎዱ ዜጎችን ማገዝ ለእኛ ትርጉም አለው፡፡ ሆኖም አንዱን በአንዱ ለመደገፍ በሚከፈቱ አገልግሎቶች ላይ ትልቅ ታክስ በተጫነ ቁጥር አገልግሎት ፈላጊው ላይ ዋጋ ይጫናል፣ በሌላ በኩል ያሰብናቸውን ለኅብረተሰቡ የሚውሉ ፕሮጀክቶች ራሳችን በራሳችን ለመደገፍ እንቸገራለን፡፡ እኔ ሥራዬን ትቼ መጥቻለሁ፡፡ በአገራችን ቀጣይነት ያለውና በሕዝቡ ላይ ለውጥ ያለው ሥራ መሥራት እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ ቀደም ኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አፍሪካ በሚለው ድርጅታችን ሰሜን ሸዋ ዘመሮ የሚባል አካባቢ የሕክምና ጓድ ይዘን ከ300 ለማያንሱ የዓይን ሕመም ላለባቸው ሰዎች ቀዶ ሕክምና አድርገን ዓይናቸው እንዲያይ አድርገናል፡፡ የካቲት 12 ሆስፒታል የጨቅላ ሕፃናት ክፍል እንዲከፈት፣ ትልቅ ደረጃ እንዲደረስ አድርገናል፡፡ ጋንዲ ሆስፒታልም ቁሳቁስ አቅርበን የጨቅላ ሕፃናት ክፍል እንዲከፈት ረድተናል፡፡ ለየካቲት ከሰጠነው ቁሳቁስ የተረፉት ዘውዲቱ እንዲሄዱ ተደርጎ እዚህም የጨቅላ ሕፃናት ክፍል ተከፍቷል፡፡ እኛ መሠረቱ እንዲጣል ረድተን የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ክፍል አሁን ላይ በየሆስፒታሉ እየተስፋፋ ነው፡፡ የምንፈልገው እንዲህ ዓይነቱን መሠረታዊ ለውጥ ነው፡፡ በየጊዜው የሕክምና ጓድ ይዞ በመሄድ ሕክምና መስጠቱ አያዋጣም፡፡ ስለሆነም ግሪን ዴቨሎፕመንት የሚባል ፕሮፖዛል ቀርፀናል፡፡ ይህን ያደረግነው ዘመሮ ላይ በነበረን ሥራ፣ የሕዝቡን ችግር ከስር መሠረቱ መቅረፍ እንጂ ከታመመ በኋላ ማከሙ ብዙም ዋጋ እንደሌለው በመረዳታችን ነው፡፡ ባየነው መሠረት ሰው ከኑሮው አኳያ ለሕመም እየተጋለጠ ነው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ ካለማግኘት፣ ከግልና ከአካባቢ ንጽሕና ጉድለት፣ ከንጹህ ውኃ አቅርቦት እጥረት ጋር የተያያዘ ችግር አለ፡፡ ከውፍረት ጋር የተያያዘ በሽታ ወይም የቲቢ ችግር አላየንባቸውም፡፡ ስለሆነም መሠረታዊ የጤና አጠባበቅ ላይ ከሠራን ማኅበረሰቡን መታደግ እንችላለን፡፡ መሠረተ ልማቱን ከረዳን፣ ራሳቸውን እንዲመግቡ፣ ሥራ እንዲፈጠር ካደረግን ኑሯቸው ይስተካከላል፡፡ በዛው ልክ ጤናቸው ይጠበቃል፡፡ ይህንን  ፕሮፖዛል ለመተግበር ከሚሊዮን ዶላር በላይ እንፈልጋለን፡፡ አንዱ ምንጫችን ደግሞ የከፈትነው ክሊኒክ ነው፡፡ ዓላማችንም ክሊኒኩ እንዳሰብነው መሥራት ከቻለ ብዙ ገንዘብ አመንጭተን ሌሎች ፕሮጀክቶችን መደገፍ ነው፡፡

ሪፖርተር፡‑ ክሊኒኩ እንደ ሜዲካል ቱሪዝም ሊያገለግል የሚችል ነው፡፡ እዚህ ላይ ምን እየሠራችሁ ነው?

ወይዘሪት ሰብለ፡- እንዳሰብነው መሄድ ከቻልን ክሊኒኩ ብዙ የውጭ ምንዛሪ ሊያመጣ ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ የምንሰጣቸው አገልግሎቶች በአፍሪካ የሉም፡፡ አንዳንዶቹ አሉ፡፡ አየር መንገዳችን ባለው ሽፋን ብዙዎችን መድረስ ከቻልን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ብቻ ሳይሆን ከውጭ ያሉ ሰዎችንም አምጥተን ማከም እንችላለን፡፡ ሜዲካል ቱሪዝሙን አስፋፍተን አገራችንንና ራሳችንን መጥቀም እንችላለን፡፡

ዶ/ር አንተነህ፡‑በዓለም የኤስቴቲክ ገበያው ተፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የኤስቴቲክ ወይም ውበት ላይ ብትሠራና አገልግሎቱን ብታስፋፋ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በተሻለ ተገልጋይ ልትስብ ትችላለች፡፡ ለምሳሌ የፀጉር መልሶ ማብቀል ላይ ብንሠራ ቀላል ነው፡፡ ብዙ የውጭ ምንዛሪ ማምጣትም እንችላለን፡፡ ስቴም ሴል ላይ ብንሠራ መካከለኛው ምሥራቅን መያዝ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም መካከለኛው ምሥራቅ ላይ ውፍረት ትልቅ ችግር ነው፡፡ ከውፍረት ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎችም አሉ፡፡ አገልግሎቱን በመስጠታችን የምናገኘው የውጭ ምንዛሪ ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቷን የአገልግሎቱ መዳረሻ መሆኗን ከሚገልጽ ካርታ ላይ እንድትሰፍር እናደርጋለን፡፡ ዓላማችንም ይኸው ነው፡፡

Standard (Image)

‹‹ፖሊሲና አቅጣጫ ባልነበረበት የተጀመረው ሥራ ዛሬ ላይ ውጤት አስገኝቷል››

$
0
0

ወ/ሮ ገነት መንግሥቱ፣

የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የቤተሰብ ዕቅድ ጽንሰ ሐሳብና አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ በይፋ የገባው የዛሬ 50 ዓመት የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል ዕድል አግኝተው ወደ ህንድ አገር በሄዱ ጥቂት ወጣት ምሁራን ነበር፡፡ ወቅቱ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1958 ዓ.ም. ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛትም 22 ሚሊዮን አካባቢ ነበር፡፡ ፊደል ከቆጠሩና ባህር አቋርጠው ከተመለሱ ጥቂት ኢትዮጵያውያን በስተቀር ሕዝቡ ለዓመታት የተገነባ ልጅን እንደ ሀብት ብቻ የመቁጠር አንድ ዓይነት አመለካከትም ነበረው፡፡ ይሁንና በአገሪቱ የነበረው ከፍተኛ የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ሞትና በወቅቱ ይታይ የነበረው ፈጣን የሕዝብ ዕድገት ያሳሰባቸው በጐ ፈቃደኞች የተደራጀ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ በመጨረሻም ሐሳባቸው ሰምሮ በወቅቱ ፓዝ ፋይንደር ፈንድ ተብሎ ይጠራ በነበረው የአሁኑ ኢንተርናሽናል ፓዝ ፋይንደር በተለገሰ የገንዘብ ድጋፍ በአንዲት በጎ ፈቃደኛ ነርስ ብቻ የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ ወ/ሮ ገነት መንግሥቱ የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ታደሰ ገብረማርያምበማኅበሩ እንቅስቃሴ ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከተመሠረተ በኋላ ከነበረው የቤተሰብ ዕቅድ አመለካከት አንፃር እክል አልገጠመውም?

ወ/ሮ ገነት፡- ከምሥረታው በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር፣ ምቹ የቤተሰብ ዕቅድ የሕግ ማዕቀፍ በሌለበት ሥራውን ሲያከናውን ነበር፡፡ የ1957 ዓ.ም. ወንጀለኛ መቅጫ ሕግም የቤተሰብ ዕቅድን ማስተዋወቅና ማሠራጨት ክልክል መሆኑን አስቀምጦ ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ አንዳንድ ባሎች ‘ለሚስቶቻችን ይህን አገልግሎት ለምን ሰጣችሁ’ በሚልም ሽጉጥ መማዘዝ ደረጃ ደርሰው ነበር፡፡ ማኅበሩ ዛሬ ያለበት ደረጃ ለመድረስ በርካታ ሀይማኖታዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ጋሬጣዎችን ተጋፍጧል፡፡ በዚህም የቤተሰብ ዕቅድ መረጃና የሥነ ተዋልዶ ምክርና የክሊኒክ አገልግሎት ለተጠቃሚዎች በመስጠት ፋና ወጊ ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ስትራቴጂዎችን እየቀየሰና አዳዲስ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎቶችን እያከለ፣ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም አሠራሩን ያስፋፉበት ሁኔታ አለ፡፡ የተገኘውን ውጤት ቢያብራሩልን?

ወ/ሮ ገነት፡- በርካታ ስትራቴጂዎች ተቀርጸው ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱና ዋነኛው በመላ አገሪቱ በሚገኙ 700 የገጠር ቀበሌዎች፣ ማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮግራም በሚል፣ የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴዎች እዚያው ባሉት ማኅበረሰቦች እንዲሠራጭ የተደረገው ይገኝበታል፡፡ ይህም ተግባራዊ የሆነው ማኅበረሰቡ የመረጣቸውና እስከ አራተኛና አምስተኛ ክፍል ድረስ የተማሩትን፣ እንዲሁም ማንበብና መጻፍ የቻሉትን በማሠልጠን እንደ ኮንዶምና ፒልስ (በአፍ የሚወሰድ እንክብል) ለማኅበረሰቡ እንዲያዳርሱ፣ ከዚህ ውጭ ያሉትን አገልግሎቶች ክሊኒክ ሪፈር እንዲያደርጉ በማድረግ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ አድርገዋል፡፡ መንግሥትም ይህንን ተግባር ወደ ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ከፍ እንዲል ሲያደርግ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም በዚህ ዓይነት ፕሮግራም ውስጥ ገብተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር የጀመረውን አገልግሎት የመስጠት ሥራ ትቶ ወጣ፡፡ ሌላው ስትራቴጂ ደግሞ የወጣቶች ማዕከላትንና ቤተ መጻሕፍትን የማቋቋም ጉዳይ ነበር፡፡ ማዕከላቱ ወጣቶቹ በሙዚቃና በሥነ ጽሑፍ የራሳቸውን ክህሎት የሚያሳድጉበትን ቤተ መጻሕፍቱ ደግሞ ከተዋልዶ ጤና ጋር በተገናኘ ትምህርትና መረጃ የሚያገኙበትን በማመቻቸት ረገድ የጎላ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በተለይ ማዕከላቱ ታዋቂ አርቲስቶችን፣ ጋዜጠኞችንና ትላልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ባለሥልጣናትን ሁሉ ያፈሩ ናቸው፡፡   

ሪፖርተር፡- የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራና ሕክምናን አስመልክቶ ማኅበሩ የሚሠራውን ቢገልጹልን?

ወ/ሮ ገነት፡- የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር የቅድመ ምርመራ አገልግሎት መስጠት የጀመረው በ1988 ዓ.ም. ነው፡፡ ከተለያዩ ሆስፒታሎች በሪፈራል የሚመጡ ታካሚዎችም በርካታ ናቸው፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት አዲስ ቴክኖሎጂ አምጥተን ሥራ ላይ ውሏል፡፡ ቴክኖሎጂው፣ ተገልጋዮች እንደመጡ ምርመራ የሚያገኙበትንና ሕክምና የሚሰጥበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ ከእኛ አቅም በላይ የሆነውን ወደ ሆስፒታል ሪፈር የምናደርግበት አካሄድም አለን፡፡ የጡት፣ የማህፀን በር ጫፍንና የፕሮስቴት ካንሰርን አስመልክቶ በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ቀዳማዊት እመቤቶች ጉባኤ ላይ ወደ አምስት ሺሕ የሚጠጉ ሴቶችን መመርመር ተችሏል፡፡ ይህም ምርመራ የተካሄደው በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉት ክሊኒኮቹ ነው፡፡ በአገልግሎቱም ታዋቂ ነው፡፡ አሁን ላይ ማኅበሩ ከ50 በላይ ክሊኒኮች አሉት፡፡ በእነዚህም ክሊኒኮች የአገልግሎት አድማሱን እያሰፋ መጥቷል፡፡ ከክሊኒኮቹም መካከል አሥሩ ለሴተኛ አዳሪዎች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ ሚስጥራዊ ክሊኒኮች ናቸው፡፡ የተቋቋሙትም ከአፋር ጀምሮ እስከ ጋምቤላ ድረስ በተለይ ሴተኛ አዳሪዎች በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ላይ ነው፡፡ ኤችአይቪ እና አባላዛር በሽታዎች ላይ ተከታታይ ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ በተለይ በኤችአይቪ ላይ እስከ ሕክምና ድረስ እየተሰጠ ያለበት ሁኔታ አለ፡፡  

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ለትርፍ ያልቆመ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሆኖ የተመሠረተውና ፍላጎት ላላቸውና በሕግ የተወሰነውን የዕድሜ ክልል ለሚያሟሉ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት መስጠት የተጀመረው መቼ ነው?

ወ/ሮ ገነት፡- ማኅበሩ ለትርፍ ያልቆመ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሆኖ በይፋ የተመዘገበው በ1967 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በ1974 ዓ.ም. የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ፍላጎት ላላቸውና በሕግ የተወሰነውን የዕድሜ ገደብ (ማለትም ከ18 ዓመትና ከዚያም በላይ) ለሚያሟሉ መስጠቱን እንዲቀጥል የሚፈቅድ መመሪያ ወጣ፡፡ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ እንዲወጣ ማኅበሩ ያደረገው ከፍተኛ ግፊትና የፖሊሲው መጽደቅም ማኅበሩ እራሱን እንዲያጠናክርና እንዲያስፋፋ አድርጎታል፡፡  

ሪፖርተር፡- መንግሥት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ዘርግቷል፡፡ ከዚህ አኳያ ማኅበሩ ከገጠሩ ማኅበረሰቦች ጋር ያለው ቅንጅት በምን መልኩ ይገለጻል?

ወ/ሮ ገነት፡- ከተለያዩ የወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤቶች ጋር ስምምነት እየተፈራረምን ነው፡፡ በስምምነቱም መሠረት ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች ላይ እየተንቀሳቀስን ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ጽሕፈት ቤቶቹ በማይደርስባቸው ጤና ኬላዎች፣ በተለይም በአፋር ክልል ባለሙያዎቻችን በደርሶ መልስ ፕሮግራም ሙያዊ እገዛ ያደርጋሉ፡፡ በተጠቀሰው ክልል የሚካሄደው ፕሮግራም በ200 ጣቢያዎች ላይ ነው፡፡ በጤና ኬላዎች የማይሰጡትን ወደ እኛ ክሊኒክ ሪፈር ይደረጋል፡፡ በመላ አገሪቱ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ሲጀመር ሥልጠና በመስጠት እገዛ ካደረጉት መካከል አንዱና ዋነኛው የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ነው፡፡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተገኘ ድጋፍ በሶማሌ ክልል በ20 ወረዳዎች፣ በቤንች ማጂ ዞን በአምስት ወረዳዎች ለሚገኙ አርብቶ አደሮች የተዋልዶ ጤና አገልግሎትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር አሁን በደረሰበት ደረጃ ላይ ምን እየሠራ ነው?

ወ/ሮ ገነት፡- በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል በ1986 ዓ.ም. ካይሮ ላይ የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ ሥራ ላይ ማዋል ይገኝበታል፡፡ ጉባኤው ያሳለፈው ውሳኔ ቁንጽል አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ ከመራቢያ አካላትና ከተዋልዶ ጤና ሒደት ጋር የተገናኙ ነገሮችን በአንድነት እንደ ተዋልዶ ጤና ታይቶ ይሰጥ የሚል ነበር፡፡ ይህም ማለት አገልግሎቱ ከቤተሰብ ዕቅድ ወደ ተዋልዶ ጤና ይምጣ የሚል ነው፡፡ ውሳኔው ተቀባይነትን አግኝቶ የተቀናጀ የተዋልዶ ጤና አገልገሎት መስጠት ተጀምሯል፡፡ በዚህም ከተካተቱት አገልግሎቶች መካከል የእናቶችና የሕፃናት ጤና አጠባበቅ፣ ኤችአይቪ/ኤድስና የአባላዘር በሽታ የመመርመርና የማከም፤ የቤተሰብ ዕቀድ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የእናቶችና የሕፃናት ጤና አጠባበቅ በእርግዝና ጊዜ ክትትል ማድረግና ማዋለድ ሲሆን፣ ይህንንም የሚያደርጉ ስድስት ከፍተኛ ክሊኒኮች አሉን፡፡ ከዚህም ሌላ የጽንስና ማህጸን ስፔሻል ክሊኒክም በማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ አለ፡፡ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትም እንሰጣለን፡፡ የአጭር ጊዜ የወሊድ መቆጣጠሪያ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ስለሚሰጡ እኛ ግን የበለጠ ትኩረት አድርገን የምንሰጠው ዘላቂና የረጅም ጊዜ የወሊድ መቆጣጠሪያ ነው፡፡ ይህም ከሦስት ዓመት በላይ የሚቆይ በክንድና በማህጸን የሚገባ ሉፕ ነው፡፡ በቋሚነት መውለድ አንፈልግም ለሚሉ ሴቶችና ወንዶች በሕክምና መውለድን የማቆም አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የወጣቶች ተዋልዶ ጤና አገልግሎትም እንሰጣለን፡፡ ለዓይነ ሥውራንና መስማት ለተሳናቸው የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ተደራሽ እናደርጋለን፡፡ ሕጉን በጠበቀ መልኩ የጽንስ ማቋረጥ ሥራ እናከናውናለን፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥራ ከተከናወነላቸው ሴቶች መካከል 95 ከመቶ በላይ ለሚሆኑት ያልታቀደ እርግዝና እንዳይመጣባቸው የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በቤተሰብ ዕቅድ አጠቃቀም ላይ ኅብረተሰቡ ያለውን ግንዛቤ እንዴት ይገመግሙታል?

ወ/ሮ ገነት፡- ኅብረተሰቡ አገልግሎቶቹን በተመለከተ አሁን የተሻለ ግንዛቤ አለው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተካሄዱ ጥናቶች ለመረዳት እንደተቻለው በቤተሰብ ዕቅድ ድሮ የተጠቃሚው ቁጥር በጣም ትንሽ ነበር፡፡ በ1982 ዓ.ም. የተካሄደው ጥናት እንዳመለከተው፣ በመውለድ ዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ሴቶች መካከል የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚዎች ወደ አራት በመቶ ብቻ ነበሩ፡፡ በ2006 ዓ.ም. በተካሄደው ጥናት ደግሞ የተጠቃሚው ቁጥር ወደ 41 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ አገር አቀፍ ጥናት እየተጠናቀቀ ሲሆን፣ የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚውም ወደ 44 በመቶ ይደርሳል ለማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ጥናቱ ገና አልታወቀም፡፡ ከዚህ አኳያ የተጠቃሚዎች ቁጥር 44 በመቶ ደርሷል ለማለት የሚቻለው ከምን መነሻ ነው?

ወ/ሮ ገነት፡- መንግሥት በጤና ኤክስቴንሽን የሠራው ሥራ ቀላል አይደለም፡፡ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ደግሞ በዚህ ላይ ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ውጤቱን ከፍ ሊያደርገው ይችላል ከሚል እምነት በመነሳት ነው፡፡ በቤተሰብ ዕቅድ ላይ ሕጉ መሻሻሉ፤ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ከታክስ ነፃ እንዲገባ መደረጉ ለተጠቀሰው ቁጥር ከፍ ማለት የየራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ሥልጠና ላይ የሰጣችሁት ትኩረት ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ገነት፡- የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ከ170 በላይ የዓለም አገሮችን በአባልነት ባቀፈው የዓለም አቀፍ የቤተሰብ ዕቅድ ፌዴሬሽን ሙሉ አባል ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ የአፍሪካ ሪጅን ማኅበራችን ከተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሙያ ለአገር ውስጥና ለኢንተርናሽናል ሠልጣኞች የሥልጠና ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል በ2005 ዓ.ም. መርጦታል፡፡ በዚህም መሠረት ቀድሞ የነበረውን የማሠልጠኛ ክፍል በማጠናከር ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ በሺዎች ለሚቆጠሩ የአገር ውስጥና የውጭ ሠልጣኞች የሙያ ሥልጠና ወይም በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ሕንፃ አራተኛው ወለል የማሠልጠኛ ማዕከል ሆኗል፡፡ ስምንቱም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቻችን የማሠልጠን ሥራ ያከናውናሉ፡፡ ለዚህም የተሟላ ፋሲሊቲ ያላቸው ማሠልጠኛዎች አሏቸው፡፡   

ሪፖርተር፡- የማኅበሩን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከግሉ ዘርፍ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ቢያብራሩልን?

ወ/ሮ ገነት፡- በአሁኑ ጊዜ ወደ 320 የሚጠጉ የግል ክሊኒኮች አብረውን እየሠሩ ነው፡፡ ለእነዚህም የግል ክሊኒኮች ‹‹ጥምረት ለቤተሰብ ጤና›› የሚል ስያሜ አውጥተንላቸዋል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ጥምረት እየተሰጠ ያለው የቤተሰበ ዕቅድ አገልግሎት ቀላል አይደለም፡፡ የግል ክሊኒኮቹ ሕክምና ብቻ ይሰጡ ነበር፡፡ በዚህ ሥራቸው ላይ በተጨማሪ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን እንዲጨምሩ በማድረግ፣ አገልግሎቱን በትናንሽ ከተሞችና ከገጠር ለሚመጡት ሁሉ ተደራሽ ማድረግ ችለናል፡፡  

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ከዕድሜው አኳያ ሲታይ ግቡን መትቷል ለማለት ይቻላል?

ወ/ሮ ገነት፡- አዎ፡፡ ምክንያቱም ምንም ሕግ፣ ፖሊሲና አቅጣጫ ባልነበረበት የተጀመረውን ሥራ ዛሬ ላይ ቆመን ስናይ ትልቅ ውጤት ተገኝቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ15 ዓመት በፊት የማኅበሩን ሥልጠና ያልወሰደ አንድም የጤና ባለሙያ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ግን መንግሥትም የራሱን አቅም ገንብቷል፡፡ ያሠለጥናል፡፡ ሌሎችም ያሠለጥናሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ማየት የፈለገውም ይህንኑ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ስትራቴጂና ፖሊሲ አለን፡፡ ሕጐችም ተሻሽለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥት በኩል የሚደረግላችሁ ድጋፍ አለ?

ወ/ሮ ገነት፡- መንግሥት በጣም ይረዳናል፡፡ አርብቶ አደር ላይ ለቀረጽነው የሦስት ዓመት ፕሮጀክት እውን መሆን መንግሥት ትልቅ ገንዘብ ሰጥቶናል፡፡ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን ከመንግሥት እናገኛለን፡፡ የተለያዩ መድሃኒቶችንም ይረዳናል፡፡ ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ፈንድ (በጀት) ከውጭ የሚያገኝበት ሁኔታ አለ?

ወ/ሮ ገነት፡- አዎ፡፡ በአብዛኛው ትልቅ ሥራ መሠራት ያለበት በዚሁ ፈንድ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ማኅበሩ በ50 ዓመት ዕድሜው የኔ ነው የሚለው የለውም፡፡ በውጭ ለጋሾች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ዓለም አቀፉ የቤተሰብ ፌዴሬሽን ይረዳናል፡፡ ከተለያዩ የረድኤት ድርጅቶች የሚመጣም ገንዘብ አለ፡፡ ከድርጅቶቹም መካከል የኔዘርላንድ ኤምባሲ፣ ዓለም አቀፉ የሥነ ሕዝብ ድርጅት (ዩኤንኤፍፒኤ)፣ ከጃፓን ኤምባሲ፣ ከፓካርድ ፋውንዴሽነ፣ አይሪሽ ፈንድ፣ ሲዲሲ ይገኙበታል፡፡ አሁን ላይ ሆነን ስናየው ግን በዓለም ላይ ከተከሰተው የተለያዩ የኢኮኖሚ ችግሮች አኳያ ዕርዳታዎች እየቀነሱ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ማኅበሩ አገልግሎቱን በአብዛኛው በነፃ መስጠት ይጠበቅበታል ወይ? የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱን ለማግኘት የመክፈል አቅም ያላቸው ተገልጋዮች በወጪ መጋራት የሚተባበሩበትንና የገቢ ማስገኛዎች የሚፈጠሩበትን ሁኔታዎች ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት እያስጠናን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ዕርዳታዎች በመቀነሳቸው ሳቢያ የተዘጉ አገልግሎት መስጪያዎች አሉ?

ወ/ሮ ገነት፡- መዝጋት ሳይሆን በአካባቢው ላሉትና ለማስተዳደር ለሚችሉ ድርጅቶች አስረክበን እንወጣለን፡፡ እኛ ከውጭ ሆነን እንረዳለን፡፡ ይህንንም የምናካሂደው ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ካስረከብናቸው ተቋማት መካከል አዲስ አበባ፣ አላባ፣ ከሚሴ፣ ወልቂጤና ወላይታ ከተሞች የሚገኙ የወጣት ማዕከላት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት እየተገለገለበት ያለው አዲስ ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ መቼ ነው የተሠራው? ለምንስ አገልግሎት እየዋለ ነው?

ወ/ሮ ገነት፡- አልሠራነውም፡፡ ቀደም ሲል በሌላ አካል የተሠራውን ገዝተን ነው፡፡ ግዥውም የተከናወነው በብድር በተገኘ ገንዘብ ሲሆን፣ ያበደረንም ፖካርድ ፋውንዴሽን ነው፡፡ ብድሩንም ከፍለን ጨርሰናል፡፡ ሕንፃው የተገዛው ሪፈራል ክሊኒክ እና የሥልጠና ማዕከል ለማቋቋም እንዲሁም ለቢሮ እንዲውልም ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም የጽንስና የማህጸን ስፔሻሊቲ ልዩ ክሊኒክ ፈቃድ አውጥተን እየሠራን ነው፡፡  

Standard (Image)

‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ የአመለካከት ተሃድሶ እንዲመጣ እንሠራለን››

$
0
0

አቶ አደራ አብደላ፣ የኤስኤኬ ቢዝነስና ፐርሰናል ዴቨሎፕመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

አቶ አደራ አብደላ የኤስኤኬ ቢዝነስና ፐርሰናል ዴቨሎፕመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ድርጅቱ ከተቋቋመ 11 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ድርጅቱ በትራንስፎርሜሽናል ሊደርሽፕ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ላይ የሚያተኩሩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ይሰጣል፡፡ አመለካከትና ማንነት ላይ የሚያተኩሩ ሥልጠናዎችን ለወጣቶችና ሕፃናት በነፃና በክፍያ ለማድረስም እየሠራ ይገኛል፡፡ የሚሰጣቸው ሥልጠናዎች በሥርዓተ ትምህርቱ እንዲካተቱ በአገር አቀፍ ደረጃ  ተደራሽ እንዲሆኑ ለማስቻል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የድርጅቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴንሥራ አስኪያጁን አቶ አደራን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ትኩረት አድርጐ የሚሠራበትን ቢገልጹልን?

አቶ አደራ፡- የድርጅቱ ዋና ትኩረት ክህሎት፣ አመለካከትና ዕውቀትን መገንባት ነው፡፡ በተለይም አመለካከት ላይ በይበልጥ ይሠራል፡፡ ይህም የሆነው በአገራችን ከፍተኛ የአመለካከት ችግር በመኖሩ ነው፡፡ የአመለካከት ክፍተት አለ ማለት ሰዎች ያላቸውን ክህሎት በአግባቡ እንዳይጠቀሙበት ያደርጋቸዋል፡፡ አመለካከታቸው ግን ከተቀየረ ያገኙትን የንድፈ ሐሳብ ዕውቀት ወደ መሬት በማውረድ ችግሮችን ለመፍታት ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የአመለካከት ችግር ከምን ይመነጫል?

አቶ አደራ፡- አመለካከታችንን የሚቀርጹት ብዙ ነገሮች ናቸው፡፡ አመለካከት ከሕፃንነት ጀምሮ የሚዳብር ነው፡፡ በሕፃናቱ ዙሪያ ከሚገኙ ከቤተሰብ፣ ከመምህራን እና አጠቃላይ ከማኅበረሰቡ አመለካከት ይቀረጻል፡፡ ወጐቻችን፣ አባባሎቻችን እና ሃይማኖታችን ማንነታችንን እና አስተሳሰባችንን ይቀርጻሉ፡፡ ሥራ በሚያበረታታ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖር አንድ ሰው ሥራ ለመሥራት ያለው ተነሳሽነት ከፍተኛ ይሆናል፡፡ በሌላውም እንደዚሁ፡፡ ጮክ ብሎ መናገር፣ ፈጠን ብሎ መራመድ፣ መምህርን ጥያቄ መጠየቅ፣ የተገኘን ሥራ መሥራትና የመሳሰሉት ይህንንም ያህል አይበረታቱም፡፡ የአመለካከት ክፍተት አለብን፡፡ ይህንን አገር አቀፍ ሥራ በመሥራት በኢትዮጵያ ውስጥ የአመለካከት ተሀድሶ ለማምጣት ነው የምናስበው፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ሰው የአመለካከት ክፍተት አለበት የሚያስብሉ ነገሮች ምን ምን ናቸው?

አቶ አደራ፡- አመለካከት ማለት ዓለምን የምናይበት ዕይታ ነው፡፡ አገርን ብንመራ፣ ድርጅት ብናስተዳድር እና በሌሎችም ሥራዎች ብንሰማራ እያንዳንዱ ሥራችን የሚወሰነው በአመለካከታችን ነው፡፡ ሰዎች አመለካከታቸውን ከቀየሩ ሰብዕናቸውም ይቀየራል፡፡ ይህ ደግሞ ነገ ለሚያደርጉት የተግባር እንቅስቃሴ ትልቅ ስንቅ ይሆናቸዋል፡፡ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በንድፈ ሐሳብ ዕውቀታቸው ከፍተኛ ደረጃ ይደርሳሉ፡፡ ነገር ግን ለነገሮች ያላቸው አመለካከት ውስን በመሆኑ በንድፈ ሐሳብ የሚያውቁትን መሬት አውርዶ ለማስፈጸም ይቸገራሉ፡፡ በዚህም ዕውቀት ሳያንሳቸው ያላቸውን ዕምቅ አቅም ሳይጠቀሙበት ይቀራሉ፡፡ የአመለካከት ክፍተት ማለት እነዚህን ነገሮች የሚያካትት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- አብረዋችሁ የሚሠሩ ሌሎች ድርጅቶች አሉ?

አቶ አደራ፡- ከባለፉት 11 ዓመታት ጀምሮ ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር አብረን ስንሠራ ቆይተናል፡፡ ለመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና ለጐንደር ዩኒቨርሲቲ የትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ ሥልጠናዎችን ሰጥተናል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝም በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥረን በትምህርት ሥርዓቱ በተለይም በቴክኒክና ሙያ አመራር ላይ ለሚገኙ ከአዲስ አበባ ለተውጣጡ ኃላፊዎች የትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ ሥልጠና ሠጥተናል፡፡ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ለሚገኙትም የሥራ ፈጠራ ሥልጠናዎች ሰጥተናል፡፡ ከዩኒሴፍ ጋርም እንደዚሁ አብረን እንሠራለን፡፡   

ሪፖርተር፡- በማኅበረሰቡ ውስጥ በርካታ ችግሮች እያሉ ራስን የማበልጸግ ፕሮግራም ላይ ለመሥራት እንዴት መረጣችሁ?

አቶ አደራ፡- ራስን የማበልጸግ ፕሮግራምን የመረጥነው በሥራ ሒደት ከሚያጋጥሙን ነገሮች በመነሳት ነው፡፡ የአመለካከት ክፍተት በተለይ እላይ ባሉ ሥራ አስፈጻሚዎችና እንደ አጠቃላይ በማኅበረሰቡ ውስጥ አለ፡፡ ራስን የመምራትና የትራንስፎርሜሽን ሊደርሽፕ ሥልጠና የሰጠናቸው ሰዎች ‘ይህን ትምህርት ከልጅነታችን ጀምሮ አግኝተነው ቢሆን’ ይሉናል፡፡ ለምንድነው እንደዚህ የምትሉት ስንላቸውም ‘ባህላችን፣ ልማዳችን በሰው ፊት ቀርበን ራሳችንን እንድንገልጽ አይፈቅድልንም፡፡ ተሸማቀን ነው ያደግነው፡፡ ድምጻችን ዝቅ ያለነው፣ ይህም በስራችን ውጤታማ እንዳንሆን አድርጎናል’ ይሉናል፡፡ እኛም ይሄንን ነገር ለምን አናጠናም ብለን የአገራችንን የሕፃናትና ወጣቶች ፖሊሲ ሪፖርት ማየት ጀመርን፡፡ በሪፖርቱ ላይ አመለካከት እና ሰብዕና ላይ ክፍተት መኖሩን ተመለከትን፡፡ ከሲቪል ሰርቪስ የሚወጡ ሪፖርቶችም እንደዚሁ ማኅበረሰቡ የአመለካከት ችግሮች እንዳሉበት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የአመለካከት ክፍተቶችን መሙላት የሚችሉ የትምህርት ዓይነቶች በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ተካትተዋል ወይ የሚለውንም ለማየት ሞከረን ነበር፡፡ ከሥነ ዜጋ ትምህርት ባለፈ ማንነት እና ማኅበራዊ ሕይወት ያተኮሩ ትምህርቶች የሚማሩበት ሁኔታ አለመኖሩን ተረዳን፡፡ በአቅማችን የበኩላችንን ለማድረግም አገራችን ውስጥ ያሉ ወደኋላ የሚያስቀሩን ጐታች አመለካከቶች ምንድናቸው ብለን ነቅሰን አወጣን፡፡ ይሉኝታ፣ አልችልም፣ ረፍዶብኛል፣ የሀበሻ ቀጠሮ የመሳሰሉት ማኅበረሰቡን ወደኋላ የሚያስቀሩ ችግሮች ለይተን አወጣን፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቀነስም በሥርዓተ ትምህርት መልክ በማዘጋጀት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሥልጠናዎች እየሰጠን እንገኛለን፡፡ በአገሪቱ 42 በመቶ የሚሆኑት የኅብረተሰቡ ክፍሎች ወጣትና ሕፃናት ናቸው፡፡ ይህንን ያህል ድርሻ የሚይዘውን የኅብረተሰቡን ክፍል ለብቻችን መድረስ ግን አንችልም፡፡ ስለዚህም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር አብረን ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ፕሮግራሙ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ይሆናል? ወይስ በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነ ነው? ሥልጠናውን የምትሰጡትስ በትምህርት ክፍለ ጊዜ ነው?

አቶ አደራ፡- በበጋው ወቅት መደበኛ የትምህርት ሥርዓቱ ካበቃ በኋላ፣ አልያም ቅዳሜና እሑድ ለመስጠት አስበናል፡፡ ለጊዜው ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ላይ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በቅርቡ ፕሮጀክቱን ለማስተዋወቅ ባዘጋጀነው ፕሮግራም ላይ የነበሩ ታዳሚዎች ፕሮግራሙ በክልሎችም ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀውናል፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ ይህን የምንሠራውም እንደ ማኅበራዊ ኃላፊነት ሲሆን፣ የተለያዩ አጋር ድርጅቶችም እገዛ ያደርጉልናል፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላም ፕሮጀክቱ ለመንግሥት ተላልፎ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን የስረአተ ትምህርቱ አካል እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ይህም ልጆቻችን ከንድፈ ሐሳብ ክህሎት ባሻገር ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ተምረው ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ ራዕያችን ጥበብ ያለው አገር መምራት የሚችል ትውልድን መፍጠር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለፕሮግራሙ ምን ያህል በጀት መድባችኋል?

አቶ አደራ፡- ፕሮግራሙን ያዘጋጀነው በማኅበራዊ ኃላፊነት ቢሆንም በነፃ ለመስጠት አላሰብንም፡፡ የተለያዩ ግብዓቶች እንገዛለን፣ አዳራሾች እንከራያለን፣ ሌሎች የተለያዩ ወጪዎችም አሉ፡፡ ይህንን ለመሸፈን እና ፕሮግራሙም ቀጣይነት እንዲኖረው መክፈል የሚችሉ ከፍለው ሥልጠናውን እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ መክፈል የማይችሉ ደግሞ ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች በምናገኘው ድጋፍ ወጪያቸውን በመሸፈን ሥልጠናውን በነፃ እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡    

ሪፖርተር፡- የምታዘጋጇቸውን ሥልጠናዎች በኅብረተሰቡ ምን ያህል ተቀባይነት አግኝተዋል?

አቶ አደራ፡- በእኛ ዕይታ ያልታየ የማንነት ቀውስ አለ፡፡ ለምሳሌ ተነጋግሮ መፍታት እየተቻለ ትዳሮች፣ የንግድ ተቋማት ይፈርሳሉ፣ እርስ በርስ አለመተማመን አለ፣ የሃይማኖት ተቋማትም የተለያዩ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ወጣቶችም ስለ አገር ደንታ የላቸውም፣ ራስ ወዳድ ናቸው ይባላል፡፡ ይህ ሁሉ ቀውስ የሚፈጠረው በአመለካከት ችግር ነው፡፡ ከቀለም ትምህርት ባሻገር ባህሪ ተኮር ዕውቀት ከሌለ አዋቂ አጥፊ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወላጆች ልጆቻቸው የችግሩ ሰለባ እንዳይሆኑ ይጨነቃሉ፡፡ በሠራናቸው ጥቂት ማስታወቂያዎችም በርካታ ሰዎች አገልግሎቱን ፈልገው ወደኛ እየመጡ ይገኛሉ፡፡ የኅብረተሰቡ ተቀባይነት ጥሩ ነው፡፡ ከጊዜ ወደጊዜም እያደገ ይገኛል፡፡  

ሪፖርተር፡- ያለው የአመለካከት ችግር አገሪቱን ምን ያህል ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል?

አቶ አደራ፡- የግል ተቋም እንደመሆናችን አገር አቀፍ ጥናት አላደረግንም፡፡ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያዊ የምናውቃቸውን የማኅበረሰቡን ችግሮች ነቅሰን አውጥተናል፡፡ ለምሳሌ የሥራ ተነሳሽነታችን ምን ያህል ነው የሚለውን ብናይ ከዓለም አቀፍ ደረጃው ዝቅ ያለ ነው፡፡ ሥራን አፍቅረን እንደ ፀጋ ቆጥረን ነው ወይ የምንሠራው? ወይም እንደ ግዴታ እንደ ዕዳ አስበነው የሚለውን ነገር ስናይ በጣም ወደኋላ የቀረንበት ነገር ነው፡፡ ሌላው የጊዜ አጠቃቀማችንን ብንመለከት ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ የሀበሻ ቀጠሮ ይባላል፡፡ በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ጊዜ አይከበርም፡፡ ይህንንም እንደ ባህል ይዘነዋል፡፡ ሀበሻ አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራት አይችልም የሚባል ነገርም አለ፡፡ ይህ ደግሞ ባለመነጋገር ሐሳብን ባለመጋራት የተፈጠረ ወደኋላ የቀረንበት ነው፡፡ የማድነቅ ባህላችንም ሌላው ችግር ነው፡፡ ለአመራር የምንሰጠው ዋጋም ችግር አለበት፡፡ መሪዎችን ለመቀበል እንቸገራለን፡፡ አመራራቸውን ከመቀበል ይልቅ የመጠራጠር፣ ከእነሱ እንከን የማውጣት ነገር ይታያል፡፡ እንደዚህ ያሉትን ችግሮች አመለካከት ተኮር ሥራዎችን ከታች ጀምሮ በመሥራት የሚቀረፉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ አገራችን ወደኋላ አስቀርቷታል፡፡

ሪፖርተር፡- ሥልጠና ከሰጣችሁ በኋላ ውጤታማነቱን የምትገመግሙበት አሠራር አላችሁ?

አቶ አደራ፡- ሥልጠናው ሲያልቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደኋላ የሚያስቀሩ አመለካከቶች ምንድናቸው ብለን ነቅሰን እናወጣለን፡፡ ከዚያም ለሠልጣኞቹ እንገልጻለን፡፡ እነሱ የሚጨምሩበት ነገር ካለ እንዲጨምሩበት እናደርጋለን፡፡ ቀጥሎ የሬሳ ሳጥን እናዘጋጃለን፡፡ ወደኋላ እንዲቀሩ የሚያደርጓቸውን አስተሳሰቦች የሬሳ ሳጥኑ ውስጥ በመክተት እንዲቀበር እናደርጋለን፡፡ ይህንንም አልችልም ቀብር ሥነ ሥርዓት እንለዋለን፡፡ በዚህ ሥልጠናው ይጠናቀቃል፡፡ ከተጠናቀቀ በኋላም በተወሰኑት ላይ ክትትል እናደርጋለን፡፡ አመለካከት በአንድ ሥልጠና የሚቀየር አይደለም፡፡ ረጅም ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን በተወሰኑት ላይ ጥሩ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ በዚህ መሠረትም ሥልጠና ከሰጠናቸው መካከል የተወሰኑትን ተከታትለን ውጤታማ መሆናችንን ማወቅ ችለናል፡፡  

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ያለውን ሥር የሰደደ የአመለካከት ችግር ለማጥፋት ምን ያህል ጊዜ ያስፈልጋል?

አቶ አደራ፡- ቻይናዎች ያደጉት ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ ለዚህም የአመለካከት ለውጥ በማምጣታቸው ነው፡፡ ይህም አገርን የማስቀደም አመለካከት፣ የሥራ ተነሳሽነት፣ አብሮ የመሥራት ፍላጐትና ሌሎችም የአመለካከት ለውጦች በመፈጠራቸው የተገኘ ነው፡፡ በእኛም አገር ሕፃናት ላይ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ላይ፣ የግል ድርጅቶች ላይ፣ አጠቃላይ ፖለቲከኞች እና የሃይማኖት ተቋማት ላይ ቢሠራ አመርቂ ውጤት እንድናገኝ ያስችላል፡፡ በሚቀጥሉት 30 እና 40 ዓመታት ውስጥም ተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ ይቻላል፡፡

Standard (Image)

‹‹የማኅበረሰቡ ችግሮች የሚቀረፉት አንድም በተራድኦ ድርጅቶች በመሆኑ መዘጋት የለባቸውም››

$
0
0

አቶ ካሌብ ፀጋዬ፣ የትምህርት ለተቸገሩ ሕፃናት ሥራ አስኪያጅ

 
ትምህርት ለተቸገሩ ሕፃናት (ኤዱኬሽን ፎር ኒዲ ፒፕል አሶሴሽን) ባጭሩ ኤንፓ በተራድኦ ድርጅትነት የተመሠረተው ከስድስት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ በተለያዩ የሕፃናት ማሳደጊያዎች ውስጥ ያደጉ ግለሰቦች ተሰባስበው ያቋቋሙት ድርጅት ሲሆን፣ ቤተሰቦቻቸው ሊያስተምሯቸው አቅም የሌላቸው ሕፃናት በአፀደ ሕፃናትና መዋለ ሕፃናት (የነርሰሪና ኪንደር ጋርደን) ትምህርት በነፃ እንዲያገኙ ያደርጋሉ፡፡ ድርጅቱ ሕፃናቱ ለትምህርት ከሚገለገሉባቸው ቁሳቁሶች ባሻገር በምግብና አልባሳትም ይደጉማል፡፡ ቤተሰቦቻቸው ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ በተለያየ ሙያ በማሠልጠንም እገዛ ይሰጣል፡፡ ስለ ድርጅቱ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ከመሥራቾቹ አንዱ የሆነውን ሥራ አስኪያጁ አቶ ካሌብ ፀጋዬን ምሕረተሥላሴ መኰንንአነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ የተመሠረተው እንዴትና ምን ዓላማ አንግቦ ነበር?

አቶ ካሌብ፡‑የድርጅቱ መሥራቾች በአጠቃላይ በተለያዩ የሕፃናት ማሳደጊያዎች ያደግን ነን፡፡ በአሁኑ ሰዓት በተለያየ ሙያ ተሰማርተን የየራሳችንን ሥራ በመሥራት ላይ ነን፡፡ እኛን በጥሩ ሁኔታ መንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝብ እዚህ አድርሶናልና እኛም በተራችን ለሌሎች ሰዎች እንትረፍ ከሚል በጎ ሐሳብ የመነጨ ነው፡፡ የጀመርነው አንድ ቤት ተከራይተን 75 ሕፃናትን በማስተማር ነበር፡፡ ልጆቹን ቤት ለቤት በማሰስና በአካባቢያችን ያለ ዕድር ውስጥ በማጠያየቅ ነው ያገኘናቸው፡፡ ሰዎች በሚነግሩን መሠረት በጣም የተቸገሩና ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ ሕፃናትን ለመደገፍ የተቋቋመ ነው፡፡ በበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ ተመዝግቦ ትክክለኛ ቅርፅ ይዞ መሥራት የጀመረው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ዘንድሮ 80 ተማሪዎች ያሉን ሲሆን እስካሁን ከ230 በላይ ሕፃናት ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተዋል፡፡ ብዙዎቹ ልጆች በጣም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ናቸው፡፡ እናቶቻቸው ልብስ ማጠብና እንጨት መልቀምን የመሰሉ ሥራዎች የሚሠሩ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ እናቶች ልጆቻቸውን ከአባት ውጪ ማሳደጋቸው ሥነ ልቦናዊ ጫናም አሳድሮባቸዋል፡፡ እናቶቹ ከሚያገኙት ደመወዝ የቤት ኪራይ ከፍለውና የዕለት ጉርሳቸውን ሸፍነው ማስተማር አይችሉም፡፡ ቁርስ ወይም ምሳ ቋጥረው ሲመጡ ባቄላ ወይም ባዶ ሰሀን የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ስለዚህ ልጆቹ ከትምህርት ባሻገር ምሳና መክሰስ እንዲያገኙም ይደረጋል፡፡ የምንሠራበት አካባቢ መጠለያ ይባላል፡፡ ከኤርትራ ተፈናቅለው የመጡ ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ የተሰጣቸው እዚህ ነበር፡፡ ሥራችንን እዚህ አካባቢ ያደረግነውም በርካታ ችግረኞች ያሉበት በመሆኑ ነው፡፡ የተቸገሩ ቤተሰቦች በጣም ብዙ በመሆናቸው ወረዳው ከመዘገባቸው መካከል በጣም ችግረኛ የሆኑትን እንመርጣለን፡፡ ቤት ለቤት እየሄድንም ያሉበትን ሁኔታ እናያለን፡፡ ብዙ ልጆች መቀበል ብንፈልግም ካለን ቦታ ጥበት አንፃር በዓመት 30 ሕፃናት ብቻ ነው የምንቀበለው፡፡

ሪፖርተር፡- ለሕፃናት መሠረታዊ ትምህርት መስጠት የድርጅታችሁ ዋነኛ ትኩረት የሆነው ለምንድነው?

አቶ ካሌብ፡‑የሁሉም ነገር መሠረት ትምህርት ነው፡፡ ሕፃናት እስከ ሰባት ዓመት ያላቸው ዕድሜ ደግሞ ወርቃማ ነው፡፡ በዛ ዕድሜ በደንብ ከተያዙ የትምህርት ፍቅር ያድርባቸዋል፡፡ ከሁሉም ነገር በፊት ትምህርት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ ሕፃናቱ ነገ የአገር ተረካቢዎች ናቸው፡፡ ልጆቹ ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ ማገዝ በእግዚአብሔር ዘንድና ለህሊናችንም ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ መጀመሪያ የሰው አዕምሮ ላይ ከተሠራ ሰውየው ሌላውን ነገር ይሠራዋል፡፡ ዕድገትም ይመጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ልጆቹ በድርጅቱ ውስጥ ተምረው ከወጡ በኋላ ድጋፉ ይቀጥላል?

አቶ ካሌብ፡‑ከጊዜ ወደ ጊዜ የኑሮ ውድነት በሚያሳድርብን ጫና ሳቢያ ብዙ ነገሮች እያጠሩን ነው፡፡ በፊት ልጆቹ ከድርጅቱ ከወጡ በኋላ የቱቶሪያል (አጋዥ) ትምህርት እንዲያገኙ እናደርግ ነበር፡፡ አሁን ግን ይኼን ማድረግ ከአቅማችን በላይ ነው፡፡ የተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ አቅማችን እየተወሰነ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ተግባር የሁሉንም ሰው ድጋፍ ይፈልጋል፡፡ እኛ ብናልፍም ሥራው መቀጠል መቻል አለበትና እገዛ ያሻናል፡፡ ልጆቹ ከድርጅቱ ከወጡ በኋላ በመድኃኔዓለምና ኪዳነምሕረት በዓላት ላይ ስለ ድርጅቱ የተጻፉ ብሮሸሮች በመበተን ድርጅቱን ሊያስተዋውቁ ይሞክራሉ፡፡ ኤንፓ የተሰኘ የእግር ኳስ ቡድን አቋቁመው በመብራት ኃይል ሜዳ የሚጫወቱ የቀድሞ ተማሪዎቻችንም አሉ፡፡ በመለስ ፋውንዴሽን ከ16 ቡድኖች ተወዳድረው የመጨረሻ አራት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ዋንጫ ከወሰዱ ድርጅቱን የሚደግፉ አካላት ትኩረት እንደሚስቡ ያምናሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ያሉባችሁ ችግሮች ምንድናቸው? ከመንግሥትና ከማኅበረሰቡስ ምን ዓይነት ድጋፍ እንዲደረግላቸሁ ትፈልጋላችሁ?

አቶ ካሌብ፡‑እዚህ የሚያስተምሩ መምህራን ደመወዝ ዝቅተኛ ቢሆንም በደስታ ያስተምራሉ፡፡ እኛ ደመወዛቸውን መክፈል እስኪያቅተን ድረስ ችግር ውስጥ ገብተናል፡፡ ኅብረተሰቡ ቢተባበር መምህራኑ እንዳይለቁ ሌሎችም ባለሙያዎችም መጥተው እንዲሠሩ ማድረግ እንችላለን፡፡ ለልጆቹ የምንመግበው መኮሮኒ፣ ሩዝ፣ እንጀራ በሽሮና ዳቦ በወተት ነው፡፡ አቅም ቢኖረን በሳምንት ሦስት ቀን ብቻ ከመመገብ ሳምንቱን በሙሉ መመገብ እንችላለን፡፡ በማንኛውም መንገድ ድጋፍ አደርጋለሁ የሚል አካል ካለ በራችን ክፍት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የዕርዳታ ድርጅት ሲባል የሚፈሩ ሰዎች አሉ፡፡ የዕርዳታ ድርጅቶችን የሚያቋቁሙ ሰዎች የሚያገኙትን ድጎማ ያላግባብ ለራሳቸው ጥቅም ያውሉታል የሚል የተሳሳተ ግምት አለ፡፡ ይህንን አመለካከት መቀየር አለብን፡፡ ሰዎች በአካል መጥተው በማየትና በመከታተል ሕፃናቱን መርዳት ይችላሉ፡፡

ትልቁ ጫና የሆነብን ነገር የቤት ኪራይ ነው፡፡ የምንከፍለው ወደ 12,000 ብር ነው፡፡ ሁልጊዜም መክፈልና አለመክፈላችን በምናገኘው ዕርዳታ ይወሰናል፡፡ ቦታው ዘለቄታዊ እንዲሆን መንግሥት ለትምህርት ቤት የሚሆን ቦታ ቢሰጠን ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ቤት ለቤት እየተዘዋወርን ስንመለከት ብዙ አካል ጉዳተኛ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት ሳይሄዱ ቤት ቀርተው አይተናል፡፡ በአካቶ ትምህርት (በኢንክሉሲቭ ኤዱኬሽን) አራት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ተቀብለናል፡፡ አሁንም ግን ቤተሰቦች መገለልን እየፈሩ አካል ጉዳተኛ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት አያመጡም፡፡ ተቋሙ ሰፍቶ በዚህ ረገድ ብዙ መሠራት አለበት፡፡ ትልቁ ተግዳሮታችን የሆነው የቦታ ችግር ከተፈታ ኅብረተሰቡ በተለያየ መንገድ እንደየአቅሙ ሊደግፈን ይችላል፡፡ ብዙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በበጀት እጥረት ሳቢያ ይዘጋሉ፡፡ ይኼ መሆን የለበትም፡፡ የማኅበረሰቡ ችግሮች የሚቀረፉት አንድም በተራድኦ ድርጅቶች በመሆኑ መዘጋት የለባቸውም፤ መቀጠል አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ዕርዳታ የሚያደርጉላችሁ ግለሰቦች ወይም ተቋማት አሉ? እናንተስ ገቢ ለማግኘት የምታደርጉት ጥረት አለ?

አቶ ካሌብ፡‑በምንሠራበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች በጣም ይደግፉናል፡፡ በጣልያን ትምህርት ቤት ውስጥ ያስተምሩ የነበሩ አራት መምህራን የኮንትራት ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ሳይመለሱ በፊት ከፍተኛ ዕርዳታ ያደርጉልን ነበር፡፡ ዕርዳታ መስጠት ለውጭ ዜጎች ብቻ የተተወ ሳይሆን እኛው ለእኛውም ማድረግ እንችላለን፡፡ የዕርዳታ ድርጅት ቢሆንም የምንሰጠው ትምህርት ጥራቱን የጠበቀ ነው፡፡ ልጆቹ ማወቅ የሚገባቸውን እንዲያውቁ መምህራኑ በፍቅር ያስተምሯቸዋል፡፡ ትምህርቱ ሥነ ጥበብን ያማከለ እንዲሆን ለማድረግም ጥረት ይደረጋል፡፡ ልጆቹን ለማበረታታት ሽልማት ይሰጣቸዋል፡፡ ልጆቹ ሲያድጉ እንደእኛ ዓይነት ድርጅት ለመክፈት እንደሚፈልጉ ሲናገሩ ስሰማ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ገቢ ለማግኘት የምናደርገው ጥናት ካለን ቦታ ጥበት አንፃር ከባድ ነው፡፡ መንግሥት የዕርዳታ ድርጅቶች ከሚረዷቸው ሰዎች ጋር ወጪ መጋራት (ኮስት ሼሪንግ) ያድርጉ የሚል አሠራር አለው፡፡ እኛ የምንረዳቸው ሰዎች በቂ ገቢ ስለሌላቸው ይህንን ማድረግ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ገቢ ማግኛ እንቅስቃሴ የግድ ያስፈልጋል፡፡ ገቢ ለማግኘት ካሰብናቸው ነገሮች መካከል ዶሮ እርባታ፣ ከብት እርባታ ይገኝበታል፡፡ ላም ብንገዛ ልጆቹ ከሚጠጡት ወተት ባለፈ መሸጥ ይቻላል፡፡ የቦታ ችግራችን ሲፈታ የምናከናውናቸው ይሆናሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ልጆቹ በድርጅታችሁ አቅራቢያ ያሉ የዕርዳታ ድርጅቶችን እንዲጎበኙ ታደርጋላችሁ፡፡ ለምን?

አቶ ካሌብ፡‑በአቅራቢያችን መቄዶኒያ የዕርዳታ ድርጅት አለ፡፡ ድርጅቱ እየሠራ ያለው ነገር በጣም የሚያስደስትና የሚያስደንቅ ነው፡፡ ሕፃናቱም ሄደው እንዲጎበኙት አድርገናል፡፡ ልጆቹ በቁርስ ሰዓት የሚሰጣቸውን ዳቦ ይዘው ሄደው ለአረጋውያኑ ሠጥተዋል፡፡ አረጋውያንን ስለመንከባከብ የሚያሳይ ድራማ በማሳየትም አዝናንተዋቸዋል፡፡ ለሰንደቅ ዓላማ ቀንና ሌሎችም በዓላት እየሄዱ በጎ ስለማድረግ እንዲማሩ እናደርጋለን፡፡ ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው የሚለውን የመቄዶንያ መሪ ቃል ጽፈው ሄደው ነበር፡፡ እኛ ሕፃናት ብንሆንም ባለን ነገር ዕርዳታ ከማድረግ ዕድሜያችን አይገድበንም የሚል አስተሳሰብ እንዲያድርባቸው ለማድረግ አስበን ነው፡፡ ሥነ ልቦናቸው ለሰዎች በጎ የማድረግን ነገር እንዲረዳ ለማድረግ ነው፡፡ ልጆቹ አካባቢያቸውን እንዲያውቁም ወደተለያዩ ቦታዎች ትምህርታዊ ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ በአካባቢያችን ያለው መላጣ ጋራ ተራራ ይጠቀሳል፡፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በወንድማማቾቹ ኢዛናና ሳይዛና የተቆረቆረው ዋሻ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፡፡ በጣሊያን ወረራ ጊዜ በፈንጂ ተመቶ ቢፈርስም ጥንታዊነቱ እንደተጠበቀ ነው፡፡ አንድ የለስላሳ ፋብሪካና ቦርን ፍሪ የእንስሳት ማቆያን የልጆቹን ሁኔታ ገልፀን ክፍያው እንዲቀነስልን በማድረግ ጎብኝተዋል፡፡ ለ150 ልጆች 7,500 ብር ወጪ ያስወጣ የነበረውን የኢትዮጲስ ዝግጅት ልጆቹ በነፃ እንዲገቡ ለማድረግም ተችሏል፡፡ ልጆቹ ማንም የለንም የሚል ስሜት እንዳይሰማቸውና ማኅበረሰቡ ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ጋር አብረው መሄድ እንዲችሉ ለማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሕፃናቱ ቤተሰቦች ሕይወታቸውን እንዲለውጡ ስለምትሰጧቸው ሥልጠናዎች ቢገልጹልን?

አቶ ካሌብ፡‑በተደጋጋሚ የቤት ሥራ የማይሠሩ ልጆችን ቤተሰቦች ምክንያቱን ስንጠይቃቸው ባለመማራቸው ልጆቻቸውን በትምህርት መርዳት እንደማይችሉ ይገልጹልናል፡፡ ከመምህራኑ ጋር በጋራ በመመካከር ለቤተሰቦች መሠረታዊ ትምህርት መስጠት ጀመርን፡፡ ከቤተሰቦቹ ጥሩ ምላሽ ስናገኝ ቦሌ ክፍለ ከተማ እናቶቹን እንዲያሠለጥንልን ድጋፍ ጠየቅን፡፡ በመጀመሪያው ዙር የትራንስፖርትና የትምህርት ቤት ክፍያ ችለን 14 እናቶች ሠለጠኑ፡፡ ከዛ በኋላ ወደ 42 እናቶች በምግብና ፀጉር ሥራ እንዲሠለጥኑ ተደረገ፡፡ ሻል ያለ ትምህርት ያላቸው እናቶች ደግሞ የኮምፒዩተር ትምህርት እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ ሥልጠናው ዘላቂነት ያለው ሥራ አግኝተው ቤተሰባቸውን እንዲደግፉ ለማድርግ ያለመ ነበር፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው እንዲሠሩ ለማድረግ የሞከርናቸው ሙከራዎች ባይሳኩም ጥረታችንን ቀጥለንበታል፡፡ ሪፖርተር፡- የድርጅቱ መሥራቾች በዕርዳታ ድርጅቶች ከማደጋችሁ አንፃር በጎ አድራጎታችሁን እንዴት ትገልጸዋለህ?

አቶ ካሌብ፡‑አንዳንዴ ተስፋ ስቆርጥ ባለቤቴ ይህን ሥራ ለምን አትተወውም ትለኛለች፡፡ ነገር ግን መልካም እንቅልፍ የማገኘው ይህንን የበጎ አድራጎት ሥራ በመሥራት ነው፡፡ ብዙ ፈታኝ ነገሮች ቢኖሩትም፣ ልጆቹ መንገድ ላይ መጥተው ሲያቅፉኝ የሚሰማኝን ደስታ የሚያክል ነገር የለም፡፡ ቁሳቁስ ያልፋል፣ ልጆቹ ግን ስማችንን ያስጠራሉ፡፡ የድርጅቱ መሥራቾች ደከመን ሰለቸን ሳይሉ በመሥራታቸው ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡ የበጎ አድራጎት ሥራዎች በዙ የሚሉ አሉ፡፡ ካለው ችግር ስፋት አንፃር ግን ምንም አልተጀመረም፡፡ ባለፈው የትምህርት ሚኒስቴር ስብሰባ ጠርቶን በሰጠን መረጃ መሠረት ከ30,000 በላይ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው፡፡ የዕርዳታ ድርጅቶች እነዚህን ክፍተቶች ይሸፍናሉ፡፡ ኢትዮጵያ እንደምትቀየርና ከድህነት ወለል በታች የሆነ ኑሮ እንደሚለወጥ እናምናለን፡፡ ይህ ዕውን የሚሆነው አንዱ ሌላውን ሲደግፍ ነው፡፡

Standard (Image)

‹‹አሁን ባለው አቅም ኤጀንሲው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሊቆጣጠር አይችልም››

$
0
0

ዶ/ር ተስፋዬ ሙህዬ፣ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር

 
ዶ/ር ተስፋዬ ሙህዬ ፒኤችዲ ዲግሪያቸውን የሠሩት በጂኦግራፊ ሲሆን፣ በፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን ደግሞ ማስተርስ አላቸው፡፡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ሠርተዋል፡፡ የዓለም ባንክ ምሥራቅ አፍሪካ ሪሀብሊቴሸን ፕሮጀክት ማናጀርም ነበሩ፡፡ ከዚያም የአማራ ክልል የትምህርትና ሥልጠና አቅም ግንባታ ፕሮግራሞች መምሪያ ኃላፊ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ሠርተዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል የተወሰነ ጊዜ ከሠሩ በኋላ እንደገና ወሎ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ ሙህዬ በአሁኑ ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርትን ጥራት ለማሻሻል ተቋሙ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በሚመለከት ምሕረት አስቻለውከዶ/ር ተስፋዬ ሙህዬ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ከባድ የጥራት ችግር እንዳለበት አጥኚዎች ይገልጻሉ፡፡ ኤጀንሲውም የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም ችግሩን መፍታት ሳይቻለው የትምህርት ጥራት እየወደቀ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ኤጀንሲውን የመምራት ኃላፊነትን እንዴት ተቀበሉ?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት እየወረደ እንደነበር ተማሪዎቼን በመመልከት እገነዘብ ነበር፡፡ ስለዚህም ወደዚህ ኃላፊነት እንድመጣ ሲነገረኝ ደንግጬ ነበር፡፡ የምንቀበለው፣ አስመርቀን የምናመጣው ተማሪ እንዴት ያለ ነው? የሚለው ሁሌም የመምህራን መወያያ ነው፡፡ ከማኅበረሰቡ የምንሰማቸው ነገሮችም አሉ፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ያለፉና ችግሩን የሚያውቀው ባለሙያ ተቋሙን ካልመራው ሁኔታው ሊቀየር እንደማይችል በማመን ኃላፊነቱ ከባድ እንደሆነ እያወቅኩኝ ተቀብያለሁ፡፡ ወደ ኃላፊነት ስገባም ያልጠበቅኳቸው ችግሮች አጋጥመውኛል፡፡ ቢሆንም በተስፋና በቁርጠኝነት ለመሥራት ወስኛለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከወራት በፊት ኃላፊነት ሲቀበሉ ኤጀንሲው በመዋቅራዊ ለውጥ ሒደት ላይ ነበር፡፡ ሒደቱ አሁንም እንደቀጠለ ይመስለኛል፡፡ የመዋቅራዊ ለውጡ ዋነኛ ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- እኔ ከመምጣቴ በፊት የመዋቅርና ተጓዳኝ የደረጃ ማሻሻያ ተደርጎ ነበር፡፡ አደረጃጀቱ በጣም ጠባብ ነው፡፡ መደቦች ዝቅተኛ በመሆናቸው እንኳን ሌላ ባለሙያ መሳብ እዚህ ያለውንም ለማቆየት የሚያስችል አይደለም፡፡ እዚህ ላይ እየሠራን ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር መሻሻል ያለበት ነገር ቶሎ ተሻሽሎ ወደ ተግባር እንዲገባ ነገሮች እንዲፋጠኑና የትምህርት ጥራት ላይ ሊታይ የሚችል ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እየጠየቀን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲደረግ የሚጠበቀው ትልቁ ለውጥ ምንድን ነው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- አቅማችንን ማሻሻል፡፡ ምክንያቱም በዚህ የቀጨጨ አደረጃጀት በቁጥር፣ በሚሸፍኑት የሥልጠና ዘርፍ አድማስ ሰፊ የሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጥራት ማስጠበቅ የሚቻል አይሆንም፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን ማሻሻል ቀርቶ ተቋማቱን መከታተል የምንችልበት ሁኔታ ላይ አይደለንም፡፡ ስለዚህም የትምህርት ሚኒስቴር ውትወታ አቅም መፍጠሩ ነው፡፡ እኛም እዚህ ላይ እየሠራን ነው፡፡ አሁን ባለው አቅም ግን ኤጀንሲው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሊከታተልና ሊቆጣጠር አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- የኤጀንሲውን አቅም ለመጨመር ምን ዓይነት ነገሮች መደረግ አለባቸው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- የመጀመርያው የሰው ኃይል መሟላት ነው፡፡ ይህ የሰው ኃይል መምጣት ያለበት የከፍተኛ ትምህርት ሁኔታን፣ የማስተማር ሒደቱን ችግሩን ከሚያውቅ ከዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ነው፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ፣ አስተማሪና አመራር ሆኖ ማሰብ የሚችል ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ደረጃ ያለን ሰው ለመሳብ ደግሞ ኤጀንሲው የሚሰጠው ደረጃ ቢያንስ ከዩኒቨርሲቲ መሻል ይኖርበታል፡፡ ሥራውም ጫና ያለው በመሆኑ ደረጃው ሳቢ መሆን አለበት፡፡ ሌላው አቅምን ለማሻሻል የሚያስፈልገው የኤጀንሲው ሥልጣን እንዲጨምር ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ኤጀንሲው የተቋቋመበት አዋጅን ለማሻሻል እየተሠራ ነው፡፡ አዋጁ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች፣ በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አስተያየት እንዲሰጥበት ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ኤጀንሲው የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በመቆጣጠር ረገድ ምንድረስ ሥልጣን አለው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- አንደኛው አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ጉዳይ ይህ ነው፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፕሮግራሞችን የመክፈት የማሠልጠን ሥልጣን  ተሰጥቷቸዋል፡፡ በአደረጃጀት፣ በሰው ኃይልና በመሳሰሉት ተቋማዊ ኦዲት እናደርጋለን፡፡ በዚህ ኦዲት መሠረት በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ዕርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ እንችላለን፡፡ በራሳችን ለብቻችን ግን ዕርምጃ መውሰድ አንችልም፡፡ አዋጁ ቢሻሻል ግን ይህን ማድረግ፣ ፕሮግራሞች ሲከፈቱም የአግባብነታቸውን ጉዳይ በመመዘን ረገድ ሥልጣን ይኖረናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ያኔ ፕሮግራሞች እንዲከፈቱ የመፍቀድ የመዝጋት አቅም ይኖራል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በመቆጣጠር ረገድ የኤጀንሲው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- እዚህ ላይ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ተማሪዎች መቆየት ያለባቸውን ዓመታት ሳይቆዩ የማስመረቅና ባልተፈቀደ ካምፓስ ትምህርት የመስጠት ችግሮች አሉ፡፡ በዚህ መልኩ ተምረው ተመርቀው ሥራ የያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ ሲኦሲ ሳይወስዱ አስተምሮ የማስመረቅ ነገር በተቋማቱ በኩል ይታያል፡፡ በዚህ መልኩ ተምረው ለተመረቁ ዕውቅና አልሰጥም ያሉ ክልሎችም አሉ፡፡ ይህንን ተከትሎ ዕውቅና አለኝ ብሎ በአደባባይ ባስተዋወቀ የትምህርት ተቋም እንዴት እንዲህ እንጭበረበራለን? የሚል አቤቱታ ለእንባ ጠባቂ ሁሉ ቀርቧል፡፡ እነዚህን ችግሮች መፍታት ያስችለናል ያልነውን ስትራቴጂ ለትምህርት ሚኒስቴር አቅርበን ነሐሴ መጨረሻ ላይ ፀድቆ ተሰጥቶናል፡፡ ስትራቴጂውን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ከሌለ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ አሁን የማስፈጸሚያ ስትራቴጂውን መፅደቅ እየተጠባበቅን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ አዲስ ዓመት ተቋማቱን በመቆጣጣር ረገድ የምትከተሉት አሠራር ምን ይመስላል?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- ተቋማቱ ከተፈቀደላቸው ውጭ መንቀሳቀስ የሚችሉበትን ዕድል መዝጋት ነው፡፡ ለምሳሌ በዚህ ዓመት ሥልጠና መስጠት የሚችሉ ተቋማትን፣ የሥልጠና ዘርፎችና ካምፓሶችን ዝርዝር አውጥተናል፡፡ ይህን ዝርዝር በተለያዩ ቋንቋዎች ለራሳቸው ለተቋማቱ ለወረዳ መስተዳድሮች በሙሉ እናሠራጫለን፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ የወረዳ መስተዳድሮች ተቋማቱ አካባቢያቸው ላይ ሲንቀሳቀሱ ፈቃድ ይኑራቸው አይኑራቸው መጠየቅ እንዳለባቸው አያውቁም፡፡ ይህ በዚህ ወር ተግባራዊ መሆን ይጀምራል፡፡ ሌላው ከዚህ ቀደም የነበረ ቢሆንም፣ ከመንግሥትም ተቋማት ጋር በቅርበት መሥራት የዚህ ዓመት ትኩረት ነው፡፡ በቅርቡ የግልም የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶችና የጥራት ማረጋገጫ ኤክስፐርቶችን ጠርተን ተነጋግረን ነበር፡፡ 

ሪፖርተር፡- የትምህርት ጥራት ወርዶ ወርዶ ወደቀ የሚባልበት ደረጃ የደረሰበት አገር ላይ የከፍተኛ  ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ የሚባል ተቋምን መምራት ምን ያህል አስቸጋሪ ነው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- እንደ ዩኒቨርሲቲ መምህር እኔም የጥራት ችግር ምን ድረስ እንደሆነ ተመልክቻለሁ፡፡ የአገሪቱ የትምህርት ጥራት ችግር ከቋንቋ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የተለያዩ ተመራማሪዎች አመልክተዋል፡፡ የትምህርት ጥራትን ችግር መንግሥትም አምኖበት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ነው፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላ ነገር የሥነ ምግባር ነው፤ በአስተማሪም በተማሪም በኩል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአቻ ግመታ ጋር በተያያዘ ምን እየሠራችሁ ነው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- ይህ ነገር የውጭ አገር ዲግሪዎችን በኢትዮጵያ መስፈርት የት ላይ ናቸው? የሚለውን የመገመት ሥራ ነው፡፡ ተግባሩ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ ተማሪ በትክክልም ከአንድ የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲ ዲግሪውን አግኝቷል ወይ? የሚለውን ሁሉ ይጨምራል፡፡ ስለዚህ የአቻ ግመታ ሥራ ሰፊ ነው፤ ጥያቄውን መመለስም ረዥም ጊዜ ይወስዳል፡፡ የተሳሳቱ ማስረጃዎችን ይዘው የሚመጡ አሉ፡፡

 

 

Standard (Image)

‹‹ፊት ለፊት ብታይም ለስኬቴ ብዙዎች ከኋላዬ አሉ››

$
0
0

ሲስተር ጥበበ ማኮ፣ የሕይወት የተቀናጀ የልማት ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ

ሕይወት ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ ድጋፍና ክብካቤ ድርጅት የተቋቋመው ከ17 ዓመታት በፊት ነው፡፡ ድርጅቱ ሕይወት የተቀናጀ የልማት ድርጅት በሚል ስያሜ ከኤድስ በተጨማሪ የልማት ሥራዎችን አቀናጅቶ መሥራት እስከጀመረበት እ.ኤ.አ. 2012 ድረስ፣ ኤድስ ላይ ትኩረት አድርጐ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ድርጅቱን የመሠረቱት ሲስተር ጥበበ ማኮ፣ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በ1970ዎቹ በነርሲንግ ከተመረቁ በኋላ ትዳር ልጅ ሳይሉ በቅጥርና በበጐ ፈቃድ አገልግሎት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከሥራቸው ጋር በተያያዘም ከአምስት ያላነሱ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ የሕይወት የተቀናጀ የልማት ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን ሲስተር ጥበበ ማኮ ምሕረት ሞገስአነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡‑ ኤችአይቪ ኤድስ ላይ መሥራት ሲጀምሩ ግንዛቤው ያልዳበረበት አስቸጋሪ ወቅት ነበር፡፡ እንዴት ወደ ሥራው ገቡ?

ሲስተር ጥበበ፡‑ ኤችአይቪ ኤድስ አገሪቷ ላይ ብዙ ወጣቶችን የገደለበት፣ እናት ልጆቿን የደበቀችበት ጊዜ ነበር፡፡ ሞትም ከፍተኛ ነበር፡፡ መጀመሪያ ድርጅቱ የተመሠረተው ዘነብወርቅ፣ አለርት አካባቢ ነው፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ በአካባቢው ድህነት በስፋት የሚታይበት፣ የሥጋ ደዌ ህሙማን ያሉበት፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሱት እህቶቻችን በብዛት በሴተኛ አዳሪነት የሚሰማሩበት፣ አካባቢው ለከተማው ቆሻሻ መጣያ ቅርብ በመሆኑ፣ ወጣቶች ከቆሻሻው ውስጥ የሚገኙ ቁሳቁሶችን መሸጥ የኑሮ መሠረት ማድረጋቸውና ወንጀል የሚሠራበት በመሆኑ፣ በአካባቢው ላይ የድህነቱ ጥልቀት የተወሳሰበ ነበር፡፡ ለህመሙ ትኩረት ባመኖሩ የታመሙ ይደበቃሉ፣ ቤተሰብ ይገለላል፣ ህሙማን ከቤት አይወጡም፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እሠራበት ከነበረው የኖርዌይ ሕፃናት አድን ድርጅት የጤና ክፍል ኃላፊነት ለቅቄ ወደ ሥራው ገባሁ፡፡ በተለይ በኖርዌይ ሕፃናት አድን ድርጅት እየሠራሁ አንዲት ከክልል መጥታ የሞተች እናትን የሚቀብራት ሰው ጠፍቶ ማየቴና ከጎኗ የነበረችው የስምንት ዓመት ሕፃን ሁኔታ፣ ቀጥታ ወደ ሥራው ለመግባት እንድወስን አድርጐኛል፡፡ ብዙ ገንዘብ ባንዴ ስላፈሰስን ብቻ ሳይሆን ሁላችንም በየምንችለው ስንተባበር ችግሩን እንቀርፋለን ብዬ የጀመርኩት ሥራ ውጤታማ ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡‑ ሥራውን የጀመሩበት ጊዜ ስለኤድስ ለመነጋገር ከባድ ወቅት ቢሆንም፣ እድሮችን ማሳተፍዎ፣ ለስኬትዎ አስተዋጽኦ ነበረው ይባላል፡፡ እንዴት ነበር ከእድሮች ጋር የምትሠሩት?

ሲስተር ጥበበ፡‑ ድንጋይ ሁሉ ተወርውሮብኛል፡፡ በስማችን ልትነግድ ነው ተብዬም ነበር፡፡ እኔ የተነሳሁት እድሮችን መሠረት አድርጌ ነው፡፡ እድር ሁሉን አቀፍ የሆነ የሕዝቡ ኢንሹራንስ ስለሆነ፣ ዘነብወርቅ የሚገኘው አቡነአረጋዊ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በሚገኙ እድሮች ነበር ሥራውን የጀመርኩት፡፡ የእድርን ግንዛቤ በመጨመር ከሞት ባለፈ አባላት ሲታመሙ እንዲረዳ ትልቅ ሥራ ሠርተናል፡፡ መንግሥትና ድርጅቶች ስለለፉ ብቻ ችግሩ ሊቀረፍ ስለማይችል ማኅበረሰቡ ችግሬ ነው ብሎ እንዲነሳ፣ ችግሩን ለመቅረፍ እንዲያግዝ አድርገናል፡፡ በወቅቱ ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ገንዘብ ቢያፈሱም ስርጭቱ እየሰፋ እንጂ እየቀነሰ አልሄደምም ነበር፡፡ ስለሆነም ከመሠረቱ ገብተን በሃይማኖት ተቋማት፣ በእድሮችና በወጣቶች አካባቢ ሠርተናል፡፡ በእድሮችና ሃይማኖት ተቋማት ላይ ስንሠራ ከባድ ነበር፡፡ ዘነብወርቅ አካባቢ እድሮች ለቤተክርስቲያን ቅርብ ሆነው ስለሚሠሩ፣ አቡነአረጋዊ ቤተክርስቲያን እድሮችንና አባላትን አሰባስበን ለማሳመን የነበረውን ጫና አልረሳውም፡፡ ለ45 ደቂቃ ያህል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አያይዤ ኤድስን እንዴት እንደምንከላከል ንግግር አደረግሁ፡፡ ተሰብሳቢውም አጨበጨበ፣ ‹ጥሩ ነው ልጆቻችንን ይዘን መጥተን ግንዛቤ እንዲያገኙ እናደርጋለን› አሉ፡፡ በኋላ ዝግጅቱን ለመዝጋት አንድ ካህን ተነስተው ንግግር አደረጉ፡፡ ንግግራቸው አምስት ደቂቃ ያህል ቢሆንም፣ ከ45 ደቂቃ በላይ ያደረግሁትን ንግግር ዜሮ ያስገባ ነበር፡፡ ፈጣሪ ብዙ ተባዙ እንደሚል በመጥቀስ፣ ምንም እንኳን የኤድስ መከላከያ ከሆኑት አንዱን ኮንዶም ተጠቀሙ ያላልኩ ቢሆንም፣ ኤድስን መከላከል ሲባል ከኮንዶም ጋር አያይዘው በመረዳታቸው ያደረጉት ንግግር፣ ተሰብሳቢው እኔን እንዲቆጣ፣ ድንጋይ እንዲወረውር አድርጓል፡፡ በወቅቱ ተስፋ ቆርጬ ነበር፡፡ ሆኖም እዛው የሚገኙ አንድ መምህር ‹ገና ብዙ ችግር ይገጥምሻል፡፡ ተስፋ አትቁረጪ!› ባሉኝ መሠረት፣ ግንዛቤ ማስጨበጡን ገፋንበት፡፡ በቤተክህነት አካባቢ ትምህርት የሚሰጡ ምሁራን በመድረኩ ትምህርት እንዲሰጡ አደረግን፡፡ ቀስ በቀስ ሕዝቡን ያሸፈቱብኝ አባትም ሆነ ነዋሪውና እድሮች ተቀበሉን፡፡ የታመሙ ሰዎችን ማጽናናትም የካህናት ሥራ ሆነ፡፡ ሲሞቱ ያለምንም ክፍያ ጸሎተ ፍትሐትና ቀብር እንዲከናወንም ረዱን፡፡ ፈተና የነበረ ቢሆንም፣ ቀስ በቀስ የእምነት ተቋማትም ሆነ እድሮችና ማኅበረሰቡ ረድቶን በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ከ50 ሺሕ በላይ ሰዎችን መድረስ ችለናል፡፡ በየቀኑ በድርጅታችን ብቻ በቀን እስከ አሥር ሰው እንቀብር ነበር፡፡ ዛሬ ይህ ተቀይሯል፡፡  

ሪፖርተር፡‑ ድርጅቱ በቤት ለቤት እንክብካቤም ይታወቅ ነበር፡፡ ብዙዎቹም በጐ ፈቃደኞች ሴቶች ነበሩ፡፡ ስለሥራው ቢገልጹልን?

ሲስተር ጥበበ፡‑ የቤት ለቤት እንክብካቤ ዋና ዓላማው የሆስፒታሎችን ጫና ለመቀነስ ነው፡፡ እንዳሁኑ ሆስፒታል ባለመስፋፋቱ፣ ያሉት ሆስፒታሎች በሌሎች ህሙማን የተጨናነቁ ነበሩ፡፡ የኤድስ ህሙማን የሚሞቱ ስለሆኑ ብዙም ትኩረት አይሰጣቸውም፡፡ ብዙዎቹም ደሃ በመሆናቸው፣ ለተጓዳኝ በሽታዎች እንኳን መክፈል አይችሉም ነበር፡፡ የቤት ለቤት እንክብካቤ በማድረግ መገለልና መድሎውን ቀንሰናል፣ ጐረቤት አሳትፈናል፣ ታማሚው ሆስፒታል ቢተኛ የአካባቢው ሰው ልጆችን ያግዛል፡፡ ይህ ሁሉ በእድር አማካይነት ከአካባቢው በሚመለመሉ በጐ ፈቃደኞች የተሠራ ነው፡፡ እድሮች ከሞት ባሻገርም በቁም መረዳዳት እንዲጀምሩ የዘረጋነው አሠራር ዛሬ ላይ እድሮች በተለያዩ ልማቶች እንዲሳተፉም መሠረት ጥሏል፡፡ በወቅቱ በእኛ ድርጅት ብቻ የ27 እድሮች ኅብረት እንዲመሠረት አድርገናል፡፡ በአዲስ አበባ በአሥር ክፍላተ ከተሞች 109 ወረዳ ውስጥ እንሠራም ነበር፡፡ ከ800 በጐ ፈቃደኞች 95 በመቶው ሴቶች ሲሆኑ፣ በየክፍላተ ከተሞቹ እድሮችም ከጐናችን ነበሩ፡፡ ኅብረተሰቡ እያገዘን የሞቱትን በክብር እየሸኘን በኋላ መድኃኒቱ መጣ፡፡

ሪፖርተር፡‑ መድኃኒቱን መቀበልም ከባድ ነበርና እንዴት ተወጣችሁት?  

ሲስተር ጥበበ፡‑ ተጽእኖ ነበር፡፡ ስሙ ዕድሜ ማራዘሚያ ስለነበር፣ ቤተክርስቲያን አካባቢ መድኃኒት የሚጠቀሙ፣ መድኃኒቱን የጣሉበት ጊዜ ነበር፡፡ እዚህ ላይ በጐ ፈቃደኞችና እድሮች ሠርተው፣ ውይይቶች ተደርገው ፀረ ኤችአይቪ ተባለ፡፡ ቤተክርስቲያንም ተቀብላን፣ በየፀበል ሥፍራው እያስተማርን ለውጥ አምጥተናል፡፡ ለዚህ የቀድሞ ፓትሪያርክ ያደረጉት አስተዋጽኦ ትልቅ ነው፡፡ ትልቁን ሥራ ታች ሠርተናል፡፡ ሆስፒታሎችን አግዘናል፡፡ መድኃኒቱን በተለይ መግዛት ለማይችሉ በቅድሚያ በነፃ ሰጥተናል፡፡ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበርም ከእኛ ጋር ሠርቷል፣ ረድቶናል፡፡ እያደር ህሙማኑ በሽታውን የመከላከል አቅማቸው ዳብሮ፣ የመተላለፍ ስርጭቱም ቀነሰ፡፡ በኤድስ ምክንያትም የሚሞት ሰው የለም፡፡ ተጓዳኝ በሽታዎችን በመከላከል፣ ከአልኮልና ከሌሎች ሱሶች በመጠበቅ፣ ፆታዊ ግንኙነቶችን በመገደብ፣ በሽታው አለብኝ ብሎ በመቀበልና ሥርዓተ ምግብን በማስተካከል መኖር ይቻላል፡፡ ይህን አቀናጅተን ኤድስ ላይ በሠራነው ሥራም ለውጥ አምጥተናል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡‑ እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ ሕይወት የተቀናጀ የልማት ድርጅት በሚል ስያሜ እየሠራችሁ ነው፡፡ በዚህኛው ፕሮጀክት ምን ተካቷል?

ሲስተር ጥበበ፡‑ የኤድስ ስርጭት፣ የታመመ ሰውና ሞት ሲቀንስ፣ አቅጣጫችንን ወደ ልማት አድርገን፣ በአራት ፕሮግራሞች ላይ እየሠራን ነው፡፡ ኤድስ ላይ የምንሠራው ቢኖርም፣ እንደ በፊቱ ለብቻው ትኩረት አንሰጠውም፡፡ ፕሮግራሙንና ሽፋናችንን አስፍተን በአምስት ዓመት መርሐ ግብራችን አካተን የኅብረተሰቡ ልማት ላይ እየሠራን ነው፡፡ አገሪቷ ያላትን የልማት ዕቅድ በሚደርስ መልኩ ዕቅድ አውጥተናል፡፡ አንዱ የሕፃናትና የወጣቶች ልማት ሲሆን፣ ይህ ፕሮግራም ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን ችግሮች መቅረፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ፣ ትምህርት፣ መጠለያ፣ የምክር አገልግሎትና የሕግ ከለላ በመስጠት ዙሪያ ሕፃናት ላይ እንሠራለን፡፡ ልጆች ባሉበት ቦታ ሳይፈናቀሉ ማኅበረሰብ አቀፍ የሆነ የጤና ክብካቤ እናደርጋለን፡፡ ልጆች ወላጆቻቸው እንኳን ቢሞቱ፣ ዘመዶቻቸው ጋር ሆነው ማንነታቸው እንደተጠበቀ፣ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን አውቀው እንዲኖሩ እናደርጋለን፡፡ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ብዙ ሕፃናት አሉ፡፡ እነዚህ ሕፃናት ሆዳቸው ባዶ መሆን የለበትም፡፡ ስለሆነም የምግብ ፕሮግራምም አለን፡፡

ሪፖርተር፡‑ በዚህ ፕሮግራም ሥር ምን ያህል ተረጂዎች አላችሁ?

ሲስተር ጥበበ፡‑ አዲስ አበባ በሁሉም ክፍላተ ከተሞችና ሰሜን ሸዋ ውስጥ አሁን ላይ 15 ሺሕ ያህል ሕፃናትና ታዳጊዎች እንረዳለን፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በስፖንሰርሺፕ የምናግዛቸው አሉን፡፡ ውጭ ያሉ በወር ለአንድ ልጅ 20 ዶላር፣ አገር ውስጥ ያሉ 400 ብር እየደገፉን፣ ገንዘቡንም ለሚያሳድጉ ቤተሰቦች በየወሩ ቀጥታ እየሰጠን የምናግዝበት አሠራር አለ፡፡ ከ15 ሺዎቹ 600 ያህሉ በስፖንሰር የሚረዱ ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና ክብካቤ እንሠራለን፡፡ ኤድስ እዚህ ውስጥ ተካቶ ይሠራል፡፡ በዚህ ፕሮግራም የግልና አካባቢ ንጽህናን ጨምሮ ጤና ነክ ነገሮች ይከናወናሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የቤተሰብን ኢኮኖሚ ማጠናከር ነው፡፡ በዚህ ሥር ቁጠባን ጨምሮ መሠረታዊ የንግድ ክህሎት ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ኢንተርፕረነርሺፕ ላይም እናሠለጥናለን፡፡ በዚህ በተለይ ለሴቶች ትኩረት እንሰጣለን፡፡ የብድርና ቁጠባ ማኅበር በማቋቋም ያለወለድ እየወሰዱ ራሳቸውን እንዲያቋቁሙ እናደርጋለን፡፡ ለዚህም መቆጠብ ግድ ነው፡፡ የዚህ ዓላማ በጣም የተቸገሩትን ከተረጂነትና ጥገኝነት ማላቀቅ ነው፡፡ ሌላው ባላቸው ቦታ ላይ የጓሮ አትክልት እንዲያበቅሉ ነው፡፡ ሰሜን ሸዋ ላይ ምርጥ ዘር እንሰጣለን፡፡ በተሰጣቸው ዘር አምርተው ለሌሎች እንዲያዳርሱ እናደርጋለን፡፡ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አትክልት እንዲያበቅሉና እንዲመገቡ፣ ብሎም እንዲሸጡ እያስቻልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡‑ ኤድስ ላይ መዘናጋት አለ ይባላል፡፡ በእናንተ በኩል መልሶ እንዳያገረሽ ምን እያደረጋችሁ ነው?

ሲስተር ጥበበ፡‑ እንደ ድሮው በጅምላ ሳይሆን ማነው ለበሽታው ተጋላጭ የሆነው የሚለውን ለይተን ሴተኛ አዳሪዎች ላይ እየሠራን ነው፡፡ ደብረ ብርሃን፣ መሀል ሜዳ፣ ፍቼ፣ ገብረጉራቻ፣ጎሃ ጽዮን ሱሉልታና ሰንዳፋ እንዲሁም በአዲስ አበባ ቂርቆስና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ላይ ፒኤስአይ እየረዳን እንሠራለን፡፡ ሴተኛ አዳሪዎቹ እንዲመረመሩ ተደርጐ፣ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ወደ ሕክምና እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ 15 በመቶ የሚሆኑ ሴተኛ አዳሪዎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው፣ ብዙ ቦታዎች ላይ ግን በጣም ትንሽ ነው፡፡

ከ50 ሺሕ በላይ ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩ ድጋፍ ብናደርግም፣ ሁልጊዜ ግን ድጋፍ እየሰጠን አንቀጥልም፡፡ ራሳቸውን በኢኮኖሚ እያጠናከርን ከድጋፍ እንዲወጡ እናደርጋለን፡፡ በዚህም ከልጅነት ጀምሮ ይዘናቸው ዩኒቨርሲቲ የገቡ፣ ተመርቀው ሥራ የያዙ አሉን፡፡

ሪፖርተር፡‑ በሠራችሁት ሥራ የመጣውን ለውጥ እንዴት ይገመግሙታል?

ሲስተር ጥበበ፡‑ ሥራው ፈተና አለው፡፡ ሆኖም ትልቅ ለውጥ አይተናል፡፡ ሞትና የታማሚዎች ቁጥር ቀንሷል፡፡ ትልቁ ነገር ሕይወት ማዳን ነው፡፡ እሱን አድርገናል፡፡ ሕፃናቱ እየተማሩ ነው፡፡ በዘነበወርቅ አካባቢ ሁለት ላይብረሪ ሠርተናል፡፡ የአካባቢው ልጆች እየተጠቀሙበት፣ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያም እያለፉ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡‑ ሥራውን ሲጀምሩ መነሻዎት ምን ነበር?

ሲስተር ጥበበ፡‑ ሥራውን የጀመርኩት በራሴ አቅም ነው፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት ያለኝን ሀብት ተጠቅሜ ነው የጀመርኩት፡፡ ትዳር የለኝም፣ ልጅ የለኝም፡፡ ጤና ባለሙያም የሆንኩት እንደ አባት የምናየው ወንድሜ ታሞ በማየቴ ነው፡፡ ገንዘብ ባይኖረኝ በእውቀቴ ወንድሜን እንከባከባለሁ ከሚለው በጐ ዓላማ ተነስቼ ሕዝባችንን ለመርዳት በቅቻለሁ፡፡ የበጐ ሥራ ከውስጤ ያለ ነው፡፡ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በ1970ዎቹ በነርስነት ከተመረቅሁ በኋላ፣ አሰብና የተለያዩ ቦታዎች ሠርቻለሁ፡፡ በሙያው የገባሁት ዩኒፎርሙ አምሮኝ፣ ብር ለማግኘት ሳይሆን፣ ሌሎችን ለመረዳት ነው፡፡ በኋላ ኖርዌይ ሕፃናት አድን ድርጅት ገብቼ ወላይታ ላይ የነበረውን የድርቅ ተጐጂ ለመታደግ ሠርቻለሁ፡፡ የፕሮጀክት ኃላፊም ነበርኩ፡፡ የራሴን ድርጅት ከ17 ዓመታት በፊት ከመመሥረቴ በፊት ሰሜን ሸዋ፣ ተጉለት፣ ጅማና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሠርቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡‑ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶች አግኝተዋል፡፡ ቢጠቅሱልን?

ሲስተር ጥበበ፡‑ የአፍሪካ ሊደርሺፕ ፕራይዝ ማለትም በአፍሪካ የአመራር ብቃት ላሳዩ መሪዎች የሚሰጥ ሽልማት ሲሆን፣ ኔልሰን ማንዴላ ዩዌሪ ሙሴቬኒና ሌሎችም ተሸልመውታል፡፡ እ.ኤ.አ. 2001 ላይ ከታችኛው ኅብረተሰብ ክፍል ገብተው ችግሮችን ከሥር ለመቅረፍ የሚሠሩም በመካተታቸው ከምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ ሆኜ ሎሬት ሲስተር ጥበበ ማኮ የሚል የአፍሪካ ሊደርሺፕ ፕራይዝ ተሸልሜያለሁ፡፡ አብሮ 50 ሺሕ የአሜሪካ ዶላር የተሰጠኝ ሲሆን፣ ይህንንም ለድርጅቴ ሰጥቻለሁ፡፡ በወቅቱ የኒውዮርክ ትራንስፖርትን የቻሉን ሼህ መሐመድ አላሙዲን ስለነበሩ፣ ለሱ የተሰጠኝን 5 ሺሕ ዶላር ጨምሬ፣ ለድርጅቱ ቢሮ ገዛንበት፡፡ እ.ኤ.አ. በ2003 ቤስት ፐርፎርማንስ ፎር ሆም ቤዝድ ኬር በሚል፣ ከሴንተር ኦፍ ኢንተርናሽናል ለርኒንግ ማዕከል ሽልማት አግኝቻለሁ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2004 ባንኮክ ታይላንድ የዓለም የኤድስ ኮንፍረንስ ሲደረግ፣ እድሮችን አሳትፌ የሠራሁበት መንገድ አዲስና የራሴ ፈጠራ ስለነበር፣ አክሰስ አዋርድ የሚባል ሽልማት አግኝቻለሁ፡፡ በዓለም ከ100 አገሮች ህንድ አንደኛ ስትሆን ከኢትዮጵያ በኛ ድርጅት ሁለተኛ ሆነን ተሸልመናል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2008 ወርልድ ኦፍ ችልድረን፣ ሕፃናት ላይ በሠራነው ሥራ የ20 ሺሕ የአሜሪካ ዶላርና ሜዳልያ ሸልሞኛል፡፡ ኤድስን በመከላሉ ረገድ ድርጅታችን ላመጣው ለውጥ ከሲያትል ፕሪቬንት አዋርድ አግኝቻለሁ፡፡ አሜሪካ ካሉ ዳያስፖራዎች እንዲሁም ከአገር ውስጥም ተሸልሜያለሁ፡፡ ይህን ሁሉ ስናገር እኔ ፊት ለፊት ብታይም ላስመዘገብኩት ስኬት ብዙ ሰዎች ከኋላዬ አሉ፡፡ ለዚህም ነው ከሽልማቱ አንድ ብር ለራሴ ሳልጠቀም ለድርጀቱ ያዋልኩት፡፡                  

 

Standard (Image)

ኢኮኖሚው ያልታደገው ዓይነስውርነት

$
0
0

ዶ/ር ፍጹም በቀለ፣ ከጎንደር ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ የሕክምና ዶክትሬት አግኝተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት በዓይን ሕክምና ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ሲሆን፣ በለንደን ስኩል ኦፍ ሐይጂን በኮሙዩኒቲ አይ ሔልዝ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በህንድ፣ በአሜሪካና በሌሎችም አገሮች አጫጭር ሥልጠና ተከታትለዋል፡፡ በሥራ ዓለምም በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚገኘው ጨንቻ ሆስፒታል ተመድበው አገልግለዋል፡፡ በአዲስ አበባና በመቐለ የሚገኙ ፍጹም ብርሃን ስፔሻላይዝድ አይ ሴንተሮች መሥራች፣ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የኢትዮጵያ የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ታደሰ ገብረማርያም በማኅበሩ እንቅስቃሴና በዓይን ሕክምና ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለማኅበሩ አጠር ያለ ማብራሪያ ቢሰጡን?

ዶ/ር ፍጹም፡- የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች ወይም የዓይን ሐኪሞች ማኅበር ከተቋቋመ 18 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ወደ 150 የሚጠጉ የዓይን ሐኪሞች አባላት አሉት፡፡ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የዓይን ሐኪሞች አንድ ዓይነት የሙያ ክህሎት እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው፡፡ ለዚህም በአገር ውስጥና በውጭ አገር ልዩ ልዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ይዘጋጅላቸዋል፡፡ ለአባላቱ አቅም ግንባታ ሥልጠና ልዩ ትኩረት የተሰጠውም፣ በትምህርት ቤት ደረጃ እኩል ቢሠለጥኑም፣ እኩል ላይሠሩ ስለሚችሉ ነው፡፡ ይህንን ማሻሻል የሚቻለው በየጊዜው ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ነው፡፡ በየዓመቱም አዳዲስ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና በአገር ውስጥ ይሰጣቸዋል፡፡ ለምሳሌ ‹‹በኮርኒያና አያያዙ፣ ወይም ሬቲናና አያያዙ›› በሚሉና ‹‹አዲስ በገባው የጨረር ሕክምናና አዲስ ዓይነት ቀዶ ሕክምና›› የሚሉ ጉዳዮችን እያነሳን፣ እናሠለጥናለን፡፡ እንዲሁም ከትምህርት ቤት ከወጡ በኋላ የመጡ ሳይንሶችን እንዲያውቁ ይደረጋል፡፡ ሥልጠናውን የሚሰጡት ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች ቢሆኑም፣ በአብዛኛው ግን ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከካናዳ፣ ከህንድና አፍሪካ ውስጥ ደግሞ ከናይጄሪያ የሚመጡ ሙያተኞች ናቸው፡፡ ሙያተኞቹም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው ይመጣሉ፡፡

ሪፖርተር፡-  በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የዓይን በሽታ ለመከላከል እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴ ላይ የማኅበሩ ድርሻ ምንድነው?

ዶ/ር ፍጹም፡- በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የዓይን በሽታ አስመልክቶ ማኅበሩ በጥናት ላይ ይሳተፋል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ምን ያህል ዓይነስውርነት አለ? ለዓይነስውርነት መነሻ የሆኑትስ ምን፣ ምን ናቸው? በሚሉት ዙሪያ በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ላይም ማኅበሩ ተሳታፊ ሆኗል፡፡ በዚህም ተሳትፎው ጥናቱ እንዴት መካሄድ እንዳለበት የሚጠቁም ዲዛይን አዘጋጅቷል፡፡ ጥናቱንም ወደ ኅብረተሰቡ ውስጥ ገብተው ያጠኑት የማኅበሩ አባል የሆኑ የዓይን ሐኪሞች ናቸው፡፡ በጥናቱም ላይ ችግሩ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ነው? ግላኮማ ነው? ረቲና ነው? ወዘተ ብለው ዘርዝረውታል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ሰው ዓይነስውር ነው የሚባለው እንዴት ነው?

ዶ/ር ፍጹም፡- የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስቀመጠው አንድ ሰው ዓይነ ስውር ነው የሚባለው፣ ከሦስት ሜትር በላይ ማየት ከተሳነው ወይም እይታው ከሦስት ሜትር በታች ከሆነ ነው፡፡ ዓይነስውር ማለት ሙሉ ለሙሉ ብርሃኑ የጠፋ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር ከ100 ሚሊዮን ሕዝቦች መካከል 1.6 ሚሊዮን ያህሉ ወይም 1.6 በመቶ የሚጠጉ ዓይነስውራን አሉ፣፡ ይህም መጠን በአሁኑ ጊዜ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም የተመዘገበ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለዓይነስውርነት ድህነት አስተዋጽኦ አለው?

ዶ/ር ፍጹም፡- በጣም አስተዋጽኦ አለው፡፡ ዓይነስውርነትን ያስከትላሉ ተብለው ከሚታወቁ ችግሮች መካከል ግማሾቹ በተላላፊና በንጽሕና ጉድለት ሳቢያ የሚከሰቱ፣ እኩሎቹ በዕድሜ ምክንያት፣ ከፊሎቹ ደግሞ መታከም ሲገባቸው ሕክምና ባለማግኘታቸው የሚመጡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የዓይን ሞራ ግርዶሽን በምንወስድበት ሰዓት ሰው በዓይን ሞራ ግርዶሽ መታወር አልነበረበትም፡፡ በቀዶ ሕክምና የሚድን ነው፡፡ በቂ የሆነ የውኃ አቅርቦት በሌለበትና የትምህርት ደረጃ እጅግ ዝቅተኛ በሆነበት አካባቢ ትራኮማ አገር ያጥለቀልቃል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ብርሃናቸውን ያጣሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ይህ በሽታ ከድህነት ተያይዞ የሚመጣ ነው፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት ደረጃ መሠረትም ትራኮማ ‹‹የድህነት በሽታ ነው›› በሽታው ሕክምና ስላገኘ አይደለም የሚድነው፣ ንጽሕናው የተጠበቀ ውኃና ትምህርት በማቅረብ፣ ጥሩ ግንዛቤ በመፍጠር ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የማከሙ ፋይዳ እስከምን ድረስ ነው?

ዶ/ር ፍጹም፡- ትራኮማ የያዘው ሰው ዓይነስውር የሚሆነው ትራኮማው ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው፡፡ ይህም ማለት የዓይን ቆዳው ፀጉር ይታጠፍና የዓይኑን መስታወት ይቦጭረዋል፡፡ በዚህን ወቅት ሕመም ይኖራል፡፡ በቀዶ ሕክምና ፀጉሩ ቀና ከተደረገ ታካሚው ከሕመም ይገላገላል፡፡ ስለሆነም ማከሙ እዚህ ላይ ነው የሚጠቅመው፡፡ በትራኮማ ምክንያት ዓይናቸው ፀጉር የበቀለባቸውን ሰዎች ቀዶ ሕክምና አድርጎ ማዳን፣ ወይም ከትራኮማ ጋር የሚመጣን ዓይነስውርነት በዚህ መልኩ መቅረፍ እንደሚቻል ግንዛቤው ሊወሰድ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ አንፃር ከድህነት ብንላቀቅና ሰዎች ንጽሕናቸውን ቢጠብቁ ኖሮ ዓይናቸው ፀጉር ወደ ማብቀል አይደርስም ነበር ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ፍጹም፡- ትክክል ነው፡፡ ኢኮኖሚያችን ከፍ ቢል፣ በቂና ንጹሕ የሆነ የውኃ አቅርቦት ሊኖር ይችል ነበር፡፡ ትምህርት ሲስፋፋ ደግሞ ስለፊት አስተጣጠብና በአጠቃላይ ስለግልና አካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ ማስተማር ይቻል ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ የተማረ ሰውና ትራንስፖርት ይኖራል፡፡ መረጃ ማግኘት ይቻላል፡፡ በዚህም ታክሞ እንደሚዳን ግንዛቤው ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ ዓይኑ ሳይታወር ይድን ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የትራኮማ በሽታ በአገሪቱ በጣም ተንሠራፍቷል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ፍጹም፡- በአገሪቱ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የትራኮማ ችግር አለ፡፡ እንደውም የትራኮማ ችግር አለባቸው ተብለው ከተፈረጁት ወይም ከተለዩት የዓለም አገሮች መካከል ዋነኛዋ ኢትዮጽያ ናት፡፡

ሪፖርተር፡- በትራኮማ ዓይናቸው ፀጉር የበቀለባቸው ሰዎች ስንት ናቸው? ይህንን ለመቆጣጠር ምን እየተደረገ ነው?

ዶ/ር ፍጹም፡- ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ወይም የዓይን ፀጉር ያለባቸው ሰዎች አሉ፡፡ ከዓይን ጋር ተያይዞ ያለውን ሥራ የሚያከናውኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች እንዲሁም ጤና ኬላዎችና ጣቢያዎች የተሳተፉበት አንድ ግብረ ኃይል ካለፈው ሦስት ዓመት ወዲህ ተቋቁሟል፡፡ በትራኮማ ሳቢያ ዓይናቸው ፀጉር ለበቀለባቸው ወገኖች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት በዘመቻ እየሰጠ ነው፡፡ ለዚህም የሚረዱ መድኃኒቶች እየቀረቡ ናቸው፡፡ የቀዶ ሕክምናው ያስፈለገው እነዚህ ወገኖች ዓይነስውር ከመሆናቸው በፊት እናድናቸው ወይም እንከላከልላቸው ከሚል ቀና አመለካከት በመነሳት ነው፡፡ አገልግሎቱንም የሚሰጡት ዓይን ውስጥ የገባውን ፀጉር በቀዶ ሕክምና የማቃናት ሥልጠና የወሰዱ ነርሶች ናቸው፡፡ ሕክምናው በዘመቻ ከተጀመረበት አንስቶ እስካለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ 300,000 ወገኖች አገልግሎቱን እንዳገኙና ከዓይነስውርነት እንደተጠበቁ ይገመታል፡፡ አገልግሎቱም የሚካሄደው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው ፕሮግራም መሠረት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግላኮማ የተባለው የዓይን በሽታ እንዴት ይከሰታል?

ዶ/ር ፍጹም፡- ግላኮማ የዓይን ግፊት ይጨምርና የዓይናችንን ስር ይጫነዋል፡፡ ሥሩ ሲጫን ደግሞ ቋሚ የሆነና ከዓይናችን ወደ አንጎላችን የሚወሰደውን ኦፕቲክ ነርቭ ይገድለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ሰዎች ዓይነብርሃናቸው ይጠፋል፡፡ ‘ግላኮማ የዓይን ብርሃን ሌባ ነው’ የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ሰውየው አያመው፣ ምን አይለው፣ እንዲሁ ዓይኑ ይጠፋል፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ዓይነስውር ሳይሆኑ የምናገኛቸው በምርመራ ብቻ ነው፡፡ ወይም የዓይን ግፊታቸውን ከለካን ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ብቸኛ መፍትሔ ምንድነው?

ዶ/ር ፍጹም፡- ስለግላኮማ አደገኛነት ማስተማር ሲሆን፣ ሌላው መፍትሔ ደግሞ ዕድሜው ከ40 ዓመት በላይ የሆነ ማንም ሰው የዓይን ግፊቱን መለካት አለበት፡፡ ቤተሰቡ ግላኮማ ያለበት ከሆነ ደግሞ ልዩ ወይም ተጨማሪ ምርመራ ሊደረግለት ይችላል፡፡ ሰው ዓይኑ ሳይጠፋ መታከም ይገባል፡፡ ለዚህም የሚሆን መድኃኒትና ቀዶ ሕክምና አለ፡፡ ግላኮማ በምርመራ ብቻ የሚገኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የስኳር በሽታ ከዚህ ጋር እንዴት ይታያል?

ዶ/ር ፍጹም፡- ዲያቤቲክስ በዓይን ላይ እያስከተለ ያለው ጠንቅ በእጅጉ ከፍተኛ ነው፡፡ ብዙ የስኳር በሽተኞች ሌላው አካላቸው እንደሚጎዳ ሁሉ፣ ዓይናቸውንም እየተጎዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር አንዳንዶቻችን አመጋገባችንን በሥነ ሥርዓት አናካሂድም፣ ስለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያለን ግንዛቤና ዕውቀት በቂ አይደለም፡፡ የዓይን ሐኪም የማማከር ልምዳችን በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ በየቦታው የመድኃኒት አቅርቦትና ሐኪም ያለመኖር ችግር አለ፡፡ እነዚህ ችግሮች ሁሉ ተደማምረው በስኳር በሽታ ቶሎ የመጠቃት ነገር እየታየ ነው፡፡ በዚህም ብዙ የዓይን ጉዳቶችን እያየን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከዓለም አቀፍ መሰል ተቋማት ጋር ግንኙነት አለው?

ዶ/ር ፍጹም፡- የዓይን ስፔሻላይዝድ ከተኮነ በኋላ ሰብ ስፔሻሊስት የሚባል አለ፡፡ ይኼውም የሬቲና፣ የግላኮማ፣ የኮርኒያ ወዘተ ሰብ ስፔሻሊስት ማለት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ሰብ ስፔሻሊስት ሥልጠና በአገር ውስጥ የለም፡፡ አባሎቻችን ሰብ ስፔሻሊስት ሥልጠና የወሰዱት ውጭ አገር ነው፡፡ ይህንንም የሥልጠና ዕድል የሚሰጠው መንግሥት ሳይሆን ኢንተርናሽናል ድርጅቶቹ ናቸው፡፡ ከሆስፒታሎች ወይም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት ፈጥረን አባላት ለአንድ ወይም ለሁለት ዓመት እየሄዱ ጥልቅ ትምህርት ያደርጋሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከዓይን ባንክ ጋር ያለው ግንኙነት እንዴት ይታያል?

ዶ/ር ፍጹም፡- የዓይን ባንክ የራሱ አካሄድ አለው፡፡ ነገር ግን ማኅበራችን የኮርኒያ ወይም የዓይን መስታወት ነቅለው የሚገጥሙ ስፔሻሊስቶች አሉት፡፡ እነዚህ ስፔሻሊስቶች ከዓይን ባንክ ጋር እየሠሩ ነው፡፡

Standard (Image)

በዩኔስኮ የአዲስ አበባ ጉባዔ ለውሳኔ የሚቀርበው የገዳ ሥርዓት

$
0
0

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከማይዳሰሱ (ኢንታንጀብል) ባህላዊ ቅርሶቿ መካከል አንዱ የሆነውን የገዳ ሥርዓት ለማስመዝገብ በእንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች፡፡ ከመስቀልና ከፊቼ ጫምባላላ በዓሎቿ ቀጥሎ የኦሮሞ ብሔር ባህላዊ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሥርዓት የሆነውን የገዳ ሥርዓት በወካይ ቅርስነት ለማስመዝገብ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ሥራው ከጫፍ መድረሱን ይገልጻል፡፡ ከኅዳር 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ በሚካሄደው የዩኔስኮ 11ኛው የኢንተርገቨርንመንታል ጉባኤ የገዳ ሥርዓት በዓለም ወካይ ቅርስነት ለመመዝገብ ተስፋ እንዳለው ባለሥልጣኑ ያወሳል፡፡ የኢሬቻ በዓልን ያቀፈው የገዳ ሥርዓት ለማስመዝገብ እየተደረገ ስላለው ተግባር በባለሥልጣኑ የባህል አንትሮፖሎጂስት፣ የገዳ ሥርዓትን በዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ የተቋቋመው የጥናት ቡድን አስተባባሪውን አቶ ገዛኸኝ ግርማን ሔኖክ ያሬድአነጋግሯቸዋል፡፡

 
ሪፖርተር፡- ገዳን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እያከናወናችሁ ያላችሁት ተግባር እንዴት ይገለጻል?

አቶ ገዛኸኝ፡‑ የኦሮሞ ብሔር ባህላዊ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሥርዓት የሆነውን የገዳን ሥርዓት በማይዳስስ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር የተለያየ ተግባራት ስናከናውን ቆይተናል፡፡ ዝግጅቱን የጀመርነው ሰኔ 2006 ዓ.ም. ሲሆን፣ የኢሬቻ በዓልም የገዳ ሥርዓት መገለጫ ከሆኑ አንኳር ባህላዊ ገጽታዎች መካከል አንዱና የሥርዓቱ አካል በመሆኑ በገዳ ውስጥ ሆኖ በሰው ልጆች ወካይ ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ ዝርዝር በኦሮሚያ ክልል በሚኖሩ ሰባት ዞኖች ለምሳሌ ለቦረና፣ ለጉጂ፣ ምሥራቅ ሸዋ ከረዩ፣ ምዕራብ ሐረርጌ ቦዳ ቡልቱ ምዕራብ ሸዋ፣ ወሊሶ፣ አምቦ እስከ ወለጋ ድረስ የመስክ ሥራ ተከናውኗል፡፡ የገዳ ሥርዓትን በተመለከተ የተሰባሰቡትን መረጃዎች በመተንተን በማጠናቀር በውስጡ እነ ኢሬቻ፣ ጉዲፈቻ፣ ዋቄፈና፣ ሲንቄ የመሳሰሉትን ሌሎች ጉዳዮችን አካትቷል፡፡ ሌላው ስለገዳ ሥርዓት ለዓለም የሚያስተዋውቅ የአሥር ደቂቃ ዶክመንተሪ ፊልም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተዘጋጅቷል፡፡ ከገዳ ሥርዓት ጋር እንዲሁም ተዛምዶ ያላቸውን ስለሥርዓቱ የሚያሳዩ አሥር ፎቶዎች ዩኔስኮ ባስቀመጠው መሠረት ተመርጠው ተያይዘዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የገዳ ሥርዓት ሲባል ምን ማለት ነው?

አቶ ገዛኸኝ፡- በዋናነት በሰነዶቹም ሆነ በፊልሙ ላይ እንደተካተተው፣ የገዳ ሥርዓት ፈርጀ ብዙ ወይም አያሌ ተቋማትን በውስጡ ያካተተና የኦሮሞ ሕዝብን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓትን የሚመራ ነው፡፡ የቅርሱ ባለቤት የኦሮሞ ብሔር የቦረና፣ የጉጂ፣ የከረዩ፣ የገብራ፣ የቱለማ፣ የመጫ፣ የኢቲ እና ሑምባና ጎሳዎች ናቸው፡፡ ገዳ አያሌ ፍቺዎች ያሉት ሲሆን በገዳ ሥርዓት ውስጥ ከአንድ በላይ የሆኑ ጽንሰ ሐሳቦችን ይወክላል፡፡ ገዳ የጊዜና የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት ነው፡፡ ለስድስተኛው እርከን ማለትም በሥልጣን ላይ ያለው መደብ (tuuta ykn gogeesa) መጠሪያ ነው፡፡ እያንዳንዱ መደብ በሥልጣን ላይ የሚቆይባቸው የስምንት ዓመታት ወቅትም ገዳ ይባላል፡፡ ገዳ የአጠቃላይ ሥርዓቱም መጠሪያ ነው፡፡

   ገዳ የኦሮሞ ብሔር አንኳር የሆኑ ባህላዊ ገጽታዎች፣ ታሪክና እምነት የሚንጸባረቁበት አገር በቀል የሆነ እውቀትን አካቶ የያዘ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ነው፡፡ የገዳ ሥርዓት የፖለቲካና ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚያስተናግዱ አያሌ የግጭት አፈታት ጥበቦችን በውስጡ ያካተቱ ተቋማት አሉት፡፡ ከነዚህም መካከል ጉዳት ያደረሰው ወገን ካሳ (ጉማ) በመክፈል የሚደረገውን ዕርቅ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሌላም በኩል በገዳ የሞጋሳ ሥርዓት አንድ በራሱ ሙሉ ፍላጎትና ውዴታ ከኦሮሞ መቀላቀልን የሚፈልግ ግለሰብም ሆነ ቡድን ይህን መብት የሚያገኝበት ሥርዓት ነው፡፡ በሞጋሳ ሥርዓት በራሱ ሙሉ ፍላጎትና ውዴታ ኦሮሞን የተቀላቀለ ሰው ኦሮሞነቱን በተቀበለ ጎሳ ዘንድ የፖለቲካ፣ማኅበራዊና የኢኮኖሚ መብቶቹን እንደዚሁም የጎሳ አባልነት ሙሉ መብት ይቀዳጃል፡፡ የገዳ ሥርዓት ካደራጃቸው የተለያዩ ተቋማት መካከል ሌላኛው ሲንቄ ነው፡፡ ሲንቄ መብት ለማስከበር የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ ሲንቄ (siinqee) ቀጭን በትር ሲሆን ለአንዲት ኦሮሞ ሴት በጋብቻ ዕለት በወላጅ እናቷ የሚሰጣት የክብር ዕቃ ወይም ስጦታ ነው፡፡ ሲንቄ የሴቶች መብት ማስከበሪያ መሣሪያ ሲሆን ሴቶች ላይ የመብት ጥሰት በሚፈጸምባቸው ወቅት ሲንቄያቸውን ይዘው ተቃውሞ በማሰማት ፍትሕ የሚያገኙበት ሥርዓትም ነው፡፡

የገዳ ሥርዓት በውስጡ የኢሬቻ ክብረ በዓልን ያካትታል፡፡ የኢሬቻ ክብረ በዓል የኦሮሞ ብሔር አባላት ለፈጣሪያቸው ዋቃ በዓመት ሁለቴ ምስጋና የሚያቀርቡበት ሲሆን በተለይ በመስከረም ወር መጨረሻ በአገር አቀፍ ደረጃ በቢሾፍቱ ከተማ በሀሮ አርሰዲ (አርሰዲ ሐይቅ) በመገኘት ሕዝቡ በአባ ገዳዎች እየተመራ እርጥብ ሣርና አደይ አበባ በሐይቁ ዳርቻ በማስቀመጥ ፈጣሪውን ዋቃ ከጨለማው ክረምት ወደ መፀው ስላሸጋገራቸው ምስጋና በማቅረብ የሚከበር ታላቅ ክብረ በዓል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የገዳ ሥርዓትን ከዓመታት በፊት ለማስመዝገብ ሙከራ ተደርጎ አሉታዊ ምላሽ ማግኘቱ ይነገራል፡፡ አሁንም ባለው የማስመዝገብ ሒደት ያለው ተግዳሮት ምን ይመስላል?

አቶ ገዛኸኝ፡- በ1990ዎቹ መግቢያ ላይ የገዳን ሥርዓት በዚህኛው የዓለም ወካይ ቅርስ ሊስት ሳይሆን ‹‹ማስተርፒስ›› ይባል በነበረው መዝገብ ውስጥ ለማስመዝገብ ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁንና በዚያን ወቅት የነበረውን ፋይል ስናገላብጥ ደረጃውን የጠበቀ አልነበረም፡፡ አንድ ቅርስን ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉትን አምስት መስፈርቶች በሚያሟላ መልኩ የተዘጋጀ አይደለም፡፡ ሌላው ደግሞ የተዘጋጁት ፎቶዎችና ቪዲዮ ዩኔስኮ ባስቀመጠው መሥፈርት መሠረት ደረጃውን ባለመጠበቃቸው፣ ዳግም እንዲስተካከሉ በተጠየቀው መሠረት ባለመመለሱ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ያኔ ከልምድ ማነስም ሊሆን ይችላል፡፡ ማስተርፒስ በሚባለው ፕሮግራም ላይ እንዳይመዘገብ እንቅፋት ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. የ2003ቱ የኢንታንጀብል (የማይዳሰሱ) ቅርሶች ጥበቃ ስምምነት ከወጣ በኋላ ማስተርስ የሚባለው ቀርቶ ወካይ የዓለም ቅርስ በሚል ተተካ፡፡ ማስተርፒስ የሚለው ቅርሱ ከሌሎች በልጦ የተመዘገበ የሚያስመስል አንድምታ አለው የሚል ስሜት በመፍጠሩ ነው የተለወጠው፡፡ በኮንቬንሽኑ መሠረት ወካይ ሲል ሌሎች ባህሎችን ወክሎ ነው የተመዘገበው ወደሚለው መጣ፡፡ በማስተርፒስ የተመዘገቡት ሁሉ ወካይ ቅርስ ውስጥ ተካተቱ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን የገዳ ሥርዓቱን የሚመለከተው ሰነድ ተሟልቶ መቅረቡ ተረጋግጧል?

አቶ ገዛኸኝ፡- አሁን የመስቀልና ጫምበላላ በዓሎች ለማስመዝገብ ከተገኘው ልምድ በመነሳት ሥራው ተሠርቷል፡፡ ጥሩ ልምድ አግኝተናል፡፡ በተለያዩ የክልሉ ዞኖች በመስክ የተገኘውን ውጤት በሰነድና በዶክመንተሪ ፊልም አዘጋጅተን መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ለአባ ገዳዎች፣ ለኦሮሞ ብሔር አባላት ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ጨምሮ ለአስተያየት ቀርቦ በተሰጠው ግብአት መሠረት ሰነዱ ከዳበረና ከተስተካከለ በኋላ ለዩኔስኮ መጋቢት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ተልኳል፡፡ ዩኔስኮም ቴክኒካሊ የተሟላ መሆኑን አረጋግጦ ሰነዱንና ቪዲዮን ድረ ገጹ ላይ በመልቀቅ ለዓለም አሠራጭቶታል፡፡

ሪፖርተር፡- በዩኔስኮ ድረ ገጽ የገዳ ሥርዓት በ2016 መዝገብ ውስጥ መታጨቱን በሚያሳየው ፋይል ግርጌ ‹‹ቅርሱ መመዝገብ የለበትም›› በሚል ተቃውሞውን ለዩኔስኮ ያቀረበው የአፍሪካ ናይሎቲክና ኦሞቲክ ሕዝብ ጥምረት (The Alliance of Nillotic and Omotic People of Africa-NOPA) አንዱ ነው፡፡ የኖፓ ተቃውሞ ምንድን ነው? የናንተስ ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ ገዛኸኙ፡- ተቃውሞ አቀረበ የተባለው ተቋም እውነተኛ ድርጅት አለመሆኑ የኢትዮጵያን መንግሥት አረጋግጧል፡፡ ጥላቻ ያላቸው ወገኖች የተቀነባበረ ሴራ እንደሆነ ነው የገመትነው፡፡ የገዳ ሥርዓት የኦሮሞ ብሔር ብቻ አይደለም ኬንያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ጎሳዎች የገዳ ሥርዓት አላቸው ነው ያሉት፡፡ እኛ ደግሞ ከተለያዩ ተመራማሪዎች ያገኘነው፣ ሌሎች እንደማሳይ ያሉት የምሥራቅ አፍሪካ ነባር ሕዝቦች ያላቸው የዕድሜ ዕርከን ነው፡፡ በዕድሜ ላይ የተመሠረተ ሥርዓት አላቸው፡፡ የኦሮሞ ገዳ ግን በትውልድ ቅደም ተከተል ላይ በመመሥረት በአምስት ቡድኖች ወይም መደቦች በመከፋፈል እያንዳንዱ መደብ በየስምንት ዓመቱ በሚከናወን ሰላማዊ የሆነ የሥልጣን ርክክብ ሥርዓት አንዱ መደብ ለሌላው ሥልጣን እየሰጠ የሚሄድበት ሥርዓት ነው፡፡ በዕድሜ የተራራቁን ማግኘት የሚቻለው በትውልድ ውስጥ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሥርዓት ያለው በኦሮሞ ውስጥ ብቻ በመሆኑ ልዩ (ዩኒክ) ያደርገዋል፡፡ በሥርዓቱ ውስጥ እንደ ዘመናዊው የመንግሥት መዋቅር የራሱ አደረጃጀት ያለው ሕግ አውጪው አካል ‹‹ጨፌ››፣ ሕግ አስፈጻሚው ‹‹አባ ገዳ››፣ ሕግ ተርጓሚም አለ፡፡ በየስምንት ዓመቱ በሚደረገው ሕግ የማውጣት ሒደት ላይ ጉልህ ድርሻ አላቸው፡፡ የገዳ ሥርዓት በሕግ የበላይነት የሚታመንበት ሥርዓት ነው፡፡ አባ ገዳው ጭምር ከሕግ በላይ አይደለም፡፡ በወጣው ሕግ መሠረት ማስተዳደር ካልቻለ ከሥልጣን እንዲለቅ ለፍርድ እንዲቀርብ የሚደረግበት ሥርዓት ያለው፡፡ ገዳው ሰፊና ውስብስብ የሆነ የተለያዩ ተቋማትና አደረጃጀቶችን በውስጡ ያካተተ ነው፡፡ ሌሎቹ ጋ እንደዚህ ዓይነት ባሕሪ አናገኝም፡፡ በቀላሉ በአንድ አካባቢ የተወለዱ የዕድሜ ቡድኖች ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ ይኼንን ለዩኔስኮ በሰጠነው ምላሽ አስረግጠን አስቀምጠናል፡፡ ሌላው ደግሞ የገዳው ሥርዓት ለሴቶች መብት አይሰጥም የሚለው አስተያየት ትክክል አለመሆኑ፣ የሲንቄ ሥርዓትን ጠንቅቆ ያለማወቅ መሆኑም አስረድተናል፡፡ ተቃውሞው ንቀት ያለበት መሆኑን ጭምር የሚያሳይ መሆኑን ገልጸን ለዩኔስኮ ሰፋ ባለ መልክ ምላሽ በመስጠት ተቃውሞው ተቀባይነት እንዳያገኝ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ ምዝገባው የተለያዩ ሒደቶችን አልፎ አሁን በጣም ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የማስመረጫ ሰነዱ መሟላት አለመሟላቱን የሚገመግም አካል አለ፡፡ ይኼ አካል በያዝነው ጥቅምት ወር ውስጥ የመጀመሪያውን ረቂቅ ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ ለኛም ሆነ ለሌሎች ፋይል ለላኩት አገሮች በኢሜይል ያሳውቃል፡፡ የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪው በይነ መንግሥታዊው (ኢንተር ገቨርንመንታል) አካል ነው፡፡ ከጠቅላላ ጉባኤ አባላት መካከል ከ24ቱ ተመራጭ አገሮች የተወከሉ ከገምጋሚው አካል በቀረበላቸው ረቂቅ መሠረት የመጨረሻውን ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2014 ጀምሮ የዚህ የኢንተር ገቨርንመንታል ኮሚቴ አባል ናት፡፡ የዘንድሮው 11ኛው ጉባኤ አዲስ አበባ በኅዳር ወር የሚካሄድ በመሆኑ የገዳ ሥርዓት ከኢሬቻ በዓል ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የገዳ ሥርዓት የመመዝገቡን ተስፋ የሚያሰፋው አንደኛው ጉባኤው በአገራችን መከናወኑ፣ እንደገና ጉባኤውን በሊቀመንበርነት የምትመራውም በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አማካይነት ኢትዮጵያ ናት፡፡ ገምጋሚው አካል ያልተሟላ ነገር አለ እንኳ ቢል፣ ፊቼ ጫምባላላ ላይ እንደተደረገው ቅርሱ መስፈርቱን ያሟላል ብለን የተለያዩ ማስረጃዎች ለማቅረብ፣ ሌሎችንም አግባብተን ለማስመዝገብ ከፍተኛ ዕድል ይፈጥርልናል፡፡          

Standard (Image)

‹‹በሐበሻ ላይ የተጠኑ ኮስሞቲክሶችን ማምረቴ ያስደስተኛል››

$
0
0

ወይዘሪት ሰናይት ተወልደ፣ የጂኤስቲ ፐርሰናል ከየር እና ቢዩቲ ፕሮዳክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዴቨሎፕመንት ማናጀር

ወይዘሪት ሰናይት ተወልደ የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተወልደው ካደጉበት አዲስ አበባ እንዳጠናቀቁ የተጓዙት እንግሊዝ ነበር፡፡ በእንግሊዝ የመጀመርያ ዲሪያቸውን በፋርማኮሎጂ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኮስሞቲክ ሳይንስ አግኝተዋል፡፡ ለ11 ዓመታት ያህል በለንደን በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቲአርትስ በመምህርነትም አገልግለዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከመጡ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ በራሳቸው ስም አንድ ምርት አምርተው ማቅረብ ምኞታቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ይኽንንም ለማሳካት በእንግሊዝ አገር እ.ኤ.አ. በ2006 የጀመሩትን ኮስሞቲክ የማምረትና ወደ ስካንዲኔቪያን አገሮች የመላክ ሥራ በኢትዮጵያም በማምጣት የኮስሞቲክ ፋብሪካ ከፍተው እያመረቱ ይገኛሉ፡፡ ወይዘሪት ሰናይት የጂኤስቲ-ፐርሰናል ከየርና ቢዩቲ ፕሮዳክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ፕሮዳክሽን ዴቨሎፕመንት ማናጀር ናቸው ምሕረት ሞገስአነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከመምጣትዎ በፊት በኖሩበት እንግሊዝ የኮስሞቲክ ፋብሪካ ከፍተዋል፡፡  ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ በአዲስ አበባ ተመሳሳይ ፋብሪካ አቋቁመዋል፡፡ ስለሥራዎ ቢያብራሩልን?

ወይዘሪት ሰናይት፡- እ.ኤ.አ. በ2006 በእንግሊዝ የኮስሞቲክ ምርቶችን አምርቼ በተለይ ወደ ስካንዲኔቪያን አገሮች እልክ ነበር፡፡ ሰናይት በሚል ብራንድ ነው ምርቶቹ የሚሸጡት፡፡ ይኽንንም ያደረኩት በስሜ አንድ ምርት የማምረት ዓላማ ከበፊት ጀምሮ ስለነበረኝ ነው፡፡ እዛ ያለውን ገበያ ሳየው፣ ለምን አገሬ ገብቼ አልሠራም ብዬ መጣሁ፡፡ አገሬ ስመጣ በእርግጥ ፈቃድ ማውጣቱና ማቋቋሙ ወደ ሦስት ዓመት ያህል ፈጅቷል፡፡ ረዥም  ጊዜ ወስዶብናል፡፡ ማምረት ከጀመርን ሁለት ዓመት ሆኖናል፡፡ በአገር ውስጥ ፍላጎቱ እየጨመረ ስለመጣ፣ እየተመላለስኩ መሥራቴን ትቼ አገሬ ለመግባት በመወሰን ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ኢትዮጵያ ጠቅልዬ በመግባት እየሠራሁ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግን እንዴት ያዩታል?

ወይዘሪት ሰናይት፡- እንደ እውነቱ ዘርፉ ትልቅ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ የኮስሞቲክ ዘርፍ የመልቲ ሚሊዮን ዶላር ንግድ ነው፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ በዘርፉ የተሰማራነው በጣት የምንቆጠር ነን፡፡  90 በመቶ ያህል የኮስሞቲክ ምርቶች ከውጭ የሚገቡ ናቸው ማለት እችላለሁ፡፡ አገር ውስጥ የምናምርተው ድርሻ አሥር በመቶ ነው፡፡ ይህ በዘርፉ ብዙ ኢንቨስተሮች ሊገቡ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ገበያው አለ፡፡ ሌላው ማየት ያለብን ጉዳይ ለምሳሌ በሻምፖ (ፀጉር መታጠቢያ ፈሳሽ ሳሙና) ውስጥ ካሉ ንጥረ ነገሮች 50 በመቶ ያህሉ ውኃ ነው፡፡ አንድ ሻምፖ ከውጭ አመጣን ማለት የውጭ ምንዛሪያችንን ውኃ ለመግዛት አዋልነው ማለት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እንደመጣል ይቆጠራል፡፡ በአገራችን ካመረትነው የውጭ ምንዛሪ እንቀንሳለን፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችንም በአገር ውስጥ እንተካለን፡፡ አሁን ላይ ለምርት ግብዓት የሚሆኑንን ብዙዎቹን ንጥረ ነገሮች ከውጭ እናመጣለን፡፡ በሒደት ግን ጥሬ ዕቃዎቹን አገር ውስጥ ለማምረት እናስባለን፡፡ ለወደፊት ጥሬ ዕቃዎችን ከአገር ውስጥ መጠቀም አቅደናል፡፡

ሪፖርተር፡- ያለቀለትን የመዋቢያ መጠቀሚያዎች (ኮስሞቲክስ) ከውጭ ማስገባት ከፍተኛ ቀረጥ የሚያስከፍል ነው፡፡ እናንተ ጥሬ ዕቃ አምጥታችሁ ስታመርቱ እንዴት ነው?

ወይዘሪት ሰናይት፡- በጥሬ ዕቃ ከሆነ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም አምራቾችንና ኢንቨስተሮችን ለማበረታታት ነው፡፡ አምራች ሲኮን አንዱ ትርፍ ለጥሬ ዕቃ የሚከፈለው ታክስ ዝቅተኛ መሆን ነው፡፡ ያለቀለት ዕቃ ሲገባ ግን ታክሱ ክፍተኛ ነው፡፡ እዚሁ ማምረቱ ከታክስ አኳያም ሲታይ አዋጭ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተለያዩ የኮስሞቲክ ምርቶች አገር ውስጥ ይገባሉ፡፡ አብዛኞችም ከውጭ በሚመጡት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በዚህ ውስጥ የአገርን ምርት ማስተዋወቁና ማስለመዱ እንዴት ነው?

ወይዘሪት ሰናይት፡- እኛ የአንድ ለአንድ ምክክር ላይ እናምናለን፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ በሚካሄዱ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች ላይ በመሳተፍ ምርቶቻችንን እናስተዋውቃለን፡፡ ለተጠቃሚው መሸጥ ብቻ ሳይሆን ምክር እንሰጣለን፡፡ ለሽያጭ ሠራተኞቻችን ሙሉ ሥልጠናም ሰጥተናል፡፡ ምክንያቱም የምናመርተው ቅባት፣ ሻምፖ፣ ኮንዲሽነር፣ ፀጉርን ከፀሐይና ከሙቀት የሚከላከል ቅባት፣ የልጆች መታጠቢያና ሎሽኖች ሁሉ በኢትዮጵያዊ ላይ ምርምር አድርገን ነው፡፡ ጥቅም ላይ የዋሉ ንጥረ ነገሮች ምን ጥቅም እንዳላቸውና ለቆዳም ሆነ ለፀጉር ያላቸውን ተፈላጊነት እናብራራለን፡፡ እንዳየነው ተጠቃሚው ሳያነብ የመጠቀም ልምድ አለው፡፡ ለፀጉር ብቻ የሚሆነውን ቅባት፣ ፈሳሽ ስለሆነ ብቻ ለቆዳ፣ ለቆዳ የሚሆነውንም ለፀጉር የሚጠቀም አለ፡፡ እዚህ ላይ ግንዛቤ እንሰጣለን፡፡ ሆኖም ብዙ ይቀረናል፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮስሞቲክ ውስጥ የሚገቡ ንጥረ ነገሮች ለዋጋው ውድነትም ሆነ ርካሽነት እንዲሁም ለምርቱ ጥራት ወሳኝ ናቸው፡፡ አንዱ ምርት አስፈላጊ ከሚባሉት ብዙዎቹን ንጥረ ነገር ሲይዝ፣ አንዱ ደግሞ ጥቂት ይዞ በርካሽ ዋጋ ሲሸጥ ይታያል፡፡ እናንተ የምታመርቱት የንጥረ ነገር ግብዓቱ ምን ይመስላል?

ወይዘሪት ሰናይት፡- አገራችን ከውጭ በሚገቡ የኮስሞቲክ ዓይነቶች ተጥለቅልቋል፡፡ የምንከፍለው ዋጋም ውስጡ እንዳለው የንጥረ ነገር ይዘት ነው፡፡ ለምሳሌ ምግብ ውስጥ ምን እንደተጨመረ እናነባለን፡፡ ይህን የምናደርገው የማይስማማን የንጥረ ነገር ዓይነት ካለ ላለመግዛት ወይም ላለመመገብ ነው፡፡ በኮስሞቲክ ሕግ በአሜሪካና በአውሮፓ ደረጃ ለኮስሞቲክ መግባት አለባቸው የተባሉ ንጥረ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህን ከመዋቢያዎቹ ማስረጃ ላይ ማንበብ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ወሳኝ የሆኑ ንጥረ ነገሮች መኖራቸውን ለማረጋገጥ ነው፡፡ በአገራችን ተጥለቅልቆ የምናየው ብዙ ብግዓቶችን የያዘ አይደለም፡፡ ዋጋው ርካሽ ነው፡፡ በኛ ፋብሪካ አንድ ሻምፖ ለመሥራት ከ15 ንጥረ ነገር በላይ እናደርጋለን፡፡ እያንዳንዱ ንጥረ ነገር የሚገባው ለፀጉር ተስማሚ እንዲሆን ነው፡፡ የነጮች ፀጉር እየቆሸሸ ሲመጣ ቅባታማ ይሆናል፡፡ ለነሱ የሚሠራው መታጠቢያ ውስጥ የሚገባው ንጥረ ነገር ቅባታማውን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ የእኛ እየቆሸሸ ሲሄድ እየደረቀ ነው የሚመጣው፡፡ ስለሆነም የሚያለሰልሰው መታጠቢያ ያስፈልጋል፡፡ የኛን ፀጉር መልሶ በሚያደርቅ ሻምፖ መታጠቡ ፀጉሩን ይጎዳዋል፡፡ ለዚህም ነው በነጮች ሳይሆን በአበሻ ላይ የተጠኑ ምርቶች የምናቀርበው፡፡ ንጥረ ነገር መርጠን የምናመርተውም የፀጉሩን ባህሪ አውቀን ነው፡፡ አንድ ሻምፖ ለመሥራት ቢያንስ የሦስት ወር የምርመራ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በምርቱ ከተሰማራችሁ ወዲህ ምን ያህል ጥናቶች አካሂዳችኋል?

ወይዘሪት ሰናይት፡- እንግሊዝ አገር በነበርኩበት ጊዜ በምርቶቻችን ላይ ብዙ ጥናቶችን አድርጌያለሁ፡፡ የአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች በሰጡኝ አስተያየት መሠረትም የቀየርኳቸው አሉ፡፡ ለኛ የሚጠቅመን በምርቶቻችን ላይ ያሉ ጉድለቶችን የሚነግረን ነው፡፡ ይህ ምርቶችን ለማሻሻል ይጠቅመናል፡፡ ሆኖም ብዙው ጥሩ ነው የሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ገበያው እንዴት ነው? ግብዎትን መትተዋል?

ወይዘሪት ሰናይት፡- አዎ፡፡ እኔ ያሰብኩት ከውጭ እየተመላለስኩ ልሠራ ነበር፡፡ እንግሊዝ ብሆን በምርምር ሥራውም እገፋበታለሁ ብዬ ነበር፡፡ ሆኖም በአገሬ ልሠራ ካሰብኩት በላይ ፍላጎቱ ስላለና ሥራው ስለተስፋፋ ሙሉ ለሙሉ መጥቻለሁ፡፡ ምርቶቻችንን ለሆቴል በሚሆን መልኩም አዘጋጅተን፣ ሆቴሎች እየተጠቀሙበት ነው፡፡ የሆቴሎችን ሎጎ አድርገን በትናንሽ መጠን በማዘጋጀት ከብዙ ሆቴሎች ጋር እየሠራን ነው፡፡ ለሆቴሎች የሚሆን ሻምፖ፣ ፈሳሽ ሳሙናና ኮንዲሽነር ከቻይና፣ ዱባይና ህንድ ነበር የሚመጣው፡፡ እኛ ግን አገር ውስጥ አምርተን ለሁሉም እንደሚመች አድርገን እያቀረብን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- 90 በመቶ ያህል ያለቀለት የኮስሞቲክስ ምርት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ገበያ እየገባ ባለበት ሁኔታ እርስዎ ከውጭ መጥተው ኮስሞቲክስ አምርተው ኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ መግባትዎን እንዴት ይገልጹታል?

ወይዘሪት ሰናይት፡- በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነት አግኝተናል፡፡ ሆኖም መለያው (ብራንዲንግ) ላይ መሥራት አለብን፡፡ ‹‹GST›› የሚለውን ማስለመድ ይጠበቅብናል፡፡ ሰው ስሙን ሳይሆን ዕቃውን አይቶ ነው የሚገዛው፡፡ ዩኒሊቨር ወይም ዳቭ ሲባል ሰው ባንዴ እንደሚያውቀው ሁሉ ‹‹GST›› ሲባል እንዲታወቅ እየሠራን ነው፡፡ ‹‹GST›› ምሕፃረ ቃል ሲሆን፣ ገሊላ ሰናይትና ተወልደ የሚለውን ይወክላል፡፡ ገሊላ እህቴ ስትሆን፣ ተወልደ አባታችን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- (ፓኬጂንግ) ማሸጊያን በተመለከተ ችግሮች እንዳሉ አምራቾች ይናገራሉ፡፡ እርስዎስ የሚሉት አለ? የአገር ውስጥ ግብዓትን መጠቀምን በተመለከተስ?

ወይዘሪት ሰናይት፡- በኢትዮጵያ ሥራውን ለመጀመር ስናስብ ዕቅድ የያዝነው ማሽን ለማምጣት ነበር፡፡ ማሸጊያ ዕቃዎች አገር ውስጥ ይኖራሉ ብለንም ነበር፡፡ ሆኖም እየዞርን ስናይ የምንፈልገው ዓይነት ማሸጊያ (ፕላስቲክ) ማግኘት አልቻልንም፡፡ ስለዚህ የራሳችንን ሞልድ (ቅርፅ ማውጫ) አምጥተን ማሸጊያ ለሚሠራ ካምፓኒ ሰጥተን ለኛ ብቻ የሚውል ፕላስቲክ እያመረተልን ነው፡፡ ይህ ያላሰብነው ወጪ ነው፡፡ ሌብሊንግ (ስለምርቱ መግለጫ) ከኬንያ ነበር የምናመጣው፡፡ አሁን ግን ሌብሊንግ ካምፓኒዎች አገራችን ስለመጡ ከዚሁ መውሰድ ጀምረናል፡፡ ጥሬ ዕቃ አሥር በመቶ ያህል ከአገር ውስጥ እንጠቀማለን፡፡ 90 በመቶ ከውጭ ነው፡፡ ወደፊት ግን ብዙውን ግብዓት ከአገር ውስጥ ለማድረግ እናስባለን፡፡ አሁን ላይ ቦታኒካል ጋርደን ካላት ሰው የተወሰነ ንጥረ ነገር እየወሰድን ነው፡፡ የቆዳ ቅባቶች ላይ ስንገባም የአገር ውስጥ ግብዓት ተጠቅመን እንሠራለን የሚል ዕቅድ አለን፡፡

ሪፖርተር፡- የፊት ቆዳ መጠበቂያዎችና መዋቢያዎች ላይ ለመሥራትም አቅዳችኋል?

ወይዘሪት ሰናይት፡- ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም ዕቅድ አለን፡፡ አሁን ብራንዲንጉን ማስተዋወቅ ላይ በቅድሚያ መሥራት አለብን፡፡ የሕፃናት መታጠቢያ፣ ሎሽንና ቤቢ ኦይል (ፈሳሽ የሰውነት ቅባት) ማምረት ጀምረናል፡፡ ከዓመት በፊት ለሰውነት የሚውል ሎሽን አስተዋውቀናል፡፡ እንደ ቅቤ የሚያገለግልና ቅባትም እያመረትን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ሠራተኞች አሉዋችሁ? ምርትስ ትቸረችራላችሁ?

ወይዘሪት ሰናይት፡- አሥር ቋሚ ሠራተኞች አሉን፡፡ በአጠቃላይ ከ20 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞች በሥራው ይሳተፋሉ፡፡ ምርቶቻችንን ለአከፋፋዮች እንሰጣለን እንጂ እኛ በራሳችን አንቸረችርም፡፡

 

Standard (Image)

‹‹መንግሥት በሐሳብ ከሚለዩት ጋርም የመነጋገር ልማድ ሊያዳብር ይገባል››

$
0
0

መጋቢ ዘሪሁን ደጉ፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ

መጋቢ ዘሪሁን ደጉ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በቲዮሎጂ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በናይሮቢ ፓን አፍሪካን ክርስቲያን ዩኒቨርሲቲ በሊደርሺፕ ሠርተዋል፡፡ በአሜሪካና አውሮፓም የተለያዩ አጫጭር ሥልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ በአሁኑ ወቅት በ2003 ዓ.ም. የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ጉባኤው ከሰላም ጋር በተያያዘ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በማስመልከት ምሕረት አስቻለውከመጋቢ ዘሪሁን ደጉ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ጉባኤው ምንን ዓላማ አድርጐ ተቋቋመ?

መጋቢ ዘሪሁን፡- 2003 ዓ.ም. ላይ በአምስት ሃይማኖታዊ ተቋማት እንደ ታስክ ፎርስ (ግብረ ኃይል) ሆኖ በሃይማኖቶች መካከል መቻቻልና መልካም ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ ነበር የተቋቋመው፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ ሰባት (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ የኢትዮጵያ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትና የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን) ሃይማኖታዊ ተቋማት ጉባኤ አድጐ በዘጠኙም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ጽሕፈት ቤቶችን ከፍተን በመሥራት ላይ ነን፡፡ በተቋቋመበት ወቅት አልፎ አልፎ በሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚታዩ አለመግባባቶችና ውጥረቶችም ነበሩ፡፡ ስለዚህ በዚያ ወቅት የነበረው ዓላማ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት የዘለቀው የሃይማኖት መከባበርን ማስቀጠል ነበር፡፡ ከዚያ ዓላማው እየሰፋ ማኅበራዊ ኃላፊነቶች ላይ መሥራት ጀመርን፡፡ አሁን ደግሞ የሰላም ተልዕኮአችን ላይ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ መረጋጋትና ሰላም እንዲሰፍን ጉባኤው ምን ዓይነት ጥረቶችን እያደረገ ነው?

መጋቢ ዘሪሁን፡- በሁለት መንገድ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ የመጀመሪያው የሃይማኖት ተቋማት በተናጥል ስለ ሰላም ስለ አብሮነት ማስተማራቸው ነው፡፡ በጋራ ደግሞ የማስተማሪያ ማኑዋሎች ተዘጋጅተው ተሠራጭተዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የአሠልጣኞች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ የውይይት ባህል እንዲኖር፣ የሕዝብ ጥያቄን መንግሥት እንዲመልስ፣ የሕዝብ ጥያቄዎችም በሰላማዊ መንገድ እንዲቀርቡ የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ ፈጣንና ሕዝብን እርካታ ሊሰጥ በሚችል መንገድ ጥያቄዎችን እንዲመልስ ውይይቶች ይኖራሉ፡፡ እታች ድረስ ባሉን አደረጃጀቶች ጥያቄ የሚያነሱ የኅብረተሰብ ክፍሎችንና የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት የማደራደር ሥራም እንጀምራለን፡፡ መተማመንና መግባባት ላይ ይሠራ ዘንድም ራሱን የቻለ ታስክ ፎርስም ተቋቁሟል፡፡  

ሪፖርተር፡- እንቅስቃሴአችሁ ምን ያህል ሰፊ ነው?

መጋቢ ዘሪሁን፡- መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ቢባልም ሁለቱም የሚሠሩት ለሕዝብ ስለሆነ በጋራ የሚሠሩባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ነገር ግን መንግሥትም ይህን ያን አድርጉ ብሎ በሃይማኖት ተቋማት ጣልቃ አይገባም፣ እነሱም እንደዚያው፡፡ በአገር ሰላምና ልማት ላይ በጋራ እንሠራለን፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማት የመንግሥት አጀንዳ ብቻ አይደለም፡፡ በተለይም የአገር ሰላም ከምንም በላይ የሃይማኖት ተቋማት ጉዳይ ነው፡፡ የራሳችን መተዳደርያ ደንብ፣ ሌሎች መመርያዎችም አሉን፤ በዚያ መሠረት ነው እንቅስቃሴያችንን የምናደርገው፣ ምንም ዓይነት ተፅዕኖም የለብንም፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅታዊው ሁኔታ ውስጥ መረጋጋትና ሰላም እንዲሰፍን የምታደርጉት ጥረት ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል? ተቀባይነታችሁስ ምን ድረስ ነው?

መጋቢ ዘሪሁን፡- የሃይማኖት አባቶች ወጥተው ስለተናገሩ ወይም በአንድ መግለጫ ነገሮች በአንድ ጊዜ ይለወጣሉ አይባልም፡፡ ተደጋጋሚ ሥራና ጥረቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንን እየሔድንበት እየሠራን ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለን ተቀባይነትም ከፍ ያለ ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ ተሰሚነታችንን የሚጨምረው ደግሞ ገለልተኝነታችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሥራውን የሚያከናውነው በገለልተኝነት ነው፡፡ ነገር ግን ተሰሚ እንዳንሆን ገለልተኛ አይደሉም ብሎ የሚሠራ የለም አይባልም፡፡ ዋናው እኛ የምንሠራው ለህሊናችን መሆኑ ነው፡፡ ገለልተኛነታችንን ጠብቀን መንግሥትን ይሔ ይሔ ነገር ትክክል አይደለም፣ ሕዝብንም እነዚህ እነዚህ ጥያቄዎች ተገቢ ናቸው፣ የሚቀርቡበት መንገድም አግባብነት ያለው መሆን አለበት እንላለን፡፡ ጉባኤው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሕዝቦች ዘንድ መተማመን እንዲኖር ባይሠራ ኖሮ የተከሰቱ ችግሮች የከፉ ሊሆኑ ይችሉ ነበር፡፡ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ግን እኛ ልንመልስ አንችልም፤ እነዚህ ጥያቄዎች መመለስ ያለባቸው በሕግና በሥርዓት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥት በኩልስ ያላችሁ ተቀባይነት እንዴት ነው?

መጋቢ ዘሪሁን፡- ባለፉት ስድስት ዓመታት እንደተመለከትነው ተቋማችን ተቀባይነት ያለውና ተፅዕኖ ፈጣሪም ነው፡፡ መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ በአግባብና በሥርዓት፤ በአፋጣኝም እንዲመልስ ሐሳባችንን ለመንግሥት አቅርበናል፣ ሐሳባችንንም ተቀብሎናል፡፡ መንግሥት በሐሳብ ከሚመስሉት ብቻ ሳይሆን በሐሳብ ከሚለዩት ጋር የመወያየት ልማድ ሊያዳብር ይገባል፡፡  እስካሁን ከመንግሥት ጋር ባደረግነው ውይይት ከመንግሥት ያገኘነው ምላሽ አዎንታዊ ነው፡፡ ስለ አገራቸው ግድ ብሏቸው ጥያቄ የሚያነሱም ሊሆኑ ይችላሉ፣ ሕጋዊነትን ተከትለው የፖለቲካ ወይም ሌላ ጥያቄ ከሚያቀርቡት ጋር የመነጋገር ልማድ ሊኖር ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ብዙ እንደሚሠራ ተስፋ እናደርጋለን፤ የፕሬዚዳንቱ የዚህ ዓመት የፓርላማ መክፈቻ ንግግርም ይህንኑ የሚያመላክት ነው፡፡ ትልቅ ተስፋ ሰጥቶናል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ የተገለጹ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚያን ነገሮች ይዘን አስፈጻሚውን አካል እነዚህ እነዚህ ነገሮች የት ደረሱ እያልን እንከታተላለን፡፡ ለሕዝብ ቃል የተገባው አልተፈጸመም ብለን እግር በእግር የማሳሰብ ሥራ እንሠራለን፡፡ እንግዲህ መንግሥት በዚህ በኩል ይሰማናል ብለን እናስባለን፡፡  

ሪፖርተር፡- የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ነፃ አይደሉም እየተባለ በተደጋጋሚ አስተያየት ይሰጣል፡፡ የሃይማኖት ተቋማቱ ላይ የሚነሳው የዚህ ዓይነት ጥያቄ እናንተ ላይስ ተፅዕኖ አያሳድርም?

መጋቢ ዘሪሁን፡- የአባል የሃይማኖት ተቋማት ነፃነት ተጠብቆ ነው በጉባኤው አማካይነት የጋራ ጉዳዮች ላይ በአንድ ላይ የሚሠሩት፡፡ እነሱ የእኛ አለቆች እንጂ እኛ የእነሱ አለቆች አይደለንም፡፡ ስለዚህ የሃይማኖት ተቋማቱ በተናጥል በሚወስዷቸው ዕርምጃዎችና የሚያደርጉት ውሳኔ ነፃ ናቸው፡፡ ጉባኤውም ጣልቃ አይገባም፡፡ ነገር ግን የዚህ ጉባኤም ነፀብራቅ ናቸው፡፡ ስለዚህም የሃይማኖት ተቋማቱ ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ እንዳይወድቅ ሁልጊዜ ይሠራል፡፡ ለምሳሌ ወደ ታች እየተወረደ ሲመጣ ገለልተኛ ያለመሆን ነገር ሊስተዋል ይችላል፡፡ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ገለልተኛ የማያስብል አቋም ሊያንፀባርቁ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን የሃይማኖት ተቋሙ አቋም ተደርጐ ሊወሰድ አይገባም፡፡ እዚህ ላይ መገናኛ ብዙኃን በብዙ መልኩ ችግር ሲሆኑ ታይቷል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ያላሉትን ነገር ከተነገረበት ዐውድ ውጭ የሚፈልጉትን ነጥሎ የማውጣት ነገርም አለ፡፡ ይህ ሕዝብ ጋ ሲደርስ የሃይማኖት አባቶች ወይም ተቋማት ገለልተኛ አይደሉም ያስብላል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት አቋም ከመንግሥት ጋር ሲመሳሰል ገለልተኛ አይደሉም፣ ከሌላው ወገን ጋር ሲመሳሰል ደግሞ ሌላ ናቸው ይባላል፡፡ ዋናው ነገር አገራችን ሰላም መሆን አለባት፣ የውስጥ ሰላማችን መረጋገጥ አለበት የሚለው ነው፡፡ ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት በምንም መንገድ መጥፋት የለበትም፣ ከየትኛውም ወገን ቢሆን ንብረትም የመሠረተ ልማት አውታሮችም መውደም የለባቸውም፡፡ እነዚህ ነገሮች ላይ በመግባባት አንድ ዓይነት አቋም ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ግጭቶች ከመፈጠራቸው በፊት የምትንቀሳቀሱበት ዕድል አለ?

መጋቢ ዘሪሁን፡- በዚህ ረገድ ውይይትን ነው የምናበረታታው፡፡ የሰላም ነገር የሚታወቀው የውይይት ባህል ሲኖር ነው፡፡ ለምሳሌ ጎንደር ወልቃይት ላይ መጀመሪያ ጥያቄ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እንዲወያዩ መድረክ አዘጋጅተን ነበር፡፡ በእርግጥ መድረኩን ለብቻችን ሳይሆን ከመንግሥት ጋር ነበር ያዘጋጀነው፡፡   

Standard (Image)

‹‹ከፍተኛ ቁጥር የሚይዙት ወጣቶች በመሆናቸው ያላቸውን አስተዋፅዖ ዜሮ ማድረግ አይቻልም››

$
0
0

የአብሥራ ቦጋለ፣ በኮንሰርቲየም ኦፍ ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ኢን ኢትዮጵያ (ኮይዶ) ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር

   ወጣት የአብሥራ ቦጋለ በኮንሰርቲየም ኦፍ ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ኢን ኢትዮጵያ (ኮይዶ) ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ነች፡፡ ድርጅቱ የተቋቋመው በስድስት በተለያዩ ድርጅቶች አመራር ደረጃ ላይ በሚገኙ ወጣቶች በ2013 ነበር፡፡ ኮይዶ ወጣቶችን ተመልክቶ በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ የነበረውን ዝቅተኛ የወጣቶች ተሳትፎ ለማጠናከር ታስቦ የተቋቋመ ነው፡፡ በአገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ የወጣት አደረጃጀቶች ጋር  የሚሠራ ኔትወርክ ሲሆን፣ የተለያዩ ቴክኒካል ድጋፎችን ይሰጣል፡፡ ጥኖቶችን በማድረግ በወጣት አደረጃጀቶች ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን በውይይት ለመሙላት ይንቀሳቀሳል፡፡ በድርጅቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ዙሪያ ሻሂዳ ሁሴንወጣት የአብሥራን አነጋግራታለች፡፡

ሪፖርተር፡- የድርጅቱ ዓላማ ምንድነው?

የአብሥራ፡- ወጣት ላይ ያተኮሩ ሥራዎች፤ በወጣት የሚመሩ ድርጅቶች አቅምና አብሮ የመሥራት ልምድ የጎለበተ አይደለም፡፡ እንዴት ተደርጎ የወጣቱን ድምፅ አንድ አድርጎ፣ አብሮ ተረዳድቶ መሥራት ይቻላል? የተለያዩ ወጣቶች ላይ ያተኮሩ ሥራዎች ሲሠሩ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ወጣቶችን እንዴት አድርጎ መድረስ ይቻላል? የሚለው ላይ ለመሥራት የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ የነበረው ትልቁ ችግር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የነበረው የወጣቶች ተሳትፎ በሚፈለገው መጠን የጎለበተ አለመሆኑ ነው፡፡ የተቀናጀ ተቋም አለመኖርም የነበሩት የወጣት ተቋማትና የሚሠሩ ሥራዎች በአገሪቱ ያሉትን ወጣቶች መወከል የማይችሉ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ በሚገኙባቸውና በሚወከሉባቸው ፕሮግራሞችና ኮንፈረንሶች ላይ የሚባሉትን ነገሮች በተገቢው መንገድ ይረዱታል ወይ፣ አቅም አላቸው ወይ የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚችል ተቋም እንዲኖር ሲባል ነው ይህ የኔትወርክ ድርጅት የተቋቋመው፡፡

ሪፖርተር፡- ለነበረው የወጣቶች አደረጃጀት ደካማ መሆን ምክንያት ምን ነበር?

የአብሥራ፡- አንድ የተለየ ምክንያት የለውም፡፡ ነገር ግን በቆይታዬ የአቅም ጉዳይ፣ የተለያዩ የመሠረተ ልማት አውታሮች አለመሟላት፣ እንዲሁም ቴክኒካል የሆነ የአቅም ውስንነት መኖር የአደረጃጀቶቹ ችግሮች መሆናቸውን ታዝቤያለሁ፡፡ አንድ በወጣቶች ላይ ሊሠራ የሚፈልግ ድርጅት ሲመጣ የወጣቱን ነባራዊ ሁኔታ ይዞ የሚነሳ ቡድን ወይም መሥሪያ ቤት ያስፈልገዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ አደረጃጀቶቹ ያስፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን አደረጃጀቶቹ አንድን ሥራ ለመሥራት አቅምና ተዓማኒነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ አንድን ሥራ መሥራት ከቻሉ ተዓማኒነት ያተርፋሉ፡፡ መሥራት ካልቻሉ ግን ባሉበት ሆነው ይቀራሉ፡፡ የለጋሽ ድርጅቶች መመዘኛ ከወጣት አደረጃጀቶች ጋር የማይገናኙ መሆን፣ ባለው የአቅም ውስንነት ምክንያት የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ከሚያውቋቸው የወጣት አደረጃጀቶች ውጪ አዲስ ያለመቀበል ሁኔታም አለ፡፡ ስለዚህም የአቅም፣ የተዓማኒነትና ሌሎችም የቴክኒክ ችግሮች ስላሉባቸው አሠራራቸው ደካማ ነው፡፡ ችግሮቹንም አንድ ላይ ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የወጣት አደረጃጀቶች መኖር ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

የአብሥራ፡- የወጣት አደረጃጀቶች በጣም ጥቅም አላቸው፡፡ የወጣቶች ፍላጎት ሲሟላ ነው ጤናማ የአገር ልማት የሚኖረው፡፡ በአገሪቱ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ወጣቶች በመሆናቸው ለልማት ያላቸውን አስተዋጽኦ ዜሮ ማድረግ አይቻልም፡፡ በመሆኑም አደረጃጀቶቹ ያስፈልጋሉ፡፡ ካልሆነ ግን አደረጃጀቶቹ ሳይኖሩ ወጣት ሲባል የሚመጣልን ሥዕል አንድ ዓይነት ይሆናል፡፡ ከአሥር እስከ 29 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በወጣትነት የዕድሜ ክልል ይመደባሉ፡፡ ነገር ግን ከአሥር እስከ 29 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ወጣቶች በተለያየ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ፍላጎታቸውም ይለያያል፡፡ ለምሳሌ ተማሪ፣ ሥራ የያዘ፣ ያገባ፣ ያላገባ ወጣት አለ፡፡ የእነዚህ ወጣቶች ፍላጎት የተለያየ ነው፡፡ እነዚህን ፍላጎቶች ለይቶ ማውጣትና ምላሽ መስጠት የሚቻለው ይህንን ማድረግ የሚችል አካል ሲኖር ነው፡፡ በተለያዩ ወጣቶችን በሚያሳትፉ ጉዳዮች ላይ ወጣቱን ለማሳተፍ የትኛውን ወጣት በየትኛው መንገድ እንዴት አድርጎ ማሳተፍ ይቻላል? የሚለው ነገር ካልታወቀ ውጤታማ አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ ብናይ በመጀመሪያ የወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሲባል ለከተማና ለገጠር አንድ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ላይ በመጀመሪያው የወጣትነት ከ10 እስከ 15 የዕድሜ ክልል ውስጥ ስለሚገኙ ወጣቶች ሳስብ ያገቡ አይመጡልኝም፡፡ ገጠር ውስጥ ግን ያገቡ አሉ ምክንያቱም እዚህ የምናያቸውና ገጠር የምናያቸው ወጣቶች አንድ አይደሉም፡፡ ስለዚህም እነዚህን ልዩነቶች በተገቢው መልኩ ለይቶ ማውጣት ውጤታማ የሆነ መርሀ ግብር ለመቅረፅ ይረዳል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል የወጣት አደረጃጀቶች አሉ? ከምን ያህሉ ጋርስ ትሠራላችሁ?

የአብሥራ፡- በአሁኑ ወቅት 14 አባል ድርጅቶች አሉን በሁሉም ክልሎች ላይ ይሠራሉ፡፡ ዓላማችን ግን ለሁሉም ክፍት እንዲሆንና ሁሉም ሰው አባል እንዲሆን ማድረግ የምንችልበት አቅም መፍጠር ነው፡፡ ይህን ስናደርግ እኛም ጋር ያለውን የአቅም ችግር ማጠናከር አለብን፡፡ አንዳንዴ ኔትወርኮች ውጤታማ የማይሆኑት ተመልሰው ዓላማቸውን ስተው ከድርጅቶች ጋር ስለሚፎካከሩ ነው፡፡ ይህ እንዳይፈጠር ደግሞ የእኛንም አቅም በደንብ ማጎልበት አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ያሉት የወጣት አደረጃጀቶች ቁጥር ከዚህ ቀደም ከነበረው በእጅጉ ቀንሷል ይባላል፡፡ ይህ ለምን ሆነ?

የአብሥራ፡- ትክክለኛው ቁጥር የለኝም፡፡ ነገር ግን በቅርቡ ባደረግነው ጥናት አብዛኛዎቹ አደጃጀቶች ጠፍተዋል፡፡ ለዚህም የተለያዩ የመሠረተ ግብዓቶች አለመሟላት በምክንያትነት ተሰተዋል፡፡ የሚሠሩባቸው ቢሮዎች አለመኖር፣ አቅም ያላቸው ፕሮጀክቶት ላይ አለመሥራት፣ ቻሪቲ ኤንድ ሶሳይቲ ኤጀንሲ ያወጣውን መስፈርት በሚገባ ተረድቶ ከመሥራት ጋር የአቅም ውስንነት መኖር ድርጅቶች ቀጣይነት እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማት ድጋፍ የሚሰጡት በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ለሚሠሩ አደረጃጀቶች እንደሆነ፣ ይህም በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ይሠሩ የነበሩ የወጣት ድርጅቶች የተቋቋሙበትን ዓላማ በመተው ድጋፍ ወደሚገኝባቸው ውስን ጉዳዮች ለመግባት እየተገደዱ እንደሆነ በቅርቡ ባወጣችሁት ጥናት ተመልክቷል፡፡ ይህ ምን ያህል ችግር እየፈጠረ ነው?

የአብሥራ፡- የዚህ ዓይነት ችግሮች የሚከሰቱት ፕሮጀክቶቹ አጫጭርና አቅማቸውም አነስተኛ ሲሆን በድርጅቶች መካከል ፉክክር ስለሚፈጥር ነው፡፡ በዚህ መልኩ ዘላቂ ውጤት ማምጣት አይቻልም፡፡ ከታች ጀምሮ መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ በተሰማሩበት ጉዳይ ውጤታማ ሆነው እንዲሠሩ ማስቻል ዓላማቸውን እንዳይስቱ ይረዳል፡፡ ለጋሾች ቅድሚያ የሚሰጧቸው ነገሮች ተፅዕኖ የሚፈጥርበት የወጣት ድርጅት ሊኖር አይገባም፡፡ ለጋሾች የሚሠሩባቸውን መስፈርቶች ከወጣቶች ፍላጎት አንፃር እንዲሆን ማስተካከል አለባቸው፡፡ ይህ ግን ለጋሽ ድርጀቶች ላይ ብቻ የሚጣል አይደለም፡፡ የወጣት ድርጅቶችም እርስ በርስ ተጋግዘው የቱ ጋር ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ለይተው ማውጣት እንዲችሉ ሆነው መቅረብ አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የወጣቱን ችግር በመለየት የለጋሾችን ትኩረት ማግኘት እንዴት ይቻላል?

የአብሥራ፡- ለጋሾች መረጃ ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን መረጃዎችን ለመስጠት በጣም ቸልተኞች ነን፡፡ ሌላው ቢቀር ሪፖርት ማቅረቢያ የተወሰነ ጊዜ እንኳን በሚያዘጋጁት ምክረ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) ያለማካተት ነገር አለ፡፡ የምንሠራውን ሥራ እያዩ የምንፈልገውን ድጋፍ እንዲሰጡን የተጠናከረ መረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ወጣቱ በሥነ ተዋልዶ በኤችአይቪና በመሳሰሉት ዙሪያ ያለው ግንዛቤ ከፍ ብሏል፡፡ በመሆኑም በጉዳዮቹ ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች ወጣቶች ጋር እየሄዱ አይደለም፡፡ ስለዚህም የወጣት ተቋማት ከፍተኛ ፍላጎት ባለው በመብት ጉዳይ ላይ ቢሰራ ይሻላል የሚሉ አሉ፡፡ አንቺ ምን ትያለሽ?

የአብሥራ፡- ወጣቶች በሥነ ተዋልዶና በኤችአይቪ ዙሪያ በቂ ዕውቀት አላቸው ብለን ከደመደምን በጣም እንሳሳታለን፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የተሠሩት ሥራዎች በሚገባ ታች ድረስ ተወርዶ ባለመሠራታቸው ክፍተቶች አሉ፡፡ ለዚህም በፊት ሲጠቀሙበት የነበሩ አሰልቺ አሠራሮችን በአዲስ በመቀየር እየሠራንበት ነው፡፡ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎትም ለማየት ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- በወጣት አደረጃጀቶች ዙሪያ ድርጅታችሁ ምን ያህል ተፅዕኖ መፍጠር ችሏል?  

የአብሥራ፡- መስራቾች ስድስት ነበርን፡፡ አሁን 14 መድረሳችን፣ አባሎቻችን በብሔራዊ ደረጃ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ መኖሩ ለእኛ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ነገር ግን በቂ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ለአደረጃጀቶቹ የምትሰጡት የቴክኒክ ድጋፎች አሉ?

የአብሥራ፡- የወጣት ድርጅቶችን መረጃ ለለጋሽ ተቋማቱ አዘጋጅቶ በመስጠት ረገድ የቋንቋ ችግሮች አሉ፡፡ ለጋሾቹ ሪፖርትም ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህን ለማዘጋጀት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችግር አለ፡፡ ይህ ደግሞ ድርጅቶች በደንብ የሚሠሩ ቢሆንም በቂ መረጃ ባለመስጠታቸው እንዳልሠሩ ያደርጋቸዋል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ነገሮች ሲኖሩ ፕሮፖዛል መጻፍና ሌሎችም ቴክኒካል ድጋፎች እናደርጋለን፡፡ 

Standard (Image)

‹‹በመልቲ ቢሊዮን ዶላር ሊመነዘሩ የሚችሉ ዕፀዋት ቢኖሩንም ደፍሮ ጥቅም ላይ ያዋላቸው የለም››

$
0
0

ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዕፀዋት ሥነ ሕይወት መምህርና የኢትዮጵያ የዕፀዋት ቤተ መዘክር ዳይሬክተር

ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው የዕፀዋት ሳይንስ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ በውጭ የተማሩባቸውን ጊዜያት ጨምሮ ከአራት አሠርታት ወዲህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያገለገሉ ነው፡፡ በባዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲው የድኅረ ምረቃ ፕሮግራምም በዕፀዋት ሳይንስ ከመጀመሪያ ዙር ተመራቂዎች አንዱ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ሰብስቤ በዩኒቨርሲቲው የዕፀዋት ሥነሕይወት መምህርና የኢትዮጵያ የዕፀዋት ቤተመዘክር ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የኢትዮጵያን የዕፀዋት ብዝኃ ሕይወት በማጥናትና በመመርመር የሚታወቁ ሲሆን፣ የእንግሊዝ የሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ ኪው ዓለም አቀፍ ሽልማትንም በቅርቡ አግኝተዋል፡፡ ምሕረት ሞገስአነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የዕፀዋት ፕሮጀክትን በመምራት ምርምር አከናውነዋል፡፡ ስለፕሮጀክቱ ቢገልጹልን?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- በ1970ዎቹ መጀመርያ አካባቢ የድኅረ ምረቃ ትምህርት እንደጨረስኩ የኢትዮጵያ የዕፀዋት ፕሮጀክት በሚል ትልቅ ጥናት መጣ፡፡ ጥናቱ በአዲስ አበባና በኡፕሳላ ዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወን ነበር፡፡ በድኅረ ምረቃ ከተመረቅነው ውስጥ ዶ/ር መስፍን ታደሰ (ኦሃዩ ዩኒቨርሲቲ መምህር)፣ በቅርቡ የሞተው ፕሮፌሰር ኢንሰርሙ ቀልቤሳና እኔ ተመረጥን፡፡ ዕፀዋት ሳይንስ እንድናጠናም ስዊድን ተላክን፡፡ ትምህርቱን ጨርሰን እንደመጣን ዋናው ሥራችን የኢትዮጵያ ዕፀዋት የተለያዩ ቤተሰቦችን ማጥናት ነበር፡፡ ሁላችንም በምናጠናቸው ላይ አቅጣጫ ተሰጠን፡፡ በተሰጠን አቅጣጫ መሠረት ምርምራችንን ማከናወን ጀመርን፡፡   

ሪፖርተር፡- የምርምሩ ዓላማ ምን ነበር?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- በመጀመርያ በዕፀዋት ሳይንስ የሠለጠነ ኢትዮጵያዊ አልነበረንም፡፡ ከ1973 ዓ.ም. እስከ 1977 ዓ.ም. በስዊድን በነበረን ቆይታ፣ በዘርፉ የሠለጠነ ባለሙያና መምህር ለመሆን በቅተናል፡፡ አንዱ ዓላማ የተማረ ሰው ማፍራት ነበር፡፡ ማስተማሩንና የዕፀዋት ምርምሩን አንድ ላይ በመጀመር ፕሮጀክቱን ለስኬት አብቅተናል፡፡ ፕሮጀክቱ በስዊድን መንግሥት የሚረዳ ሲሆን፣ የሚያስተባብሩት ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ነበሩ፡፡ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን በሙሉ ለማየት ዕድል ሰጥቶኛል፡፡ የተወሰኑ የውጭ ዜጎች ምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙትን ዕፀዋት እንዲያጠኑ ሲደረግ፣ ለእኛ የተሰጠን የዕፀዋት ቤተሰቦች በኢትዮጵያ የሚገኙ፣ አስቸጋሪና እኛ ብቻ መሥራት ያለብንን ነበር፡፡ በወቅቱ ሥራውን የጀመርነው ኤርትራን ጨምረን ነበር፡፡ ስንጨርሰውም ኤርትራን ጨምረን ነው፡፡ ምክንያቱም ዕፀዋት ወሰን አያውቁም፡፡ ኤርትራና ትግራይ ውስጥ ያሉ ዕፀዋት ብዙ ልዩነት የላቸውም፡፡ ጥናታችንንም ከኤርትራ ከቀይ ባሕር ጀምረን በኬንያ፣ በሶማሊያ፣ በሱዳን በአጠቃላይም የአገሪቱን ወሰን ይዘን ዕፀዋቱ ያሉባቸውን አጥንተንና ሰብስበን ናሙና መላክ ነበረብን፡፡ ጥናቱን በ1972 ስንጀምር 18 ሺሕ የዕፀዋት ናሙና ብቻ ነበረን፡፡ አሁን በዩኒቨርሲቲያችን ከ100 ሺሕ በላይ ናሙና አለን፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ ምናልባት 20 በመቶ የነበረው የዕፀዋት ናሙና ሽፋን አሁን ላይ 96 በመቶ ሆኗል፡፡ ትልቁ ሥራና የፕሮጀክቱ ዓላማ ናሙናዎችን ማደራጀትና ያሉበትን ሁኔታ፣ ስፍራና አጠቃላይ ሥነ ምኅዳራቸውን ማወቅና ምርምሩን ማሳተም ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ ሦስት ዋና ዓላማዎች ነበሩት፡፡ ሰው ማሠልጠን፣ ኢትዮጵያን በዕፀዋት መሸፈንና ሌሎችን ተቋማት መርዳት ነው፡፡      

ሪፖርተር፡- ዕፀዋቱ ታውቀውና ተለይተው፣ ናሙናም ተደራጅቶ ጥናቱም በጽሑፍ ተጠርዟል፡፡ ይህን ማድረጉ ያለው ፋይዳ ምንድን ነው? የእናንተ ጥናት ሊረዳቸው የሚችላቸው ተቋማት እነማን ናቸው?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- የግብርና፣ የደንና የአካባቢ ጥበቃ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የዕፀዋት ስያሜ ለሚፈልጉና ሥራቸው ከዕፀዋት ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለተያያዙ ተቋማት ሁሉ ይረዳል፡፡ የዕፀዋት ጥናት ፕሮጀክት ስናካሂድ ኢትዮጵያ ውስጥ የቱን ዕፀዋት በየትኛው ስፍራ ይገኛል፣ የሚገኙበት ስፍራ፣ ዓይነታቸው፣ የሸፈኑት ስፍራ አጠቃላይ ዕፀዋቱ የሚገኙበትን ሁኔታ የያዘ መረጃ ከተፈለገ ባዘጋጀናቸው ጥራዞች ውስጥ ይገኛል፡፡ ማንኛውም ሥራው ከዕፀዋት ጋር ግንኙነት ያለው ተቋም ይዞ እንዴትና በምን አቅጣጫ የራሱን ሥራ ማከናወን እንዳለበት በመረጃው ላይ ተመርኩዞ መሥራት ይችላል፡፡ ሳይንሱን የሚያውቁ ሰዎች በፕሮጀክቱ መሠልጠንም ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ በመጀመርያ ሦስታችን በፒኤችዲ ሠልጥነናል፡፡ ከእኛ ሌላ ስምንት ሰዎችን ፕሮጀክቱ ለፒኤችዲ አብቅቷል፡፡ ለዕፀዋት ስያሜ ከመስጠት ባለፈም፣ በሥነምኅዳር፣ ፊዝዮሎጂና በሌሎችም ዘርፉን ሊያግዙ በሚችሉ የትምህርት ዓይነቶች ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ አሁን ላይ አካባቢያችን ያሉትን በሙሉ ማወቅ የሚያስችል መረጃ ይዘናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ዕፅ ቢገኝ ኢትዮጵያ ብቻ አለ ለማለት የኬንያ፣ የዓረብ አገሮች ሁሉ መታወቅ አለበት፡፡ ስለእነዚህ መረጃ ሊሰጡ የሚችሉ መረጃዎች አሉን፡፡     

ሪፖርተር፡- እናንተ መረጃዎች አሏችሁ፣ በጥናትና በምርምር የታገዙ መጻሕፍት አሳትማችኋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት የዕፀዋት ዝርያዎች እንዲሁም ናሙናዎች፣ የትኞቹ በኢትዮጵያ ብቻ እንደሚገኙ ለይታችኋል፡፡ ከጥናት አልፎ ምድር ላይ ጥበቃ እንዲያገኙ እስከምን ተጉዛችኋል?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- በዩኒቨርሲቲያችን ከ100 ሺሕ በላይ የዕፀዋት ናሙናዎች ሲኖሩ በኢትዮጵያ ደግሞ 6 ሺሕ የዕፀዋት ዝርያዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 600 በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ ናቸው፡፡ ይህን ማወቁ ብቻውን አይበቃም፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ፋይዳው ምንድን ነው? ስንል ቀጣይ ደረጃ መሄድ አለብን፡፡ የመጀመርያው መረጃውን ዲጂታል አድርጎ ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ማድረስ ነው፡፡ መረጃውን ማግኘትና ስለኢትዮጵያ ዕፀዋት ማወቅ የሚፈልጉ ሁሉ ማግኘት አለባቸው፡፡ ዋናውና ትልቁ ጉዳይ 6 ሺዎቹን ምን እናድርጋቸው? ጠቀሜታቸው ምንድነው? የሚለው ነው፡፡ የዕፀዋት ጥናቱን በ2001 ዓ.ም. እንደጨረስን ምርምሩን የሠራነውና ድጋፍ የሚሰጡን አካላት ተመካክረን የኢትዮጵያ የዕፀዋት ሽፋንን ለማወቅ ፕሮጀክት ቀርፀን ‹‹Atlas of the Potential Vegetation of Ethiopia›› የሚል መጽሐፍ አውጥተናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የትም ቦታ ስለሚገኝ ዕፀዋት ከመጽሐፉ መረጃ ማግኘት ይቻላል፡፡ ኡጋዴን ወይም ሌሎች ስፍራዎች ቢኬድ ያለው የዕፀዋት ዓይነት በምስልም ታግዞ ይገኛል፡፡ ይህንን ተመርኩዞ ሰዎች የት ይሠፍራሉ፣ ለእርሻ የሚሆነው ቦታ የቱ ነው? የሚሉትን ለመለየት፣ ለልማት የሚውሉ ቦታዎች የዕፀዋቱን ደኅንነት በጠበቀ መልኩ እንዲሆኑ፣ በአጠቃላይም ይህንን መሠረት አድርጐ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የመሬት አጠቃቀም ካርታ እንዲሠራ ያግዛል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ በኢትዮጵያ ዕፀዋት ላይ የተሠሩት ጥናቶች ዋና መሠረት ናቸው፡፡ የዩኒቨርሲቲውን ጥናቶች በጽሑፍም ሆነ በኤሌክትሮኒክስ አዘጋጅተናል፡፡ ባገኘነው መድረክ ሁሉ ተጠቀሙበት፣ የአገሪቱን የመሬት አጠቃቀም የተደራጀ እንዲሆንና ሥራዎች ተመጋጋቢ እንዲሆኑ ያግዛል ብለናል፡፡ ግን የሚሰማን የለም፡፡     

ሪፖርተር፡- በአካል ቀርባችሁ ያነጋገራችሁት የመንግሥት ተቋም የለም?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- ልከናል፡፡ ሄደናል፡፡ አንዳንዴ ዋና የሆኑ ሰዎችን እንኳን ማግኘት ሳንችል ቀርተናል፡፡ ለሚመለከታቸው ተቋማት በምንችለው አቅም ጥናቱን ለማሠራጨት ሞክረናል፡፡ እንዴት ብዬ ልንገርሽ … ለምሳሌ የካርታ ሥራዎች ድርጅት ʻከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ፕሮጀክት አለን፣ ለተማሪዎች ልናወጣ ነውʼ ብሎ ሰጥተናል፡፡ በተለያየ ጊዜ ሞክረናል፡፡ የስንቱን በር እንደምናንኳኳ ግራ ይገባናል፡፡ ይኼ ጥናት አለን ተጠቀሙ ስንል፣ ፍላጐት ከሌለ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያጠናል እንጂ የሚተገብርበት መሬት የለውም፡፡ ተግባራዊ ለሚያደርጉት ግን አሳውቀናል፡፡ እኛ መሬታችን ላይ ያለውን አጥንተን ጂአይኤስን መሠረት አድርገን የሠራነውን የዕፀዋት ካርታ ሳይሆን የውጪዎቹ የሠሩትን ማመን ይቀላል፡፡ የእኛ አገር አሠራር እራሳችን ያፈራነውን መረጃ ከመጠቀም ይልቅ ፈረንጆቹ የሠሩትን ማመን የሚቀል ይመስለኛል፡፡  

ሪፖርተር፡- ጥናቱን ተግባራዊ ማድረግ ኢትዮጵያን ምን ያስጠቅማታል?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- ለምሳሌ በምዕራብ ኢትዮጵያ በበቃ ውስጥ ያለው የቡና ተክል ያለበት ስፍራ ይታወቃል፡፡ እዚያ ስፍራ ደን አለ፡፡ ያ ስፍራ ለልማት ተብሎ ቢሰጥና ዛፉ ቢቆረጥ፣ ያንን ደን፣ ሥነምህዳሩንም አጣነው ማለት ነው፡፡ ዛፉ ከሌለም ቡናው አይኖርም፡፡ በኢትዮጵያ 12 ዓይነት ሥነ ምህዳሮች አሉ፡፡ ይህንን መሠረት አድርጐ የትኛው ስፍራ መከለልና መጠበቅ አለበት፣ የትኛው ስፍራ ለልማት ይሆናል ተብሎ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ እውቅና ተሰጥቶትና ተከልሎ ዕፀዋቱ ለትውልድ ሲተላለፉ መቆየት አለባቸው፡፡ በጋምቤላ ለምሳሌ የተለየ የዕፀዋት ዓይነት አለ፡፡ በአማራ ክልል ያለው የእጣን ዛፍ መከለል አለበት፣ ትግራይና ሌሎች ክልሎችም እንዲሁ፡፡ ያሉትን ዕፀዋት መንጥረን በልተን ትውልድ እንዳያየው ማድረግ ትክክል አይደለም፡፡ ከሕዝብ ጋር በመነጋገር ዕፀዋት ተጠብቀው የሚቆዩበትን መንገድ ማጠናከር እንችላለን፡፡ ስምጥ ሸለቆ እኛ ልጅ በነበርንበት ጊዜ ከዕፀዋቱ ብዛት ማለፍ አይቻልም ነበር፡፡ ዛሬ ዓይን እስኪደክም ተሄዶ የሚታየው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የስምጥ ሸለቆ እውነተኛውን የዕፀዋት ሥርጭት የያዘ ሁኔታ የለም፡፡ ለአቢጃታና ሻላ ሐይቅም ሆነ አካባቢ ምን ጥበቃ ተደረገ? ምንስ ቀርቶናል? የሚለው ሲታይ ተመንጥሯል፡፡ በእያንዳንዱ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የዕፀዋት ስፍራዎች በተወሰነ ደረጃ ጥብቅ መሆን አለባቸው፡፡ ይህንን በተመለከተ ለፌዴራልም ሆነ ለክልል መረጃ ለመስጠት ዝግጁ ነን፡፡ ከብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ ሆኖም ብዙዎች ጥናቶችን የሚወስዱት ለግል እንጂ ለተቋማዊ ጥቅም አይደለም፡፡ እኛ ደግሞ ጥናቱ ወደትግበራ እንዲለወጥ አገሪቷም ሆነች ሕዝቦቿ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ጥናቱን በምትሠሩበት ጊዜና ካጠናቀቃችሁ በኋላ በዕፀዋት ሽፋኑ ላይ ምን አያችሁ?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- የዛሬ 20 ዓመት ላንጋኖ፣ አቢጃታና ሻላ እንዲሁም ሌሎች የአገሪቱ ስፍራዎች የሄደ ሰው ዛሬ ቢሄድ ልዩነቱን በግልጽ ያየዋል፡፡ በፊት ያነሳኋቸው ፎቶዎች ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ካነሳኋቸው ጋር ሲነጻጸሩ ይሰቀጥጣል፡፡ ባሌም ሆነ ሌሎች ስፍራዎች ብንሄድ እንዲሁ ነው፡፡ ሰው እየገፋ ነው የሚመጣው፡፡ ከሰው ጋር መነጋገር፣ ማስተማር፣ የኑሮ ማስተካከያ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማድረግ አቅሙ ያላቸው የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ናቸው፡፡ ድሮ ‹‹አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራት አታውቁም›› ሲባል እንዴት? እል ነበር፡፡ ግን እውነት ነው፡፡ በተናጠል ብዙ እንሠራለን፡፡ ግን አቀናጅተን ለዘላቂ የአገራችን ዕድገት አንሠራም፡፡ ለዘለቄታ ማሰብ አለብን፡፡ መንግሥት ይመጣል፣ ይሄዳል፡፡ ትውልድና አገር ቀጣይ ናቸው፡፡ ትውልዱንና አገርን አስበን መጓዝ አለብን፡፡ ከፕሮፖጋንዳ ባለፈ የተቀናጀ ሥራ በአርሶ አደሩ፣ በተመራማሪው፣ በተማሪውና በመንግሥት በጋራ መሠራት አለበት፡፡ የዕፀዋት ሀብታችን ‹‹ኦፍላ በግ አለ ሲሉት ይሞታል›› እንደሚሉት ሆኗል፡፡ ተመናምኗል፡፡  

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ መአዛ ያላቸው ዕፀዋት ላይም ጥናት ሠርታችኋል፡፡ ለመድኃኒት፣ ለተለያዩ መዋቢያ ቅባቶች የሚውሉ ዓይነትም አሉ፡፡ ግን ጥቅም ላይ ሲውሉ፣ የውጭ ምንዛሪ ሲያስገኙ አይታይም፡፡ ችግሩ ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- አንዳንድ የባህል መድኃኒት የሚፈልጉ ሰዎች በግል ይጠይቁናል፡፡ ተቋማት ግን ጥናቱን ተንተርሰው ምን እናድርግ፣ ከዚህ በኋላ ወዴት እንሂድ አይሉም፡፡ ካልተሳሳትኩ በስተቀር የእኛ ሀብታም ያለ ነገር ላይ ይበረታል፡፡ አዲስ ነገር ለመጀመር የገንዘብ ድፍረት የለንም፡፡ ባለሀብቶችም ደፍረው አይመጡም፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ 46 ዓይነት የእሬት (Aloe) ዝርያዎች አሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ካላቸው ዝርያ አንዱን ብቻ በተለያዩ ዓይነቶች በመጠቀም በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ያገኛሉ፡፡ እሬቱ ተጨምቆ የሚጠጣ ጁስ ይሆናል፡፡ ለምግብ፣ ለመድኃኒት፣ ለፀጉር እንዲሁም ለፊት መዋቢያ ቅባቶችና ለተለያዩ የኮስሞቲክስና ምግብ ዓይነቶች ግብዓት ይሆናል፡፡ የእሬት ትልቁ ጥቅም ጥሩና ለም ቦታ አይፈልግም፡፡ አርሶ አደሩ ከማሳው መጥፎና ምርት የማይሰጥ ቦታ ላይ ቢተክለው ያድጋል፡፡ ሌሎች ሰብሎችንም አያበላሽም፡፡ ወደ ውጭ ተልከው ብዙ ቢሊዮን ዶላር ሊያስገኙ የሚችሉ ዕፀዋት አሉን፡፡ ነገር ግን እነዚህን አቀናጅቶ ጥቅም ላይ የሚያውላቸው ደፋር ባለሀብት የለንም፡፡ እሬት የመልቲ ቢሊዮን ዶላር ቢዝነስ ነው፡፡ ዕፀዋቶቻችን ሀብታችን ናቸው፡፡ ግን ሀብትና የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ድጋፍ እንዲሁም ሊሠራ የሚችል ባለሀብት ያስፈልገናል፡፡ ግብርና መር ኢንዱስትሪ የሚያስፋፋ ባለሀብት ከመጣ እኛ አለን፡፡ ዕውቀቱ አለ፡፡ የሚተገብረው ግን የለም፡፡ በመልቲ ቢሊዮን ዶላር ሊመነዘሩ የሚችሉ ዕፀዋት አሉን፡፡ ሆኖም ደፍሮ ጥቅም ላይ ያዋላቸው የለም፡፡    

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም የእናንተው ዩኒቨርሲቲ መሽሩም (እንጉዳይ) ላይ ጥናት አድርጐ ወደ ሕዝቡ እንዲገባ፣ በየሱፐር ማርኬት እንዲሸጥ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ይህንን መከተል አትችሉም?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- ተመራማሪው ዶክተር ዳዊት ብዙ ሞክሮ በኋላ ወደ ኅብረተሰቡ ገብቷል፡፡ የእሱም ዓላማ መሽሩምን ማስተዋወቅና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ነበር፡፡ ይህንን አሳክቷል፡፡ ግን እያንዳንዱ ተመራማሪ ባለኢንዱስትሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ተመራማሪው የምርምሩ ውጤት ተግባራዊ ሆኖ ሰው ቢጠቀም፣ ለተመራማሪው ትልቁ ደስታው ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የዘንድሮውን የእንግሊዝ የሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ ኪው ዓለም አቀፍ ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ከሁለት ወር በኋላ ለንደን ላይ በሚከናወነው የሜዳልያ ሥነ ሥርዓት ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለመሸለም ያበቃዎት ምንድን ነው? በንግግርዎት ኢትዮጵያ ካላት የዕፀዋት ሀብት ተጠቃሚ እንድትሆን የሚረዳ ዓይነት ይሆናል?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- የሽልማቱ መሥፈርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕፀዋት ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ በመሆናቸው ላይ የሠራ፣ ለኅብረተሰቡ ያስተዋወቀ እንዲሁም ማስተማር የሚሉትን የሚይዝ ነው፡፡ የአንድ ነገር ሳይሆን የተለያዩ ሥራዎች ድምር ውጤት ነው፡፡ ከሮያል ቦታኒክ ጋርደን ጋር ምን ያህል በቅንጅት ሠርቷል የሚለውም ይታያል፡፡ ለፒኤችዲ በ1973 ዓ.ም. ሥራ ስጀምር መጀመርያ የጐበኘሁት እንግሊዝ የሚገኘውን ቦታኒክ ጋርደን ነው፡፡ እኛ 100 ሺሕ ናሙና አለን ብዬሽ ነበር፡፡ እነሱ የዓለም ሁሉ ዕፀዋት ማለትም ሰባት ሚሊዮን አላቸው፡፡ በዓለም ዕፀዋት ላይ ጥናት መሥራት የሚፈልግ፣ ሮያል ቦታኒክ ጋርደን ውስጥ ሁሉንም ባንድ ስፍራ ያገኛል፡፡ ወደ ስፍራው በተለያዩ ጊዜያት ለሥራ እሄዳለሁ፡፡ ፕሮጀክቶችም አሉን፡፡ ስሄድ የግሌን ሥራ ብቻ አልሠራም፡፡ እዚያ ካሉት ጋር በጋራ እንጽፋለን፣ መጽሐፍ እናሳትማለን፡፡ ኢትዮጵያን የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶችም አብረን እንሠራለን፡፡ ገንዘብ ለማግኘትም ፕሮጀክት አስገብተናል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ተሸላሚ ሆኛለሁ፡፡ ይህ ሽልማት የተሰጠው ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡ ሽልማቱ ለተማሪዎቼ፣ ለሥራ ባልደረቦቼና ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዕውቅና ነው፡፡ ከብዙ አጋሮቼ መሃል በተለይ በቅርቡ በሞት የተለየንን ዶክተር ኢንሰርሙ የኔው አካል ነው ብዬ እወስደዋለሁ፡፡ ስለሥራዬ ሳስብ ሁሌም እሱ አለ፡፡ 37 ዓመት አብረን ሠርተናል፡፡ አብረን ተምረናል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በኬምስትሪ ዲፓርትመንት የምትሠራው ባለቤቴ ዶክተር ንግሥት አስፋው ሁሌም ከጐኔ በመሆንና በማገዝ እዚህ እንድደርስ ትልቁን ሚና ተጫውታለች፡፡ እኔም ለሽልማት የበቃሁት የእነዚህ ሁሉ ድጋፍ ስላልተለየኝ ነው፡፡

በሜዳልያው ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ በሚደረገው ንግግር ኢትዮጵያን ማጉላት፣ ያላትን ማስተዋወቅና ባላት እንዴት አብሮ መሥራት ይቻላል በሚለው ላይ ትኩረት አደርጋለሁ፡፡ የአየር ንብረት ለውጡ በዕፀዋት ላይ ያሳደረው ተፅዕኖም አንዱ አጀንዳዬ ይሆናል፡፡       

Standard (Image)
Viewing all 290 articles
Browse latest View live